ከአገሬ አወቀ
አንድ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት ከኢትዮጵያ ወደ ጃፓን አገር የተላከ ቡና ውስጥ የፀረ ተባይ የኬሚካል ዝቃጭ (Pesticide Residue) በመገኘቱ ምክንያት ተመላሽ ስለመደረጉና እስራኤልም ከኢትዮጵያ የሚላከው ሰሊጥ በውስጡ ያለው የፀረ ተባይ የኬሚካል ዝቃጭ መጠን ከፍተኛ ነው በሚል ላለመግዛት መወሰኗ ይታወቃል፡፡ ሩሲያና ሞሮኮ በፊናቸው የተላከ ሰሊጥ ይሁን ሌላ ምርት በውስጡ የማይፈለግ የፀረ ተባይ ኬሚካል ዝቃጭ ተገኝቷል በሚል ተመላሽ እንዳደረጉ ከባለሥልጣናት ሪፖርት ተደምጧል፡፡
በእርግጥ እነዚህ የየአገሮቹን የጥራት ደረጃን ባለማሟላታቸው ከውጭ ተመላሽ የተደረጉት (ቡናና ሰሊጡ) ከዛ በኋላ የት እንደደረሱ አላውቅም!!!፡፡
በቅርቡ ደግሞ በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዝዋይ ከተማ ፋብሪካውን የተከለው አንድ ድርጅት፡-
- የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ዳይሜቶይት የተባለ የፀረ ተባይ ማምረቻ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም 48,000 ሊትር ዳይሜቶይት የፀረ ተባይ ኬሚካል ምርት አምርቶ መሸጡን፤
- በአክሲዮን ማኅበሩ ተመርቶ ግን ሳይሸጥ በመጋዘን ውስጥ እያለ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ከ13,000 ኪሎ ግራም በላይ ማንኮዜብ የተባለው የፀረ ዋግ ኬሚካል ምርት ስለመሸጡ፤
- በህንድ አገር 14,000 ሊትር ምርት ጥቅም ላይ ውሎ 4,000 ያህል ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰና ወደ 730 ያህል ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ፤ በባንግላዲሽ እንዲሁ ከአሠርት ዓመታት በፊት ጥቅም ላይ ውሎ ከፍተኛ ጉዳትና እስከ ዛሬ የዘለቀ ፀፀት ጥሎ እንዳለፈ የተነገረለትና ኢንዶሰልፋን የተባለ ፀረ ተባይ ምርት ለማምረት የሚውል ከ90,000 ኪሎ ግራም በላይ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ጥሬ ዕቃ ገዝቶ በአገራችን የሕግ አግባብ ሥልጣን ከተሰጠው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ዕውቅና ውጪ ጉምሩክን እንዲያልፍ በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዳስገባ፤
- ከፍ ሲል የተጠቀሱት የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት የፀረ ተባይ ጥሬ ዕቃና የፀረ ተባይ ምርት ከአክሲዮን ማኅበሩ እንዲወገድ ሲታገል የነበረውና የተፈጸመውን ድርጊት ያጋለጠው፤ የአክሲዮን ማኅበሩ የጥራት ማረጋገጫ ባለሙያ፤ በዚህ የመንግሥት ልማት ድርጅት ውስጥ የታየውንና አካባቢን ብሎም የሕዝብን ጤና ለከፍተኛ አደጋ የማጋለጥ አቅም ያለውን ምግባረ ብልሹና ኃላፊነት የጎደለው አሠራር ያጋለጠው ባለሙያ ከድርጅቱ ስለመባረሩ፤
ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ሬዲዮ በተከታታይ ባሠራጫቸው ዜናዎች ተደምጧል፡፡
አበው ሲተርቱ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ ይህ ባለሙያ አካባቢንና ሕዝብን ሊመጣ ከሚችል አደጋ በመታደጉ ሊሾምና ሊሸለም ሲገባ በተቃራኒው መንግሥት በአንድ በኩል አረንጓዴ ልማትን ዕውን ለማድረግና በሌላ ወገን ደግሞ ይህን መሰል የመልካም አሰተዳደር ችግር የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ባወጀበት ማግሥት እንዲህ ያለ ለሕግም ለሞራልም ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲፈፀም መመልከታችን የመንግሥትን አዋጅ ዘመቻ መሰል ግንጥል ጌጥ አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ የፌደራል ኦዲት መሥሪያ ቤት በቅርቡ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት አስደንጋጭ ጉዳይ በማለት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት የተባለው ሌላው የመንግሥት የልማት ድርጅት የተለያዩ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈ ከሁለትና ሦስት ወራት በኋላ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ እየሸጠ እንደነበረ አጋልጧል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች አገራችን በፀረ ተባይ ቁጥጥር ረገድ ያለችበትን የከፋ ሁኔታ በቁንፅል ለማሳየት የቀረቡ ማሳያዎች እንጂ የችግሩን ስፋት በሙላት ለመተንተን አይደለም፡፡ የቀረቡት ማሳያዎች በአገራችን ውስጥ በርካታ የፀረ ተባይ ኬሚካል አስመጪ ድርጅቶች ከመኖራቸውና ከደካማ የቁጥጥር ሥርዓቱ አንፃር ሲታሰብ ምናልባት ከዚህም የከፋ ኃላፊነት በጎደለው/በጎደላቸው አስመጪ/አስመጪዎች እስካሁን ላለመፈጸሙና አሁንም እየተፈጸመ ላለመሆኑ ምንም ዋስትና የለንም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ብርቱ ጥያቄ በእውነት እዚህ አገር የፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት አለ ወይ የሚል ይሆናል፡፡ እኔ እስኪገባኝ ድረስ ለጥያቄው ያለን መልስ አሉታዊ ነው፡፡ እንዲያው ለምናልባቱ የፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት አለ ከተባለ ደግሞ የፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ባለቤት ማነው? ባለቤቱስ በባለሙያ ተደራጅቷል? ብቃት ባለው ሁኔታ እየተመራ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ሥርዓትና የሥርዓቱ አስተዳዳሪ የሆነ አካል ባለበት አገር እንዲህ ያለ ሥር የሰደደ ችግር ሊፈጠር አይችልምና!!!፡፡
መንግሥት በአገሪቷ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ በመቅረፅና ተግባራዊ እንዲሆን በማድረጉ ምክንያት ሁሉም የዘላቂ ልማት ሥራዎች በአንፃሩ እንዲተገበሩ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ አረንጓዴ ልማት ፖሊሲ መከተል ያስፈለገበት ዋናው ዓላማ በአገሪቷ የሚከናወኑ ማናቸውም የልማት ሥራዎች ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡ በአገሪቷ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የተፈጥሮ አካባቢን የማይበክሉና ጪስ አልባ እንዲሆኑ ማስቻል ብቻውን አረንጓዴ ልማቱ ሙሉ እንዲሆን አያደርግም፡፡ የዘርፉ ምሁራን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አስፈላጊነት ሲተነትኑ የምንኖርባት ምድር የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ፣ ለሰው ልጆች ምቹ እንድትሆን፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ ምርት ማምረት፣ ተስማሚ የሆነ አየርና አካባቢ እንዲኖር ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ዓላማዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋናው ዓላማ ስለ አረንጓዴ ልማት ትንተና ለመስጠት ሳይሆን በመጀመሪያ እርሻችን አረንጓዴ ነውን? የሚል ጥያቄ በፖሊሲ አውጪዎችና ያገባኛል በሚሉ ሁሉም ባለድርሻዎች መካከል እንዲነሳ ለማድረግና እርሻችን አረንጓዴ እንዲሆንና የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ መርሕን የተከተለ እንዲሆን የበኩሌን አስተያየት እንደዜጋ ለመስጠት ነው፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ ጥናት መሠረት አብዛኛው የአገራችን የግብርና ሥነ ምኅዳር (አግሮ ኢኮሎጂካል ዞን) በእርሻ ላይ ለሚከሰቱት ለተለያዩ ተባዮች ምቹ በመሆኑ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማቅረብ ብቻ ያለ ፀረ ተባይ ኬሚካል በቂ ምርት ማግኘትም ሆነ በምግብ ራስን ለመቻል አዳጋች ነው፡፡ በመሆኑም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ እርሻ ላይ ለሚከሰቱት ተባዮች፣ ዋጎችና በሽታዎች መቆጣጠሪያነት የተለያዩ ኬሚካሎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ትርፍ ምርት አምራች በሆነው የአገሪቱ አካባቢ ያሉት አርሶ አደሮች የተለያዩ ኬሚካሎች አስፈላጊነት በመገንዘብ በአግባቡ ባይሆንም ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ምን ዓይነት ኬሚካሎች ናቸው ለተጠቃሚው እየቀረቡ ያሉት? ማነው በአብዛኛው የፀረ ተባይ ኬሚካል ንግድ፣ ሽያጭና ችርቻሮ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ያለው? በማንና በምን አግባብ ነው የፀረ ተባይ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት? ምን ዓይነት የፀረ ተባይ ኬሚካል ቁጥጥር፣ አስተዳደርና ክትትል ሥርዓት አለ? የሚሉት ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ውጭ አገር ሄደው ተመላሽ የተደረጉ የግብርና ምርቶቻችን በምናይበት ጊዜ፤ ዓብይ ሊባሉ የሚችሉ ችግሮችን ስንፈትሽ፤
- የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት፣
- የተከለከለ ወይም፣
- ጥቅም ላይ የዋለው ፀረ ተባይ ዝቃጭ በምርቱ ውስጥ ከተፈቀደው መጠን በላይ ተከማችቶ መገኘቱ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ይህም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ጥራቱን ያልጠበቀ ኬሚካል ጥቅም ላይ እየዋለ ስለመሆኑ ወይም ኬሚካል ጥራት በጎደለው ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ወይም ሁለቱንም ባላሟላ አኳኋን ኬሚካል ጥቅም ላይ እየዋለ ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው፡፡ ውጭ ሄደው ተመላሽ የተደረጉትን ትተን እዚህ አገር ውስጥ በየቀኑ ገበያ እየቀረቡ ያሉት የግብርና ውጤቶች ከዚህ ዓይነት ችግር ነፃ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በአገራችን በየቀኑ ገበያ ላይ የሚቀርቡ የግብርና ውጤቶች ምን ዓይነት ፀረ ተባይ መድኃኒትና ምን ያህል የፀረ ተባይ ዝቃጭ እንደያዙ ማወቂያ መንገድ ሥራ ላይ ባለመኖሩ እንጂ ወደ ውጭ ከተላከው የከፋ እንደሆነ ማን ያውቃል? ዓለም የደረሰችበት ወቅታዊ የሳይንስ ሃቅ እንደሚያረጋግጠው ማንኛውም ፀረ ተባይ ኬሚካል በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ውሎ ሲያድር ከፍተኛ የሆነ የኅብረተሰብ የጤና ቀውስ ወይም ችግርና የተፈጥሮ አካባቢ ብክለትን ያስከትላል፡፡ ለዚህም ነው አገሮች የተቀናጀ የተባይ መቆጣጠርያ ሥርዓት በመዘርጋት ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉት፡፡
ስለዚህ በአገራችን ግብርና የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲን የተከተለ ሆኖ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ የተባይ መቆጣጠርያ ሥርዓት (Integrated Pest Management) የመዘርጋት ሥራ አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ፣ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የጎን ጉዳት በመቆጣጠርና በመቀነስ የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ሥርዓትን መዘርጋት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ለዚህም ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን በተመለከተ የግብይት ሰንሰለቱን ትኩረት ሰጥቶ በመመርመርና በተገቢው ለማደራጀት፤
- ትክክለኛና ጥራቱን የጠበቀ ኬሚካል ወደ አገር ውስጥ ስለመግባቱ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፤
- የአገር ውስጥ ፀረ ተባይ አምራቾችም ቢሆኑ ትክክለኛና ጥራቱን የጠበቀ ኬሚካል አምርቶ ወደ ገበያ ስለማውጣታቸው መቆጣጠርና ማረጋገጥ፤
- በተለይም ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ዕውቀቱ ባላቸው ባለሙያዎች ብቻ እንዲነገዱና እንዲሸጡ ማድረግ፤
- በእርሻ ላይ ለሚከሰተው ተባይ ወይም በሽታ ጥራቱን የጠበቀና ትክክለኛው ኬሚካል በትክክለኛው መጠን በአሠራር ደንብ መሠረት በባለሙያ የተደገፈ ርጭት መፈጸም፤
- ኬሚካል የተረጨበት የግብርና ምርት ለምግብነት ከመዋሉ በፊት ወይም ገበያ ከመውጣቱ በፊት ከሰው ንኪኪ ነፃ ሆኖ መቆየቱን መቆጣጠርና፤
- ወደ ገበያ የሚቀርበው የግብርና ምርቶች በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ እህሎች፣ ቡና፣ ጫትና የመሳሰሉት በውስጣቸው ያለው የፀረ ተባይ ዝቃጭ መጠን መለካትና በጤናና በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን በመቆጣጠር መሥፈርቱን የማያሟሉ የእርሻ ምርቶችን ማስወገድ የሚቻልበት ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻም በአገራችን ወጥ፤ ከሌሎች የሕዝብና አካባቢ ጤና ከሚመለከቱ ሕጎችና ፖሊሲዎች ጋር የሚስማማ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ያረጋገጠ በተለይም ሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያማከለ የሕዝብና አካባቢ ጤና በመጠበቅና በመንከባከብ ዋና ዓላማ ሥር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የፀረ ተባይ ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት መቋቋም በተለይም የቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተሟላ የፍተሻ ሥራ የሚከናወንበት ላቦራቶሪ እውን ማድረግ ከፖለቲካ ተፅዕኖ የፀዳ በዘርፉ ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች የሚመራ እንዲሆን ማስቻልና ለአስመጪዎች፣ ለአምራቾች፣ ለነጋዴዎች፣ ለግብርና ሠራተኞችና ለተጠቃሚዎች ተገቢና ተከታታይ ግንዛቤን ለመፍጠርና ለማጎልበት የሚረዱ ሥልጠናዎችን ማደራጀት፣ መተግበርና በየጊዜው ውጤታማነታቸውን ባለድርሻዎችን ባሳተፈ መንገድ በመፈተሽና አስፈላጊ የሆኑ ማሻሻያዎችን ያካተተ ስትራቴጂን በመፈለግ ተግባራዊ ማድረግ ወቅቱ ግድ የሚላቸው ገሃድ ሃቆች ናቸው፡፡
አለበለዚያ ዛሬ በአገራችን የሚስተዋለው የተዝረከረከና ፋይዳ ቢስ የፀረ ተባይ ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት የሕዝብ ጤናና አካባቢን አደጋ ላይ እንዳይጥልና ምናልበትም የአረንጓዴ ልማት ሐሳባችን ከፖለቲካዊ ፍጆታ ባሻገር የሕዝብን ሁለንተናዊ ደኅንነትና ጥቅም ማስከበርን ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስና ትልሞችን ተግባራዊ ማድረግ አርቆ አስተዋይነት ነው፡፡ ቸልተኝነታችን ውሎ አድሮ ለትውልድ የሚተርፍ የከፋ መዘዝ ይዞ መምጣቱ አይቀርምና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!!!!!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡