Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፍጥነት መንገዱና የፈጠነው ጥገና

ባሳለፍነው ቅዳሜ ወደ አዳማ ተጉዤ ነበር፡፡ ጉዞዬን ያደረኩት ከቃሊቲ መናኸሪያ በአዲሱ የፍጥነት መንገድ ነበር፡፡ ከከተማ ከወጣሁ ቆየት ብያለሁ መሰለኝ የፍጥነት መንገዱ ግራ ቀኝ የማውቀው አልመስልህ አለኝ፡፡ የመንገዱ ግራና ቀኝ በቀደመው ውበት ደረጃ ላይ አልነበረም፡፡ አንድ አዲስ የተመለከትኩት የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች በመንገዱ ግራና ቀኝ በተወሰነ ርቀት መቀመጣቸው ነበር፡፡ ይህ መዘጋጀቱ በጣም ጥሩ ዕርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደዋዛ የሚጣል ቆሻሻ ወይም በዚህ መንገድ ያለ ይሉኝታ የሚወረወሩ ውኃ መያዣ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች የመንገዱን ገጽታ መቀየራቸው መላ ሊበጅለት ይገባል ተብሎ ነበር፡፡ ይህንን መንገድ የሚያስተዳድረው አካል በተለይ ለውኃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች ማጠራቀሚያ ያስቀመጠውም ለዚህ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ማጠራቀሚያዎች መኖራቸውን አውቆ የተጠቀሙበትን ፕላስቲክ ከማጠራቀሚያው እያኖሩ ያሉት ምን ያህሎቹ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጋል፡፡ በቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቹ ዙሪያ እንዲሁም በመንገዱ ግራና ቀኝ የተጣሉ ቆሻሻዎች ማጠራቀሚያውን በአግባቡ እየተገለገልንበት አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ እነዚህ ማጠራቀሚያዎች የያዙትን ቆሻሻ በቶሎ የማንሳት ይህንን መንገድ ፅዱ ለማድረግ የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ መንገደኛ እኛ መከወን የሚኖርብን ቀላል ነገር እንዳለ ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን መንገድ እንዳይቆሽሽ በማሰብ በተወሰኑ ርቀቶች የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቹ መቀመጣቸውን መልካም ቢሆንም፣ በርግጥ ተጓዦች ይጠቀሙታል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ምክንያቱ በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር የሚሄድ መኪና ውስጥ ያለ አሽከርካሪ ከመኪናው ወርዶ ቆሻሻ የመጣሉ ዕድል አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ የፍጥነት መንገድ የምንጓዘው ቢበዛ 40 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ ለዚህች የጉዞ ጊዜ ተጓዦች የተጠቀሙበትን ፕላስቲክ ይዘው ከፍጥነት መንገዱ ከወጡ በኋላ ቢያስወግዱ፣ አሁን የምንነጋገርበት ነገር በሙሉ መፍትሔ ያገኝ ነበር፡፡ ይህንን የማድረግ ትዕግሥት አጥተን ‹‹ወደ ፍጥነት መንገዱ ስትገቡ የውኃ ማሸጊያ ጥላችሁ እለፉ›› የተባለ ይመስል ለችግሩ ምክንያት መሆናችን ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተጓዦች ይህንን በማድረግ ቢተባበሩ ምንአለ?

ይህንን እያሰብኩ የፍጥነት መንገዱን አጋመስን፡፡ የተሳፈርኩበት መኪና ሾፌር ግን ለግል ጉዳዩ መቸኩሉን እየገለጸ ስለነበር በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር መንዳት ባለበት የፍጥነት መንገዱ መስመር በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር መንዳት መጀመሩ ከተሳፋሪው ‹‹ኧረ ቀስ በል›› የሚለው ተደጋጋሚ ድምፅ ከሐሳቤ መለሰኝ፡፡ ከዚያም ትኩረቴ ወደ ሾፌሩ ሆኖ እኔም ኧረ ባክህ ቀስ በል አልኩ፡፡ አጅሬ ግን ማናችንንም አልሰማም፡፡ የእኛን ድምፅ ጆሮ ደባ ልበስ ብሎ በፍጥነቱ ቀጠለ፡፡ ትንሽ ከተጓዝን በኋላ ግን ፍጥነቱን ለመቀነስ የሚያስገድድ ነገር ተፈጠረ፡፡ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር ይንዱ የሚል ምልክት ፊት ለፊታችን አየን፡፡ በዚህ መንገድ 40 ኪሎ ሜትር መንዳት ያልተለመደ ነበርና ግምቴ ይህ ሊሆን የቻለው አደጋ ተፈጥሮ ይሆናል የሚል ነበር፡፡ እንደዚያ የበረረ ተሽከርካሪ ለተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች በዝግታ መንዳት ግድ ሊሆንበት ነው ማለት ነው፡፡ የፍጥነት መንገዱ ላይ በሚችሉበት ያህል ሲነዱ የነበሩ ሁሉ ፍጥነታቸውን አቀዝቅዘው በአንድ መስመር መጓዝ ጀመሩ፡፡ ጠጋ ብዬ ስመለከት ግን ሁለት ተሽከርካሪዎች የሚጓዙበት መስመር ተዘግቶ በአንዱ ብቻ እንዲጓዙ የተደረገው በአደጋ ምክንያት አለመሆኑን አረጋገጥኩ፡፡

እኔን የከነከነኝና ፍጥነት ተቀንሶ ለመጓዝ የተገደድንበት ምክንያት ሁለት አሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችለው የፍጥነት መንገዱ ክፍል ከፍተኛ በሚባል ደረጃ እየታደሰ መሆኑ ነው፡፡ ትላልቅ ማሽኖች አስፋልቱን እነደ አዲስ እንደሚገነባ መንገድ እየቆፈሩት ነው፡፡ ወዲያው ፍጥነት መንገዱ ሥራ የጀመረበትን ጊዜ አሰላሁ፡፡ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሦስት ዓመት ነው፡፡ በሦስት ዓመቱ ከባድ ጥገና ውስጥ መግባቱ ለምን? በከፍተኛ የጥራት ደረጀ የተሠራና ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የፈሰሰበት ይህ መንገድ፣ የአገልግሎት ዘመኑን ሳይጨርስ ወይም የዕድሳት ጊዜው ሳይደርስ እንደገና በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ወጪ እየወጣበት ከፍተኛ ዕድሳት ውስጥ መግባቱ እጅግ ግራ ያጋባል፡፡ የመንገዱ ባህሪ በፍጥነት አገልግሎት እንዲሠራ በመሆኑ ምቹ መሆን ስላለበት መጠነኛ ጥገና እያደረጉ መጠንቀቁ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢሆን ይህንን መንገድ በሦስት ዓመቱ በዚህን ያህል ደረጃ እየታደሰ መሆኑ ጤናማ ነገር አያሳይም፡፡ ምክንያቱም ያለችግር ከአሥር ዓመታት በላይ ያገለግላል ተብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ያህል ደረጃ የተበላሸበት ምክንያት ግራ የሚገባ ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡

መንገዱ በብድር ነውና የተሠራው የሚከፈለው ዕዳ ትንሽ እንኳን ፈቀቅ ሳይል ሌላ ወጪ የሚጠይቅ ጥገና ውስጥ የተገባበት ምክንያም ግልጽ አይደለም፡፡ ከፍጥነት መንገዱ ተገልጋዮች የሚከፈለውን የአገልግሎት ዋጋ እያሰሉ ለዕዳው ማቅለያ የሚወሰዱ መሆኑ ሲታሰብና ዕዳውን ፈቀቅ ማድረግ ሳይቻል ለዕድሳት የመዳረጉ ነገር ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ ሊመልስ ይገባል፡፡

ደግሞስ አሁን ለጥገና ወይም ለዕድሳት የሚወጣወን ወጪስ ማነው የሚሸፍነው? በዚህ ዓይነት ይህ መንገድ ዕዳው እየጨመረ መሄዱ አይደለምን? ደግሞስ የተባለውን ያህል ሳያገለግል ለከፍተኛ ጥገና የተዳረገው በምን ጉድለትና በማን ስህተት ነው? ይህ ሊመለስ የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ወገብ የሚያጎብጥ ወጪ የጠየቁ ፕሮጀክቶች የአገልግሎት ዘመናቸው የሚረዝም እንደሚሆን ጭምር ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ መሠራታቸው ከሆነ ያለ ዕድሜያቸው አርጅተው ሲጠጋገኑ ማየት ትልቅ ብክነት ተደርጎም ሊወሰድ ይገባል፡፡ ነገ ደግሞ በሌላኛው መስመር ጥገና ሊደረግ ይችላል፡፡ ችግሩ ይነገረን፡፡ ፈጣኑ መንገድ በፍጥነት ወደ ጥገና የገባው ለምንድነው?

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት