Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየሥነ ጽሑፍ ምሽቶች አበርክቶ

የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች አበርክቶ

ቀን:

የሥነ ጽሑፍ ወዳጆች፣ ስለ ሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮች ሲያስቡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ማስታወሳቸው አይቀርም፡፡ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መገኛ የሆነው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባለው የባህል ማዕከል በርካታ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ተካሂደዋል፡፡ የበርካታ አንጋፋ ጸሐፍት መነሻም ማዕከሉ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ባሻገር የሌሎች ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችም የሥነ ጽሑፍ ምሽቶቹን በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ ምሽቶቹ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች የቀረቡባቸው እንዲሁም ዛሬ ላይ በሥነ ጽሑፍ ስመጥር የሆኑ ባለሙያዎች የወጡባቸውም ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ በዕውቀቱ ሥዩምን ማንሳት ይቻላል፡፡

የሩሲያን ባህል ማዕከል (ፑሽኪን) ሌላው በሥነ ጽሑፍ ቤተሶቦች ዘንድ የማይዘነጋ ቦታ ነው፡፡ የፑሽኪን የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች እንደ ባህል ማዕከል ሁሉ የብዙዎችን ቀልብ ይገዙ ነበር፡፡ በርካታ ወጣት ገጣሚዎች የሥነ ጽሑፍ ችሎታቸውን በማዳበር ረገድ ፑሽኪንን ይጠቅሳሉ፡፡

- Advertisement -

ፑሽኪን የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ ያላቸው እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ አድናቂዎችም መገናኛ ሆኖ ለዓመታት አገልግሏል፡፡ እንደ ባህል ማዕከልና ፑሽኪን ተከታታይነት ባይኖራቸውም፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና በኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማኅበርም ይዘጋጁ ነበር፡፡

የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን በማዘጋጀት ከተቋሞች ጎን ለጎን በግል ተነሳሽነታቸው መርሐ ግብሮች ያሰናዱም ይጠቀሳሉ፡፡ በወር አንድ ጊዜ አንዳንዴም ሁለቴ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን ማካሄድ ጀምረው ያቋረጡም አሉ፡፡

የመጻሕፍት ምረቃ፣ የመጻሕፍት ዳሰሳና ውይይት እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ከሚጠቀሱ ክንውኖች መካከል ናቸው፡፡ ሥነ ጽሑፍ ይቀርብባቸዋል፡፡ ስለ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ውይይትም ይካሄድባቸዋል፡፡

የጦቢያ ግጥምን በጃዝ ወርሐዊ የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብር ተጠቃሽ ከሆኑ የቅርብ ጊዜ ዝግጅቶች አንዱ ነው፡፡ አበባው መላኩ፣ ኤፍሬም ሥዩም፣ ምሥራቅ ተረፈና በረከት በላይነህ በመርሐ ግብሩ ከሚጠቀሱ ገጣሚዎች መካከል ናቸው፡፡ ግጥምን በጃዝ ማቅረብ የበለጠ እንዲለመድ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሥነ ጽሑፍ በመዳሰስ ዕውቅናን ያተረፈው በአጭር ጊዜ ነበር፡፡

የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ከዝግጅቱ መጀመሪያ ሰዓት ቀድመው በመገኘት ቦታ ይይዛሉ፡፡ መርሐ ግብሩ በሚካሄድበት አዳራሽ ወንበር ማግኘት ያልቻሉ፣ በአዳራሹ ኮሪደርና አዳራሹ ውስጥ ወለል ላይ ተቀምጠውም ዝግጅቱን ይከታተላሉ፡፡ መርሐ ግብሩ እንደ ‹‹እያዩ ፈንገስ›› ያለውን የአንድ ሰው ተውኔት ጨምሮ ብዙ ታዋቂ መሰናዶዎች በማካተቱ የበርካቶችን ትኩረት መሳቡም ይታወሳል፡፡

ከፑሽኪን የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብር አንስቶ የጦቢያ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን አዘውትራ ትካፈል የነበረው ማህሌት አጥናፉ ናት፡፡ በቢዝነስ ዘርፍ ብትሰማራም ሥነ ጽሑፍ ስለምትወድ መሰል መርሐ ግብሮች አያመልጧትም፡፡ ‹‹ሥነ ጽሑፍ የማኅበረሰቡን ስሜት በማንፀባረቅ ያለውን ሚና ለመገንዘብ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን መከታተል በቂ ነው፤›› ትላለች፡፡

የሥነ ጽሑፍ ምሽቶቹ መልዕክት አዘል የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ለሕዝብ የማድረስ ጠቀሜታ እንዳላቸው ታምናለች፡፡ በተለይም ወጣት ጸሐፍት ሥራዎቻቸውን በመድረክ እንዲያቀርቡና አሳትመው ለሕዝብ እንዲያደርሱም ይረዳሉ ትላለች፡፡ ‹‹ፑሽኪን ይቀርቡ የነበሩ ጽሑፎች ጠንካራ ነበሩ፡፡ ያኔ ግጥም ያቀርቡ ከነበሩት ብዙዎቹ መጽሐፍ አሳትመዋል፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ማህሌት፣ ጦቢያ ግጥም በጃዝን በየወሩ ከሚታደሙ መካከል ትገኝበታለች፡፡ በመርሐ ግብሩ ከቀረቡ መሰናዶዎች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትችት ያዘሉትን ግጥሞችና ወጎች ትጠቅሳለች፡፡ ‹‹መሰል መድረኮች በብዛት አይገኙም፡፡ የማኅበረሰቡን ስሜት የሚያንፀባርቁ ሲሆኑ፣ ታዳሚዎችም የመካፈል ጉጉት ያድርባቸዋል፤›› ትላለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ሥነ ጽሑፍ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ነቅሶ ከማውጣት ባሻገር የመፍትሄ አቅጣጫ ማመላከት አለበት፡፡ የተለያዩ መጻሕፍት ታትመው ገበያ ላይ መዋላቸው አንድ መንገድ ቢሆንም ከግላዊ ንባብ በተጨማሪ የቡድን ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሐሳቦችን ለማንሳት የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች እንደሚጠቅሙም ትናገራለች፡፡

‹‹የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በየጊዜው ሲጀመሩና ሲቋረጡ አያለሁ፡፡ አዘጋጆቹ ቀጣይነትን ከግምት ባስገባ ሁኔታ መጀመር አለባቸው፤›› ትላለች፡፡ መሰል መርሐ ግብሮች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም መካሄዳቸውም መበረታታት እንደሚገባውም ታክላለች፡፡

የግጥምን በጃዝ ሐሳብ ሳይስፋፋ በፊት የነበሩትን የፑሽኪን፣ የባህል ማዕከልና የደራሲያን ማኅበራት የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች የሚያጣቅሰው ለአንድ ዓመት ጦቢያ ግጥምን በጃዝን ካዘጋጁት አንዱ በፍቃዱ ዓባይ ነው፡፡ ቀደምቱ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ጠንካራ እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ ብዙዎቹ የሥነ ጽሑፍ ፍቅር ባላቸው ሰዎች እንደሚዘጋጁና እንደ ገቢ ማግኛ ከመታየት ይልቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መድረክ ማግኘታቸው እንደሚጎላም ይናገራል፡፡

ግጥም በጃዝን ያካተቱ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች እየገነኑ ሲመጡ ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ተደምጠዋል፡፡ በአንድ ወገን ግጥም ከሙዚቃ ጋር ተጣጥሞ መቅረቡን የወደዱ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ግጥም የራሱ ዜማና ቀለም ስለላው ያለ ሙዚቃ መቅረብ አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ሆኖም ወቅቱ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በርካታ ታዳሚዎችን ያፈሩበት ነበር፡፡

የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ማግኘታቸው ለዕድገታቸው እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ አንዱ ነው፡፡ ‹‹በመርሐ ግብሮቹ ሰዎች መናገር የሚፈልጉትን ነገር ግን ያልቻሉትን ጸሐፍቱ ስለሚናገሩ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ ሄደ፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ በመንግሥት ላይ ያሉ ቅሬታዎች ወይም ሌሎችም መባል  ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች በሥነ ጽሑፍ መቅረባቸው በርካታ ታዳሚዎችን ስቧል፡፡

‹‹ባለፈው አንድ ዓመት የኢትዮጵያን አንድነትን የሚሰብኩ ሥራዎች ለማቅረብ ሞክረናል፤›› ይላል፡፡ ታዳሚዎች እንዲባሉላቸው የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ገጣሚዎች ወይም ዲስኩር አቅራቢዎች ማለት የሚፈልጉትም ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባ ያምናል፡፡ ጽሑፎቹ ወቀሳን የሚያስተጋቡ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሔ ሐሳብ ጠቋሚ ጭምር መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ‹‹ታዳሚው የሚመራው መርሐ ግብር ሳይሆን የጥበብ ሰዎች የሚመሩት መሆን አለበት፤›› ሲልም ያስረዳል፡፡

በፍቃዱ እንደሚለው፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች መበራከት ለዘርፉ አስተዋፅኦ ቢኖረውም፣ አንዱ መርሐ ግብር ከሌላው የሚለይበት ዝግጅት ይዞ መምጣት አለበት፡፡ ከወራት በኋላ የሚጀምረው መርሐ ግብር ልዩ ልዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት እንደሚሆን ያስረዳል፡፡ በየጊዜው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት ለውይይትና ክርክር መነሻ የሚሆኑ ነጥቦች በመድረኩ እንደሚደመጡም ያክላል፡፡

በኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዙሪያ የሚካሄዱ ውይይቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ አከራካሪ ነጥቦችን በማንሳት የተለያዩ ወገኖች ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ሁሉም የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ተመሳሳይ ይዘትና ቅርጽ ከሚኖራቸው አንዳቸው ከሌላቸው የተለያዩ መሆን እንዳለባቸውም ያስረዳል፡፡

ተመሳሳይ አስተያየት የሰጠን የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን አዘውትሮ የሚከታተለው ስመኝ እሸቱ ነው፡፡ ‹‹መርሐ ግብሮቹ ለታዳሚዎች አንዳች ነገር የሚጨምሩ መሆን የሚችሉት አንዳቸው ከተቀረው የተለዩ ሲሆኑ ነው፤›› ይላል፡፡ ግጥምን ጨምሮ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥልቶች መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚቻል ያክላል፡፡

የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮች ሲታቀዱ፣ ሥነ ጽሑፍን ኅብረተሰቡ ጋር ከማድረስ ባሻገር የጸሐፍትን ቁጥር ማብዛትን ታሳቢ ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል፣ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የሚቀርቡባቸው እንዲሁም በጸሐፊዎች መካከል ውድድር የሚካሄድባቸው መርሐ ግብሮች መኖራቸው ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹የኮሌጅ ቀን ግጥሞች›› የመሰሉ ስብስቦች፣ የመሰል መርሐ ግብሮች ውጤት መሆናቸውንም ያነሳል፡፡

በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብሮቹን ከመታደም በተጨማሪ ሽልማት በመስጠት ያበረታቱም ነበር፡፡ በአሁን ወቅት የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በራስ ሆቴል፣ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ወይም ለሌሎች ሆቴሎች ይከናወናሉ፡፡ ስመኝ እንደሚለው፣ መርሐ ግብሮቹ በባህል ማዕከሎች፣ በቴአትር ቤቶች ወይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚቀርቡበት ዕድል ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡

‹‹የሥነ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብና በሌሎችም የጥበቡ ዘርፎች የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ብዙኃኑን ቢስቡ ጥሩ ነው፤›› ይላላ፡፡ ለምሳሌ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ወደ 1,500 የሚጠጋ ታዳሚ የሚያገኙበት ወቅት አለ፡፡ ሆኖም ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር ብዙ ተሳታፊ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ መርሐ ግብሮቹ በቦታ ሳይወሰኑ በተለያዩ አካባቢዎች ቢካሄዱ የተሳታፊዎችን ቁጥር መጨመር እንደሚቻልም ያምናል፡፡

ኅብረ ትርኢት በሚል ስያሜ የሚዘጋጀው የኪነ ጥበብ ምሽት ወራትን ያስቆጠረ መርሐ ግብር ነው፡፡ ግጥም በጃዝ፣ ወግ፣ ዲስኩር፣ የባህል ሙዚቃ፣ ተውኔትና ሌሎችም መርሐ ገብሮች ይካተታሉ፡፡

ድርና ማግ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ከተጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥሯል፡፡ አዘጋጁ ጌታቸው ዓለሙ እንደተናገረው፣ መርሐ ግብሩ በባህልና ኪነ ጥበብ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ የየወሩ የመጨረሻው ሐሙስ ዕለት ይካሄዳል፡፡ በዚህ ወር መርሐ ግብሩ ሁለተኛ ዙሩን ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋረንሲስ ሆቴል አካሂዷል፡፡

በአዘጋጁ ገለጻ፣ መርሐ ግብሩ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ሥራቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡ የባህል ሙዚቃ፣ ዲስኩር፣ ወግና ሲትኮም (አስቂኝ ተውኔት) የመርሐ ግብሩ አካል ናቸው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ ሲጠነሰስ ጸሐፍት ሥራዎቻቸውን ለታዳሚ የሚያደርሱበት መድረክ ማመቻቸትን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ድርና ማግ፣ ባለሙያዎች ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ በማመቻቸት ውስጥ ታዳሚዎችን ለሥነ ጽሑፍ ቅርብ ማድረግንም ግቡ አድርጓል፡፡ ‹‹አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ነገረ ጥበባቸውን ለማቅረብ የሚችሉበትን መድረክ ለማመቻቸትና ብሎም ምሽቱን የጥበብ ቤተሰቦች ከሚመርጧቸው የመዝናኛ ስፍራዎች  አንዱ ማድረግ ዓላማችን ነው፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡

በሥነ ጽሑፍ ምሽቱ ሁለተኛ ዙር መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፣ ሠዓሊና ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኰንን፣ ደራሲና ሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ተዋናይ ሰሎሞን ቦጋለ እንዲሁም ገጣሚያኑ ባዩልኝ አያሌውና ታገል ሰይፉ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በሚቀጥሉት ወራትም ሌሎች ባለሙያዎች መድረኩን ይረከባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...