Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ፎሌ በአያና ጩጳ››

‹‹ፎሌ በአያና ጩጳ››

ቀን:

ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የሃይማኖት በዓላት ውስጥ ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ የገና ጾም ከተፈታ ሁለት ሳምንታት በኋላ መላውን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚያሰባስብ ክብረ በዓል ጥምቀት ቀዳሚ ነው፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎችም የአካባቢውን ወግና ሥርዓት በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይስተዋላል፡፡ በምሥራቅ አርሲ ዞን ከጥምቀት በዓል ጎን ለጎን ‹‹ፎሌ›› ተጨማሪ ድምቀትን ይሰጣል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ገዳ ሥርዓት ውስጥ ፎሌ አንዱ ነው፡፡ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ገዳ ስምንት እርከኖች ሲኖሩት ፎሌ በሦስተኛነት ደረጃ ይቀመጣል፡፡ በነዚህ የስምንት ዓመታት ቆይታ ውስጥ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ እስኪ ሞት ድረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ ግዴታዎች መወጣት ይኖርበታል፡፡

ፎሌ በገዳ ከተቀመጡት እርከኖች ሦስተኛ ላይ ሲሆን፣ ዕድሜያቸውም ከ16 እስከ 24 መካከል ይገኛሉ፡፡

በየስምንት ዓመት ከሚከበረው የገዳ ሥርዓት ባሻገር በተለይ በጥምቀት ወቅት  የሚከናወነው የፎሌ ሥርዓት የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ አከባበር አለው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቆጂ ከተማ የጥምቀት (አያና ጩ) በዓል በከተማዋ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ በገጠር አካባቢ የሚገኙት በከተራው ቀን ወደ ታቦቱ ማደሪያ ሲያመሩ በፎሌዎቹ ድባብ ታጅበው ነው፡፡  ፎሌ ረዘምና ቀጠን ያለ በተለያዩ ቀለማት ያጌጠ ቀጭን ዱላ በመያዝ ጋሻ፣ የዝንጀሮ ፀጉርን ጭንቅላቱ ላይ በማድረግ እንዲሁም የነብር ቆዳና የጥሩንባ ድምፅ በማሰማት ዕለቱን ያደምቃል፡፡

ዕለቱን በጭፈራ ከማድመቅ ባሻገር በገዳ ሥርዓት ፎሌ ሥርዓቱን እንዲከታተል፣ እንዲጠብቅ፣ እንዲያወግዝና እንዲተች ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ለምሳሌ ባሏ የሞተባትን ሴት ከሌላ ወንድ ጋር ብትታይ ‹‹ሲገባ›› ብለው ለኅብረተሰቡ እንደሚያሳውቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ሲገባ ማለት ተከረቸም እንደማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጌጣ ጌጦች የተዋቡት ፎሌዎች ታቦቱን ከተሳለሙ በኋላ ታቦቱን ሊሸኝ ወደመጣው ሕዝብ መሀል ሆነው በማሞገስ፣ በማመስገንና በመተቸት ደምቀው ይውላሉ፡፡

የበቆጂ ከተማ ተወላጅ የሆነው ጸሐፊና የሕግ ባለሙያ ውብሸት ስጦታው በየዓመቱ ባህሉን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ አካባቢው ያቀናል፡፡ ‹‹ፎሌ የባህሉ ድምቀት፣ ትውፊትና እምነት እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ማሳያ ነው፤›› በማለት አስተያየቱን ይሰነዝራል፡፡ እንደየአካባቢው የፎሌ አከባበር የተለየ ቢሆንም መሠረቱ ግን ገዳ እንደሆነ አቶ ውብሸት ያስረዳል፡፡

በበቆጂ ከተማ የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ የሚታደመው ውብሸት የፎሌዎች ምርቃትና ሙገሳ አይረሳኝም ይላል፡፡ ሁሉም ወጣት ፎሌ ሆኖ መቀጠል ባይችልም እስከ 40 ዓመቱ ግን አገልግሎ ለአንጋፋው (ታላቅ) አስረክቦ መውጣትና ወደ ቀጣዩ የገዳ እርከን መሸጋገር ይችላል፡፡

በገዳ ሥርዓት ፎሌ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ጥፋት ቢያጠፋ እንኳን ከጥፋቱ እንዲቆጠብ ይነገረዋል እንጂ ቅጣት አይተላለፍበትም፡፡

በተለይ በገዳ ሥርዓት ፎሌ እርከን ላይ የሚገኙ አካባቢያቸውን በመጠበቅና የአካባቢውን የቤት እንስሳ ከአራዊት መጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ይባላል፡፡

ፎሌ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ለሚከሰት የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ሲሆን ተስተውሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የደረሰውን ረብሻ ተከትሎ ዘንድሮም ክብረ በዓሉ ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ፎሌ ኃላፊነቱን ወስዶ በሰላም እንዲጠናቀቅ የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል፡፡

ለሦስት ቀናት በየቆየው የበቆጂ የጥምቀት በዓል አከባበር ፎሌ ገጠር ድረስ ጥሩንባውን እያሰማና እየጨፈረ ሸኝቶ ከተመለሰ በኋላ የአካባቢው ገበሬ ጠላ ጠምቆና ከብት አርዶ ደግሶ ስለሚጠብቀው ወደ ጎጆ ቤት ያመራል፡፡

በጋሻ፣ በጌጣ ጌጦች እንዲሁም በምርቃት የታጀበ ጭፈራቸውን እያዜሙ ቦታ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ መደብ ላይ በማረፍ ከፊታቸው በተቀመጠ ወንበር ላይ ጥሬ ሥጋ፣ ጥብስ፣ ዳቦ፣ ጠላና አረቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ አንጋፋው (ታላቅ) አገሩን፣ ባህሉን፣ ሕዝቡና መሬቱን፣ ምርቱንና ዝናቡን እንዲሁም ደግሶ የተቀበላቸውን ከመረቁ በኋላ ወደ ምግቡ ይመለሳሉ፡፡

በበቆጂ ከተማ ወጣ ብለው የሚገኙት ቤተ ክርስቲያናት በዲሚካኤል፣ እግዚአብሔር አብ ባለወልድ፣ መድኃኔ ዓለምና ቅድስት ማርያም የመሳሰሉ ቤተ ክርስቲያናት ለዘመናት በፎሌ ደምቀው እንደተከበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ይመሰክራሉ፡፡ በገዳ ሥርዓት የትኛውንም እምነት መከተል እንደሚቻል የተለያየ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የፎሌ ሥርዓት ከበዓላት አከባበር ባሻገር በደስታ፣ በሐዘን፣ በደቦ ሥራና በአደን ላይም ይከናወናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ይተላለፋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...