Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በመረጃ የበለፀገ ኅብረተሰብ በመፍጠር ቢያንስ የሰው ሕይወት ሕልፈትን መቀነስ ይቻላል››

አቶ ፈጠነ ተሾመ፣ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ሥጋት በመሆኑ የዓለም መሪዎች ጭምር ዋነኛ አጀንዳ አድርገውት መምከር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ድንበር የማያግደው ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ነገም ሥጋት ሆኖ መቀጠሉ እየታየ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ተደጋጋሚ አደጋዎችን አስተናግዳለች፡፡ ወደፊትም የሚያጋጥሙዋት በርካታ አደጋዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ ይህንን ተለዋዋጭ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጡንና ባህሪውን በመከታተል ትንበያ መስጠት ያለባቸው ተቋማት ሥራ ከብዷል፡፡ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በመተንበይና የትንተና መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ያለበት ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ትንተናዎች ምን ያህል ተሳክተዋል? በትንበያው መሠረት አደጋን ለመቀነስ ምን እየተሠራ ነው? የአየር ፀባይ ለውጥስ ከኢትዮጵያ አንፃር እንዴት ይታያል? ዘንድሮ በበልግ ወቅት የዝናብ እጥረት የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ ስለተተነበየ ምን ያህል አደጋ አለ? በሚሉት ጥያቄዎችና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የኤጀንሲውን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ እንደ ዋነኛ አጀንዳ ታይቶ፣ ተፅዕኖውን ለመቀነስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የሚያሳየው የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ከሚያስከትለው ችግር ባሻገር፣ ትንበያዎችን እያወሳሰበ አስቸጋሪ  እያደረገ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር ኤጀንሲያችሁ ይህንን ተለዋዋጭ እየሆነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከታትሎ ሁነኛ ትንበያ ለመስጠት የሚያስችል አቅም አለው? ችግሩን የሚመጥን የትንበያ አቅም አለን ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ፈጠነ፡- እንደሚታወቀው ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከሚሰጠው ትንበያ አንፃር ሁለት ነገር መታየት አለበት፡፡ አንደኛው የአየር ሁኔታ የሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛው የአየር ፀባይ ነው፡፡ የአየር ሁኔታ የሚባለው ለአጭር ጊዜ የሚለዋወጥ ነው፡፡ የአየር ፀባይ የምንለው ደግሞ በተለምዶ እንደሚባለው የአየር ንብረት ለውጥ የምንለው ነው፡፡ እነዚህን በመያዝ በኤጀንሲው የሚከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ የአየር ሁኔታን በተመለከተ የአጭር ጊዜ ትንበያዎች ይሰጣሉ፡፡ በጥቅል የምንሰጣቸው የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ትንበያዎች ናቸው፡፡ የአጭር ጊዜ የምንለው ከሰዓት አንስቶ እስከ ሦስት ቀናት ያሉትን የሚያካትት ነው፡፡ የቀኑን ከፍተኛና ዝቅተኛ ሙቀት፣ ዝናብ መኖር አለመኖሩን የምንገልጽበት ማለት ነው፡፡ መካከለኛ የምንለው ከአሥር እስከ 30 ቀናት ላሉ ጊዜያት የሚሰጡ ትንበያዎች ናቸው፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ያለውንና ወቅቶችን አካተን የምንሰጠው ትንበያ የረዥም ጊዜ ብለን የምንጠራው ነው፡፡ እነዚህ የአጭር ትንበያዎች አገሪቷ ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ለምሳሌ የየቀኑን የአየር ትንበያ ስንሰጥ ምግብ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ ሊታይ ይችላል፡፡ አለባበስና አመጋገባችንን እንድናስተካከል ይረዳናል፡፡ ጤና ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ ላይም እንዲሁ፡፡ የረዥም ጊዜ ትንበያ የሚሰጠው ደግሞ በተለይ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ነው፡፡ ዕቅድ ለሚያዘጋጁ አካላት የወቅትን ወይም የረዥም ጊዜ ትንበያን ቀድመህ ስትሰጥ፣ በቀጣይ ወቅት ምን ሊኖር እንደሚችል ቀድመህ አውቀህ እንድትዘጋጅ ይረዳሃል፡፡

ለምሳሌ የበልግ ወቅት ብለን በምንጠራው ከየካቲት እስከ ግንቦት ድረስ ባሉት ወራት ውስጥ በበልግ ዋነኛ የዝናብ ተጠቃሚ የሚሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አሉ፡፡ በበልግ ወቅት የበልግ ዋነኛ ዝናብ የሚያገኙ የደቡብ አጋማሽ ክፍሎች አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በበልግ ወቅት ምን መሠራት አለበት? የሚለውን ቀድሞ ትንበያ ቢሰጥ ለዕቅድ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እነዚህን ትንበያዎች እያዘጋጀን እንሰጣለን፡፡ ስለዚህ አሁን የትንበያ አቅማችን እያደገ ነው፡፡ ሌላው የአየር ፀባይ ለውጥ የምንለው የረዥም ጊዜ ለውጥ ነው፡፡ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ጊዜ ወዲህ ከ30 እስከ 40 ዓመታት የሰበሰባቸው መረጃዎች አሉት፡፡ እነዚህን መረጃዎች በጥናት ላይ ተደግፎ ዛሬ ላይ ያለው የአየር ሁኔታ ይህንን ይመስላል፣ በሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ምንድነው ሊመጣ የሚችለው ብሎ የሚያመላክትበት ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ በጥናትና በምርምር የሚደገፍ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ማከናወን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ እሱ መረጃውን ያቀብላል፡፡ ሌሎች የምርምር ተቋማት ደግሞ ይህንን መረጃ ይዘው መሥራት አለባቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ይህንን ክላይሜንት ፕሮዳክሽን የሚባለውን ሌሎችም መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በእርሻና በመሬት አጠቃቀም ላይ ምንድነው ሊያስከትል የሚችለው? የሚለውን ነገር ለመተንበይና ለማስቀመጥ ይጠቅማል፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷልና እንዲህ ያለው የምርምር ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የአየር ንብረት ለውጡ አመጣቸው የሚባሉ ተፅዕኖዎች እየሰፉ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በአገራችንም ይህ በሰፊው እየታየ ነውና ለውጡ የፈጠራቸው ክስተቶች ምንድናቸው? በምሳሌ ቢገልጹልኝ?

አቶ ፈጠነ፡- በአየር ንብረት ለውጥ ብዙ አካባቢዎች እየተለወጡ ነው፡፡ ሙቀት እየጨመረ ነው፡፡ ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጡ እየጠነከረ በመሆኑ ነው፡፡ ሙቀት ሲጨምር ብዙ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ የዛሬ 30 ዓመት ወባ አይገኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ትንኝ ማየት ትችላለህ፡፡ የወባን ተፅዕኖ ያመጣል አያመጣም የሚለው በግልጽ ትርጉም የሚሰጠው ቢሆንም ትንኝ አለ፡፡ አሁን ደጋ በሆኑ አካባቢዎች የወባ ትንኞችን ታያለህ፡፡ ይኼ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዘው እየመጡ ያሉ ትልልቅ ችግሮች መኖራቸውን ያሳይሃል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በጤና ላይ የሚሠሩ አካላት ትኩረት አድርገው የጤና ትርጉም ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ብቻ የሚጠበቅ ሥራ አይደለም፡፡ አሁን ከአየር ንብረቱ ለውጥ ጋር ተያይዞ ከጤና ተቋማት እየቀረበ ያለው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ የተለያዩ አዳዲስ በሽታዎች እየመጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ኤልኒኖን ተከትለው የመጡ በሽታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት ያልነበረ ቢጫ ወባ የሚባለው አሁን ተከስቷል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ አተትንም ብትወስድ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ በተከሰተ ድርቅ የሚመጣ ነው፡፡ በድርቁ ሳቢያ አየሩ ሲበከል የውኃ አካላት ይበከላሉ፡፡ የተበከለውን ውኃ ስትጠጣ ትልቅ የጤና ቀውስ ይመጣል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ በሽታዎች ሁሉ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርቅና ጎርፍ በመጣ ቁጥር የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከየበሽታዎቹ ባህሪ በመነሳትና በአብዛኛው ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ጥገኛ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚመለከታቸው ዘርፎች በሙሉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እያያችሁት ካለው ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጡ በኢትዮጵያ አመጣቸው የሚባሉ የተለያዩ ክስተቶች አሉ፡፡ እንደ ሥጋት የሚታዩና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ናቸው የሚባሉትን መግለጽ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የመጡ አደጋዎችንስ እንዴት መቀነስ ይቻላል?

አቶ ፈጠነ፡- የአየር ንብረት ለውጡን ተከትሎ የሚመጡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አየር ይበክላል፡፡ ለአየር ብክለቱ ምክንያቱ ደግሞ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ሊሆን ይችላል፡፡ በከተሞች የተሽከርካሪዎች መብዛትና አጠቃቀም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ አዲስ አበባን በምሳሌነት እንይ፡፡ በአዲስ አበባ የአየር ብክለት መከታተያ ተክለናል፡፡ በዚህ መሣሪያ ባደረግነው ክትትል የወሰድነውን ናሙና ስንመለከት አየር ተበክሏል በምንለው ደረጃ ባንፈርጅም ምልክቶቹ ይታያሉ፡፡ የካርቦን ሞኖክሳይድ መጨመር ይታያል፡፡ ይህ ምልክት በብዛት የታየው ጠዋት ወደ ሥራ መግቢያ፣ ምሽት 11 ሰዓት ከሥራ መውጫ ላይና ምሳ ሰዓት ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ሰዓታት የሚኖረው የትራፊክ ፍሰት በካርቦን ሞኖክሳይድና በናይትሮጂን ኦክሳይድ ላይ እየጨመረ የሚሄድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይኼ ዞሮ ዞሮ በዚሁ ከቀጠለ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ሰፊ ነው፡፡ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ይህንን የሚቀንስ የመላመድና የማቅለል ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አሁን እንደተጀመረው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ባቡር ማስፋፋትና ታዳሽ የኃይል አማራጮች መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በናፍጣ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን መቀነስ ለችግሩ መፍትሔ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ከአየር ብክለት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ችግር መቀነስ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የእኛ የኃይል ምንጭ ምቹ ነው፡፡ ምክንያቱም የኃይል ምንጫችን ከውኃ፣ ከንፋስና ከፀሐይ ብርሃን የሚገኝ ነው፡፡ ከእነዚህ የሚገኝ ኃይል ብክለት አይኖረውም፡፡ ይህ ሲባል ግን የኢንዱስትሪና የልማት ሥራዎች አይከናወኑም ማለት አይደለም፡፡

ሌላው ደኖችን መትከል ያስፈልጋል፡፡ አልፎ አልፎ የሚመጡ ነገሮች የሚመጥ ስትራቴጂ መነደፍ አለበት፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተብሎ በአገር ደረጃ እየተሠራ ያለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን የሚያመላክተው አንዱ ይኼ ነው፡፡ ሁለተኛው የአየር ንብረቱን ለውጥ ተከትሎ በሽታዎች እየተወለዱ ነው፡፡ ኤልኒኖን ተከትለው የመጡ በሽታዎች አሉ ነው የሚባለው፡፡ ስለዚህ እንደ ቆላ ዝንብ ያሉት እጨመሩ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ከፍተኛና ደጋማ የሆኑ ቦታዎች ወደ ወይና ደጋ እየተለወጡ ነው፡፡ ወይና ደጋ ብለን እንጠቅሳቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደ ቆላነት እየተለወጡ ነው፡፡ ድሮ በወይና ደጋ ብቻ ይበቅሉ የነበሩ ተክሎች ሌላ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች እየበቀሉ ነው፡፡ ድሮ በደጋ ብቻ የሚበቅሉ ነገሮች በወይና ደጋ አካባቢዎች እየበቀሉ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በፊት በቆላ አካባቢ ብቻ የሚበቅሉ ተክሎች አሁን ወደ ወይና ደጋ እየመጡ ነው፡፡ ይህ የሆነው በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ነው፡፡ አየር ወለድ በሽታም ይመጣል፡፡ ተፅዕኖው ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም እዚህ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሊሠሩ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በተጨማሪ የአየር ብክለትም ሌላው ሥጋት ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ እንደ ኒውዴልሂ በመሳሰሉ ከተሞች እየደረሰ እንዳለው በዓይን የሚታይ ከፍተኛ የአየር ብክለት እየተጠቃች ነው ባይባልም፣ ከወዲሁ ጥንቅቄ ካልተደረገ ችግሩ የማይከሰትበት ምክንያት የለም፡፡ እናንተም ምልክቶች መታየታቸውን እየገለጻችሁ ነውና በተለይ ተሽከርካሪዎች ከሚያደርሱት የአየር ንብረት ብክለት ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን ብክለት ለመቀነስ ከተፈለገ ይህንን ሥራ ማነው ተረክቦ ሊሠራ የሚችለው? ኃላፊነቱ የማነው? የአየር ብክለት የዚህን ያህል መጠን እየታየ ከሆነ ደግሞ በብሔራዊ ደረጃ የሚከናወን ሥራ አለ? እናንተስ ይህንን ቀድማችሁ እያሳወቃችሁ ነው?

አቶ ፈጠነ፡- ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በአየር ሁኔታ ላይ ጥሩ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ የሚቀሩና መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ትኩረት በመስጠት መሠራት ያለባቸው ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም በዚህ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያ ጥሩ እየተንቀሳቀሰች ነው ብለን እንደ ምሳሌ ለማንሳት ከምንችላቸው አንዱ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጀመሩት ድርድርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሞከሩ ያሉ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ የአገሮች ዳር ድንበር የማይወስነው ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ሥራ ብቻ ሊከላከለው አይችልም፡፡ ይህንን ትንበያ ስንሰጥ የምንመለከተው የእኛን ብቻ አይደለም፡፡ የእኛ ጣቢያ ለአንድ ነገር ሊጠቅመን ይችላል፡፡ ግን እሱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ማየት ይጠበቃል፡፡ የህንድ ውቅያኖስ መታየት አለበት፡፡ ከውኃ አካላት የሚነሱ ነገሮች ተፅዕኖ አላቸው፡፡ የፓስፊክ ውቅያኖስ መሞቅና መቀዛቀዝ በእኛ አገር አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ የሳይቤሪያ የአየር ግፊት ምንድነው? የሰሐራ የአየር ግፊት ምን ይመስላል የሚለውን ሁሉ መመልከት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ክስተት ነው፡፡ በእኛ በኩል በብሔራዊ ደረጃ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የአካባቢውን የአየር ንብረት እየተመለከትን ጭምር መረጃ ይሰጣል፡፡ ዞሮ ዞሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ክስተቱ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ በብሔራዊ ደረጃ መሥራት አለብን፡፡ ይህንን ነገር እንዴት ነው መያዝ ያለብን ስንል አንደኛ ዕውቀቱ መኖር አለበት፡፡ ዕውቀቱ ከመጣና ሳይንሱ ምንድነው የሚለውን ከተረዳን በኋላ፣ ሳይንሱ በሚጠይቀው አግባብ የማጣጣምና የማላመድ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ይህ ማለት ተግባብቶ መኖር ማለት ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህ ነገሮች መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ የደኖች መጨፍጨፍ የአየር ንብረት ለውጥን ያባብሳል ተብሎ ከተወሰደ ደን መተከል አለበት፡፡ ደን ለመትከል የአርሶ አደሩን ንቅናቄ ሊፈልግ ይችላል፡፡ በተፋሰስ ጥበቃ የተጀመሩ ጥሩ ሥራዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየተሠሩ ያሉ ነገሮች መሬት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ ይህንን እንደ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስቴርና የአካባቢና ደን ጥበቃ ሚኒስቴር የመሳሰሉት መሥራት አለባቸው፡፡ ሁለተኛ የአደጋ መከላከል ደግሞ አደጋው ሲመጣ ፕላን ማድረግ አለበት፡፡ በእኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ፕላን ማድረግ አለበት፡፡ በዚህ ደረጃ የተሠራ ነገር አለ፡፡ አንደኛ ተቋማቱ አሉ፡፡ ይኼ አንድ ጉዳይ ሆኖ ተደጋግፈው አብረው መሥራት አለባቸው፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራው የብሔራዊ አደጋና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር እየተሠራ ነው፡፡ የመጠባበቂያ ፕላን ያስፈልጋል፡፡ የተረጂ ቁጥር የሚጨምር ከሆነና ድርቅ ካለ ኤጀንሲው በሚሰጠው መረጃ ላይ ተመርኩዞ ፕላን ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ እየመጣ ያለ አቅም አለ፡፡ ጥሩ አቅም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እየሰፋ ከመጣው የአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ኃላፊነት አለባቸው የሚባሉት የእናንተን መረጃ ይዘው ምን ያህል ተቀናጅተው ይሠራሉ?

አቶ ፈጠነ፡- አዎ በዚያ ደረጃ ትልቅ ዕርምጃ መውሰድን ይጠይቃል፡፡ በሠራኸው ሥራ ተኩራርተህ የምትቀመጥበት አይደለም፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የሚሄድ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ማስቀረት አይቻልም፡፡ በአሜሪካ ላይ ሃሪኬን ከባድ የሆነ ተፅዕኖ ሲያደርስ ነው የቆየው፡፡ ስላደግህ ይህንን ሙሉ ለሙሉ ልታስቀረው አትችልም፡፡ በመረጃ የበለፀገ ኅብረተሰብ በመፍጠር ቢያንስ የሰው ሕይወት ሕልፈትን መቀነስ ይቻላል፡፡ ከእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የመሬት መንቀጥቀጥ ላይኖር ይችላል፡፡ ግን የድርቅና የጎርፍ መፈራረቅ አለ፡፡ እነዚህን ነገሮች ለምሳሌ የጎርፍ ክስተት የሚበዛባቸው አካባቢዎች ተለይተው ከተፋሰስ ባለሥልጣናት ጋር አብሮ መሥራት ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ከተፋሰስ ባለሥልጣን፣ ከውኃ፣ ከመስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ ከአደጋ መከላከል ጋር በጋራ በቅንጅት መሥራት ይገባዋል ማለት ነው፡፡ በድርቅ ረገድም በተመሳሳይ መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ከትንበያችሁ ምን ያህሉ ይዟል? ወይም የሰጣችሁት ትንበያ በትክክል እንዳላችሁት ሆኗል? ትንበያችሁስ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አደጋዎች እንዳይደርሱ ከማድረግ አኳያ ምን ያህል ረድቷል?

አቶ ፈጠነ፡- አንደኛ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መስጠት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል፡፡ በተለይ የወቅት ወይም የረዥም ጊዜ ትንበያን መስጠት ለብዙ አገሮች አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በሰጠነው ትንበያ ብቻ ላይ ተመርኩዘን አንቆምም፡፡ በየጊዜው እንከልሳለን፡፡ ስለዚህ ብዙ ነገር ለመከላከል ተችሏል፡፡ አንደኛ በተፋሰሶች ጎርፍ በሚያጋጥምበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል እኛ እንተነብይና ወዲያው ከተፋሰስ ጋር ከተያያዙ ተቋማት ጋር መረጃ እንለዋወጣለን፡፡ በትንበያው መሠረት የተፋሰሱ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ያሉ ነዋሪዎች ቀድመው እንዲነሱ ይደረጋል፡፡ ባለፈው ክረምት ላይ ተፍኪ በቾ ላይ የሆነውንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እዚህ አካባቢ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ተችሏል፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየመጣ ስለሆነ ጥንቃቅ ይደረግ ተብሎ መረጃ ተሰጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት መረጃዎች የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ወይም የንብረት ጥፋት መቀነስ ይችላሉ፡፡ ንብረቶች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ቢያንስ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የሚደረግበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ድሮ ትንበያውን ስትናገር ሰውም ስለማያምን ዕርምጃ አይወስድም፡፡ ዛሬ ግን ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ ከድርቅ አኳያ ኤልኒኖ ሲከሰት ድርቅ ስለሚኖር መንግሥትና ውሳኔ ሰጪ አካላት ይህንን መረጃ ተጠቅመው ዕቅድ እንዲያወጡና እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ የኤጀንሲው መረጃ ለውጥ እያመጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የትንበያ መረጃ አሰጣጣችሁ ላይ ብዙ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ትንበያዎች ሲሰጡ በዝርዝር ነው፡፡ የእናንተ ደግሞ የአየር ንብረቱን ሙቀትና ቅዝቃዜ መጠን ከመጥቀስ ያለፈ አይደለም፡፡ ይህንን መረጃ ይዞ ኅብረተሰቡ ይጠቀማል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በተለይ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው መረጃ ዝርዝር ጉዳዮች የሉትም፡፡ ለምሳሌ በአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታ ሊጐዱ የሚችሉ ዜጎች ዘንድ የሚደርስ አይደለም፡፡

አቶ ፈጠነ፡- በቴሌቪዥንና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መረጃዎች የራሳቸው ውስንነት አለባቸው፡፡ በጥናትም እንደተረጋገጠው አሁን ያለው የቴሌቪዥን መረጃ ብቸኛ አማራጭ አይደለም፡፡ በዚህ መጠቀም አንድ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ያለውን ክፍተት መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ ስንት ሰው ቴሌቪዥን አለው? ሰሞኑን በቀረበ ጥናትም ይህ ታይቷል፡፡ አርሶ አደሩ በቴሌቪዥን ከሚሰማው ይልቅ በግብርና ልማት ባለሙያዎች በኩል በሚደርሰው መረጃ ነው እየተጠቀመ ያለው፡፡ እዚህ ላይ ሚዲያዎች የማይተካ ሚና ቢኖራቸውም ስንቱ ይከታተላቸዋል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በመረጃ አሰጣጡ ላይ ብዙ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ያለው የመረጃ አሰጣጥ ቅንጫቢ መሆኑን እኛም ተረድተናል፡፡ ሙሉው መረጃ እየቀረበ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ መሻሻል ስላለበት ከእነሱ ጋር እየተነጋገርን ለመፍታት እየሞከርን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በቂ ነው ባንልም ዝርዝር መረጃዎች በእኛ ድረ ገጽ ላይ አሉ፡፡ስለስስስብብስስለለለ 25 ብዙ አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እኛም ያለን ግምገማ ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን የእኛ መረጃ በየክልሉ ሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎች እንዲወርድ ይደረጋል፡፡ ይህም ጥሩ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአሜሪካ አንዳንድ ግዛቶች ሃሪኬን ያስከተለው ጉዳት ከመድረሱ በፊት አደጋው ይደርስባቸዋል ተብለው የተገመቱ ነዋሪዎች ከሳምንታት በፊት ተነግሮአቸው ከአካባቢያቸው እንዲወጡ በመደረጉ ጉዳቱን ቀንሷል፡፡ ይህ ትንበያው በዝርዝር ቀርቦ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ እዚህ ግን መረጃዎቹ ቁጥርን የሚገልጹ ብቻ መሆናቸው የመረጃ አሰጣጡን ውስን አያደርገውም?

አቶ ፈጠነ፡- ትክክል ነው፡፡ እኛም ይህንን እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ የመን ላይ የደረሰ ነገር ካለ እኛ ዘንድ የሚደርስበትን ጊዜ በመገምገም እንናገራለን፡፡ ለዚህ ነው አዋሽ ቤዚን ላይ በበቾ አካባቢ የተከተለውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ የተቻለው፡፡ እንዲህ ያለውን ሁኔታ የምንጠቀምበት ነገር አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ትንበያዎችን መፍትሔ ሆነዋል፡፡ ተዓማኒነቱ በጣም ጨምሯል፡፡ ግን የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ድርቅን በተመለከተ አሁን ከመደበኛ በታች ዝናብ ያገኛሉ በተባሉ ቦታዎች ድርቅ ነው ማለቴ ባይሆንም ዝቅተኛ፣ መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እዚህ አካባቢ ያገኛል ከተባለ ለአርሶ አደሩ ሁኔታው ቀድሞ ተነግሮታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቦረና፣ የባሌና የጉጂን በተመለከተ የባሌ የደቡብ ኦሮሚያ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች የተተነበየውን መረጃ ወደ ታች ያወርዱታል፡፡ ኪስ ቦታዎች ሳይቀር መረጃ የሚሰጥበት መንገድ አለ ማለት ነው፡፡ ግንኙነት የምናደርግበት መንገዳችን ሚዲያ ብቻ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮን በልግ በተመለከተ ቅድሚያ ትንበያ ሰጥታችኋል፡፡ መጪው በልግ ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖረው ይችላል? ዝናብ የሚጥልባቸው ቦታዎች እንደሚኖሩ ተንብያችኋልና ስለዚህ ጉዳይ እስቲ ያስረዱኝ?

አቶ ፈጠነ፡- የዘንድሮው የበልግ ወቅት ትንበያችን የሚያሳየው የአገሪቱ ምዕራባዊ አጋማሽ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛል የሚል ነው፡፡ የአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ አጋማሽ አካባቢ ደግሞ መደበኛ ዝናብ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ብቻ መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እንደሚኖር ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ይኖራል፡፡ ይጠበቅ የነበረ ግን የማይኖር ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ቀደም ብለው ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩልኝ ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ሊኖር ይችላል በተባሉት የአገሪቱ ክፍሎች ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለው፣ ግን ድርቅ አለ ልል አልችልም ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ምንድነው? ዝናብ ካልኖረ ድርቅ ይኖራል፡፡

አቶ ፈጠነ፡- ዞሮ ዞሮ የዝናብ እጥረት እዚያ አካባቢ ሊያጋጥም ይችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እሺ ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚኖር ከሆነ ተፅዕኖው እንዴት ይገለጻል?

አቶ ፈጠነ፡- ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ የሚወስነው የማቅለልና የማላመድ ስትራቴጂያችን ነው፡፡ ቶሎ ዕርምጃ ከተወሰደና ችግሩ መኖሩ ታውቆ ጥንቃቄ ከተደረገ፣ አንዳንድ ጊዜ ወደ ረሃብ ሳይቀየር ችግሮችን ትቋቋማለህ፡፡ ይህ ሲሆን ድርቅ አለ፣ ግን ረሃብ የለም ትላለህ፡፡ ድርቅ አለ ረሃብ የለም የምትልበት ምክንያት መረጃን ተንተርሶ ዕርምጃ ስለተወሰደ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እዚህ አካባቢ ላይ እጥረት እንዳለ ከኤጀንሲው ተጠቁሟል፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ውሳኔ ሰጪ አካላት ለከብቶች መኖ የሚሆን በሆነ አጋጣሚ የሚገኘውን የዝናብና እርጥበት መያዝ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህንን ነው የምንመክረው፡፡ እጥረት ስለሚያጋጥም ተፋሰሶችና ግድቦች ካሉ በአጋጣሚ የሚዘንበው ዝናብ መለቀቅ የለበትም፣ መባከን የለበትም፡፡ መያዝ አለበት፡፡ ዝናቡ ከተያዘ ከብቶች የመጠጥ ውኃ ያገኛሉ፡፡ ሰዎችም አይጎዱም፡፡ ሌላው ዝናቡ አጭር መሆኑ ከታየ የአጭር ጊዜ ተክሎች እንዲተከሉ ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች መሠራት አለባቸው ማለት ነው፡፡ አንደኛው ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመረጃ የበለፀገ ኅብረተሰብ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ መገንባት ነው፡፡ ይኼ በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ይህንን መረጃ ያገኙ ሰዎች መረጃ ላይ ተመርኩዘው የረዥም ጊዜ ዝናብ ካለ፣ በረዥም ጊዜ የሚደርሱ እህሎችን መዝራት ይችላሉ፡፡ አጠር ያለ ወቅት ከሆነ ደግሞ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ እህሎችን መዝራት ይጠበቅባቸዋል ማለት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ይኖራቸዋል ተበለው በተለዩት አካባቢዎች ያለፈው ዓመት የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ ምን ያሳይ ነበር?

አቶ ፈጠነ፡- ባለፈው ዓመት በልግ ብዙ ጉዳት አልነበረውም፡፡ አጀማመሩ ጥሩ ነበር፡፡ ወደ መጨረሻው አካባቢ ግን ችግር ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ሶማሌ፣ ቦረናና ጉጂ ላይ ድርቅ አስከትሏል፡፡ ስለዚህ በሆነ አጋጣሚ የሚገኘው ዝናብ ካልተያዘ ወደ ድርቅ ሊቀየር ይችላል፡፡ ከብቶች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ የሚፈናቀሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚፈናቀሉ ካሉ ድርቅ ካለ ሁለት ነገሮች መታየት አለባቸው፡፡ በተፈጥሮ አደጋ የሚፈናቀሉ ሰዎች አሉ፡፡ በሰው ሠራሽ አደጋ የሚፈናቀሉ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰው ሠራሽ አደጋ ምንድን ነው? የአደጋ መከላከል ተቋም እዚህ ላይ ተግባሩ ምንድነው?

አቶ ፈጠነ፡- የተለያዩ ግጭቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ በድንበር ላይ ያለው ውኃ ፍለጋ ሊጋጭ ይችላል፡፡ በግጦሽ ፍለጋም ሊጋጭ ይችላል፡፡ ድርቅ ከሆነ አደጋው ሁሉን አቀፍ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በዚህ ደረጃ ነው መዘጋጀት ያለባቸው፡፡ እነሱ ብቻ አይደሉም፡፡ የአርብቶ አደሩ ጽሕፈት ቤት ይህንን መረጃ ወስዶ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አደጋው ይመጣል ተብሎ በሚፈራው መሠረት አደጋ መከላከል ጣልቃ መግባት አለበት፡፡ ከወረዳ አቅም ላይ መሆኑን ካሰበ ጣልቃ መግባት ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩን ለአንድ ዘርፍ ብቻ የምንተወው አይደለም፡፡ የጤና ጉዳይ ይኖራል፡፡ ይህንን የአደጋ መከላከል ብቻ ይሥራው ብለህ የምትተወው አይደለም፡፡ ድርቅ ካለ ትምህርትም ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴርም የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ግድብ ባለባቸው አካባቢዎች ይህ የዝናብ እጥረት ይኖራል?

አቶ ፈጠነ፡- በብዛት የለም፡፡ ምክንያቱም 12 ተፋሰሶች ያሉን ከዚህ ውጪ ነው፡፡ ምናልባት አዋሽ ላይ መደበኛ ነው ያለው፡፡ የተወሰነ ጉድለት ሊኖር ይችላል፡፡ ግን የተያዘ ውኃ ካለ ችግሩ አይኖርም፡፡ አዋሽ ላይ ተይዟል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...