Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሄደው የሚሠሩባቸው የዓረብ አገሮች ተለዩ

ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሄደው የሚሠሩባቸው የዓረብ አገሮች ተለዩ

ቀን:

ወደ ዓረብ አገሮች በብዛት እየሄዱ በቤት ሠራተኝነት በሚቀጠሩ ዜጎች ላይ በ2005 ዓ.ም. መጨረሻና 2006 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ በደረሰ የሞት፣ ከባድ የአካል ጉዳትና እንግልት ሳቢያ መንግሥት ጥሎት የነበረውን የጉዞ ዕገዳ ከተነሳ በኋላ፣ በሕጋዊ መንገድ ሄደው መሥራት ለሚፈልጉ ዜጎች መንግሥት አገሮቹን ለይቶ አስታወቀ፡፡

መንግሥት የሁለትዮሽ ድርድርና ስምምነት የተፈራረመባቸው አገሮች ለጊዜው ኩዌት፣ ኳታርና ጆርዳን ብቻ በመሆናቸው ዜጎችም መሄድ የሚችሉት ወደነዚህ አገሮች ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከሌሎች አገሮች ጋር ገና በመነጋገር ላይ መሆኑን፣ ከሊባኖስ ጋር ድርድሩ ተጠናቆ ፊርማ ብቻ እንደሚቀር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በርካታ ሠራተኞች ከምትፈልገው ሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈርሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለቀረበ በቅርብ ቀን ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ጥሎት የነበረው የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ዕገዳን እንዲያነሳ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዕገዳውን ማንሳቱን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ዕገዳው ከተነሳ በኋላ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አጠቃላይ ስለአሠራሩ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሚኒስቴሩ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋናው አድማሱ፣ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራና የሰው ኃይል ጥናት ሥራ ሥምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አበበ ኃይሌ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ላይ ዕግድ የጣለው ነባሩ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመርያና ውስብስብ የአሠራር ሒደት ችግር በማስከተሉ ነው፡፡ ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉን፣ አካላቸው መጉደሉን፣ ለእንግልትና ለተለያዩ ችግሮች በመዳረጋቸው ችግሩን ለማስወገድ ዕገዳው መጣሉን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ኃላፊዎቹ ገልጸው፣ ሁሉንም ችግሮች ለመቅረፍ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ የነበረው የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 632/2001ን መቀየር እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይህም ተግባራዊ ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መቀየሩን አስረድተዋል፡፡ አዋጁን ለማውጣትና ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ መፍጀቱንና ይህም የሆነው ከፌዴራል እስከ ክልሎች ድረስ ያለውን አሠራር በመፈተሽ፣ የነበሩትን በርካታ ክፍተቶች በመሙላት፣ አደረጃጀቱንና አሠራሩን ወጥ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት እንደ ትንሽ ሥራ ተቆጥሮ በሌላ ሥራ ላይ ተደርቦ ይሠራ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዎቹ፣ አሁን ግን ለብቻው እንደ አዲስ ተዋቅሮና በጄኔራል ዳይሬክተር የሚመራ ሆኖ ሁለት ዳይሬክተሮችና ከ100 በላይ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፌዴራሉን መነሻ በማድረግ በክልልም አደረጃጀት መፈጠሩንና ሥራው በአገር ደረጃ የሚሠራ በመሆኑ፣ ባለድርሻ አካላት አባል የሆኑበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተደራጅቶ እየተመራና ቁጥጥርም የሚደረግበት መሆኑን አክለዋል፡፡ የውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎችን በሚመለከት አቶ ብርሃኑ እንደገለጹት፣ ከ2006 ዓ.ም. በፊት 497 ኤጀንሲዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሕጋዊ መንገዱን ጠብቀው የሚሠሩ ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ግን በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥቷቸው ከሦስት ጊዜ በላይ ዕግድ ተጥሎባቸው የነበሩ 97 ኤጀንሲዎች በአዲሱ አሠራር እንዳይቀጥሉ መሰረዛቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የአዲሱን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ 980 ኤጀንሲዎች ተመዝግበው የተለያዩ ቅፆችን መውሰዳቸውንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

የተመዘገቡት በርካታ አመልካቾች ቢሆኑም፣ በሕጉ መሠረት የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው የብቃት ማረግገጫ የወሰዱት 20 ኤጀንሲዎች ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከ90 በላይ የሚሆኑ ኤጀንሲዎችም ብዙ መሥፈርቶችን አሟልተው ጥቂት ነገሮች ብቻ እንደቀሯቸውና በቅርቡ የብቃት ማረጋገጫ ሊያገኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ያገኙ ኤጀንሲዎች ከሚኒስቴሩ የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም የተሳሰሩ፣ በሃይማኖት ጭምር አንድነት ያላቸውና ቋንቋን መሠረታዊ መመዘኛ ያደረጉ ናቸው ስለመባሉ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ወደዚህ ሥራ ለመምጣት ዘመድ አዝማድ አያስፈልግም፡፡ የምንጫወተው በዜጎች ሕይወትና በአገር ገጽታ ላይ ነው፤›› በማለት ጥቅማ ጥቅምና ልዩ ግንኙነት ቦታ የላቸውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኤጀንሲዎች በዝግ ሒሳብ 100,000 ዶላር እንዲያስቀምጡ በአዋጅ ጭምር መደንገጉ ተገቢ አይደለም ስለመባሉ በሰጡት ምላሽ፣ ሁሉም ኤጀንሲዎች ያለምንም ችግር እያስቀመጡ የባንክ መግለጫ ማምጣታቸውንና እንደ ችግር እንዳልታየ አስረድተዋል፡፡

አሠራሩን በሚመለከት አቶ ብርሃኑ እንዳስረዱት፣ የአገር ውስጥ ኤጀንሲዎች በሕጉ የተቀመጡትን መሥፈርቶች በፍጥነት የሚጨርሱበት አሠራር ተቀምጧል፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ ኤጀንሲዎች አገር ውስጥ ካለው ኤጀንሲ ጋር የሚያደርጓቸው ውሎችና በውጭ አገር ስላለው ሥራ ትክክለኛነት፣ በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆንስላዎች ለመክፈት ዝግጅት አጠናቋል ተብሏል) ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በዚህ መሠረት እስካሁን ይህንን ደረጃ ያለፉና ብቃታቸው የተረጋገጠው ኤጀንሲዎች 20 ብቻ መሆናቸውን በድጋሚ አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ዝግጅትን በሚመለከት ማንኛውም ወደ ውጭ አገር ሄዶ ለመሥራት የሚፈልግ ዜጋ እስከ ስምንተኛ ክፍል የተማረ መሆን እንዳለበትና ዋና መሥፈርት መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ ስምንተኛ ክፍል ማጠናቀቁ የተረጋገጠ ተመልማይ ከአንድ እስከ ሦስት ወራት የሚፈጅ የክህሎት ሥልጠና ወስዶ በሲኦሲ ብቃቱ መረጋገጥ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ሥልጠናው የሚሄዱበትን አገር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ሁኔታዎችንም የሚያስገነዝብ በመሆኑ፣ በዜጎች ላይ የሚፈጥረውን ብዥታ የሚቀርፍ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ሕጋዊ የሰዎች ዝውውር በሕጋዊ መንገድ ሲከናወን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ያስቀራል የሚል እምነት ባይኖርም ‹‹በእጅጉ ይቀንሳል›› ያሉት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ ወደ ውጭ መላክን መንግሥት የማያበረታት ቢሆንም ዜጎች ተዘዋውረው የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማክበር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ለደኅንነታቸው ሕጋዊ መንገድን ምርጫቸው እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናን በሚመለከት የገለጹት አቶ ብርሃኑ በክልል ጭምር 40 የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት መዘጋጀታቸውን፣ መምህራንም የአሠልጣኝነት ሥልጠና ወስደው ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዜጎች ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊት የጤና ምርመራ ማድረግ ስላለባቸው፣ በባህረ ሰላጤው አገሮች ምክር ቤት መሥፈርት መሠረት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥፈርቱን አሟልተዋል ያላቸውን 66 የጤና ተቋማት መርጦ መዘጋጀታቸውንም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኤጀንሲዎች ግንኙነታቸው በአሠሪው አገር ካሉ ቀጣሪዎች ጋር እንዳልነበረና ግንኙነታቸው ከወኪሎቻቸው ጋር በመሆኑ ችግር ሲፈጠር መንግሥት፣ ኤጀንሲው፣ ወኪሉና አሠሪዎቹ ያለባቸውን ግዴታና መብት የሚገዛ ሕግ በማስፈለጉ ኢትዮጵያ ያንን ተግባራዊ ማድረጓን አቶ አበበ ኃይሌ አስረድተዋል፡፡

ዜጎች ከተለያዩ ክልሎች አዲስ አበባ መጥተው ወደ ውጭ መሄዳቸውን እንጂ ስለሚገጥማቸው ማንኛውም ነገር እንደማያውቁ ጠቁመው፣ አሁን ግን የክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤቶችን ያሳተፈና 75 በመቶ ምልመላ እዚያው ተጠናቆ የሚመጣ መሆኑን አክለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ለኤጀንሲዎች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ሲሆን፣ ሌሎች መሥፈርቶችን እንደየክልሎቹ ጥያቄ በማሟላት በሁሉም ክልሎች ተዘዋውረው የመሥራት መብት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲዎች ሠራተኞችን የሚመለምሉት በውጭ አገር ካላቸው ወኪል ኤጀንሲ (አንድ ኤጀንሲ በውጭ አገር ሊኖረው የሚችለው ሁለት ወኪል ነው) የሚደርሰው ክፍት የሥራ ድርሻ በቆንስላዎች ተረጋጋጦ ከመጣለት በኋላ መሆኑን አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዲሱ ሕግ በሚደነግገው መሠረት የሚሠራ መሆኑን፣ ፓስፖርት አዲስ አበባ አውጥቶ ሱዳን ቪዛ መጠየቅ ሕገወጥ መሆኑንና ይህም በሁለቱ አገሮች መካከል ባለ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፍትሔ እንደሚያገኝ አስረድተዋል፡፡ ሕገወጥ ደላሎች አሁንም ቢሆን ሕጋዊው መንገድ ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ ነው በማለት ዜጎችን ሊያሳስቱ ስለሚችሉ ኅብረተሰቡ መታገል እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...