የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በወልዲያ፣ በቆቦና በመርሳ ከተሞች በነበረው ግጭት የ13 ንፁኃን ዜጐችና የሁለት የፀጥታ ኃይል አባላት በድምሩ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገለጸ፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ ክልሉ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉና ለዜጎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ አካላትን አጣርቶ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በተለይም በጥምቀት በዓል ማግስት በወልዲያ ከተማ ለሰባት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖ ያለፈውን ክስተት ክልሉ አውግዟል፡፡
“በወልዲያ ከተማ የተፈፀመውን ድርጊት በሚመለከት ምንም እንኳን አንዳንድ ቡድኖች የሀይማኖቱ ሥርዓት በማይፈቅደው መልኩ ተንኳሽ ተግባራት መፈፀማቸው ስህተት መሆኑን ብናምንም፣ መነሻው ምንም ይሁን ምን የሰው ሕይወት መጥጋቱና በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተደረገው ተኩስ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፤” ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
“ከዚህም ጋር ተያይዞ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በሚካሄድበትና ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት ፀጥታ ያደፈረሱም ይሁን በታዳሚዎች ላይ ጥይት የተኮሱ፣ ሰው የገደሉና ልዩ ልዩ ጉዳት ያደረሱ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፤” ብሏል፡፡
ግጭቶቹ ከተከሰቱባቸው ከተሞች ነዋሪዎች ጋር በመነጋገርም ከተሞቹ ወደቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሆነም መግለጫው አክሏል፡፡