Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግንባታ ፈቃድ ዕጦት ተገምሶ የተሠራው ሕንፃ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ጳውሎስ ተክለማርያም ለተለያዩ የቢዝነስ አገልግሎቶች የሚውል ሕንፃ ለመገንባት እንቅስቃሴ ከጀመሩ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የቢዝነስ ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስችላቸውን ቦታ ሲያፈላልጉ ቆይተው ከአራት ዓመታት በፊት ቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስድስት ሁለት ቦታዎች ያገኛሉ፡፡

ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ በሚወስደው ዋና ጐዳና ከኢትዮ ሴራሚክ ሕንፃ ጐን ካገኙዋቸው ሁለት የተለያዩ ቦታዎች፤ አንደኛው 348 ካሬ ሜትር ሌላኛው ደግሞ 568 ካሬ ሜትር ስፋት የነበራቸው ናቸው፡፡ ሁለቱም ቦታዎች ሕጋዊ የግለሰብ ይዞታዎች መሆናቸውን በማረጋገጥ ከቦታው ባለቤቶች ጋር በመደራደር ለመግዛት ይወስናሉ፡፡

ኩታ ገጠም የሆኑትን ሁለት ቦታዎች ለመግዛት የወሰኑት በአንዱ ቦታ ብቻ ያሰቡትን ሕንፃ ለመገንባት በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በሁለት የተለያዩ ካርታዎች የተመዘገቡትን ቦታዎች ደባልቆ መሥራት ይቻላል የሚል እምነት ይዘው እንደነበር አቶ ጳውሎስ ይናገራሉ፡፡    

ስለዚህ እነዚህን ቦታዎች ቀላቅሎ በአንድ ካርታ አጠቃሎ መሥራት እንደሚቻል በማረጋገጥ አንደኛውን ቦታ በ1.5 ሚሊዮን ብር፤ ሁለተኛውን ደግሞ በ2.5 ሚሊዮን ብር ይገዛሉ፡፡ የሁለቱንም ቦታዎች ካርታ በስማቸው ያዞራሉ፡፡

የባለቤትነት ማረጋገጫውንና ካርታዎቹን በስማቸው ለማዞር ከ750 ሺሕ ብር በላይ ለመንግሥት ወጪ በማድረግ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መውሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሕጋዊ መሥፈርቶችን ካሟሉ በኋላ ወደ ግንባታ ለመግባት ይዘጋጃሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ዕቅዳቸው ሕንፃውን በአንድ ዓመት ገንብተው ማጠናቀቅ ነበር፡፡ ለዚህ እንዲረዳቸው ሁለቱን ቦታዎች በመቀላቀል አንድ ካርታ እንዲሠራላቸው ማድረግ ቀዳሚ ስለሆነ ይህንን ለማስፈጸም ወደሚመለከተው የአዲስ አበባ መሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱን ቦታዎች በአንድ በመቀላቀል ካርታ ማግኘት እንደማይችሉ ይገለጽላቸዋል፡፡

ይህ የማይቻል ከሆነ በተናጠልም ቢሆን በሁለቱም ቦታዎች ላይ ግንባታ ማካሄድ የሚያስችላቸው ፈቃድ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው በቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት የነበራቸውን ምኞት ከማሳካት አኳያ በአማራጭነት የቀረበ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጳውሎስ፣ በአንደኛው ቦታ ላይ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችላቸውን የግንባታ ፈቃድ ሲያገኙ በሁለተኛው ይዞታቸው ላይ ግን ለግንባታ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ይቀራል፡፡ በአንደኛው ይዞታቸው ላይ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘት ያልቻሉበት ምክንያት በቦታው ላይ የቀበሌ ቤት አለበት የሚል ነው፡፡

አቶ ጳውሎስ፣ ‹‹ቦታውን ስንገዛ የቀበሌ ቤት አልነበረም፡፡  ይህንንም ቀበሌውና ክፍለ ከተማው አረጋግጠዋል፡፡ የቀበሌ ቤት አርፎበት ነበር የተባለው ቤት በ24 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ቢሆንም፣ ከአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የተሰጠው ምላሽ፤ የግንባታ ፈቃድ ሳይሰጥበት በቆየው ቦታ ላይ አለ የተባለው የቀበሌ ቤት ባይኖርም በጂአይኤስ ሲታይ ቤቱ መኖሩን ያሳያልና የግንባታ ፈቃድ መስጠት አይቻልም፤›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በቀበሌ ቤቱ ነዋሪ ነኝ የሚል ጠያቂ ያልቀረበ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጳውሎስ፣ ይህን እውነታ ለግንባታ ፈቃጁ መሥሪያ ቤት ለማስረዳት ለዓመታት ወደ ከተማው አስተዳደር ቢመላለሱም የግንባታ ፈቃዱን ሊያገኙ እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡

ይህ ያልተጠበቀ ክስተት የእነ አቶ ጳውሎስን የመሥራት ፍላጐት ያደበዘዘ ሲሆን፣ ተስፋ ሳይቆርጡ የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ በዚህ  ውጣ ውረድ የሕንፃውን ግንባታ ባሰቡት ጊዜ ለመጀመር እንዳላስቻላቸው ያስታውሳሉ፡፡

በቦታው ላይ ግንባታ ማካሄድ ያልተቻለበት ምክንያት እንዲጣራ የአስተዳደሩ የሕግ ክፍል እንዲመረምረው ተደርጎም የሕግ ክፍሉ ካካሄደው ምርመራ በመነሳት አቶ ጳውሎስ ግንባታ ለማካሄድ የሚከለክላቸው ምንም ነገር እንደሌለ የሚያመላክት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡  ከሕግ ክፍሉ ማብራሪያ በኋላም ቢሆን ግን የግንባታ ፈቃዱን ሊገኝ አልቻለም ይላሉ፡፡ ድርጊቱ የቱንም ያህል ቢያማርራቸውም ፈቃድ ይገኛል በሚል ተስፋ ያለሥራ ከመቀመጥ በማለት በአንደኛው ይዞታቸው ላይ ግንባታ ለመጀመር ይወስናሉ፡፡ ይህ ውሳኔ ቀላል እንዳልነበር የሚናገሩት አቶ ጳውሎስ፣ ዲዛይኑን በመቀየርና ባልተፈቀደላቸው ቦታ ላይ ሊያርፍ የሚችለውን የሕንፃ አካል በማስቀረት አዲስ ዲዛይን በድጋሚ ለማሠራት ይወስናሉ፡፡ አዲስ ያሠሩትን ዲዛይን ይዘው የግንባታ ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡ በአንደኛው ቦታ ላይ ግንባታ ማከናወን እንደሚችሉም ይፈቀድላቸዋል፡፡ ወደዚህ ውሳኔ የገቡት ግንባታ ለማካሄድ ፈቃድ እየተጠባበቁበት ባለው ቦታ ላይ ፈቃድ እንደሚያገኙ በማመንና በቀሪው ቦታ ላይ ሊያርፍ የሚችለውን የሕንፃ አካል ገጥሞ ለመሥራት በማሰብ ነበር፡፡ 

በሁለቱም ቦታዎች ላይ ለመገንባት በታሰበው ዲዛይን መሠረት ሕንፃውን መገንባት ቢቻልም፣ የታሰበውን የሕንፃ ዲዛይን ከፍሎ አንደኛውን ክፍል ብቻ መገንባታቸው ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

ለአንደኛው ቦታ የግንባታ ፈቃድ ሳይገኝ ሌላኛው ሕንፃ ተገንብቶ ባለበት ከዚህ በኋላ ፈቃዱ ገና ለገና ተገኝቶ ቀሪውን የሕንፃ ክፍል ከተጠናቀቀው ሕንፃ ጋር አዋቅሮ መገንባቱም ቢሆን ላልተፈለገ ድካምና ወጪ የሚዳርጋቸው ስለመሆኑም ይገልጻሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከዚህ ውጭ አማራጭ ስለሌለ በዚህም መንገድ ቢሆን ቀሪውን የሕንፃ ክፍል ለመገንባት የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ወደ ፈቃጁ አካል መመላለሳቸውን አላቆሙም፡፡

በአንደኛው ቦታ ላይ ሲካሄድ የቆየው የሕንፃ ግንባታ በአሁን ወቅት ተጠናቋል፡፡ ሕንፃውን ሙሉ የሚያደረገው ሌላኛው የሕንፃ ክፍል ግን የግንባታ ፈቃድ ባለመገኘቱ  ቦታው ታጥሮ እንዲቀመጥ አስገድዷል፡፡

24 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የቀበሌ ቤት አለ በሚል ሰበብ በሕጋዊ መንገድ የተያዘና ካርታ ያለው ቦታ ላይ ግንባታ እንዳይካሄበት ፈቃድ መከልከሉ ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት እንደሌለው አቶ ጳውሎሰ ሳይተቹ አላለፉም፡፡ የበለጠ አስገራሚው ነገር ከዚህ ቦታ ላይ ለመንገድ ተብሎ 77 ካሬ ሜትር ተቆርሶ መወሰዱ ነው፡፡ ለመንገድ ተብሎ ለተወሰደው 77 ካሬ ሜትር ቦታ ካሳ መከፈል የነበረበት ቢሆንም፣ ካሳ ያለመጠየቃቸውን አቶ ጳውሎስ ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ያደረጉት ቀሪው ቦታ ለሕንፃው ግንባታ በቂ ሆኖ ስተለኘ ነው፡፡ ነገር ግን የግንባታ ፈቃድ ለመስጠት የተጠቀሰው በ24 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ የቀበሌ ቤት በመኖሩ ምክንያት መከልከሉ በአንፃሩ በመንገድ ግንባታው ከይዞታቸው ላይ የተወሰደው 77 ካሬ ሜትር ቦታ ታሳቢና ተመዛዛኝ አለመደረጉን ተችተዋል፡፡

እንደ አቶ ጳውሎስ ገላጻ፣ በአንደኛው ቦታ ላይ የግንባታ ፈቃድ ያልተገኘበት ምክንያት አሳማኝ ባይሆንም፣ ሙሉ ሕንፃውን ለመገንባት በነበራቸው ጉጉት ሳቢያ መፍትሔ ይሆናል በማለት ያቀረቡት ሌላ ሐሳብም ነበር፡፡ ይህም 24ቱ ካሬ ሜትር በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ ተሰልቶ እንግዛው የሚል ነበር፡፡ ሐሳቡ አማራጭ በማጣት የቀረበ እንጂ የተሻለና ለእሳቸው የሚጠቅም ስለሆነ እንዳልነበር ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ይህም የመፍትሔ ሐሳብ አወንታዊ መልስ አላገኘም፡፡ ‹‹ጉዳዩን መርምሮ ሊወስንልን የሚችል አካልም አላገኘንም፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህም ችግሩ ምን እንደሆነ ግራ መጋባታቸውን ይናገራሉ፡፡

አሁን ግን ነገሩ ስላስመረራቸው ድምፃቸውን በማሰማት መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ሕንፃው ከሦስት ዓመት በፊት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረና፣ የሕንፃው መጠናቀቅም ተከትሎ ለመንግሥትም ትልቅ ገቢ ያገኝ ዘንድ ያግዝ ነበር የሚሉት አቶ ጳውሎስ፣ የግንባታ ፈቃድ ያልተሰጠበት ምክንያት አሳማኘ ሊሆንላቸው እንዳልቻለና ለአማራጮችና ለሐሳቦችም ዝግ የሆነ አሠራር እንደገጠማቸው ገልጸዋል፡፡ የሕንፃው ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃና ከሚያስገኘው ገቢ መንግሥት ሊሰበስብ የሚችለው ታክስ መታሰብ ነበረበት ያሉት አቶ ጳውሎስ፣ ለዜጐች የሚፈጥረው የሥራ ዕድል፣ በሙሉ ዲዛይኑ ሕንፃው ቢሠራ ለከተማው የሚሰጠውም ውበት ታሳቢ መደረግ እንደነበረበት ሞግተዋል፡፡

ከአስተዳደሩ የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚገልጸው ግን፣ ቅሬታ አቅራቢው አሁንም በተለያዩ እርከኖች ካሉ የቅሬታ ሰሚ አካላት  ዘንድ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑ ነው፡፡ የቅሬታ አቀራረቡም እስከ ከንቲባው ጽሕፈት ቤት ድረስ ይዘልቃል፡፡ ከይዞታቸው ላይ ቦታ ተወስዶም ከሆነ ካሳ ማግኘት እንደሚገባቸው የሚገልጸው የጽሕፈት ቤቱ መረጃ፣ በዚህ ቦታ ላይ ተፈጥሯል የተባለውን ችግር መርምሮ ተጨማሪ ምላሽ ይሰጥበታል ተብሏል፡፡

ለግንባታ ፈቃድ ክልከላው መነሻ የሆነው የቀበሌ ቤት ከሆነም የቦታው ገዥዎች ይህንን ማረጋገጥ እንደነበረባቸውም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡ በበኩላቸው አቶ ጳውሎስ ቅሬታቸውን ከንቲባው ጽሕፈት ድረስ ማድረሳቸውንና እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች