Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተናግረን ነበረ ሰሚ አጣን እንጂ!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ በግራ ጎኔ ተኝቼ ማን ወክሎኝ እንደሆነ አላውቅም፣ ማንን እንደ ወከልኩም እንጃ፣ በአንዴ ከደላላነት ወደ ፖለቲከኝነት ተመንድጌ ለምርጫ ስወዳደር በህልሜ ሳይ ቀውጢ ጩኸት ሰማሁ። ‹‹ገና ሳልመረጥ ይኼ ሕዝብ የሚጮህብኝ ምን አድርጌው ነው?›› ስል ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ኧረ ውረድ!›› ስትል በሰመመን እሰማታለሁ። ‹‹ገና ሥልጣን ላይ ሳልወጣ ምን ብዬ ነው የምወርደው?›› ስላት ብርድ ልብሱን ገፈፈችኝ። የጥር ስስ ንፋስ ላዬ ላይ ሽው ሲል ብድግ አልኩ። ለካ ጩኸቱ ከጎረቤት ነው። ‹‹ህልምና ቅዠት መምታታታቸው ሳያንስ በምርጫና በተመራጭነት ዕጣ ያለተፈጥሯችን ይጫወቱብን ጀመር ማለት ነው?›› እያልኩ ሮጬ ወጣሁ። ነገር በዝቷል ዘንድሮ። ከነገሩ በጥቂቱ ላጫውታችሁ።

ባይገባኝም ህልሜና ገሃዱ ዓለም ደህና አድርጎ ሲገባኝ፣ የአሜሪካ ዴሞክራሲ እኮ እንደ አፍሪካ አይደለም ማለት ጀምሬያለሀ። ‹የጠቅል አሽከር› ብሎ ነገር እዚያ የለም። በሰማዩ ላይ ሁለት ፀሐይ እንደማይወጣ ሁሉ፣ አንድ ሰው መወከል አለበት እንጂ፣ ሁሉም መንጋጋት እንዴት ይቻለዋል? ጎረቤታችን ሁሌም የአፍሪካንና የአሜሪካን ነገር ካላነፃፀሩ የማይሆንላቸው ናቸው፡፡ ‹‹ትናንትና ቡና ጠርቼዎ ምነው ቀሩ፤›› ብላ በጎን ሐዘናቸውን ልትበርዝ ጣልቃ ትገባላች። በግራና በቀኝ አዋክበን እንባቸውን ካስቆምናቸው በኋላ ለከሰዓት ቡና ተቀጣጥረን እኔና ማንጠግቦሽ ተመልሰን አልጋችን ውስጥ ገባን። ‹‹አይገርምህም?›› ብላ ጀመረች ማንጠግቦሽ። ‹‹ምኑ?›› አልኳት።

‹‹ባሻዬ የዕድሩ ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ትናንትና ነው። ግን ማንም ያወቀ የለም። እኚህ ሴትዮ ዕድሩ ላይ ያላቸው መተማመን ምን ያህል እንደሆነ ታውቃለህ? ባሻዬ እንዳይቀድሙኝ ብቻ እንጂ ስሞትማ ሠርግ አስመስለው እንደሚያስቀብሩኝ አልጠራጠርም ነው የሚሉት፡፡ ግን ይኼው ባሻዬ በትናንትናው ዕለት የዕድሩ ሊቀመንበርነት ምርጫ ለመሸነፍ ጫፍ ላይ ደርሰው በአንድ አብላጫ ድምፅ መመረጣቸውን ሊያውቁ ቀርቶ ለምርጫ መቅረባቸውንም አልሰሙም . . . ›› ስትለኝ ‹‹እ . . . ም፤›› ብዬ ዝም አልኩ። እንኳን ሌላው እኔ ራሴ ባሻዬ ለምርጫ መቅረባቸውን፣ ቀርበው መወዳደራቸውን ስላልሰማሁ አፍሬያለሁ። ይኼኔ ባሻዬ አሜሪካዊ ቢሆኑ ኖሮ ብዬ ሳስብ፣ ለሊቀመንበርነት ቀርቶ ለመኖር በእግዜር መታሰባቸውን ሳስብ ቀኑ መሽቶ እንደሚነጋ ታየኝና መኖሬን ጠላሁት። እንኳንም ግን ሕይወት በሰው ልጅ አብላጫ ድምፅ የሚወሰንና የሚሻር አልሆነ አትሉም!

እናላችሁ ስለዚህ ገንዘብን በውጭ ምንዛሪ ስለማሸሽ ነገር ሰሞኑን ብዙ ስሰማ ነበር። ያለመተዋወቅን ጉዳይ ሳነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የትናንትን አያድርገውና ከአምስት ከስድስት ዓመታት በፊት አዲስ አበባን በቀበሌያቸው ስም በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ ማፊያዎች እንደነበሩ የምታውቁ ታውቃላችሁ። መቼም አልሰማንም አላየንም ባይ ካለ ይገርመኛል። ስንቱ ሚስቱን በአደባባይ ተቀማ? ስንቱ ገንዘቡን ተነጠቀ? ስንት ልጃገረዶች ያለፍላጎታቸው ተገደው ተደፈሩ? ስንቱ የፍትሕ ያለህ ብሎ እሪ አለ? የሰማ አልነበረም። ምክንያቱስ ካላችሁ አለመተዋወቅ። ሕዝቡ ያውቃቸዋል። አውቋቸው ይፈራቸዋል። በተረፈ መንግሥት፣ ‹‹ኧረ በሕግ አምላክ! አንድ በልልን!›› ሲባል ‹ምንድነው የምታወሩት?› ይል ነበር አሉ። አሉ ነው እንግዲህ። የአሉባልታ መብታችን መቼም አልታገደም። አንድ ቀን ከእነዚያ ጎረምሶች መሀል አንደኛው ይሞታል አሉ። ኮንሰርት ይዘጋጅ ይባላል። ሬዲዮና ቴሌቪዥን በእጃቸው ነው አሉ። ባነር ተሰቀለ፡፡ ፍላየር ተበተነ። በቀረው ደግሞ ማታ ማታ እየዞሩ በየመሸታ ቤቱ ትኬት መሸጡን ተያያዙት።

እንግዲህ ስላለመተዋወቅ አይደል የምናወራው? ያው እንደለመደው አንዱ ጥጋበኛ በዕድሜ ጠና ወደሚል ወደ አንድ ሰው ጠጋ ብሎ 20 ቲኬት ያስቀምጣል። ‹‹ምንድነው?›› ይላል ሰውየው። ‹‹ጓደኛችን በድንገት ስለሞተ ለእሱ መታሠቢያ ኮንሰርት እያዘጋጀን ነውና አሁን ወሬ ሳታበዛ የ20 ትኬት ዋጋ አምስት ሺሕ ብር ዱብ በል . . . ›› ይላል አሉ። ጉድ እኮ ነው። ይኼ ሁሉ እንግዲህ ተወልደን ባደግንባት አዲስ አበባ ነው። ሰውዬው፣ ‹‹እኔ ሊገባኝ አልቻለም፣ ይኼ ጓደኛችሁ ለአገር ያበረከተው አስተዋፅኦ ምንድነው? ማነው ስሙ? ይታወቃል?›› ብሎ ሲጠይቅ አሉ ያ ወሮበላ የትም እንደለመደው፣ ‹‹አቦ ምን ወሬ ታበዛለህ? ዱብ በል ብያለሁ ዱብ በል . . . ›› ብሎ ማስፈራራት። ለካስ ይኼን ሁሉ የሚባባለው በከፍተኛ ደረጃ ባለሥልጣን ጋር ኖሯል። ዋጋውን አገኘ። እኔማ በወሬ በወሬ ይኼን ጉድ ስሰማ ወይ አለመተዋወቅ ጣጣው እያልኩ አገሬን የወረራትን የትዕቢት ቫይረስ ረገምኩ። ዞሮ ዞሮ ግን ለማለት የፈለግኩት ካልተዋወቅን፣ ካልተጠናናን በቃ አንከባበርም ማለት ነው? ሕግ ብቻ የማይገዛን ለምንድነው? ኧረ ከምን ይሆን የተፈጠርነው? ንገሩኝማ በሞቴ!

እናላችሁ፣ ‹‹ሰበቡ ነጠላ ለብሼ . . . ›› የምትለዋን ዜማ ኤፍኤሞቻችን ለምን እንደረሷት እንጃ። ግን ይኼ የእኛ ሥራማ የማያሳይ፣ የማያሰማው ነገር የለም። ደላላነቴን የምወደው ከማገኘው ሽቀላ የምወስደው ኮርስ ብዛት እያደር እየጨመረ እንደሚሄድ ካወቅኩ በኋላ ነው። እውነት እውነት እላችኋላሁ ሕይወት ትልቅ ትምህርት ቤት ናት። ደላላነት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ በሉት። ሕገወጥ ካልሆናችሁ ማለቴ ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ምን ደላላው ብቻ? ሌላውም በሕገወጥና በሕግ አክባሪ ሁለት ጎራ የተከፈለ ነው። ኧረ ምን ተማሪው ብቻ? ሹመኛውስ? ምን ሹመኛው ብቻ? ነጋዴውስ? ኧረ ምን ነጋዴው ብቻ? አከራዩስ? ተከራዩስ? እያላችሁ በጎደለ እንድትሞሉ ለእናንተ ልተወው እንጂ ያደክማል። ያልከፈለ ልብና ያልተከፈለ አዕምሮ ያለው ሰው ማግኘት ከባድ ሆኗላ። ‹የት ሄጄ ልፈንዳ› ሲሉ መዋል ሆኗል በልጅነታችን ሽበት በሽበት የሚያደርገን ያለው። እኔ ልሙት።

ብቻ እንዲያው ምን ብታይ፣ ምን ብትሰማ ይሆን እንዲህ ልትፈነዳ የደረስከው? ብላችሁ ጠይቁኝ። ጎሽ። ከመጠያየቅ ብዙ እንማማር ነበር እኮ በደጉ ጊዜ። እንዲህ እንደ ዛሬው ማን ስለሆንክ? ምን ስለሆንክ? ይሏት ንቀት ሳታበጣብጠንና ሳታናንቀን በፊት ነው የማወራችሁ። እና እናንተ ስትጠይቁኝ እኔ ስመልስ በቀደም አባትና ልጅ በልጅየው ስም ያለን የተከራየ መኖሪያ ቤት እንዳሻሽጥላቸው ያገኙኛል። ያላቸው መግባባት፣ መናበብና መረዳዳት እኩዮች እንጂ አባትና ልጅ አይመስሉም። ብዙ አባትና ልጅ እናውቃለና። እና እኔም ተፍ ተፍ ብዬ ቤቱን አሸጥኩት። ምሳ ካልጋበዝንህ ሲሉኝ ምን ገዶኝ አልኩ። ልክ መኪናቸው ውስጥ እንደ ገባሁ ደግሞ ኮሚሽኔን አስታቀፉኝ። ቅብርር የጃንሆይ ዘር ማለትስ ዛሬ ነው እላለሁ በልቤ። ቻፓ በጊዜ ወደ ኪስ ከገባ፣ ከዘንድሮ የምግብ ቤቶች ዋጋ መናር አንፃር ጋባዥ ሲገኝ፣ ከዚህ በላይ ምን ጃ የሚያስብል ነገር ይኖራል ታዲያ?

በሉ እንሰነባበት። የሆድ ነገር ነውና ሆዴን ቆርጦኛል። በዚያ ላይ ግብዣ ነው። የትኛው ክትፎ ቤት ይሆን የምንሄደው? አሃ ለካ ፆም ነው። እያልኩ ሆዴን ሳስብ አባትና ልጅ ስለወርቃማ ቢራና ወርቃማ ትውልድ ማስታወቂያ ሰምተው አንድ አንድ መባባል። ልጅ፣ ‹‹በቅጡ ባልተረዳችሁት ፍልስፍና ገበሬ እንጂ ምንም ዓይነት ወዝ አደር በሌለባት አገር ወዝ አደሩ ያሸንፋል እያላችሁ፣ ዓለም ስቆባችሁ፣ ደግሞ እሱ ሳያንስ ከአብሮ አደጎቻችሁ፣ ከወንድሞቻችሁ ጋር እርስ በርስ ተጫርሳችሁ፣ ወርቃማ ትውልድ ሲሏችሁ፣ ብለውም በብቅል ሲያሟችሁ እንዴት የእኛን ነገር ተውት አትሉም?›› ማለት። አባት፣ ‹‹አንተ ምኑ ገብቶህ፣ ምኑን ዓይተህ፣ ምኑ ተሰምቶህ እንዲህ ትላለህ? ከፋም ለማም የድርሻችንን፣ የገባንን፣ የመሰለንን ያደረግነው ለአገር ነው። ቀስ ብለህ እደግ . . . ›› ብለው ቱግ ማለት።

ይኼ ወደ ለየለት የአባትና ልጅ ማቆሚያ የሌለው ክርክር መውሰድ። እኔ ወርቁም፣ ብሩም፣ ነሐሱም ጠፍቶኝ ሆዴ መጮህ፡፡ ኋላ ምን ይሆናል? ልጅ፣ ‹‹እንዲያውም እዚህ ጋ አውርደኝ፣ የምሄድበት አለ . . . ›› ብሎ መሀል መንገድ ላይ ወርዶ ተነጠለ። አባት በንዴትና በብስጭት መሪ ጨብጠው ሲብከነከኑ ሳይ እንኳን እህል ጥሬ እንደማይቆረጠምላቸው ገብቶኝ፣ ‹‹ግድ የለም ሌላ ቀን እናድርገው። እኔም ሥራ አለብኝ . . . ›› ብዬ ወረድኩ። ኋላ ከባሻዬ ጋር ስንጫወት ነገሩን ባካፍላቸው ድንቅ ብሏቸው ጉድ ሲሉ ቆይተው፣ ‹‹ለነገሩ ስምና ስያሜ ሰጪው ተቀባዩም ተምታቶባቸዋል። እኛስ ባይምታታብን ምን ይገርማል?›› ብለው ዝም አሉ። ተናግረን ነበረ ሰሚ አጣን እንጂ ማለትስ አሁን ነው፡፡ መልካም ሰንበት።

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት