በልማት ምክንያት በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ከመሀል አዲስ አበባ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን በድጋሚ ለማቋቋም ጥናት መካሄዱ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ከመሀል ከተማ የተነሱትን ከማቋቋም አኳያ ራሱን የቻለ ጥናት መካሄዱን አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው፣ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አማካይነት የመሀል ከተማ የልማት ተነሺዎችን ማቋቋም የሚያስችል ጥናት መካሄዱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
ነገር ግን ጥናቱ ለካቢኔ ቀርቦ ውይይት እንዳልተደረገበት አቶ ኤፍሬም ገልጸው፣ ውይይቱ ከተደረገ በኋላ አስተዳደሩ በሚሰጠው አቅጣጫ የሚታይ ይሆናል በማለት ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
በድጋሚ ፈርሳ እየተሠራች ያለችው አዲስ አበባ ከተማ በነባር መንደሮችና በማስፋፊያ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን፣ እንዲሁም አርሶ አደሮችን አፈናቅላለች፣ በማፈናቀል ላይም ትገኛለች፡፡
በተለይ በቂ ምትክ ቦታና ካሳ ሳይከፈላቸው ተፈናቅለው ለከፋ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ለገቡ አርሶ አደሮች፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካይነት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
አቶ ኤፍሬም እንደተናገሩት፣ በተያዘው በጀት ዓመት ችግር ውስጥ ያሉ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም 309 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡
እስካሁን ረዘም ላለ ጊዜ የተለያዩ ጥናቶች ሲጠኑ፣ ተቋም ሲደራጅና ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ አርሶ አደሮችን የመለየት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡
አርሶ አደሮችን ለማቋቋም ዘመናዊ ዶሮ ዕርባታ፣ ዘመናዊ ከብት ዕርባታ፣ ካባና የመሳሰሉ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች፣ የብረትና የእንጨት ሥራዎች ውስጥ ለማሠማራት ዲዛይን መሠራቱን አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የእነዚህን ሼዶች ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደሮችን ብቻ በማቋቋም ሳይወሰን፣ በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ የሚገኙ የመሀል ከተማ ተፈናቃዮችን በድጋሚ ለማቋቋም የሚያስችለውን የመጀመርያ ዙር ጥናት ማካሄዱ ታውቋል፡፡ ከመሀል ከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች የተነሱ ነዋሪዎች በከተማ ዳር በተሠሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ የራሳቸው ይዞታ ያላቸው ደግሞ ምትክ መሬትና ካሳ ተሰጥቷቸው ተነስተዋል፡፡ ነገር ግን ኑሮአቸው ከመሻሻል ይልቅ ለከፋ ችግር የተዳረገባቸው ነዋሪዎች በመኖራቸው፣ አስተዳደሩ አዲስ የማቋቋሚያ ዕቅድ ለማውጣት መንቀሳቀሱ ተመልክቷል፡፡
የጥናቱ ዝርዝር ግኝት ባይታወቅም፣ በርካታ አቅመ ደካሞችና ወጣቶች ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው እንደሚገኙ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡