Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየክለብ ምሥረታ ጅምር ስኬት እንደማይሆን ከብርሃንና ሰላም በላይ ምስክር ከየት?

የክለብ ምሥረታ ጅምር ስኬት እንደማይሆን ከብርሃንና ሰላም በላይ ምስክር ከየት?

ቀን:

በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በትልቁ ትኩረት ከሚሰጡት እግር ኳስ ጀምሮ ሌሎችም ስፖርቶች በኢትዮጵያ ሲመሠረቱ እንዴትና ለምን እንዲሁም በምን ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚቋቋሙ ብቻ ሳይሆን፣ ተጠያቂነትም ስለሌለው የፈረሱ ቡድኖችና ክለቦች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይታመናል፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹አፈርሳለሁ›› የሚለው ቃል ክለብ አቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት ሳይቀር ማስፈራሪያ እስከመሆን መድረሱ እየታየና እየተሰማ ነው፡፡

ስፖርት በተለይም በዚህ ወቅት እየሰጠ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ በተጨማሪ፣ መንግሥታት ለትልልቅ ፖለቲካዊ ስኬቶቻቸው ማስፈጸሚያ መሣሪያም አድርገው እየተጠቀሙት ይገኛል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ መንግሥት ለስፖርቱ ያለው አመለካከት ከዚህ ‹‹በተራቃኒ ነው›› ተብሎ ባይወሰድም፣ በአፈጻጸም ችግር ስፖርቱ ከመርህ ይልቅ ስሜት እንዲመራው በመሆኑ ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ሆኖት መቆየቱ ይወሳል፡፡

በአገሪቱ ሁሉም ስፖርቶች በሥጋት ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ በኅትመት ኢንዱስትሪው በቀዳሚነቱ የሚጠቀሰው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ በአትሌቲክስና በብስክሌት ክለብ ማቋቋሙን አብስሯል፡፡ ድርጅቱ ቀደም ሲል በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ሲፎካከር የነበረ የእግር ኳስ ክለብ መሥርቶ እንዲፈርስ ያደረገ መሆኑ ባይካድም፣ ያለፈውን ስህተት ላለመድገም በጥናት ላይ በመመሥረት ለጊዜው አትሌቲክስና ብስክሌት፣ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ደግሞ የእግር ኳስ ክለብ ለመመሥረት ቅድመ ሁኔታዎች እያጠናቀቀ መሆኑ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ ገልጸዋል፡፡

 ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ሐሙስ ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በድርጅቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአትሌቲክስና የብስክሌት ክለብ ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ መግለጫውን የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በኅትመት ኢንዱስትሪው አንድ ክፍለ ዘመን ሊደፍን ከጫፍ የደረሰው ብርሃንና ሰላም በአገሪቱ ስፖርት ላይ ግን ያን ያህል ተሳትፎ ሳይኖረው መቆየቱን ጭምር አብራርተዋል፡፡

የድርጅቱ ሠራተኞች እንደ አጠቃላይ በስፖርቱ ያላቸው እንቅስቃሴ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አለመሆኑን ያስረዱት አቶ ተካ፣ የድርጀቱ ሠራተኞችና የማኔጅመንቱ አባላት በስፖርቱ እንቅስቃሴ ከጀመሩ ትክክለኛው ቀንና ዓመተ ምሕረቱ ባይታወቅም፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ግን ከ1956 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እግር ኳስ በመመሥረት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዳንኤል ኃይሌ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶችን በመግለጽ በበኩላቸው፣ ብርሃንና ሰላም ቀደም ባሉት ዓመታት ከእግር ኳስ በተጨማሪ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በአትሌቲክስና በመረብ ኳስ የጎላ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የሠራተኞችን ተነሳሽነትና ፍላጎት ከግምት በማስገባትና በቂ በጀት በመመደብ በ1988 ዓ.ም. በአዲስ መልክ የተደራጀ ቡድን አቋቁሞ ከአንድ ዓመት የሁለተኛ ዲቪዚዮን ቆይታ በኋላ፣ በ1989 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ተቀላቅሎ ጠንካራ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የቡድኑ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታ ከአንድ ዓመት ሳይዘል፣ ወደ ነበረበት ሁለተኛ ዲቪዚዮን እንዲወርድ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚያው በሁለተኛ ዲቪዚዮን እያለ ቡድኑ እንዲበተን መደረጉ ጭምር የሚታወቅ ነው፡፡

ፍላጎትና ጅምር እስከ ምን?

      እንደ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተካ ገለጻ ከሆነ፣ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እግር ኳስ ቡድን የነበረው ቢሆንም ን አመሠራረቱና ፍጻሜውን መነሻ በማድረግ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ተገቢነት እንዳላቸው አምነው፣ አገሪቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት ስፖርቱን ለማሳደግ እያደረገች ካለው ተጨባጭ ቁርጠኝነት እኳያ ብርሃንና ሰላም ለዚህ አንዱ የመፍትሔ አካል ለመሆን መዘጋጀቱን ያስረዳሉ፡፡

      ምክንያቱን አስመልክቶ ኃላፊው፣ ስፖርት የድርጅቱን ገጽታ ለመገንባትም ሆነ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ማኅበራዊ ኃላፊነትም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ነው ሁለት ክለቦች ማለትም አትሌቲክስና ብስክሌት እንደ መነሻ ሊቋቋሙ የቻሉት ሲሉም ያክላሉ፡፡ በዚህ መሠረት በአትሌቲክስ ስድስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች፣  በብስክሌት ደግሞ አምስት ወንድ በማውንቴን ብስክሌት ተወዳዳሪዎችና አሠልጣኞቻቸው ጭምር ምርጫና ምልመላ የተከናወኑ ስለመሆኑ ጭምር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስረዳሉ፡፡

ከቡድኖቹ ቀጣይነትና ዋስትና አኳያ ለተነሳው ጥያቄ አቶ ተካ፣ ‹‹ድርጅቱ እነዚህን ሁለት ክለቦች ለማቋቋም ሲያስብ፣ መጀመርያ ያደረገው ቀደም ሲል የፈረሰው የእግር ኳስ ቡድን ዕጣ ፈንታ በዚያ መልኩ ሊደመደም እንዴት እንደቻለ ማጣራትና ማጥናት አንዱ ኃላፊነት ነበር፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሠልጣኝ የነበሩት አቶ ሰብስቤ ይባስ ጉዳዩን እንዲያብራሩ ተደርጓል፡፡ ‹‹በግሌ መረዳት የቻልኩት ቡድኑ መጀመርያውኑ ሲቋቋም በጥናት ላይ ተመሥርቶ አልነበረም፡፡ ከአደረጃጀት እስከ ቡድን ኃላፊዎች የራሱ የሆነ መዋቅራዊ ይዘት አልነበረውም፡፡ በፋይናንስ ረገድም ቢሆን የድርጅቱ ጥገኛ እንጂ የ‹እኔ› የሚለው አንዳች የገቢ ምንጭ አልነበረውም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በጥናት ጭምር ግምት ውስጥ ገብተው በሚገባ ታይተዋል፡፡ ተሞክሮውንም ጥሩ ማሳያ አድርገን ወስደነዋል፤›› ብለው፣ እንደ አትሌቲክስና ብስክሌቱ እግር ኳሱን ለማደራጀት ጊዜ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት የተሟላና ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመግለጫው እንደተብራራው፣ በዚህ የውድድር ዓመት ተቋቁመው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ የተደረጉት አትሌቲክስና ብስክሌቱ በቀጣይ ለሚቋቋሙት  ስፖርቶች መነሻነት እንዲያገለግልና ከድርጅቱ ወጪ የሆነ ቡድኖቹ የራሳቸው አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው እንዲደራጁ እንደሚደረግ በኃላፊው ተገልጿል፡፡ በበጀት ደረጃም 4.5 ሚሊዮን ብር ለጊዜው መያዙ ተነግሯል፡፡

በፋይናንስ ረገድ ከብርሃንና ሰላም የበለጠ አቅም ያላቸው ተቋማት ቡድኖችን ያፈረሱበት አጋጣሚ መኖሩን ያከሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ድርጅታቸው የእነዚህም ሆነ የሌሎችን ተሞክሮ በማየት በተለይ የቡድኖቹ መዋቅራዊ ይዘት ላይ የማያዳግም መልኩ አደረጃጀቱን መዘርጋት የሚያስችል አሠራር እንደሚከተል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
      ድርጀቱ በአሁኑ ወቅት ላቋቋማቸውም ሆነ በቀጣይ የሚቋቋሙት ቡድኖች ምን ዓይነት የገቢ ምንጭ ተዘጋጅቷል? ለሚለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አንዱና በቋሚነት ገቢ እንዲያመነጭ በዕቅድ የተያዘው ከድርጅቱ የሚገኘው ተረፈ ምርት ሲሆን፣ ሌላው በድርጅቱ ተጠያቂነቱና ቁርጠኝነቱ ካለ በፋይናንስ ደረጃ ያን ያህል የጎላ ችግር ቡድኖቹን ሊገጥማቸው እንደማይችል ጭምር አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ 259 ሚሊዮን ብር ማትረፉን የገለጹት ኃላፊው፣ ከትርፉ ለስፖርት ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብርና ከዚህም በላይ በጀት መመደብ የሚቻልበት አሠራር ስለመኖሩም ተናግረዋል፡፡

ትልቁና መሠረታዊ የሚሉት ኃላፊው፣ ክለብ ሲመሠረት ከስሜት ነፃ በመሆን መልኩ ትርጉሙን ጭምር በውል ተረድቶ ማደራጀትና መምራት ከተቻለ፣ ውጤታማ ማድረግ የማይቻልበት አንዳች ነገር እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱ ይህን መግለጫ ከሰጠበት ዕለት አንስቶ እያንዳንዱን የቡድኖቹን እንቅስቃሴ መጠየቅ የሚዲያው ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

የሴቶች ስፖርት የተሰጠው ትኩረት ለምን አነሳ?

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአትሌቲክሱም ሆነ በብስክሌቱ በብዛት የያዛቸው አትሌቶች ወንዶች ብቻ ለምን ሆነ? የሚል ጥያቄ በመግለጫው ዕለት ቀርቦ ነበር፡፡ ለጥያቄው መነሳት ምክንያት ሆኖ የቀረበው ደግሞ፣ በተለይም በአትሌቲክሱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች አገሪቱን የሚያኮራ ውጤት እየተመዘገበ ያለው በእንስት አትሌቶች ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

ለአትሌቲክስ ቡድኑ በዋና አሠልጣኝነት የተመደቡት ቀደም ሲል በሙገር ሲሚንቶ አትሌቲክስ ክለብና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በማራቶን ዋና አሠልጣኝነት የሚታወቁት አቶ መላኩ ደረሰ፣ የቀረበው ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው አምነው፣ ለጊዜው ካልሆነ አሁን ያለው አሠራር ቀጣይነት እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና አሠልጣኙ ከሆነ፣ ለድርጅቱ ባስገቡት ዕቅድ መሠረት በቀጣይ መሥራት የሚፈልጉት እሳቸው በሚፈልጉት መጠን ፕሮጀክት ላይ ወርደው ሠርተው ለቡድኑም ሆነ ለአገር የሚጠቅሙ ተተኪዎች ማፍራት መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ግን እሳቸው በሚፈልጉት መጠን እንስት አትሌቶችን ማግኘት እንዳልቻሉም ተናግረዋል፡፡

የብስክሌት ቡድኑ ዋና አሠልጣኝና ተወዳዳሪ አቶ ሮቤል ገብረ ማርያም በበኩሉ፣ በብስክሌት አገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊወክል የሚችል አቅም ቢኖርም፣ ያንን በአግባቡ መጠቀም ግን ባለመቻሉ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ እንደ ብርሃንና ሰላም ሁሉ ሌሎች መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ለስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...