በጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)
አንድ የሆነ ነገር ‘እንዴት ነው የሚሠራው?’ ብሎ መሠረታዊ መርሆች ላይ ለመድረስ መጣር ዘመን አመጣሽ አዲስ ፍላጎት ሳይሆን፣ የሰው ልጆች በዚህ ምድር መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ይመስለኛል። ሰዎች እሳትን ለመጀመሪያ ጊዜ ካዩበት ቅጽበት ምናልባትም እንዴት ነው የሚሠራው ብለው ከመጠየቃቸው በፊት አስቀድሞ የሌሎች ነገሮችን አሠራር እንዴትነት ሲጠይቁ ነበር። አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስ ሲበሉ ምናልባትም ሰይጣን የነገራቸው ነገር ‘እንዴት ነው የሚሠራው?’ የሚለው ጥያቄ በሐሳባቸው ውስጥ ከነበረስ ማን ያውቃል? ሳይንሳዊ ምርምር ቅርፅ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንዲሁም የሰው ልጆች ዘመናዊ ማተሚያን ጥቅም ላይ ካዋልን በኋላ፣ በነገሮች አሠራር እንዴትነት ዙሪያ ያለን እውቀት በከፍተኛ ደረጃ ንሯል። የጋራ እውቀታችን ባደገ ቁጥርም ‹‹የምር ግን እንዴት ነው የሚሠራውና የሚሠ(!)ራው?›› እያልን መቀጠላችን ነው አዳዲስ ግኝቶችን የሚወልደው።
በተለይ ዛሬ ላይ ሆነን እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ መልስ ብናገኝላቸው ይጠቅሙናል ብዬ ከማስባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ “ኢሕአዴግ እንዴት ነው የሚሠራው?” የሚለው ጥያቄ ነው።እርግጥ ይህን ጥያቄ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በራሱ በኢሕአዴግ፣ በተቃዋሚዎቹና በተራው ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት ዘርፈ ብዙ መልስ የተሰጠበትና የሚሰጥበት እንደሆነ አላጣሁትም። በእነዚህ አካላት በሚሰጠው መልስ ዙሪያ ከመልሱ ይልቅ ቁምነገሩ ያለው መልስ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ኢሕአዴግ በዚህ ምላሽ ፕሮፓጋንዳዊ መንገድ ነው የሚከተለው፡፡ ተቃዋሚዎች ‘ባላንጣችን’ እንዴት ነው የሚሠራው ዓይነት ትንታኔ ነው የሚሰጡት። ተራው ሕዝብ የተቃዋሚዎችን መልስ መነሻ አድርጎ እዚያ ላይ የተለያዩ የአሻጥር መላምቶችን ጨምሮ ነው የሚያሰፋው። ይኸው በዚህ መንገድ እየተጓዝን ሁለት አሥርት ዓመታትን አልፈን ወደ ሦስተኛው እየተጠጋን ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ችግሮቻችን ተባብሰው እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ ያለብንን ጫና እጅግ እየከበደ እንደመጣ እገነዘባለሁ። ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው የሚጠቁበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። ‘አፍሪካ ውስጥ የትም ቦታ እንግዳ አይደለሁም። ልሆንም አልችልም!’ በሚል እሳቤ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ሰዎችን ትደግፍ በነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንግዳነት እንዲሰማቸው ከመሆን አልፈው፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው የሚፈሩበት ብቻ ሳይሆን በማንነታቸው ተለይተው የሚሞቱበትና ንብረታቸው የሚቃጠልበት ሁኔታ እየተደጋገመ ነው።
ኢሕአዴግ በሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ እንደ ድርጅት ከቆየበት የጊዜ ርዝመት ረገድ፣ ከሰደደው ሥር አኳያ፣ እንደ ድርጅት ‘መዋቅሬ፣ አደረጃጀቴ፣ ርዕዮተ ዓለሜ፣ ወዘተ እንዴት ነው የሚሠራው?’ ብሎ ራሱን መፈተሽና ራሱን መረዳት አለበት። እስካሁን እንደነበረው፣ አሁንም በቅርቡ እንደሆነው ከዓመታት በፊት በዚህ ጋዜጣ እንደተባለው ‘ራሱ ንሰሐ ገቢ፣ ራሱ ንሰሐ ተቀባይ፣ ራሱ ይቅርታ ጠያቂ፣ ራሱ ይቅር ባይ’ ሆኖ ከመቀጠል ይልቅ፣ ‘ወዴት እየሄድኩ ነው? አገሪቱንስ ወዴት እየወሰድኳት ነው? ዕጣ ፈንታዬስ ምንድነው?’ ብሎ መጠየቅ አለበት ኢሕአዴግ። ይህን ጥያቄ ከምር ጠይቆ ከእሱ ውጭ የሆኑ የተለያየ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሠረት ያላቸው ኢትዮጵያዊያንን አሰባስቦ ወይም እንዲሰባሰቡ ፈቅዶ አዲስ መልስ ሲያገኝና ወደ ተግባር ሲገባ ብቻ ነው አሁን እንደ ገዥ ፓርቲ፣ ወደፊት ደግሞ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ መቀጠል የሚቻለው ብዬ አምናለሁ። እንደዚያ ሲሆን ደግሞ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ጥሩ ይሆናል።
ኢሕአዴግ ያሉበትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት ጊዜና ጉልበት መጠየቁ አይቀርም። ይሁንና መደረግ ያለበት ከተደረገ እንጂ ከላይ እንዳልኩት ራሱ ለራሱ ወይም ለሕዝቡ እስካሁን እንደተለመደው ‘የአፈጻጸም ችግር ነው ያለብኝ’ ብሎ መቀጠሉ የትም አያደርሰውም። በፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የምር የሆነ ጥራትና ቀጣይነት ያለው ሕዝብ የሚያምንበት ሐሳብና አካሄድ ቅደም ተከተል በማበጀት በፍጥነት መተግበር ያስፈልገዋል። በይፋም በህቡዕም የሚገጥመውን የተቃውሞ መጠንና ኃይል በጉልበት በመጨፍለቅ ሳይሆን፣ ሕዝቡን የማርካት ዕርምጃዎች በመውሰድ ማለዘብ ያስፈልገዋል።
ለረጅም ጊዜ መቆየቱን መነሻ አድርጎ ‘ይህም ያልፋል፣ ብዙ ነገርም አልፈን መጥተናል’ ከማለት ይቅል፣ ለአዳዲስ ዕይታዎችና ድምፆች ክፍት የሆኑ ዓይኖችና ጆሮዎች ሊኖሩት ይገባል። አለበለዚያ ምንጣፉ ከእግሩ ሥር እየተጎተተ መሄዱ የግድ መሆኑን ማወቅ አለበት።
‘አንድ ዓይነት ነገር እየደጋገመ በማድረግ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ሞኝ ነው’ የሚባል ነገር አለ። ከላይ ወደ ታች፣ ከታች ወደ ላይ የሚዘረጉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች፣ መረጃ ላይ የተመሠረቱ አሠራሮች፣ ደንበኛን ማዕከል ያደረጉ መንገዶች፣ አርሶ አደር ተኮር ልማታዊ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት የተላቀቀ፣ ወዘተ እያሉ የአንድ ሰሞን ዘመቻዎች የተለመዱ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ግን እንዳሁኑ የምር ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙ፣ እንቅፋቶች ሲበዙ፣ ከፊት ለፊት የተደቀኑ ምርጫዎች ግራ ሲያጋቡ፣ ‘ድርጅቱንም አገሪቱንም መሄድ ወዳለባቸው ትክክለኛ አቅጣጫ ማስኬድ የሚቻለው እንዴት ነው?’ ለሚለው ዓቢይ ጥያቄ የሚመጥኑ መልሶች አይሆኑም። ‘ያለፈ ልምድ ላይ መተማመን የሚቻለው መቼና የት ነው?’፣ ‘መቼስ ነው ፍንትው ያለ ነገር እንዳይታየን የሚያደርገን?’፣ ‘በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግ ማድረግ ያለበት ትክክለኛው ነገር ምንድነው?’፣ ‘የድርጅቱ የአሁንና የወደፊትም ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?’፣ ‘ድርጅቱ ውስጥ ምን እየሆነ ነው ያለው?’ በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ጥርት ያለ መረዳት መፍጠር ወሳኝ ይመስለኛል።
ድርጅታዊ ፊዚክስ
ጥሩ ሐኪም የሕመም ምልክቶችን በአግባቡ ለመረዳት መጀመሪያ የሰውነታችንን ብልቶች በአጠቃላይ አንድ ላይ እንዴት እንደሚሠሩ ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። በተበታተኑ ምልክቶች ብቻ ሳይነዳ አጠቃላይ የሕመሙን ሥርዓታዊ መነሻ ለማወቅ ቢሞክር ነው ሁነኛ መረዳትና ፍቱን መድኃኒት ለማዘዝ የሚችለው።
ኢሕአዴግም ውስጣዊ ድርጅቱ በተለይ የካድሬ ሥርዓቱ እንዴት እየሠራ እንዳለና እንዴት መሥራት እንዳለበት የምር ካልተረዳው፣ ለስኬቱም ለውድቀቱም እውነተኛውን መነሻ ማስቀመጥ አይችልም። የዚህ ጽሑፍ ሥጋና ነፍስ ሆኖ የቀረበው ‘ድርጅታዊ ፊዚክስ’ የንግድ ኩባንያም ሆነ ሌላ ዓይነት ድርጅት የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ ሙሉ ውስጣዊም ውጫዊም ሥርዓቱን በማየት መፍትሔ ለመፈለግ የሚያግዝ ዓተያይ ነው። የድርጅቱን ሁለንተናዊ ስኬት ለማምጣት፣ በውስጡ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች ውጤታማነትን ለማጎልበት፣ የአባላቱን እውነተኛ ዕርካታ ከፍ ለማድረግ የሚረዳ፣ ከተራው አባል እስከ ሙሉ ድርጅቱ የሚፈትሽ ምልከታ ነው ድርጅታዊ ፊዚክስ።
የኢሕአዴግ ተራ አባል እንኳ ላልሆነ የእኔ ቢጤ ግለሰብ የድርጅቱን አሠራር ማወቅም ሆነ እንዴት ሊሻሻል እንደሚችል መናገር እንዴት ይቻለዋል? መልሱ ወዲህ ነው። የድርጅታዊ ፊዚክስ አራማጅ የሆነው ሌክስ ሲስኒ እንደሚለው በተፈጥሮ ፊዚክስ ጠቅላይ ገዥ መርሆች ላይ ተመሥርቶ እየተገፋበት ያለውን ድርጅታዊ ፊዚክስን ተጠቅሞ ማንኛውንም ዓይነት ድርጅት እንደ ድርጅት፣ መፈተሽና መተንተን ይቻላል የሚለው ነው የዚህ ጽሑፍ መነሻም መድረሻም። በዚያ ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ይሁነኝ ብለው በቅርብ ርቀት ከሚከታተሉ ሰዎች አንዱ አድርጌ ነው ራሴን የምቆጥረው። ለዓመታት የተጠራቀመው ምልከታዬም ፍተሻው ውስጥ መንፀባረቁ አይቀርም።
ደረቁ ፊዚክስ ቁስንና ኃይልን ለየብቻ፣ ከዚያ አልፎ በሁለቱም መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያጠና መስክ ነው። መስኩ ተፈጥሮ ከሥር መሠረቱ ሲታይ እንዴት እንደሚሠራና እንደሚናኝ ለመረዳት ይሞክራል። የፊዚክስ ሕጎች በኬሚስትሪም፣ በባይሎጂም፣ በሕክምናም፣ በምህንድስናም ጥቅም ላይ የሚውሉ በመሆናቸው ፊዚክስ የሳይንሶች ሁሉ መሠረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ደረቁን ፊዚክስ ከተለመደው ምኅዳሩ አውጥተን ዓይነተ ብዙ ድርጅቶችን ቀረብ ብለን ለማጥናት መጠቀም እንችላለን ነው የድርጅታዊ ፊዚክስ መዘውር። ድርጅታዊ ፊዚክስ ድርጅቶችን በሰላ ዓይን የምናይበትን ሁለንተናዊ መነጽር ይሰጠናል። ድርጅቶችን የምንገልጽበትን ቋንቋ፣ ለትንተና የምንጠቀምባቸው የገፊና ውጤት ክትትሎሽ ጽንሰ ሐሳቦችን ያቀብለናል። የድርጅቶች የተፈጥሮ ባህርያት፣ ቅጣቸውና ጠባዮቻቸውን ለመረዳት የሚያግዙን ነገሮችን ያደርስልናል።
ፊዚክስ የሚያቀብለን ቋንቋ ባህል ተሻጋሪና መልክዓ ምድር ዘለል የሆነ ትርጉም እንዲኖረው አድርጎ ነው። ኢትዮጵያዊው የፊዝክስ ሊቅ ከፈረንሣዊው ወይም ከካናዳዊው በዚህ የዘርፋቸው ቋንቋ ያለምንም ችግር ይግባባል። የፊዚክስ የገፊና ውጤት ተከታትሎ መምጣት እሳቤ አንድ የሆነ ነገር ሲደረግ አስቀድሞ የሚታወቅ፣ በቦታና በጊዜ የማይገደብ ውጤት እንደሚገኝ ያስረዳናል። ኤሌክትሪካዊም ሆኑ ሥነ ሕይወታዊና መሰል ሥርዓቶች የሚጋሯቸው ቅጦች፣ ጠባዮችና ባህርያት አሏቸው፡፡ በአማናዊው ፊዚክስ ሕጎች መሠረት። በሌላ አባባል የነባሮቹ የፊዚክስ ሕጎች ዘዋሪ ሚና ከእንጀራ መጋገሪያ ምጣዳችን አንስቶ በጠፈር መንኮራኩር በኩል የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳርን አካቶ እስከ ከዋክብት ሥርዓትና ከዚያ በላይ ይሄዳል። እነዚህ ሕጎች እንደ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ኩባንያዎች፣ አገሮችና መሰል ‘ውስብስብና ተለዋዋጭ ሥርዓቶች’ ላይም ተግባራዊ ሚና አላቸው። በአንድ ቃል እነዚህ ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ ወይም ተስማምቶ አዳሪ ሥርዓቶች “ድርጅቶች” ብለን እንግለጻቸው።
ድርጅታዊ ፊዚክስ የድርጅቶች ክንዋኔ መነሻና መድረሻ ነፀብራቅ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያሳውቀናል። ክንዋኔውን ለማሻሻል መደረግ ያለበትን ነገር ለመለየት የሚያስችል የጋራ መነጽር፣ የጋራ ቋንቋ፣ ብሎም የገፊና ውጤት ቅደም ተከተልን ያስለየናል።
እንደ ሌክስ ሲስኒ አባባል የድርጅታዊው ፊዚክስ መሠረታዊ ሐሳብ ከላይ የተጠቀሰውን በድርጅቶች ውስጥ የተሻለ ክንዋኔ ማሳካት ነው። በዚህ አቅጣጫ መጓዝ ለድርጅቶች ውጤታማ መሆን ወሳኝ ነው። ፊዚክስ የቁስ አካል፣ የኃይል ብሎም የሁለቱ መስተጋብር ሳይንስ ነው ካልን፣ “የአስተዳደር ሳይንስ” ደግሞ ድርጅቶችን ለመምራት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መርሆችንና ዘዴዎችን የሚያመለክት ከሆነ’፣ “ድርጅታዊው ፊዚክስ” ደግሞ ሁለቱን አስተሳስሪ አድርገን መቁጠር እንችላለን።
በአገራችን ኅብረተሰቡ በተለይ ወሳኝ ክፍል የሆነው ወጣቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ በከፍተኛ ደረጃ በተለወጠበት ዘመን ሳይቀር፣ የኢሕአዴግ አብዛኛዎቹ የአስተዳደር ንድፈ ሐሳቦች ለዘመናችን የማይመጥኑ የወጣቱንም ሆነ የሌላውን ኅብረተሰብ ወቅታዊ ፍላጎት ግምት ውስጥ ያላስገቡ ድሮ ላይ የተቸከሉ ናቸው። አገራችን ከፍተኛ የችግር ረግረግ ውስጥ ነው ያለችው። እንደ አገር በጥፋት ጎዳና ላይ እየሄድንበት ያለው ፍጥነትም እጅግ አስፈሪ ነው። ኢሕአዴግ አዳዲስና ተለዋዋጭ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባ የአስተዳደር ሥርዓት ለውጥ ሳይደርግ አመርቂ ውጤቶችን ለማስገኘት አይችልም። ከዘመኑ እሳቤና ርዕዮት ጋር የሚጋጩ የአስተዳደር ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ተተክሎ አገሪቱ ያሉባትን ወቅታዊ ችግሮች በቅጡ መረዳት አይችልም። በቅጡ ያልተረዳውን ችግር ደግሞ መፍታት አይቻለውም። ለዘመናችን የሚሆኑ መፍትሔዎችን በተፈላጊ ፍጥነት የሚያቀርቡ አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦች ያስፈልጉታል። ከላይ የተጠቀሱት በዋናነት እንደ ገዥ ፓርቲነቱ ኢሕአዴግን የሚመለከቱ ቢሆኑም፣ ሌሎቻችንም እንደ ንቁም እንደ ፍዝም ተዋናይነታችን የየድርሻችን ማንሳታችን አይቀርም። ቀጥሎ የምናያቸው ስድስቱ የድርጅታዊ ፊዚክስ መርሆች በአንድ ድርጅት ውስጥ የሚገኝ ዓይነተ ብዙ ጉልበት ሁለንተናዊ ጥቅም ላይ እንዴት ይዋል? እንዴትስ ከዘመኑ ጋር ይራመድ? ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ያስገኛሉ።
ስድስቱ መርሆች
ኢሕአዴግ ከውድቀት ተርፎ ተጠናክሮ መቀጠልን ካላመ፣ ራሱንም አገሪቱንም በዕድገት ጎዳና በፍጥነት ማንቀሳቀስ ከፈለገ፣ በተሻለ ሁኔታ ለውጥን አቅዶ በተሳካ መንገድ ዕቅዱን በተግባር ለማዋል ካሰበ፣ ቀጥሎ አንድ በአንድ የሚዘረዘሩት ስድስቱን መርሆችን ማወቅ ይገባዋል።
መርሆ 1 – ከሚሠራበት አካባቢ አኳያ አካባቢውን ለውጦና ራሱም ተለውጦ የማይቀጥል ድርጅት ሊኖር አይችልም
ድርጅቶች እርስ በርስ የተቆራኙ ብልቶችና የተያያዙ ንዑስ ሥርዓቶች ያሏቸው ውስብስብ ሥርዓቶች ናቸው። በአካባቢያቸው የሚገኝ ሁኔታን ይቀርፃሉ፡፡ ይለውጣሉ። ለአካባቢያዊ ሁኔታዎች ግብረ መልስ ስለሚሰጡም ይለወጣሉ። ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ነው፡፡ የፊዚክስ ሕግ ነውና። ኢሕአዴግ የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ግንባር ነው። የየራሳቸው አካባቢ ያላቸው፡፡ በመልክዓ ምድራዊ አካባቢ ብቻ ያልታጠረ። ከጊዜ ጋር በየራሳቸውም፣ በጋራ እንደ ግንባርም በለውጥ ሒደት ውስጥ ማለፋቸው የግድ ነው። አውቀው ይለውጡ፣ ይለወጡ ሌላ ጥያቄ ሆኖ።
አንድ የሆነ ነገር በትክክል እንዴት እንደሚሠራ ለመረዳት ነገሩን በየብልቱ ፈታትቶ መበታተን ብቻ በቂ አይደለም። ነገሩን በተሳሰረ ወጥ ሥርዓትነት ዓውድ ማየት ስንችል የተሻለ መረዳት እንፈጥራለን። እንዲያውም ‘ማንኛውም ሥርዓት ከብልቶቹ ድምር በላይ ነው’ የሚባለው። ይህ ነባራዊ ሀቅ ለፖለቲካ ድርጅትም ያስኬዳል። ብዙ ተቃዋሚዎች ሆን ብለውም ሆነ ሳያውቁ ኢሕአዴግን በታትነው ነው ማየት የሚፈልጉት። እንዲያውም ‘ሕወሓት/ ኢሕአዴግ’ ሲሉ ‘ሕወሓት’ የሚለው ላይ አጽንኦት ሰጥተው ነው። ከላይ እንዳልኩት ኢሕአዴግ የየራሳቸው ታሪክ፣ ፍላጎትና ጉልበት ያላቸው አራት ብሔራዊ ድርጅቶች ግንባር ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕለታዊ ሕይወታቸውን ከግንባሩ በተለይም ከየብሔራዊ ድርጅቶቹ ጋር የሚያያዙ ካድሬዎችና አባላት ያሉት ግንባር ነው። አራቱ ድርጅቶች ከ27 ዓመታት በላይ አብረው ሲሠሩ አካባቢያቸውን ቀርፀዋል፣ ግብረ መልስ ተቀብለዋል፣ ሰጥተዋል። የድርጅቶቹ የውስጥ ትስስርም ሆነ ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን ትስስር በቅጡ የሚያሳይ መነጽር ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ ትንታኔ ያስፈልገናል። ኢሕአዴግን ውስብስብ እንደሆነ እንደ አንድ ተለዋዋጭ ሥርዓት መመልከት ስንጀምር ነው እንደ ሥርዓት እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ጠቃሚ ግንዛቤ የምናገኘው። ከውስጣዊና ከውጫዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ስናየው ኢሕአዴግ በተለያየ ጊዜ ራሱን ሲለዋውጥ እናየዋለን።
የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣ የ1993 ዓ.ም. የሕወሓት ክፍፍል፣ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ፣ የአቶ መለስ ሞት ኢሕአዴግን በአንድም በሌላም መንገድ እንዲለወጥ አድርገውታል። ‘የማይለወጥ ነገር ለውጥ ብቻ ነው’ ከሚለው ዘመን ተሻጋሪ ሀቅ በተፃራሪ፣ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግ የማይለወጥ አድርገው የሚያምኑ እስኪመስሉ ድረስ ኢሕአዴግን ያሳብቃሉ ብለው ያሰብዋቸውን የቆዩ ክስተቶች ላይ ሲቸከሉ ይታያሉ። ለምሳሌ የ1967 ዓ.ም. የሕወሓት ‘ማኒፌስቶ’ ያነሳሉ፣ አሁንም ድረስ ሁሉን ነገር የሚቆጣጠረው ሕወሓት ነው ይላሉ። ሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ቆሞ ቀር አድርጎ መቁጠር አለ። እርግጥ ሆን ተብሎ ለፕሮፓጋንዳ በሥሌት የሚደረገው እንዳለ ሆኖ ለውጥ አምጪ ታክቲካዊና ስትራቴጂካዊ መንገዶችን በቅጡ ካለመለየት ጋር የሚያያዝ ምክንያትና መነሻ እንዳለውም መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዋናነት ግን ኢሕአዴግ ራሱ በውስጥ ያሉት አባል ድርጅቶቹም ራሳቸውንና ሌላውን ብሔራዊ ድርጅት የሚያዩት እንደ ድሮው ነው? የማይለወጥ፣ መለወጥ ያለበት(ቸው)፣ መለወጥ የሚገባው(ቸው) አድርገው ነው? ወይስ ያኔ 1983 ዓ.ም. ላይ እንደነበረ(ሩ) አድርገው ነው? እዚህ ላይ ለውጥ ስል ማንኛውም ዓይነት ለውጥ ማለቴ አይደለም። ለአገሪቱ ተግዳሮቶች፣ ነባራዊ ሁኔታዎችና ለሕዝቡ መሠረታዊም ወቅታዊም ፍላጎት የሚመጠን አስቸኳይ የለውጥ ሒደት ላይ ያልገባ ኢሕአዴግ፣ ዕጣ ፈንታው ከጨዋታ ውጪ መሆን ነው በድርጅታዊ ፊዚክስ መርሆ አንድ መሠረት።
መርሆ 2 – ለመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ ተገዥ የማይሆን ድርጅት ሊኖር አይችልም
ቴርሞዳይናሚክስን ሥነ ወበቅ ብለን እንያዘው። በመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ መሠረት በአንድ ሥርዓት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የሚኖረው የኃይል መጠን ውስን ነው። አንድ ድርጅት እንደ ሥርዓት በሕይወት ለመቀጠል በየጊዜው አዲስ ኃይል ያስፈልገዋል። አዲሱ ኃይል የሚገኘው ደግሞ ከእሱ ውጪ ከሆነው አካባቢ ነው። በፊዚክስ ሕግ መሠረት በድርጅቱ ውስጥ ያለው ኃይል በጊዜ ሒደት እየተመናመነ ሄዶ ድርጅቱን ህልው ሆኖ ከማይችልበት ደረጃ ያደርሰዋል። እንደሚታወቀው በሥነ ምኅዳራዊው ዓለም ሳይቀር የዕፅዋት በቀዳሚነት በእነሱ መሠረትነት ደግሞ የእንስሳት (ሰውን ጨምሮ) ሕይወት እንዲቀጥል የሚያስችለው ውጫዊው የታዳሽ የኃይል ምንጭ ፀሐይ ስላለች ነው። በእምነት ዓለምም ቢሆን የአማኞች የእምነት ሕይወት የሚቀጥለው በቀጣይነት በሚያገኙት ውጫዊ የመንፈሳዊው ዓለም ኃይል ምክንያት ነው።
ከኢሕአዴግ አኳያ ስናየው ‘ኃይል’ ማለት ሥልጣን፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ ለሐሳብ ገበያ የሚያቀርበው አሸናፊ ሐሳብ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕዝባዊ ተቀባይነት ነው። በኢሕአዴግ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ዘርፈ ብዙ ኃይልም ቢሆን ውስን ነበር፣ ነውም። ስለዚህ ኢሕአዴግ በራሱ ውስጥ የነበረው ኃይል እስካሁን አምጥቶታል። ከአሁን በኋላ ግን ይወስደዋል ብዬ አላምንም። ከራሱ ድርጅታዊ ግቢ ውስጥ አድርገን ከማንወሰዳቸው ወይም መውሰድ ከሌለብን አካባቢዎች ነው ኢሕአዴግ አዳዲስ ዓይነተ ብዙ የኃይል ፍሰቶች ማግኘት ያለበት፡፡ ህልው ሆኖ መቀጠል ከፈለገና ከተጠቀመበት። ከእነዚህ አዳዲስ የኃይል ፍሰት ምንጮች መካከል በዋናነት ሕዝቡ፣ ሕገ መንግሥቱ፣ የሕግ ሥርዓቱ፣ ኢኮኖሚው፣ የማኅበረሰቡ እሴቶች፣ ወጎችና ባህሎች፣ ወዘተ ናቸው። አዲስ የግንባሩ አወቃቀር (ለምሳሌ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት መቀየር፣ የካድሬ ሥርዓትን ማስቀረት)፣ አዲስ የፌዴራል አወቃቀር (ለምሳሌ ቋንቋና ብሔር መሠረት ካደረገው ውጪ)፣ አዲስ የተወካዮች ምክር ቤት ስብጥር (ለምሳሌ አሁን ኢሕአዴግ ከያዛቸው መቀመጫዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉን ትቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሟያ ምርጫ አገር ውስጥ ያሉትን ጥርስ ባላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲያዙ ማድረግ)፣ አዲስ የካቢኔ ስብጥር፣ ወዘተ፣ አዲስ የኃይል ምንጮች ናቸው።
ግንባሩም ሆነ ብሔራዊ ድርጅቶቹ ከውስጣዊ አቅማቸው ወጥተው ከየአካባቢያቸው ጋር ከፍተኛ ትስስር ከፈጠሩ፣ ኢሕአዴግ አዲስ የኃይል አቅርቦት ስለሚያገኝ የተሳካለት ለውጥ የማምጣት ዕድል ይኖረዋል። ይህ ዓይነት ትስስር ከሌለ ደግሞ ግንባሩ አዲስ የኃይል አቅርቦት ስለማይኖረው፣ በበረሃማ ደሴት ውስጥ ያለምንም ምግብና ውኃ አቅርቦት የሚኖር ሰው ቢውል ቢያድር እንጂ መጥፋቱ፣ መሞቱ እንደማይቀርለት ሁሉ ኢሕአዴግም ከጨዋታ ውጪ መሆኑ አይቀርም በመርሆ ሁለት መሠረት።
መርሆ 3 – ለሁለተኛው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ ተገዥነቱን አውቆ የማይንቀሳቀስ ማንኛውም ድርጅት ኃላፊ ጠፊ ነው
ሁለተኛው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ ሁሉም ነገር ከጊዜ በኋላ አፈር ድሜ እንደሚበላ ይነግረናል። አፈር ድሜ መብላቱ የሚመጣው ከዕድሜ ጋር እየጨመረ በሚመጣው ብትንነትና ፍርሰት (ኤንትሮፒ) ምክንያት ነው። የሰው ልጆችን ጨምሮ የማንኛውም ሥርዓት ሕይወት ለዚህ የማይቀር ሀቅ ተገዥ ነው። ማናቸውም ቢሆኑ ከዚህ ሊያመልጡ አይችሉምና። የሰው ልጅ እያረጀ ሲመጣ ሞቱ የሚፈጥነውም በዚህ ሕግ አስገዳጅነት ነው።
ከመጥፋት ለመዳን አንድ ድርጅት ያለውን ኃይል ወይም ጉልበት የብትንነትና የፍርሰትን ኃይልን ለመቆጣጠርና ለመመከት ማዋሉ ተፈጥሯዊ ነው። ከጊዜ ብዛት የፍርሰት ጉልበት እየጨመረ ሲመጣ ድርጅቱ ካለው ውስጣዊ ጉልበት የበለጠውን እጅ ለምከታ ወጪ ለማድረግ እየተገደደ ይመጣል። በዚህ ምክንያት ለድርጅቱ ውስጣዊ ግንባታና አዲስ አቅም ለመፍጠር ሊውል የሚገባውና የሚችለው ጉልበት በመጠንም በዓይነትም ውሱን እየሆነ ይመጣል። ለዚያ ነው ትልቅ ስኬትን ለማሳካት የሚያልም ድርጅት ከአንድ እስከ ሦስት የቀረቡትን መርሆችን ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀስ የሚያስፈልገው።
ኢሕአዴግም በቅጡ የተገኘ ብሎም በቅጡ የሚቀዳ አዲስ ኃይልና ጉልበት ከላይ ከመርሆ ሁለት ሥር ከተጠቀሱት ምንጮች ካላገኘ መበታተኑና መፍረሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ መርሆ መሠረት።
መርሆ 4 – ድርጅቶች ህልውናቸውን በስኬት ማስቀጠል የሚችሉት አካባቢያቸውን በመለወጥና በመቅረፅ ነው። ይህ አካባቢ ላይ አዋጪ ተፅዕኖ ማሳደር እንደ ድርጅትም በውስጡ እንዳሉት ክፍሎችና ንዑስ ክፍሎችም የሚከወን ነው
በፊዚክስ የጥናት መስክ አንድ ድብልቅልቁ የወጣ ሥርዓት በሚታይበት ጊዜ ተገማች ባልሆነ ቅጥ እንዲሁ በነሲብ የሚንቀሳቀስ ጠባይ ያለው ይመስላል። በአስተውሎት ሲታይ ደግሞ ነሲባዊ የሚመስለው እንቅስቃሴ ድግግሞሽ ባላቸው ቅጦችና ኃይሎች የተዋቀረና የሚነዳ ሊሆን ይችላል። ድግግሞሾቹ በሥርዓቱ ወጥ ግዙፍ አካል ደረጃም፣ በሥርዓቱ ንዑሳን ብልቶች ደረጃም ሊከሰቱ ይችላሉ። ማንኛውም ዓይነት ድርጅትም ድብልቅልቁ እንደ ወጣ ሥርዓት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተመሳሳይ መነጽር ሲታይ ጠጋ ብሎ ለሚያጠናው በሁሉም የድርጅቱ እርከኖች የሚገኙ የተለያዩ ቅጦችና የውስጥ ኃይሎች አሉት። ከትንንሽ ሥራዎች እስከ ትልቁ የድርጅቱ መገለጫ ጠባይ ድረስ ያሉት ነገሮች የሚወሰኑት በእነዚህ ቅጦችና የውስጥ ኃይሎች ናቸው።
እዚህ ላይ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ። ድርጅቱ ከእሱ ውጭ ያለውን አካባቢ የሚቀርፅበትና የሚለውጥበት መንገድ ምን ይመስላል? ለአካባቢው በየጊዜው የሚሰጠው ምላሽስ ምን ዓይነት ነው? ድርጅቱ አባላቱን፣ የበታች መወዋቅሩንና በአጠቃላይ ሙሉ ድርጅቱን የሚያስተዳድረው እንዴት ነው?
ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች በአንድ ድርጅት ውስጥ መገኘት ያለባቸው አራት ቀዳማዊያን ኃይሎችን ለመተንተን ይጠቅማሉ። እነዚህ አራት ቀዳማዊያን ኃይሎች በድርጅቱ ውስጥ የሚንፀባረቁ ግለሰባዊም ሆኑ የጋራ ጠባዮች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። አራቱ ቀዳማዊያን ኃይሎች አምራች ኃይል፣ አረጋጊ ኃይል፣ ሥራ ፈጣሪ (አዲስ ነገር አግኚ) ኃይልና አንድ አድራጊ ኃይል ይባላሉ። እያንዳንዱ ቀዳሚዊ ኃይል በሆነ ጊዜና ቦታ ጎልቶ በሚታይ የጠባይ ቅጥ ራሱን የሚገልጽ ሲሆን፣ ሁልጊዜ ግን አራቱም ሥራ ላይ መሆን አለባቸው። ከአራቱ ኃይሎች አንድ ወይም ከአንድ በላይ ኃይል ከድርጅቱ ከጎደለ ወይም ከተዳከመ፣ ድርጅቱ ውሎ አድሮ መጥፋቱ አይቀርም። በውስጡ መገኘት ስላለባቸው እነዚህ ኃይሎች ድርጅቱ የሚያዳብረው መረዳት በአጠቃላይ በድርጅቱ ሥርዓት ውስጥ እየተደረገ ያለን ማንኛውም ጉዳይ ከሥር ከመሠረቱ ለመረዳት ከመጥቀሙም በላይ፣ ተፈላጊውን ለውጥ በሚፈለገው መጠንና ዓይነት እንዲሁም ወቅት ለማሳካት ይጠቅመዋል።
ኢሕአዴግ ውስጥ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት እነዚህ አራት ኃይሎች ሥራቸውን እየሠሩ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ከራሱ ርዕዮተ ዓለም አኳያ። አሁን ላይ ቆመን ኢሕአዴግ በውስጤ አምራች ኃይል አለኝን? አረጋጊ ኃይልስ? ሥራ ፈጣሪ (አዲስ ነገር አግኚ) ኃይልስ? አንድ አድራጊ ኃይልስ? ብሎ ራሱን ቢጠይቅ የሚያገኘው መልስ ግልጽ መሰለኝ። ስለዚህ በዚህ መርሆ መሠረት የኢሕአዴግ ዕጣ ፈንታ ግልጽ ነው።
መርሆ 5 – ማንኛውም ድርጅት በአካባቢው ላሉ ሁኔታዎች ተገዥ መሆኑን አውቆ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ራሱን ማስማማት አለበት
በዘገምተኛ ለውጥ ዘዋሪ መርሆ መሠረት በአካባቢያቸው የሚፈጠሩ ተገዳዳሪ ሁኔታዎችን አሸንፈው ሕይወታቸውን የሚያስቀጥሉት ጠንካሮቹ ወይም ብልሆቹ አይደሉም። ራሳቸውን ተለዋዋጭ ከሆነ አካባቢያቸው ጋር አስማምተውና አጣጥመው የሚኖሩት ናቸው ሳይከስሙ በሕይወት የመቀጠል አቅም የሚኖራቸው።
ለዚያ ነው አንድ ድርጅት የሚኖርበትንና ሥራ የሚያከናውንበትን አካባቢ በተሳሳተ መንገድ ካነበበ ትልቅ ስህተት የሚሆነው። አካባቢውን በተሳሳተ መንገድ ሲያነብ ለወትሮ ለድርጅቱ አዲስ የጉልበት ምንጭ ሊሆን የሚችለው አካባቢ በተቃራኒው ጉልበት አስጨራሽ ይሆንበትና ወደ መጨረሻው ውድቀት መግፋቱ አይቀርም። ከውድቀት ለመዳን ድርጅቱ የሚሠራበት አካባቢ ሁልጊዜ በመቀየር ሒደት ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ኑባሬውን አፅንቶ ከአዳዲሶቹ ሁኔታዎች ጋር ራሱን ማጣጣም ይጠበቅበታል። የተሳካ ማስማማት ዕውን ማድረግ ደግሞ የድርጅቱ ቁሳዊና ኅሊናዊ ምርቶች ከድርጅቱ የመፈጸም አቅም፣ ከአካባቢው ፍላጎት (የሕዝባዊው ገበያ ፍላጎት) ጋር ተመጋጋቢ ወይም ተደጋጋፊ አድርጎ ማስኬድን ይጠይቃል። ኢሕአዴግ ከላይ እንዳልኩት በተለያየ ወቅት ራሱን የለወጠም ቢሆንም፣ ያደረጋቸው ለውጦች (መለወጦች) አካባቢውን በተገቢ ሁኔታ፣ ጊዜውን ጠብቆ ሳይዘገይ በማንበብ የተደረጉ ለውጦች አይደሉም። ይልቁንም ኢሕአዴግ ብዙ የአገሪቱ ሁኔታዎች በተለዋወጡበት ጊዜ እንኳን ራሱን ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ሲያጣጥም አናየውም። የኢሕአዴግ ሰዎች ይህ በሁኔታዎች ወይም ከሁኔታዎች ጋር አለመለወጥ ‘መስመር’ ብለው የሚጠሩትና እንደ ጥሩ ነገር የሚኮሩበት ጉዳይ ነው። በድርጅታዊ ፊዚክስ ዓይን ግን የዚህ ዓይነት ‘መስመር’ ብሎ አንድ ቦታ ላይ መቸከል ክሽፈት ነው። ለምሳሌ በወደብ ጉዳይ ላይ፣ በኤርትራ ነክ ጉዳዮች ላይ፣ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ላይ፣ ወዘተ ኢሕአዴግ ‘አልሰማም አለማም’ የማለት ያህል ተቸክሎ በመቅረቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች፣ እየከፈለችም ነው።
መርሆ 6 – ማንኛውም ድርጅት ለእንቅስቃሴ ሕጎች ተገዥ ነው
በፊዚክስ ሦስቱ የኒውተን የእንቅስቃሴ ሕጎች ተብለው የሚጠሩ ሕጎች አሉ። እነዚህ ሕጎች በመላው ሁለንታ የሚገኙ አካላት ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጀርባ ያሉትን መሠረታዊ መርሆችን ይገልጣሉ። ሦስቱ ሕጎች ከማንኛውም አካል መንቀሳቀስ ወይም አለመንቀሳቀስ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ የፍዘት፣ የሽምጠጣና የአፀፋ ግብረ ጉዳዮችን የሚተነትኑና የሚያብራሩ ናቸው። ከእነዚህ ሕጎች የምናገኘው መሠረታዊው ቁምነገር ማንኛውም ድርጅት የሚያደርገው ለውጥም ሆነ የሚያሳየውን እንድርድረት ለመረዳት ይጠቅማል። ትንተናው ላይ ተመሥርተን የምንደርስበትን ማጠቃለያ ይዘን ደግሞ ድርጅቱ ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት መጠቀም እንችላለን። ለምሳሌ በፍዘት ሕጉ መሠረት ማንኛውም ድርጅት የሆነ የለውጥ ኃይል የተለየ ነገር እንዲያደርግ ካላስገደደው በስተቀር፣ ለወትሮው የሚያደርገውን ነገር ብቻ እያደረገ ለመቀጠል መዳዳቱ አይቀርም። የቆመ ድንጋይ የሆነ ኃይል ካልገፋው ቆሞ እንደሚቀረው ማለት ነው። ኢሕአዴግ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ ሲቆይ ከአንድ ዙር ፍዘት ወደ ሌላ ዙር ፍዘት ሲሸጋገር የመጣ ነው። በመሀል የሚፈጠሩ ውስጣዊም ውጫዊም ግፊቶች ያደረጉት ነገር ቢኖር አንድ ወጥ የፍዘት ጎዳና ላይ ብቻ እንዳይቆይ ነው። ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት በውስጡ ያከማቸው ዓይነተ ብዙ ‘መጠነ ቁስ’ ግንባሩ ለውጥን እንዳያመጣ ገትሮ ለመያዝ መዳዳቱ ተፈጥሮዓዊ ነው። የአንድ ድርጅት የመፈጸም አቅሙም ሆነ ፍጥነቱ የሚወሰነው በውስጡ ያለውን መጠነ ቁስ በማስተዳደር አቅሙ ነው። በድርጅቱ የሚከወን ማንኛውም ድርጊት በመጠን ተመጣጣኝ የሆነ፣ ግን ተቃራኒ/ተቃዋሚ የአፀፋ ግብር እንደሚያስከትል ከሕጎቹ አንዱ የሚገልጠው ነገር ነው።
በቅርብ ዓመታት ደግሞ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በተከሰቱት አመፆች ምክንያት ኢሕአዴግ ለዓመታት ከሚገኝበት ወቅታዊ ፍዘት ወጥቶ የተወሰነ መነቃቃት ያለበት እንቅስቃሴ እንዲያሳይ ያደረገው ይመስላል። የዚህ መነቃቃት ዘላቂነትና አዛላቂነት የሚለካው ግን ከላይ ከተቀመጡት አምስት መርሆች አንድምታ ጋር በጣምራ ሲታይ ነው። ኢሕአዴግ ስድስቱን መርሆች በቅንጅት አይቶ ራሱን መለወጥ ካልቻለ ዕጣ ፈንታው አዎንታዊ አይሆንም።
ማጠቃለያ
በሌክስ ሲስኒም ይሁን በእኔ ዕይታ የድርጅታዊ ፊዚክስ መርሆች በተቻለ መጠን ከነባሩ የፊዚክስ ሕጎች ጋር በቅርበት እንዲቆሙ ተደርገው ቢሠለፉም፣ በሁለቱም መካከል የዓላማና የትርጓሜ ልዩነት እንዳለ ግን ማስመር ያስፈልጋል። ዋናው ልዩነት የሰዎች ስብስብ የሆኑት ኢሕአዴግን ጨምሮ ዓይነተ ብዙ ድርጅቶች የተፈጥሮ ፊዚክስ ከሚያጠናቸው የግዙፉ ዓለም አጥንትና ጉልጥምት ይበልጥ ውስብስብ መሆናቸው አንዱ ነው። ሲጀመር የሰዎች ስብስብ ስንል ብዙ የማይታወቁ ነገሮች አሉትና። እንደዚያ ሆኖ ድርጅቶችን ከማቅናት አኳያ ድርጅታዊ ፊዚክስ እንደ ማያ፣ እንደ መፈተሻ፣ እንደ መዳሰሻ ስንጠቀምበት የምናገኘው ግንዛቤ ከራሳችን ክህሎት፣ ልምድ፣ አቅም፣ ሀብትና የድጋፍ ሥርዓት ጋር በማቀናጀት የምንፈተሸውን ድርጅት የበለጠ ለመረዳት ያስችለናል የሚለው ነው ቁምነገሩ።
የድርጅታዊ ፊዚክስ ፍተሻችን ማጠቃለያ ኢሕአዴግ የራሱንም የአገሪቱንም ዕጣ ፈንታ ማሳመር ካለበት የምር የሆነ ለውጥ ማድረግ አለበት የሚለው ነው። የምር ለውጥ እንዲመጣም ከምሁራን፣ አቅም ካላቸው ታዋቂ ሰዎች፣ አገር ውስጥ ካሉ የተቃውሞ ፖለቲካ ሰዎች፣ ወዘተ የተውጣጡ ሰዎች ያሉበት የመማክርት ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ተግባር የሚቀየር ምክር መጠየቅ አለበት። በዙሪያችን ከበው ያሉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ አሰፍስፈው እየጠበቁ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ፣ የመማክርት ኮሚሽኑን በአዋጅ በቋሚነት እንዲደራጅ ማድረግ ይገባዋል።
የምንገኘው ውስብስብ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ዓለሙ ደግሞ በመረጃ ጎርፍ ተጥለቅልቋል፣ በመረጃ ናዳ ተዋክቧል። አገራችን ሕዝቡ የሚያምንበት የመረጃ ክምር ፈታሽ፣ ተንታኝና አደራጅ ያስፈልጋታል። ከመረጃው ክምር ገለባውን ከፍሬ የሚለይ አበጣሪ ያሻታል። ወጥ በሆነ መንገድ እውነተኛ መረጃዎችን እያደራጁ ለጥበብ መር አገራዊ ውሳኔዎች መወለጃ የሚሆን እንቁላልና ዘር የሚያሰናዱ ያስፈልጓታል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከ19 ዓመታት በላይ በአውሮፓ፣ በቻይና እንዲሁም በካናዳ በየክረምቱም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያስተማሩ ሲሆን፣ በመደበኛነት ካናዳ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካልጋሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን በማስተማርና በምርምር ሥራ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአዛላቂ ልማት ላይ የማማከር ሥራ ይሠራሉ። በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የስቴሌንቦሽ ኢንስቲትዩቱት ፎር አድቫንስድ ስተዲስ ፌለው ሆነው በአፍሪካ የአዛላቂ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ምርምር እያደረጉ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡