Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ከድርቅ ይልቅ በኮሙዩኒኬሽን ቀውስ መቸገሩን አስታወቀ

መንግሥት ከድርቅ ይልቅ በኮሙዩኒኬሽን ቀውስ መቸገሩን አስታወቀ

ቀን:

በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ቀውስ መቋቋም ቢቻልም መንግሥት በኮሙዩኒኬሽን ቀውስ መቸገሩን አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ  (ዶ/ር) ዓርብ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ መቋቋም ቢቻልም እንኳ፣ አገሪቷ በኮሙዩኒኬሽን ቀውስ ሳቢያ ተቸግራለች፡፡ በድርቅ ምክንያት ያጋጠሙ ችግሮችን መንግሥት በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡ 8.5 ሚሊዮን ዜጎች ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከድርቅ ይልቅ በኮሙዩኒኬሸን ቀውስ ምክንያት በአገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮችን ማግዘፍና ማቀንቀን ለበርካታ ግጭቶች መፈጠር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አንድ ቦታ ችግር ሲፈጠር ሥራዬ ብሎ ያንን ችግር በማጋነንና ውጥረት ነግሷል ብሎ በማቀጣጠል ችግሮችን የሚያባብሱ አካላት እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን ቀውስ እንዲፈጠር ሥራዬ ብለው የሚሠሩ አካላት ትክክለኛ መረጃ የሚያሠራጩ አካላትን በማስፈራራት፣ ወደነሱ ጎራ እንዲሄዱ የሚያደርጉ ኃይሎች እንዳሉ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በመጀመርያ የኢትዮጵያን ስም በመልካም የሚገልጹ ፔጆችን ይከፍታሉ፡፡ ኋላ ግን ኢትዮጵያን የሚያዋርዱ፣ ዜጋንም እንደ ዜጋ የማይቆጥሩ፣ ሁከትን የሚሰብኩና ጥላቻን የሚያስፋፉ ሆነው ነው የምናገኛቸው፤›› ብለዋል፡፡

ይኼንን የኮሙዩኒኬሽን ቀውስ ከሚፈጥሩ አካላት መካከል ጋዜጠኞችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ራሳቸውን የጋዜጠኝነት ካባ አልብሰው ያገኙትን ትንሽ ችግር ቅርንጫፍ እያወጡለት የሚያሠራጩ ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጋዜጠኞች በአብዛኛው ስማቸውን በመቀየር ወይም ተጠያቂ ለማድረግ በሚያስቸግር መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለው የኮሙዩኒኬሽን ፍሰት ችግር እንዳለበትም ተናገረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች የኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሆነ ጠቁመው፣ በውስን ክልሎች ኮሙዩኒኬተሮች ዘንድ መረጃን የመደበቅ ችግር እንዳለ አክለዋል፡፡

በኮሙዩኒኬሽን ቀውስ ምክንያት ጥቃቅን ችግሮች በብዛት እየተሠራጩና ገዝፈው እየወጡ፣ ሌሎች ችግሮችና ቀውሶች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑናቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህንን የኮሙዩኒኬሽን ቀውስ ለመፍታት በፌዴራል መንግሥት የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ፣ ይህ ችግር በቅርቡ ይቀረፋል ተብሎ እንደሚታሰብ አክለው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በአገሪቱ ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያና በሌሎች አጎራባች ከተሞች ግጭቶች መከሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከኢሕአዴግ ስብሰባ በኋላ ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶች እንደቆሙ ጠቁመው፣ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ አካባቢ የተፈጠረው ችግር የተለየ የሚያደርገው ኢሕአዴግ ችግሮቹን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ብሔርን ከብሔር የሚከፋፍሉ የጥላቻ ዘፈኖች መክፈትና አንድን ጠላት ሌላውን መላዕክ አድርጎ መቅረፅ ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ የሚጠቅም እንዳልሆነ አስታውቀው፣ የአገሪቱን ገጽታ እያበላሹ አገሪቱ ሁልጊዜ ትችት እንዲቀርብባትና መንግሥትም አምባገነን እንደሆነ ለመሳል የሚደረጉ ሙከራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያና በሌሎች አጎራባች ከተሞች በግጭት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያል እንደሆነ በሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ወደፊት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተለያዩ ወቅቶችና አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መንግሥት ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ወደፊት ተጣርቶ ይገለጻል ስለሚል፣ ነገር ግን ለሕዝቡ ሲገለጽ አይታይምና በዚህ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው? ተብለው ከጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ ለሕዝብ ይገለጻል የተባለው መረጃ ሁሉ ሳይገለጽ የቀረበት አጋጣሚ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በወልዲያና አካባቢው የሕዝቡ ጥያቄ የልማት እንጂ ሌላ አይደለም ብለዋል፡፡ ሕዝቡ እርስ በራሱ እንዲጋጭና እንዲጠራጠር የሚያደርጉ አካላት እንደነበሩ ግን  ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አካላት እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው ሲሆን፣ ጋዜጠኞችና ሕዝቡ የሚያውቃቸው እንደሆኑ ከመናገር ውጪ በዝርዝር ማንነታቸውን አልጠቆሙም፡፡

ባለፈው ሳምንት በቢሾፍቱ ግጭት ተከስቶ የአንድ ሰው ሕይወት እንደ ጠፋ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቢሾፍቱ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ግጭቱ ግን ያን ያህል የሚጋነን አይደለም፡፡ የከተማው መስተዳድር በቁጥጥር ሥር አውሎታል፤››  ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ግምገማ ካደረገ በኋላ ግጭቶች አሁንም መቀጠላቸው መንግሥት የችግሩን ስስ ብልት አላገኘም ብሎ መደምደም እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን በነበረው ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም፣ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...