Tuesday, November 28, 2023

የችግሮችን ምንጭ ያለመረዳት እያስከፈለ ያለው ዋጋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአንድ ወር በፊት ለአሥራ ሰባት ቀናት አድርጎት የነበረውን ዝግ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፣ በአገሪቱ ለተከሰቱ ግጭቶችና በግጭቶቹ ምክንያት ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ መግለጹ ይታወሳል፡፡ በዚህም የአገሪቱን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለማስቆምና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባልም፣ በወንጀል ተጠርጥረውና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ከእስር እንደሚፈቱ ቃል ተገብቷል፡፡ በተገባው ቃል መሠረት በፌዴራልና በክልል ደረጃ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር መለቀቃቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚሠራና እስረኞችን እንደሚፈታ፣ በዚህም በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ይፈጠራል ብሎ እንደሚያምን ሲናገር ቢሰማም፣ በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አሁንም ድረስ መቆም እንዳልቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከተማ የቃና ዘገሊላን በዓል በሚያከብሩ ወጣቶችና በፀጥታ አካላት መካከል ግጭት እንደተፈጠረ፣ በግጭቱም የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንደጠፋ፣ እንዲሁም በአካልና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት እንዳደረሰ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡  

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የተጀመረው ግጭት ወደ መርሳ፣ ቆቦና ሌሎች ከተሞች ተስፋፍቶ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች ሕይወት ሲጠፋ የአካል መጉደልና ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም አስከትሏል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደ ስብሰባ ከመግባቱ አስቀድሞ በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ከመዳረጋቸውም በላይ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዮአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በዚህ ችግር ሳቢያ አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሁለቱም ወገኖች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ተፈናቃዮች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ፣ ንብረት አፍርተው መኖር እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንያቶች በኦሮሚያ ክልል ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የተቃውሞ ሠልፎች ሲካሄዱ ነበር፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭትና በኦሮሚያ ክልል ሲካሄዱ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ረገብ ሲል ደግሞ፣ ችግሩ ወደ አማራ ክልል ተሸጋግሮ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት በማድረስ ላይ ነው፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው የተፈጠረው ግጭት ዋነኛ ምክንያት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ መፍታት ባለመቻሉ እንደሆነ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም፣ በክልሉ ሥር ሰዶ የቆየ የአመራር ብቃት ማነስና የአፈጻጸም ጉድለቶች እንደነበሩ ጠቅሶ፣ በዚህም ሳቢያ የሕዝብ እርካታ በሚፈለገው ልክ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ አስታውቋል፡፡ በክልሉ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ወልዲያ ከተማ ኅዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከነማና በመቐለ ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል በወልዲያ ሊካሄድ በነበረው ውድድር በደጋፊዎች መካከል ከጨዋታው በፊት ግጭት ተነስቶ እንደነበረ፣ በዚህም ሳቢያ የሰው ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን አስታውሷል፡፡ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከተማ ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት እንደ ጠፋ፣ አካል እንደ ጎደለና ንብረት እንደወደመ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

ግጭቶቹ መነሻቸው መሠረታዊ የሆኑ የኅብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቅሬታዎች እንደሆኑ መግለጫው ጠቁሞ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ወቅታዊ መነሻዎች አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉ እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

አንዳንድ የግጭት አዝማሚያዎች ማንነትን እየለዩ ጥቃት የሚሰነዘርባቸው እንደሆኑ፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረት በአጭር ጊዜ ውድመት እየደረሰበት እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የግለሰቦች ሀብትና ንብረት፣ የመንግሥት ተቋማትና ተሽከርካሪዎች ውድመት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

ኢሕአዴግ ችግሮች ዳግመኛ እንዳይከሰቱ እንደሚሠራና የሕዝቡን ጥያቄም ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ቃል ቢገባም፣ ግጭቶችን አሁንም ማስቆም እንዳልተቻለ የፖለቲካ ተንታኞች አስረድተዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ ኢሕአዴግ አሁንም የአገሪቱን ችግሮች እፈታለሁ ብሎ ቃል ቢገባም እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ አቶ የሸዋስ ከሁለት ዓመት ወዲህ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ኢሕአዴግ ራሱ የፈጠራቸው ችግሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. በአገሪቱ ተደርጎ በነበረው አገራዊ ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ ማለቱና ሕዝቡ ደግሞ ድምፄን ለአንተ አልሰጠሁም የሚል ቅሬታ በማንሳቱ፣ ለችግሩ አለመቆም አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላም ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ ችግሮች እየተከሰቱ እንደሆነና እነዚህን ችግሮች ማስቆም ያልተቻለው በተለያዩ መሠረታዊ ምክንያቶች እንደሆነ  ያስረዳሉ፡፡

የመጀመርያው ምክንያት አድርገው የጠቀሱት ኢሕአዴግ ባደረገው ግምገማ ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ ነቅሶ አለማውጣቱና ለችግሮቹም ትክክለኛና ተገቢ መፍትሔ አለማበጀቱን ነው፡፡ ከመልካም አስተዳዳር፣ ከአፈጻጸምና ከአመራር ጋር የተያያዙ በርካታ ጉድለቶች እንዳሉና በእነዚህ ችግሮች ላይ መፍትሔ አለማስቀመጥ፣ ብሔር ተኮር የሆኑና የአገሪቱን አንድነትና አብሮ የመኖር እሴቶች የሚሸረሽሩ ሕጎች መኖርና እነዚህን ሕጎች በደንብ መፈተሽ ባለመቻሉ ግጭቶችን ማስቆም እንዳልተቻለ አንዱ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡

ሁለተኛ ምክንያት ብለው የጠቆሙት የፌዴራል አደረጃጀቱን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ይጠቅማል? ወይስ አይጠቅምም? ከሚል እሳቤ የተወሰደ እንጂ በደንብ እንዳልተገመገመ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ፌዴራሊዝምን ጥያቄ የሚያስገባ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ፌዴራሊዝም ለዚህ አገር አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ብሔር ተኮር የሆነና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ይጠቅማል? አይጠቅምም? የሚለው ጭራሽ አልታየም፤›› ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡

ሦስተኛ ምክንያት ብለው ያነሱት ጉዳይ የፕሮፓጋንዳ ሥልቱ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከአንድነት ይልቅ በልዩነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው፡፡

አቶ የሽዋስ ኢሕአዴግ አጥፍቻለሁ ካለ በኋላ ሕዝቡ ይቅርታውን መቀበሉንና አለመቀበሉን ሳያውቅ መልዕክቱን በሚዲያ ብቻ በማስተላለፍ በሥልጣኑ መቀጠሉ ስህተት እንደሆነ፣ አሁን በወልዲያና በሌሎች አካባቢዎች እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች ሌላው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

 ዶ/ር ነገሪ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ዓርብ ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የኢሕአዴግን ይቅርታ ሕዝቡ መቀበሉንና አለመቀበሉን ሳያረጋግጥ በመቅረቱ ነው ግጭቶቹ አሁንም መቆም ያልቻሉት የሚሉ ወገኖች ስላሉ፣ በዚህ ላይ የመንግሥት ምላሽ ምንድነው የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታን የሚቀበል እንደሆነና ሕዝቡ ይቅርታውን ስለመቀበሉም በተለያዩ መንገዶች ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በንጉሡ ነገሥቱም ሆነ በደርግ ዘመን የአገሪቱ ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭ ሆኖ እንደማያውቅ አቶ የሸዋስ ጠቁመው፣ የኢሕአዴግ ምርጫም  ከይስሙላ ያለፈ አይደለም ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም ያልቻለበት ሌላው ምክንያት በፌደራሊዝም ሥርዓቱ ሳቢያ እየተፈጠሩ ባሉ አለመግባባቶች እንደሆነ ተንታኞቹ ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ከጊዜ ወዲህ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እየጎላ፣ ዘረኝነትና ብሔረተኝነት እየጎለበተ በመምጣቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ በወልዲያ አካባቢ በተፈጠረው ችግር አንዳንዶች የግጭት አዝማሚያዎች ማንነትን እየለዩ ጥቃት የሚሰነዘርባቸው እንደሆኑ ገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ልደቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት እየተከሰተ እንደሆነ ገልጸው፣ ይኼ ደግሞ አደገኛ አዝማሚያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ልደቱ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች እኩል መሆኑንና በተለየ ተጠቃሚ ሆኗል የሚባለው ስህተት እንደሆነ ገልጸው፣ በአራቱ ግንባር ድርጅቶች መካከል ግን የበላይና የበታች አለ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች አንዱ ምክንያትም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተለይ በወልዲያ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወጣቶች ያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎችና ያስተጋቧቸው የነበሩ መፈክሮች ይኼንን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር በበኩላቸው፣ በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ዋነኛው መነሻቸው የብሔርተኝነት ስሜቱ እያየለ በመምጣቱ ነው ብለዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሲሠራበት የነበረ የፖለቲካ ሥራ ውጤት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ልደቱ ከዚህ በፊት ግጭቶች ይከሰቱ የነበረው በኢሕአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢሕአዴግ አማካይነት እንደ ጠፉ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ኢሕአዴግና ሕዝቡ መጋጨት እንደ ጀመሩ ጠቁመው፣ የኢሕአዴግና የሕዝቡ ግጭት አሁን መልኩን በመቀየር ሕዝቡ እርስ በርሱ መጋጨት እንደ ጀመረ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ብለው ያቀረቡት ደግሞ ባለፉት ወራት በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚማሩ በተማሪዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ግጭት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እንደማያውቅ አቶ ልደቱ አብራርተዋል፡፡ ተማሪ ከሥርዓት ጋር ሲጋጭ እንጂ እርስ በርሱ ታይቶ አያውቅም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ኢሕአዴግ የገባቸውን ቃሎች ባለማክበሩ የተነሳ የሕዝቡ እምነት እየተሸረሸረ እንደመጣ አስረድተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ከግምገማው በኋላ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ ቃል እንደገባና እስካሁን ድረስ በገባው ቃል መሠረት ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ልደቱ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ የፖለቲካ እስረኛ የለኝም ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ፓርቲ እስካሁን ለተፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት ወስጃለሁ፣ ተጠያቂው እኔ ነኝ፣ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ ካለ በኋላ የታሰሩት ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ማለት እርስ በራሱ የሚጋጭ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ ‹‹ጥፋቱን ሲያምን ሥርዓቱን በመቃወም ተሳትፎ ያደረጉ ሰዎች ያነሱት ጥያቄ ትርጉም እንደነበረው የሚያመላክት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አቶ ልደቱ በአገሪቱ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲፈጠርና ግጭቶች እንዲቆሙ ከተፈለገ መደረግ ያለበት፣ ኢሕአዴግ የፖለቲካ እስረኛ አለኝ ብሎ ማመን እንዳለበት አውስተዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ደግሞ፣ ‹‹መንግሥትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ ችግሩ ውስጣዊ ነው፡፡ ዋነኛው ድክመቱ ያለው አመራሩ ላይ ነው፡፡ ችግሮችን መፍታት አለብን በማለት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይኼ እየሆነ ባለበት ጊዜ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንገብ በዜጎቻችን ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት ላይ፣ እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ጥቃትና ውድመት ሲፈጸም ታይቷል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ ኢሕአዴግ አሁንም የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ተንታኞች አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ችግሮችን ማስወገድ የሚቻለው ኢሕአዴግ አሁንም ሁሉን ነገር እኔ እፈታዋለሁ ከሚል አባዜው በመውጣት፣ መላ የአገሪቱን ሕዝብ ያሳተፈ ውይይት ማድረግ ሲችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ የሸዋስ በዚህ የመፍትሔ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ በመላ አገሪቱ ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው ኢሕአዴግ ከሥልጣን ሲለቅ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ ኢሕአዴግ ችግሮቹን እፈታለሁ ብሎ ብዙ ጊዜ ሙከራ እንዳደረገና ሊሳካለት እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ልደቱ ችግሮቹ ሊፈቱ የሚችሉት በሁለት መንገዶች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የመጀመርያው መፍትሔ መሠረታዊ የሆኑ ችግሮችን እንደገና በመገምገምና አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው መፍትሔ ብለው የጠቆሙት ጉዳይ ኢሕአዴግ ችግሩን የፈጠርኩት እኔ ነኝና የመፍትሔው አካልም እኔ ነኝ የሚል አባዜ ስላለበት ከዚህ አባዜው ሊወጣ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እንዴት ነው በሚለው ላይ በሰጡት ማብራርያ፣ ‹‹በከፍተኛ ወጪና በዓመታት ድካም የተገነባን ልማት እያወደሙ ለሕዝብ የሚጠቅም ተጨማሪ ልማት ማምጣት ይቻላል ወይ? በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃትስ እየፈጸሙ እውነት ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን መታገል ይቻላል? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚያስነሳ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አንዳንድ ወጣቶች ከጊዜያዊ ስሜት ወጥተው በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመመራት፣ በሰከነ መንፈስ ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ትውልዱ ነቅቶ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹በዚህ ቦታ የተፈጠረ ግጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል፣ የዚህ ብሔር ንብረት ወደመ፣ በእሳት ጋየ፣ ወዘተ. የሚሉ ቃላትን ዘወትር በመጠቀም የዜጎችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አጠናክሮ ማስቀጠል አይቻልም፤›› ሲሉ ጠቁመው፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ በሆነ፣ በዴሞክራሲያዊና በሠለጠነ መንገድ ለመንግሥት ለውጥ መታገል ይቻላል፡፡ ከዚያ ውጪ በሌሎች እጅ እሳትን ለመጨበጥ መሞከር ጉዳቱ የከፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች አሁንም ድረስ መፍትሔ ማግኘት ያልቻሉት፣ ኢሕአዴግ የችግሮቹን ብልት በትክክል ባለመግኘቱ እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን ማስቆም የሚቻለው መላ የአገሪቱ ሕዝብ ትክክለኛ ውይይት ሲያካሂድና የሕዝብ ፍላጎት ምን እንደሆነ በትክክል መረዳት ሲቻል እንደሆነም ያክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -