Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምያሻቀበው ስደት

ያሻቀበው ስደት

ቀን:

በጦርነት፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በእምነት ምክንያት መከሰስ፣ መታሰርና መገደል ሰዎች ያለፍላጎታቸው ከአገራቸው እንዲሰደዱ ወይም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ፣ ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. (ጁን 21 ቀን 2016) የተከበረውን የዓለም ስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ‹‹ግሎባል ትሬንድስ›› በሚል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር 65.3 ሚሊዮን መድረሱን አሳይቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 ከአገራቸው የተሰደዱ ሰዎች ላይ ተመርኩዞ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በዓለም ከ113 ሰዎች አንዱ በጦርነት ወይም መከሰስን በመፍራት ከአገሩ ተሰዷል፡፡ በየደቂቃው 24 ሰዎች የተሰደዱ ሲሆን፣ ይህም ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ ጨምሯል፡፡

ከመንግሥታትና ከአጋር ድርጅቶች የተገኙ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ በ2015 ማብቂያ ላይ የተሠራው ጥናት 65.3 ሚሊዮን ሰዎች መሰደዳቸውን ሲያመላክት፣ ከ12 ወራት በፊት ከነበረው 59.5 ሚሊዮን ስደተኞች ጋር ሲነጻጸር የ5.8 ሚሊዮን ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም በስደተኞች ታሪክ ትልቁ ቁጥር ነው፡፡

ሰዎች በአገራቸው ያለን ጦርነት በመሸሽ፣ መታሰርና መገደልን በመፍራት በባህር ሲያቋርጡ ይሞታሉ፡፡ በየብስ ሲጓዙም በተዘጉ ድንበሮች ምክንያት ሕይወታቸውን በረሃ ላይ ያጣሉ፡፡ ሆኖም ስደተኞች እንዳይገቡ በማለት አገሮች ድንበሮቻቸውን መዝጋት ቢጀምሩም፣ የስደተኞችን ፍሰት መከላከል አልተቻለም፡፡ ይልቁንም ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ስደት ተበራክቷል፣ የስደተኞች ቁጥርም አሻቅቧል፡፡ በተለይ አይኤስ በዓረብ አገሮች ውስጥ የፈጠረው አለመረጋጋት፣ በኢራቅና በሶሪያ ያሉ ጦርነቶች በአፍሪካ ያለው ድህነትና የፖለቲካ ሽኩቻ በ2015 ለተመዘገበው ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ሚና ተጫውቷል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚለው፣ በዓለም ከተመዘገበው 7.4 ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከ113 አንዱ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂ፣ ስደተኛ ወይም በአገሩ ሆኖ ከቀየው የተፈናቀለ ነው፡፡ በ2015 ማብቂያ ላይ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች በበለፀጉ አገሮች የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ውሳኔ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ይህም በኤጀንሲው ታሪክ ትልቁ ቁጥር ነው፡፡

40.8 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በአገራቸው ውስጥ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እዛው በሚገኙ መጠለያዎች የገቡ ናቸው፡፡ 21.3 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ተሰደዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ሰዎች ተገደው ከቀያቸው ወይም ከአገራቸው እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ያለፉት አምስት ዓመታት የስደት አሉታዊ ጎን ማሳያ ሆነዋል፡፡ ብዙዎች በበረሃና በየብስ ቀርተዋል፡፡ መዳረሻ አገር ካገኙትም ሕጋዊ ተቀባይነት በማጣት ይሰቃያሉ፡፡ የስደተኞች አያያዝም ችግር ያለበት ነው፡፡ የመሰደዳቸው ምክንያት ውስብስብ ቢሆንም፣ ኤጀንሲው እንደዋና ምክንያት ያነሳቸው የርስ በርስ ጦርነት በተለይም ሶማሊያና አፍጋኒስታንን በተከታታይ ለሦስትና ለአራት አሠርታት ያህል የፈተናቸው የውስጥ ግጭት ለስደተኞች መበራከት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በሶሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመን፣ በቡሩንዲ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና በዩክሬን የተከሰቱ የርስ በርስ ጦርነቶች፣ እንዲሁም በማዕከላዊ አሜሪካ የሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ከሶሪያ 4.9 ሚሊዮን፣ ከአፍጋኒስታን 2.7 ሚሊዮን፣ ከሶማሊያ 1.1 ሚሊዮን ስደተኞች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኞች ኤጀንሲ ስር የሚገኙ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ በኤጀንሲው ስር ካሉ ስደተኞችም ግማሽ ያህሉን ይሸፍናሉ፡፡ በአገራቸው ውስጥ ሆነው ከቀያቸው በመፈናቀል ኮሎምቢያ 6.9 ሚሊዮን፣ ሶሪያ 6.6 ሚሊዮን፣ ኢራቅ 4.4 ሚሊዮን በማስመዝገብ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡

በ2015 በኤጀንሲው ኃላፊነት ስር ከነበሩት 86 በመቶ ያህሉ ስደተኞች በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የተጠለሉ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱርክ 2.5 ሚሊዮን ስደተኞች በማስጠለል ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች፡፡ ቱርክ በ2014 ብቻ 1.6 ሚሊዮን ስደተኞችን አሠልጥናለች፡፡ ከስደተኞቹም አብዛኞቹ ከሶሪያና ኢራቅ የተሰደዱ ናቸው፡፡ በፓኪስታን የሚገኙት ሁሉም ስደተኞች ከጎረቤት አፍጋኒስታን የተሰደዱ ናቸው፡፡

በ2015 በስደተኞች መዝገብ ከሰፈሩት 51 በመቶ ያህሉ ልጆች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከወላጆቻቸው የተጠፋፉ ወይም ከአገራቸው ብቻቸውን የተሰደዱ ይበዛሉ፡፡ በተለይ የአፍሪካ ሕፃናት የስደት ሰለባዎች ናቸው፡፡ በዓለም ከፍተኛውን የስደተኞች ቁጥር ከሚያስተናግዱ አሥር አገሮች አራቱ በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ አገሮች ከተጠለሉ ስደተኞች ከ57 በመቶው በላይ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችና ሕፃናት ናቸው፡፡ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ በአፍሪካ ትልቁን የስደተኞች ቁጥር የሚያስተናግዱ አገሮች ሲሆኑ፣ በ2013 ማብቂያ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን አስጠልለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ለስደተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ቢሠራም የፍላጎቱን ያህል አልተሳካለትም፡፡ ካስቀመጣቸው ዓላማዎች ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ ወይም በሄዱበት አገር የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖራቸው ማስቻል የሚገኙበት ሲሆን፣ ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ውጤቱ አመርቂ አልሆነም፡፡ በ2014 በዓለም ከሚገኙ ስደተኞች አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ ወደአገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በሰው አገር ያሉትም ቢሆኑ ሥራ በሕጋዊ መንገድ ለመሥራት ያላቸው ዕድል አናሳ ሲሆን፣ የሥራ ፈቃድ ለማግኘትም ይቸገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...