Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረቡ ሁለት ሐሳቦች እየተፋጩ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የንግድና የዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤቶችን ለመለያየት ታቅዷል

በመላ አገሪቱ የሚገኙትን የንግድ ኅብረተሰብ ይወክላሉ የተባሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሱ አባላትን እንደያዙ ይነገራል፡፡ እነዚህ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ቀድሞ በንግድ ምክር ቤት አሁን ደግሞ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የሚል መጠሪያ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

ይሁንና እነዚህን ተቋማት ከ12 ዓመታት በፊት እንደ አዲስ እንዲዋቀር ያደረገው አዋጅ ቁጥር 341/95 ከወጣበት ጊዜ አንስቶ አዋጁ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡

በተለይም ዘርፍ ምክር ቤቶች ከታች ጀምሮ በራሳቸው መዋቅር እንዲደራጁና በየደረጃው ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር ተጣምረው እንዲደራጁ መደረጉ፣ የንግድ ምክር ቤቶችን እንቅስቃሴ በተፈለገው ደረጃ አላራመደም በሚል የተለያዩ መከራከሪያዎች ሲቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡

አዋጁ አለበት የተባሉ ክፍተቶች ላይ ጥናቶች ተደርገው ጉዳዩ ለሚመለከተው ለንግድ ሚኒስቴር ጭምር ሲቀርብም ነበር፡፡ በዚህ መነሻነት ንግድ ሚኒስቴርና የዘርፍ ማኅበራትን ጉዳዮች የሚመለከተው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአዋጁ መሻሻል ላይ አወንታዊ ምላሽ በመስጠታቸው፣ አዲስ ረቂቅ ተሰናድቶ ለማጽደቅ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ከተነገረም ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ምን ዓይነት ቅርፅ ሊይዙ ይገባል? የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል የተባለ አዲስ ረቂቅ ለውይይት መቅረቡንና በረቂቁ ላይ የሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሥራ መሪዎችና የንግድ ዘርፍ አመራሮች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመምከር ላይ ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ውይይት ላይ አዋጁን ለማሻሻል ሁለት የተለያዩ ሐሳቦች ተንሸራሽረው ነበር፡፡ የዚህ አዋጅ መሻሻል ተገቢነትን አምኖ እንዴት አዋጁ ይሻሻል የሚለው ላይ መምከሩ መልካም እንደሆነም የሚገልጹ የውይይት ተሳታፊዎች፣ የሚሻሻለው አዋጅ እስካሁን ያለውን አዋጅ በተለየ መልኩ የሚቀይር እንደሆነም ከቀረበው ረቂቅ መረዳት ይቻላል ይላሉ፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አዋጁን ለማሻሻል ከቀረበው ሐሳብ ውስጥ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለየብቻቸው ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ ማድረግ አንዱ ነው፡፡

ይኼ ሐሳብ አሁን ዘርፍ ማኅበራት በሚል መጠሪያ የሚንቀሳቀሱትን ለብቻ የኢንዱስትሪ ምክር  ቤት በሚል መጠሪያ እንዲደራጁ የሚያደርግ ነው፡፡ ቀድሞም ንግድ ምክር ቤት የሚል መጠሪያ ያለው ንግድና አገልግሎትን የመሳሰሉትን የንግድ ዘርፎችን የሚያንቀሳቅሱ የንግዱ ኅብረተሰብን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቶች አሁን ሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት በአባልነት የሚይዙት አምራቾችንና እንደ ጋራዥ፣ አትክልና አበባ፣ ጨርቃ ጨርቅ የመሳሰሉ ማኅበራትን ነው፡፡

ዘርፍ ምክር ቤቶች ራሳቸውን ችለው የኢንዱስትሪ ማኅበራት ምክር ቤት በሚል ለብቻቸው መቋቋም አለባቸው የሚል አቋም ያለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በዚህ ረገድ ያስጠናውን ጥናትና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት የማቋቋሚያ አዋጅን እንደ መነሻ ሰነድ በመያዝ ነው፡፡

የንግዱና የዘርፍ (የአምራች ኢንዱስትሪ) ማኅበራት ምክር ቤት የተለያየ አደረጃጀት እንዲከተሉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ገፊ እየሆኑ ያሉ ምክንያቶች መኖራቸውን የሚጠቁመው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከጅምሩ በ1939 ዓ.ም. ሲቋቋም የተጀመረው ንግድን ብቻ መሠረት በማድረግ ነው ይላል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በፊት በነበሩት በደንብ ቁጥር 90/1939 እና በአዋጅ ቁጥር 148/1970 የዘርፍ ማኅበራት ራሳቸውን የቻለ አደረጃጀት ያልነበራቸው መሆኑንም ያስታውሳል፡፡ አሁን የምክር ቤት ዋነኛ ትኩረት በንግዱ ላይ እንዲሆንና ለአምራቹ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት አናሳ እንዲሆን ይህ የምክር ቤቱ ታሪካዊ አመጣጥ በራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት እንደሚቻል ጠቅሶ፣ ይህም በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ድጋፍ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት ያረጋገጠው እንደሆነ ገልጿል፡፡

የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ምክር ቤቱ ጥገኛ መሆን በቢሮ፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በሌሎች ድጋፎች ይገለጻሉ የሚለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰነድ፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (በአፍሪካም ሳይቀር) የንግዱና አምራቹ ዘርፍ ተለያይቶ የተቋቋመ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላል፡፡ ለምሳሌ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ በአውሮፓ ደግሞ እንግሊዝና ጀርመን ይገኙበታል በማለት ኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ ለብቻው መገንጠሉ አግባብ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

አንድ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል በድጋሚ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ሆኖ ይታያል፡፡ ለምሳሌ አንድ ነጋዴ በከተማ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በግለሰብ ነጋዴነቱ አባል ይሆናል፣ አምራች ስለሆነ ደግሞ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ይሆናል፡፡ ይህም የአባልነት መደጋገም ያስከተለ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከመንግሥት የክትትልና የድጋፍ ተግባራት አንፃር ሲታይ ደግሞ የንግዱ ማኅበረሰብ በሥራው ሒደት ገጥሞኛል ብሎ የሚያነሳቸው ችግሮችና የሚጠይቃቸው መፍትሔዎች ከአምራቹ ማኅበረሰብ ችግሮችና ከሚጠይቃቸው መፍትሔዎች ጋር የተለያዩ መሆንም፣ ዘርፍ ምክር ቤቱ ለብቻው መውጣት ይኖርበታል ብሎ ካስቀመጣቸው ምክንያቶች ውስጥ ተካቷል፡፡  

ከዚህ የሚለየው ሁለተኛ ሐሳብ ደግሞ ኢንዱስትሪውን ለብቻ ንግዱን ለብቻ ነጣጥሎ በየራሳቸው ምክር ቤት ማቋቋምን የሚቃወም ሲሆን፣ ሁሉንም ንግድና ዘርፍ በአንድ ላይ ያጠቃለለ አንድ ንግድ ምክር ቤት ሊኖረን ይገባል የሚል ነው፡፡ ይኼም ምንም ዓይነት መነጣጠል ሳይኖር ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበረው አንድ ንግድ ምክር ቤት ሊኖረን ይገባል የሚል ነው፡፡

በሁለቱም ሐሳቦች ላይ ማብራርያ የተሰጠ ሲሆን፣ ሐሳቡን ወደ አንድ ለመሰብሰብ እንደ አዲስ እንዲወጣ የተፈለገውን አዋጅ ለመቅረፅ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ተጨማሪ አስተያየቶችንና ሐሳቦችን ይዘው እንዲቀርቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ተለያይተዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች እንደሚገልጹት፣ በዚህ ረቂቅ ሐሳብ ላይ ተጨማሪ ግብዓት ይዘው በመቅረብ ደግሞ የሚመክሩትም ከነገ ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ እንዳገኘነው መረጃ ከሰኞ በኋላ የሚደረገው ውይይት ላይ አንድ አቋም ላይ ተደርሶ አዋጁ በዚህ በጀት ዓመት እንዲፀድቅ ፍላጎት ያለ መሆኑን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች