Saturday, March 2, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለጎደለባቸው ማረፊያ

ለጎደለባቸው ማረፊያ

ቀን:

ወ/ሮ ምስኳሊ ኩምሳ በከፋ ዞን ሊሙኰሳ ወረዳ ከምሴ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ባደረባቸው የማሕፀን ካንሰር ሕመም ምክንያት ባለቤታቸውን አስከትለው ለሕክምና አዲስ አበባ ከመጡ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ ሕክምናውን የጀመሩት በየዕለቱ 110 ብር በሚከፈልበት አልቤርጎ ውስጥ እየተቀመጡ ቢሆንም የያዙት ገንዘብ ከስድስት ቀናት በላይ ሊያኖራቸው አልቻለም፡፡ ከአልቤርጎው መልቀቅም ግድ ሆነባቸው፡፡

የቀራቸውን ገንዘብ ይዘው በየዕለቱ 30 ብር እየከፈሉ ግለሰብ ቤት መቀመጥና ሕክምናቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡ ከአሥር ቀናት በኋላ ግን ከትውልድ ቀዬአቸው ሲመጡ የቋጠሩት ገንዘብ ተሟጠጠ፡፡ ቦርሳቸውም ባዶ ሆነ፡፡ የነበራቸው አማራጭ በሆስፒታሉ በረንዳ ላይ ውሎ ማደር ነበርና በዚህ መልኩ ለስምንት ወራት ያህል አሳልፈዋል፡፡

በስተመጨረሻም እንደ እሳቸው ላሉ ወይም አቅምና መጠጊያ ዘመድ ለሌላቸው ታካሚዎች የሕክምና ክትትላቸውን እስከሚጨርሱ ድረስ በነፃ የሚያርፉበት ጎጆ አቅም የለሽ የሕሙማን ማረፊያ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ባቋቋመው ማረፊያ ገብተው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ በዚህም ማረፊያ ከገቡ 15 ቀናት ሆኗቸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፈው ወር መጀመርያ አካባቢ ሕክምና ፍለጋ ከሚዛን ቴፒ የመጡት አርሶ አደር ወንድሙ ዘጌም ለሕክምና ብለው አዲስ አበባ በመምጣትና ማረፊያ በማጣት ከሚሰቃዩ ሕሙማን አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸውም ለቀን ከ100 ብር በላይ እየከፈሉ ለአሥር ቀናት ያህል አልቤርጎ መቀመጣቸውን ይናገራሉ፡፡ ኪሳቸው ከተራቆተ በኋላ አልቤርጎውን ለቀው ወጡ፡፡ ዘመድ አዝማድ የላቸውምና ጎዳና እየዋሉና እያደሩ ሕክምናቸውን ቀጠሉ፡፡ እየለመኑ መብላት፣ ሲጠፋም ጦም ማደር ግድ ሆነ፡፡ 

አንገታቸው ላይ የወጣውን ዕጢ ለመታከም ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጡት አቶ ወንድሙ፣ ባለቤታቸውንና ሦስት ልጆቻቸውን ቤት ትተው በመውጣታቸው ሁለት ሐሳቦች ወድቀውባቸዋል፡፡ አንደኛው ሐሳብ ማሳቸው ጦም ማደሩና ለሥራ ያልደረሱ ልጆቻቸው ሰብሳቢ ማጣታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለሕክምና የቋጠሩት ገንዘብ መሟጠጡ ነው፡፡

በተለይ ለሕክምና የቋጠሩት ገንዘብ ሕክምናውን በቅጡ ሳያገኙ ማለቁ ችግራቸውን አጉልቶት ነበር፡፡ ሆኖም ብዙ ከተሰቃዩ በኋላ ተሳክቶላቸው በጎጆ አቅም የለሽ ማረፊያ ቤት ተጠቃሚ ለመሆን መብቃታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ማረፊያ ከአልጋ በተጨማሪ ልብስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹የሌሊት ቁር፣ የጠዋት ብርድና የቀን ሙቀት ሳይፈራረቅብኝ አለምንም ችግር ሕክምናዬን እየከታተልኩ ነው፡፡ ጎጆ አቅም የለሽ የሕሙማን ማረፊያ ባይኖር ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ዶ/ር ሰሚር ሱልጣን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማሕፀንና ጽንስ ሐኪምና የመጨረሻ ዓመት ስፔሻሊስቲ ትምህርት ተከታታይ ናቸው፡፡ የድርጅቱ የቦርድ አባል ሲሆኑ፣ ‹‹ታካሚዎች ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቅንብርና ስንብት ክፍል፤ አቅም የሌላቸውና ረዥም ጊዜ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ሲያመጡ በማረፊያው በነፃ እንዲገለገሉ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ መልኩ በማረፊያው ውስጥ የሚገኙ ተመላላሽ ታካሚዎች ሕክምናቸውን እስከሚጨርሱ ድረስ የመኝታ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በሳምንት ለሦስት ቀናት ማለትም ሰኞ፣ ሮብና ዓርብ ምግብ ይቀርብላቸዋል፡፡ ማረፊያውን የሚጠቀሙትና የምግብ አገልግሎትም የሚያገኙት በነፃ ሲሆን፣ ምገባውም የሚካሄደው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡

ከተለያዩ ክልሎች እየመጡ በማረፊያው ውስጥ ከሚገኙት ታካሚዎች መካከል አብዛኞቹ የካንሰር ሕሙማን ሲሆኑ፣ የነርቭና የልብ ሕሙማንም ይገኛሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ማረፊያው አገልግሎት የሚሰጠው በዚሁ ሆስፒታል ሕክምናቸውን ለጀመሩት ታካሚዎች ብቻ ነው፡፡ ወደፊት ግን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በዘውዲቱ፣ በየካቲት 12 እና በምንልክ ሆስፒታሎች ውስጥ ለማቋም እንደታቀደ ዶ/ር ሰሚር ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሰሚር፣ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመሆኑ፣ ሆስፒታሉ በቅርብ ርቀት በመገኘቱ፣ የድርጅቱ አመራሮችም የሆስፒታሉ ሐኪሞችና ተጠቃሚዎቹም የዚሁ ሆስፒታል ታካሚዎች በመሆናቸው ለአሠራሩ ሥምረት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሆስፒታሉ ቅርብ መሆኑ ደግሞ ታካሚዎቹ ተሽከርካሪ ሳያስፈልጋቸው በእግራቸው ሄደው ለመመለስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡

ዶ/ር ሰላሜነሽ ጽጌ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፔዲያትሪክና የቻይልድ ሔልዝ ዲፓርትመንት የመጨረሻ ዓመት ስፔሻሊስት ተማሪ፣ የድርጅቱ መሥራች፣ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ሰላሜነሽ፣ ማረፊያው በአንድ ጊዜ 104 ታካሚዎችንና አስታማሚዎቻቸውን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን 40 ያህል ታካሚዎችንና አስታማሚዎቻቸውን እያስተናገደ ነው፡፡

ጎጆ አቅም የለሽ የሕሙማን ማረፊያ የተቋቋመው ተከታታይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በአቅም ማነስ ምክንያት የገጠማቸውን ችግሮች በተረዱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወጣት ሐኪሞች ነው፡፡ ዓላማው በአቅም ማነስ ምክንያትና መጠጊያ ዘመድ በማጣት በየበረንዳው ውለው እያደሩ የረዥም ጊዜ ሕክምና የሚከታተሉ ታካሚዎችን ለመታደግ ነው፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው ፈቃደኛ የሆኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦች በቋሚነት በየወሩ በሚለግሱት ገንዘብ ነው፡፡

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ በሚገኘው ተክለሃይማኖት ጤና ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቋቋመው ይህ ማረፊያ ባለአንድ ፎቅ ሕንፃ ሲሆን፣ ስምንት የመኝታ ክፍሎች፣ የምግብ ማብሰያ (ማዕድ ቤት)፣ ሁለት የጋራ መፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች፣ እንዲሁም መዝናኛ አዳራሽ አለው፡፡

በእያንዳንዱ መኝታ ክፍልም ስድስት ርብራብ አልጋዎች፣ የልብስ ማስቀመጫ ቁም ሳጥን ያለ ሲሆን፣ በየኮሪደሩም የመጠጥ ውኃ ማጣሪያ ተቀምጧል፡፡ ማረፊያው ውስጥ ጫት መቃምና ትምባሆ ማጨስ አጥብቆ የተከለከለ ነው፡፡ ከፊት ለፊቱም ሰፋ ያለ መናፈሻ አለው፡፡

ይህ ዓይነቱን ሕንፃ በነፃ ገንብተው ለድርጅቱ ያስረከቡት የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የቃሊቲ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ በጋራ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...