Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮንትራት መምህራንን የሙያ ብቃት ለማሳደግ

የኮንትራት መምህራንን የሙያ ብቃት ለማሳደግ

ቀን:

ኮንትራት አስተማሪዎች የፔዳጎጂ (የመምህርነት ሥልጠና) ባይወሰዱም በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በመምህርነት ያገለግላሉ፡፡ በርካታ አገሮች ከኢኮኖሚ ቀውስ ወይም የመምህራን እጥረት ጋር በተያያዘ ኮንትራት መምህራንን እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ፡፡ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ ሲሠራና  የፕሮፌሽናል መምህራን ቁጥር ከተማሪዎች ቁጥር ጋር ሳይመጣጠን ሲቀር እነዚህ መምህራን ይቀጠራሉ፡፡

መምህራኑ በማስተማር ሙያ ባይሠለጥኑም እንዲሁም ሙያዊ ብቃት ባይኖራቸውም በመንግሥታት፣ በአንድ ማኅበረሰብ ወይም በትምህርት ቤቶች ቀጣሪነት እንዲያስተምሩ ይደረጋል፡፡ ኮንትራት መምህራን በመላው ዓለም የሚገኙ ሲሆን፣ አፍሪካ ውስጥ ያሉት በቁጥር ያመዝናሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመምህርነት ሥልጠና ያልወሰዱ ግለሰቦች በቋሚነት ባይቀጠሩም በኮንትራት መምህርነት ይሠራሉ፡፡ መንግሥትም እንደ ተባባሪ መምህራን ከቀጠራቸው በኋላ ሙያዊ ብቃታቸው እንዲጎለብት ሥልጠና የሚወሰዱበት መንገድ የሚያመቻችበት አሠራር አለው፡፡

በየክልሉ ያሉ መምህራን ቁጥር ካሉት በርካታ ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ በመሆኑ፣ ኮንትራት መምህራን ይቀጠራሉ፡፡ እነዚህ መምህራን ትምህርትን በማዳረስ ረገድ አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም፣ በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ይነሱባቸዋል፡፡ የኮንትራት መምህራን በሙያው ባለመሠልጠናቸው የሚሰጡት ትምህርት ምን ያህል ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚል ጥያቄ ይደመጣል፡፡ በተያያዥ መምህራኑም በዘርፉ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ መምህራኑ እንደ ሌሎች የሲቪል ሰርቪስ አስተማሪዎች ጥቅማ ጥቅም አያገኙም፡፡ ብዙ ጊዜ በቅጥር ሁኔታቸው ደስተኛ ስለማይሆኑ በሙያው አይገፉበትም፡፡

ጉዳዩ በተለያዩ አገሮች የመወያያ አጀንዳ ሲሆን፣ አፍሪካ ውስጥም ብዙ ኮንፈረንሶች ተዘጋጅተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ከሰኔ 13 እስከ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የተካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስም በኮንትራት መምህራን ዙሪያ አጠንጥኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ25 አገሮች የተውጣጡ መምህራን፣ በኰንትራት መምህራን ዙሪያ ጥናት የሠሩ ተመራማሪዎችና የመምህራን ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተው የየአገራቸውን ተሞክሮ አስደምጠዋል፡፡

ከተሳታፊ አገሮች መካከል ኮንጎ፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ኒጀርና ቶጎ ጥቂቱ ሲሆኑ፣ የኮንትራት መምህራንን ሁኔታ ለማሻሻል ይረዳሉ ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች አስደምጠዋል፡፡ የኮንትራት መምህራን ያለባቸው ኃላፊነት ምንድነው ከሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ጀምሮ፣ የሚገጥሟቸው ችግሮች፣ የትምህርት ጥራት ጉዳይና ማኅበረሰቡ ስለ መምህራኑ ያለው አመለካከትም መወያያ ሆነዋል፡፡ መምህራኑ ፕሮፌሽናል የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸትና ከሥራቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሙያውን እንዳይለቁ መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎችም ተመልክተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሾመ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ የተማሪዎችና የመምህራን ቁጥር አለመመጣጠን የሚፈጥረውን ችግር ለመቀነስ ኮንትራት መምህራን ቢቀጠሩም፣ መምህራኑ ሙያዊ ብቃት ያላቸው አለመሆናቸው ሌላ እንቅፋት ነው፡፡ ‹‹መምህራኑን ከቀጠርናቸው በኋላ ሥልጠና ብንሰጣቸውም በቂ ስላልሆነ እንደ ፕሮፌሽናል መምህራን ትምህርት መስጠት አይችሉም፤›› ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡

በእርግጥ መምህራኑ በክረምት መርሐ ግብር የመምህርነት ሥልጠና ቢወስዱም የትምህርት ደረጃቸው አሁን ካለበት ከፍ እንዲል መደረግ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል የሚሰጠው ሥልጠና ወደ ሰርተፊኬትና ዲግሪም እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ መምህራኑ በተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲሠሩ ማበረታቻ የመስጠት ሥራም ይሠራል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የዩኔስኮ ኢንተርናሽናል ታስክፎርስ ኦን ቲቸርስ ዳይሬክተር ኤዲም ኢዱብራ፣ በኮንፍረንሱ ላይ ከ25 አገሮች የተውጣጡ ተሞክሮዎች መቅረባቸው፣ የየአገሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጥናቶቹን በመመርኰዝ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲያስተካክሉ ያስችላል ብለዋል፡፡

‹‹ኮንትራት መምህራን በአፍሪካ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ትምህርት ማግኘት የማይችሉ ታዳጊዎችን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢሆንም፣ የተሻለ ለውጥ እንዲታይ ፕሮፌሽናል መሆን አለባቸው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥትና ማኅበረሰቡም መምህራኑን ቢፈልጓቸውም ደመወዛቸው አነስኛ በመሆኑና የሚሠሩበት ሁኔታ የተመቻቸ ባለመሆኑ ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደሚገደዱም ተናግረዋል፡፡ ሁኔታው እንዲለወጥ መንግሥታት መሥራት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡

ተሞክሯቸውን ካቀረቡ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካና ቻይና ይጠቀሳሉ፡፡ በየአገራቸው የኮንትራት መምህራን ማኅበረሰቡን በእጅጉ ቢጠቅሙም፣ ቢከበሩም፣ ካሉባቸው የኢኮኖሚ ጥያቄዎች አንፃር በሙያው ለረዥም ጊዜ ሲዘልቁ አይታዩም፡፡ ለመምህራኑ ሥልጠና በመስጠት ወደ ፕሮፌሽናል መምህርነት ማሸጋገርና የብቃት ምዘና ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ጥናቶቹ ያመለክታሉ፡፡ በተያያዥም መምህራኑ የተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እንዲያስተምሩ ካልተደረገ፣ አገልግሎታቸው ስለሚቋረጥ ጉዳዩ ሊታሰብበት እንደሚገባ አጥኚዎቹ አሳስበዋል፡፡

የዩኔስኮ ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ካፓስቲ ቢዩልዲንግ ኢን አፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ዩሜኪ ዩዜኪ እንደተናገሩት፣ በኮንፍረንሱ አፍሪካ ውስጥ ያለው የኮንትራት መምህራንን ሁኔታ የሚያመላክቱ ተሞክሮዎች ቀርበዋል፡፡ በቀጣይ ፖሊሲ አውጪዎች በትምህርት ሥርዓቱ መከተል ያለባቸውን መንገድ እንደሚያመለክትም ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...