Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየድሮን መመርያ እየተዘጋጀ ነው

የድሮን መመርያ እየተዘጋጀ ነው

ቀን:

  • የአቪዬሽን ፖሊሲ እንዲከለስ ተወሰነ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እያደገ የመጣውን የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ የድሮን መመርያ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የድሮን ቴክኖሎጂ አዲስ በመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች የድሮን ሕግ የላቸውም፡፡ ድሮኖች አነስተኛና በቀላል ዋጋ የሚገዙ በመሆናቸው በማንኛውም ግለሰብ እጅ እየገቡ ነው፡፡ ድሮን ለስለላ፣ ለውጊያ፣ ለቅኝት ፎቶግራፍና ለቪዲዮ ቀረፃ፣ ለመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎቶች አቅርቦትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ይውላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም ግለሰቦችና ኩባንያዎች ድሮን ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ ናቸው፡፡ የፕሮጀክቶች ምርቃት፣ ሠርግና ሌሎች ማኅበራዊ ክንዋኔዎች በድሮን ካሜራ ሲቀረፁ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድሮኖች በየትኛው የሕግ ፈቃድ ወደ አገር እየገቡ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ማንኛውንም በራሪ አካል ወደ አገር እንዲገባና አገልግሎት ላይ እንዲውል ፈቃድ የመስጠት ሥራ በአዋጅ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ቢሆንም፣ ከባለሥልጣኑ ዕውቅና ውጪ ድሮኖች በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ እየገቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሐሙስ ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፣ የድሮን ቴክኖሎጂ አዲስ በመሆኑ የተዘጋጀ የሕግ ማዕቀፍ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም አገር አዲስ ቴክኖሎጂ በመሆኑ በብዙ አገሮች ሕግ ገና አልተዘጋጀለትም፤›› ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ ድሮን አነስተኛ መጠን ያለው በመሆኑ በግለሰቦች በማንኛውም ሥፍራ መብረር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ያልተገራ የድሮኖች እንቅስቃሴ ለአገር ደኅንነትና ለአውሮፕላኖች በረራ ደኅንነት ሥጋት እየሆነ እንደመጣ የገለጹት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር የድሮን አስተዳደር መመርያ በማዘጋጀት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ረቂቅ የድሮን መመርያ ሰነዱን የተለያዩ አካላት እየተመለከቱት ነው፡፡ በቅርቡ ዝግጅቱ ተጠናቆ ይፀድቃል የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በበለፀጉት አገሮች ድሮኖች ከአውሮፕላኖች ጋር የተላተሙበት አጋጣሚ እየተዘገበ ነው፡፡ ይህ በበረራ ደኅንነት ላይ የተጋረጠ ሥጋት ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈ ድሮን ለስለላና ለተኩስ ጭምር ሊውል የሚችል ቴክኖሎጂ በመሆኑ ወደ አገር የሚገቡ ድሮኖች መጠን፣ ዓይነትና በሚኖራቸው ቴክኖሎጂ ተለይቶ የፈቃድ መመርያ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡ ድሮኖች ሊንቀሳቀሱባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ተለይተው ገደብ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

አፍሪካ ውስጥ የድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ሕግ በማውጣት ሩዋንዳ ቀዳሚ ስትሆን፣ በቅርቡ የኬንያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኗ የድሮን ሕግ በማውጣቱ ሁለተኛ አገር ሆናለች፡፡

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና ትራንስፖርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ብሔራዊ የአቪዬሽን ፖሊሲ እንዲከለስ ተወሰነ፡፡ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ ታሪክ ያላት ቢሆንም፣ እስካሁን የአገሪቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚመራበት ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ የላትም፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ብሔራዊ የአቪዬሽን ፖሊሲ ማርቀቁ ይታወሳል፡፡ የአቪዬሽን ፖሊሲው የግሉ ዘርፍ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሳተፍ የሚያበረታታ፣ የኤርፖርቶች ልማት፣ የአየር ክልል አስተዳደርና ሌሎች ብዙ ዘርፎች ያሉት ሲሆን፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር አማካይነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ነበር፡፡ በተለይ የግል አየር መንገዶች የብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲውን መፅደቅ በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ኮሎኔል ወሰንየለህ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በተፈጠሩ የአደረጃጀት ለውጦች ምክንያት የአቪዬሽን ፖሊሲው እንዲከለስ መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመጣመሩና በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት የአቪዬሽን ፖሊሲውን እንደገና ማጤን እንዳስፈለገ አስረድተዋል፡፡

የሰባ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአገሪቱን የአቪዬሽን ዘርፍ ሲመራ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱን የአየር ክልል ማስተዳደር፣ የኤር ናቪጌሽን አገልግሎት መስጠት፣ ለአውሮፕላኖች የበረራ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት፣ አየር መንገዶች የሥራ ፈቃድና ለበረራ ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መስጠት ዋና ዋና ሥራዎቹ ናቸው፡፡ ባለሥልጣኑ ዘመናዊ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች በመግዛትና የተለያዩ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በማሠልጠን አሠራሩን በማዘመን ላይ እንደሆነ ኮሎኔል ወሰንየለህ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አውሮፕላን ለማሳረፍ በነጭ አንሶላ ምልክት ከመስጠት በመነሳት ዛሬ የዘመናዊ ራዳር ባለቤት ለመሆን በቅተናል፤›› ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት፣ በአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽንና በአውሮፓ አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ በየጊዜው የአሠራር ጥራቱ ፍተሻ እንደሚደረግለት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅትና በፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን ባካሄዱት ፍተሻ አመርቂ ውጤት ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡  

ይሁን እንጂ የባለሥልጣኑ የሥራ ሒደት አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ የሰው ኃይል ፍልሰት መሥሪያ ቤቱን እየተፈታተነ ያለ ዋነኛ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በሚገባ የሠለጠነ የአቪዬሽን ባለሙያ ፈላጊው ብዙ በመሆኑ፣ በገበያው የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ ባለሙያዎቻችን መሥሪያ ቤቱን እየለቀቁ ይሄዳሉ፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እንደ ኢንስፔክተርና ፓይለት የመሳሰሉ ባለሙያዎችን መቅጠር ደግሞ ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቅ ስለሆነ፣ መሥሪያ ቤቱ በዚህ በኩል ትልቅ ፈተና እንዳጋጠመው አስረድተው የደመወዝ ማሻሻያ ጥያቄ ለመንግሥት ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ባለሙያውን ሊያቆይ የሚችል የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ለመንግሥት አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከመልካም አስተዳደርና ግዥ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ በአንዳንድ የድርጅቱ ሠራተኞች ስለሚነሱ ቅሬታዎች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ማኔጅመንቱ የአሠራር ለውጥ ለማድረግ ሲነሳ ከሠራተኛው አካባቢ የሚገጥመው ተቃውሞ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከሥራ ባህል ጋር የተያያዙ ችግሮች ይገጥሙናል፡፡ የሥራ ጠባዩ ሆኖ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እንደ ልብ እየገቡ እየወጡ የሚሠሩበት አይደለም፤›› ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ ‹‹በዲሲፒሊን ጉድለትና በሙስና ጋር በተያያዙ ችግሮች ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች የድርጅቱን ስም ጥላሸት ለመቀባት እየተሯሯጡ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሙስና የተጠረጠሩ አራት ሠራተኞች ጉዳይ ከነማስረጃው ለፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መተላለፉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በምርመራ ላይ ያለ ጉዳይ በመሆኑ ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...