Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀረጥ ነፃ መብት የፖሊሲ ማስተካከያ ሊደረግበት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከውጭ አገሮች ለሚገቡ ዕቃዎች ለባለሀብቶችና ለተቋማት ሲሰጥ የቆየው የቀረጥ ነፃ መብት፣ የፖሊሲና የአፈጻጸም ማስተካከያ ሊደረግበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ማክሰኞ ኅዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነበር ይኼ የተገለጸው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ ባልቻ ለምክር ቤቱ እንደገለጹት፣ መንግሥት ለባለሀብቶችና ለተለያዩ ተቋማት በሰጠው የቀረጥ ነፃ መብት በአብዛኛው የሚገቡ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ ቢውሉም፣ ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶች (ግለሰቦች) መብቱን ያላግባብ እየተጠቀሙ መሆናቸውን በባለሥልጣኑ በተደረገው የኢንተለጀንስ ጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር አሁንም ጥብቅ አይደለም፤›› ካሉ በኋላ፣ በርካታ ባለሀብቶች ከቀረጥ ነፃ ያስገቧቸውን ዕቃዎች ለሌላ ትርፍ ማግኛ እንደሚያውሉና ችግሩ መስተካከል እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሒደት ያለውን ችግር ለመቅረፍ አገራዊ ጥናት ተከናውኖ እየተጠናቀቀ ስለሆነ፣ በሚቀርበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የፖሊሲና የአፈጻጸም ማስተካከያ ይደረጋል፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ማብራርያ የሰጡት አቶ ሞገስ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በሕግ ለተፈቀደላቸው የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መብት ተጠቃሚዎች 32.4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የቀረጥ ነፃ አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰጠው የቀረጥ ነፃ አገልግሎት 36.9 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ2.7 ቢሊዮን ብር ወይም በ7.38 በመቶ ዝቅ ያለ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

 የቀረጥ ነፃ መብት የተሰጣቸው 26.04 በመቶ ለኢንቨስትመንቶችና ለአምራች የግል ድርጅቶች፣ 27.27 በመቶ ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ 11.7 በመቶ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ 4.04 በመቶ ለሕክምና መሣሪያዎች፣ ሁለት በመቶ ለኤምባሲዎችና ለአምባሳደሮች ሲሆኑ፣ ቀሪው 28.95 በመቶ ደግሞ ለሌሎች አካላት የተሰጠ አገልግሎት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት መንግሥት ለቀረጥና ለታክስ የተወው ገንዘብ በግማሽ ዓመቱ ከተሰበሰበው ጠቅላላ 90.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ37.1 በመቶ ድርሻ እንዳለው ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለሥልጣኑ ከግማሽ በላይ የሆነውን አገልግሎት መስጫ ጊዜውን በመንግሥት ለተሰጡ የቀረጥ መብቶች መስተንግዶ እንደሚያውለው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች