Sunday, April 21, 2024

የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት ቁርጥ ያሉ ውሳኔዎች ያልተላለፉበት 30ኛው የመሪዎች ጉባዔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጥር 20 እና 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በአሁኑ የመሪዎች ጉባዔ የፀረ ሙስና ዘመቻ፣ የአፍሪካ ኅብረት ማሻሻያ፣ ነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት፣ የአፍሪካን የአየር ክልል ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነፃ ማድረግና በአኅጉሪቱ በሚታዩ የፀጥታ ሥጋቶችና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ባለፈው እሑድና ሰኞ በተካሄደው 30ኛው የመሪዎች ጉባዔ የአርባ ዘጠኝ አገሮች መሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡

አወዛጋቢና አከራካሪ ንግግር በማድረግ ይታወቁ የነበሩት የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በጉባዔው ላይ አለመገኘት፣ የጉባዔውን ድምቀት በመጠኑም ቢሆን ቀንሶት እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው ታዳሚዎች ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋችና የአሁኑ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሐ በጉባዔው ላይ መገኘት ድምቀት ሰጥቶት እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ጉባዔው ሲከፈት ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል ከተሰጣቸው መሪዎች አንዱ አዲሱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንትና የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሐ ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሐ ንግግር እንዲያደርግ ዕድል ሲሰጣቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች አዳራሹን በፉጨትና በጭብጨባ አድምቀውት ታይቷል፡፡ አብዛኛዎቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው ሞቃት አቀባበል አድርገውለታል፡፡ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ ማስረከብ ባልተለመደበት አኅጉር (ከጥቂቶች በስተቀር) እንደ ላይቤሪያ ዓይነት በምርጫ ያሸነፈን ተወዳዳሪ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ ማስረከብ ለአፍሪካውያን አዲስ ተሞክሮ ሆኖ እንደተወሰደ ሲነገር ተደምጧል፡፡  

ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሐ ባደረጉት ንግግር፣ በአገራቸው የተካሄደው ምርጫ አሸናፊ በመሆናቸው ደስተኛ እንደሆኑ ጠቁመው፣ እሳቸውም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሐ በአገሪቱ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በፕሬዚዳንትነታቸው የሚያገኙትን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በ25 በመቶ በመቀነስ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲውል መወሰናቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ለጉባዔው ድምቀት ከነበሩ ጉዳዮች ሌላኛው አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ያደረጉት ንግግር ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ተክተው ለመጀመርያ ጊዜ በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ የተገኙ መሪ ሲሆኑ፣ ባደረጉት ንግግርም ሮበርት ሙጋቤ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና መንግሥታቸው የእሳቸውን ክብር በሚመጥን ቦታ እንዳስቀመጣቸው አስረድተዋል፡፡

ሰኞ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. 30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ አልተጀመረም፡፡ መሪዎቹ በዝግ የሚያደርጉት ስብሰባ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የጊዜ ሰሌዳ ቢወጣለትም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ተኩል ነው ከዝግ ስብሰባው መውጣት የቻሉት፡፡ በወቅቱም ከተለያዩ አገሮች የመጡ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ መሰላቸትና ድካም ታይቶባቸው ነበር፡፡ መሪዎቹ በዝግ ያደረጉት ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ትልቁና ኔልሰን ማንዴላ ተብሎ በሚጠራው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ፣ የዓረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ፣ የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር፣ የዚምባብዌና የላይቤሪያ ፕሬዚዳንቶች ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹ዘላቂ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለአፍሪካ ሥር ነቀል ለውጥ›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ መሃማት፣ የአፍሪካ ኅብረት ማሻሻያን በአፋጣኝ ተግባራዊ በማድረግ አፍሪካ ራሷን የቻለች አኅጉር መሆን አለባት ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ መሪዎች በአፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፋ የመጣውን ሙስና መከላከል እንዳለባቸውና የዘወትር የቤት ሥራቸው አድርገው እንዲሠሩና የሚታይ ለውጥ እንዲያመጡ አሳስበዋል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናና የአፍሪካን የአየር ክልል ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነፃ ማድረግ፣ አፍሪካዊያን በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች መተሳሰር እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡

በአፍሪካ በተለይም በደቡብ ሱዳን፣ በቻድና በሶማሊያ የሚታየው የፀጥታ ችግር  እንዲፈታ መሪዎች ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው፣ አኅጉሪቱ ከምትታወቅበት የእርስ በርስ ጦርነት እንድትወጣ፣ ከድህነት፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከሌሎች  ችግሮች ነፃ ሆና ለዜጎቿ ምቹና ሰላሟ የተረጋገጠ እንድትሆን ሊቀመንበሩ አሳስበዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካ ያሉባትን ችግሮች በራሷ መፍታት የምትችል አኅጉር እንድትሆን መሪዎች ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል፡፡ ስደትን፣ ድህነትን፣ ኢፍትሐዊ አሠራርንና ሌሎች ተግዳሮቶችን በመመከት መሪዎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአፍሪካ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለማንም የሚተው ሳይሆን፣ አፍሪካውያን በራሳቸው መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አፍሪካ ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ለሌሎች አኅጉሮች ተምሳሌት እንደሆነች ዋና ጸሐፊው ገልጸው፣ ኅብረቱና ተመድ በቅንጅት እንዲሠሩ ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡   

ለሁለት ቀናት በቆየው የመሪዎች ጉባዔ ትኩረት ተሰጥቶዋቸው ከነበሩ ጉዳዮች  አንዱ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት የሚለው ሲሆን፣ አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ሐሳቡን እንደደገፉ ቢገለጽም፣ አለመግባባቶች እንደነበሩ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር ፖል ካጋሜ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት በሚደረገው ጥረት ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋጣዊ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጆ ኦባሳንጆና የኅብረቱ የኢኮኖሚ ኮሚሽነር ሙችንጋ ሙቻቹ ናቸው፡፡

ለጋዜጠኞች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና መመሥረት የ2063 አጀንዳ እንደሆነና የአኅጉሪቷን ሕዝቦች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ለማስተሳሰር ታቅዶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣናው ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ 1.2 ቢሊዮን አፍሪካውያን በንግድ እንደሚተሳሰሩና በዚህም ለአኅጉሪቱ በዓመት 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝላት ተጠቁሟል፡፡ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው ስምምነት ላይ ሲደርስና በመሪዎች ተፈርሞ ወደ ተግባር ሲገባ፣ በዓለም የንግድ ድርጅት ተቋም መሥፈርት መሠረት ትልቁ የዓለም ነፃ የንግድ ቀጣና ይሆናል ተብሎ እንደሚገመትም ለጋዜጠኞች ገለጻ ተደርጓል፡፡

የዚህ ዓይነት የንግድ ቀጣና መመሥረት ያስፈለገበት ምክንያት በአፍሪካ ደረጃ የሚካሄደውን የንግድ ልውውጥ ቀላል ለማድረግና ዜጎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ብሎም ጥራት ያለው ምርት ከአኅጉሪቱ ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የንግድ ቀጣናው ከተመሠረተ በኋላም በጥቃቅንና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ አፍሪካውያንን ከመጥቀሙም ባሻገር፣ ሴት አፍሪካውያንን የሚያበረታታ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአፍሪካ መፍታት እንደሚገባ በጉባዔው ላይ መብራራቱን የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበር ፖል ካጋሜ ጠቁመዋል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናው ሲፀድቅ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ችግር በማስወገድ፣ የአኅጉሪቱ ዜጓች እንዳይሰደዱና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከ30ኛው የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በርካታ የጎንዮሽ ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የአፍሪካን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ መሥራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የተደረገው ምክክር ሲሆን፣ ይህን ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዋና ሊቀመንበርነት መርተውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. 2025 በአፍሪካ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት መሪዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ ቃል ገብተው እንደነበር፣ ከዚያ ስምምነት ወዲህ ዘርፉን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት መሻሻሎች እንደታዩ ጠቁመዋል፡፡ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግብርና የአኅጉሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ብዙ ቀሪ ሥራዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ችግራቸውን በራሳቸው የሚፈቱ አፍሪካዊያንን ከመፍጠር አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ አፍሪካ ለምንድነው ከሽብርና ከፀጥታ ሥጋት ነፃ መውጣት ያልቻለችው በሚለው ጉዳይ ላይ፣ የኅብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር አምባሳደር እስማኤል ሸርጉይ ጋዜጣዊ መግጫ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚሽነሩ በአፍሪካ በተደቀኑ የፀጥታ ችግሮችና እየተወሰዱ ባሉ ዕርምጃዎች ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ እንደ ጠቆሙት፣ በአኅጉሪቱ በዋናነት በሦስት አካባቢዎች የሰላምና የፀጥታ ሥጋቶች ተደቅነው ይገኛሉ፡፡

በአፍሪካ ቀንድ በዋናነት በደቡብ ሱዳን ያለው የፀጥታ ችግር አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን አድንቀዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሰላም ስምምነቱን የሚያፈርሱ አካላት ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በአፍሪካ ሁለተኛ የፀጥታ ሥጋት ብለው ያነሱት የሶማሊያን ጉዳይ ሲሆን፣ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በቀጣናው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) እና የጎረቤት አገሮችን ጥረት አድንቀው፣ ጥረቱ ወደፊት መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የአሚሶም ጦር ከሶማሊያ ይወጣል እየተባለ የሚወራው ወሬም ውሸት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ አኅጉርም ሆነ ሌሎች ክፍለ ዓለማት አሁን በአገሪቱ ያለውን መንግሥት በማጠናከር ወደፊት በአገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን በትኩረት ሊሠራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች አሚሶምን በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ መደገፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በሦስተኛ ደረጃ የፀጥታ ችግር ያለበት ቀጣና የሳህል አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በማሊ ተሠማርተው የነበሩ ወታደሮች በአሸባሪዎችና በአጥፍቶ ጠፊዎች እየተገደሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣናው ራሱን እስላሚክ ስቴት (አይኤስ) እያለ የሚጠራው ቡድን በስፋት ተንሠራፍቶ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በሌሎች አገሮች የተካሄደው ዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ዘመቻ በቀጣናውም ተግባራዊ በማድረግ ንፁኃንን መታደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በሊቢያ በዘመናዊ ባርነት የንግድ ሰንሰለት ውስጥ አፍሪካውያን እየተሰቃዩ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ሰንሰለት ለመበጣጠስና የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ አሁንም ግን በቀጣናው ያለውን ችግር ለመፍታት የሁሉም አኅጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በቻድ የሚታየው የፀጥታ ችግር አሁንም ትልቁ ፈተና መሆኑን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉተሬዝ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በአኅጉሩ ያለውን የሽብር ድርጊት ለመዋጋት አገሮች መቀናጀት እንዳለባቸውና ከተመድ ጋር በመሆን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የወቅቱ ዋነኛ ፈተና የሆነው ሽብርተኝነትና የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ዋና ጸሐፊው አክለው ገልጸዋል፡፡  

ለችግሩ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች እየተለዩ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ መልካም አስተዳደር በማስፈን ዜጎች የማይሰደዱባትና ሠርተው የሚኖሩባት አኅጉር መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ በጉባዔው ተብራርቷል፡፡

ለ30ኛ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ተጠናቋል፡፡

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ እ.ኤ.አ. በ2018 የአፍሪካ መሪዎች ማከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ በዝርዝር አለመቅረባቸውን በጉባዔው የተሳተፉ የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጉባዔ ሙስናን መከላከል አለብን የሚል መፈክር ከማስተጋባት ውጪ፣ ሙስና ሲፈጽሙ የተገኙ መሪዎች በኅብረቱ ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል? የመልካም አስተዳደር እንቅፋት በሆኑ መሪዎች ላይ ከዚህ በፊት ኅብረቱ ምን ዓይነት ዕርምጃ ወስዷል? ወደፊትስ ምን ዓይነት ዕርምጃ ይወስዳል? በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በቻድ፣ በማሊና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ግጭቶች ሲከሰቱና ንፁኃን ዜጎች ሲሞቱ የአፍሪካ ኅብረት ምን ዓይነት ዕርምጃ ወስዷል? አሁንስ ይህን ችግር ለማስወገድ ምን ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ አቅዷል? የአኅጉሪቱን ዜጎች ከስደት ለማስቆም ከዚህ በፊት ምን ዓይነት ሥራ ሲሠራ ነበር? አሁንስ ምን ለመሥራት አቅዷል? የሚሉ ጥያቄዎች ቢጠይቁ ምላሽ እንደማይገኝላቸው ከጋምቢያ የመጡ አንድ ዲፕሎማት ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በመዝጊያው ላይ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ ጉባዔው ለአፍሪካ በሚጠቅሙና ቀዳሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መምከሩን ቢያወሱም ጉዳዮቹ ምን እንደሆኑ በዝርዝር አላብራሩም፡፡ የአኅጉሪቱን ኢኮኖሚ ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ አገሮች ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች ለአጀንዳ 2063 ስኬትና የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት እየተደረገ ባለው ጥረትም ሁሉም አገሮች ስምምነት ላይ እንደደረሱና የሚቀሩ ጉዳዮች መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሩዋንዳ ኪጋሊ በሚካሄደው ጉባዔ ላይ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም፣ ወደ ሥራ ለመግባት ስምምነት ላይ መደረሱን ፖል ካጋሜ ተናግረዋል፡፡

የኅብረቱን የማሻሻያ ዕቅድ በበላይነት የሚመሩት ፖል ካጋሜ፣ አፍሪካ በኢኮኖሚም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ራሷን የቻለች አኅጉር እንድትሆን እንደሚሠሩ በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትን ወጪ በአባል አገሮች ለመሸፈንና ኅብረቱ ጥርስ ያለው እንዲሆንና ጠንካራ ሥራ እንዲያከናውን የሚጠቁሙ የውሳኔ ሐሳቦች አለመተላለፋቸውን ተሳታፊዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በአፍሪካ የሚታየውን ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ድህነት፣ ሙስናና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት መሪዎች ቁርጠኝነታቸው በጉባዔው አለመንፀባረቁ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -