Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሲዳማ ዘመን መለወጫ በዓል ከብሔረሰቡ ተወላጅ አልፎ የዓለም በዓል መሆኑ አስደስቶናል››

ወ/ሮ ምሕረት ገነነው፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ቱሪዝምና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ

ሐዋሳ የቱሪስት መዳረሻና የመዝናኛ ከተማ እየሆነች የመጣች ሙደ ነች፡፡ ይህች ከተማ በአገር ውስጥ ቱሪስትም እየጎበኛት ይገኛል፡፡ በ1991 ዓ.ም. የነበረው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ጎብኚ 19.136 ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር ደግሞ 150,000 ጎብኝተዋታል፡፡ ጠቅላላው የአገር ውስጥም የውጭ ጎብኚ ደግሞ በ1991 ዓ.ም. 21.668 የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት እስከ ግንቦት 2008 ዓ.ም. 195,000 ሆኗል፡፡ ሌላው የሲዳማ የዘመን መለወጫ የጫምባላላ በዓል በዚህ ዓመት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ ይህም ለከተማዋ የቱሪስት መዳረሻነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ቱሪዝምና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ምሕረት ገነነውን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጨንባላላ በዓል በቅርቡ በዩኔስኮ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- በመጀመሪያ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የጫንባላላ በዓል የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ዘንድሮም በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ ከሌሎች በዓሎች የሚለይበት የራሱ የሆነ ነገሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ ቀኑ የፍቅር የመቻቻል ቀን ነው፡፡ በዛን ቀን ከብት የማይመታበት ሕፃን ልጅን እንኳ የማይቆጣበት ሲሆን፣ ሰዎች ቢያስቀይሙህ እንኳን ምንም ዓይነት ዕርምጃ የማትወስድበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት ነው፡፡ በበዓሉም ቀን ጉርሳሜ የሚባል ምግብ ነው የሚቀርበው፡፡ ይህ ከብሔሩ ተወላጅ በተጨማሪ ለመላው ዓለም አስተማሪነቱ ትልቅ ነው በዓሉ ጉድማሊ በሚባል ሥፍራ በሚከበረው በዚህ በዓል ከአንድ መቶ ሺሕ ሕዝብ በላይ ይገኝበታል ብለን እንጠብቃለን፡፡ የበዓሉን መከበር ዘላቂነት ለማረጋገጥ ይህን ቦታ ከማልማት ጀምረናል ብሔረሰቡን፣ በዓሉን የሚያመላክቱ በርካታ ሥራዎች በውስጡ እየተሠሩም ይገኛል፡፡ ዙሪያውም በዓሉን በሚያመለክት መልኩ ታጥሯል፡፡ ማንኛውም የበዓሉ ታዳሚ ቱሪስቱን ጨምሮ ከዚህ ሲወጣ በዓሉን ያስታውስበት ዘንድ የተለያዩ ዕደ ጥበብ መሸጫዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓሉ የኛ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ጭምር ስለሆነ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሐዋሳ የቱሪስት ፍሰቱ ምን ያህል ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- የቱሪስት ፍሰቱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው የመጣው በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪስት እየጨመረ ነው፡፡ ለምሳሌ ብንመለከት በ1999 የአገር ውስጥ ጎብኚ 19,136፣ የውጭ ዜጋ ጎብኚ 2,532 በድምሩ 21,668 ነበሩ፡፡ በዚህም የተገኘው ገቢ 1,529,599.33 ሲሆን ይህ ቁጥር በ2007 ዓ.ም. ስናየው ደግሞ የአገር ውስጥ 173,199 የውጭ አገር ዜጋ ጎብኚ 42,705 ሺሕ ሲሆን የተገኘው ገቢ ደግሞ 191,382,851 ነው በያዝነው ዓመት ደግሞ እስከ ግንቦት 2008 ዓ.ም. በጠቅላላው 195,000 ጎብኝተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስቱ ቁጥር ይህን ያህል እየጨመረ ከመጣ አሁን ምን ያህል ሆቴሎች ተገንብተዋል? በእነዚህ ምን ያህል የሥራ ዕድልስ ተፈጥሯል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- የሆቴሎች ቁጥር እንደ ቱሪስቱ እየጨመረ ነው የመጣው ደረጃውንም እያሳደጉ ነው ማስፋፊያ በመውሰድ ወደ ሥራ የገቡም አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያሉን ሆቴሎች 4062 አልጋ ያላቸው 90 ሆቴሎች ሲሆኑ ብዙዎቹም ባለኮከቦች ናቸው፡፡ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች 268፣ ቁርስ ቤቶች 745፣ የጀበና ቡና 305 ባህላዊ መጠጥና ግሮሰሪ 176፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሁለት ናይት ክለቦች በጠቅላላው እነዚህ ሲሆኑ፣ የፈጠሩት የሥራ ዕድል ደግሞ ለወንድ 4,083 ለሴቶች 4,376 በጠቅላላው 8,459 ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሐዋሳ ከተማ የሚጎበኙ ቦታዎችስ እንዴት ናቸው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ሐዋሳን ከሌላው ቱሪስት መዳረሻ የሚለያት ከዓመት ዓመት በማንኛውም ወቅት መጎብኘት መቻሏ ነው፡፡ በመጎብኘት ረገድ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው ሐይቅ ሲሆን፣ አሁን አሁን ደግሞ ሃይማኖታዊና ዓመታዊ ክብረ በዓሎች እየሳቡ ነው፡፡ ለምሳሌ የገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል የፕሮቴስታንት ፕሮግራሞች እንዲሁም የጫምባላላ በዓል በሰፊው ቱሪስት እየሳቡ ያሉ ናቸው፡፡ የሚጎበኙ ቦታዎችም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት፣ ሐረፋማ ትክል ድንጋይ፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት ጣሊያን ሲጠቀምበት የነበረ መድፍ፣ ሃይማኖታዊ ባህል የታኅሳስ፣ ሐምሌ ገብርኤል በረመዳን፣ ለመዝናናት እንዲሁም የፕሮቴስታንት እምነት የተለያዩ ኮንፈረንሶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌላው የተፈጥሮአዊ መስዕብ የምንለው የታቦር ተራራ፣ አለሞራ ተራራ፣ ኩዩዋታ ተራራ አሉ፡፡ በተለይም የመጨረሻው ተራራ በእንስሳት እየተሞላ ይገኛል፡፡ የታቦር ኤኮቱሪዝም ብለን የጀመርነው ፕሮጀክትም አለ፡፡ ይህም በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሲጀመር የከተማዋን የቱሪዝም ገጽታ አንድ ደረጃ ያሳድገዋል ብለን እናምናለን፡፡ እንዲሁም የቡርኪቱ ፍልውኃ አለ፡፡ ይህ ፍሉዋኃ ከሌሎች ፍልውኃ የሚለየው ሦስት ነገሮች አሉት፡፡ በራሱ በተፈጥሮው የመታጠቢያ፣ የመታጠኛና የሚጠጣ ያለው ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ እያለማንና እየተንከባከብን የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሐዋሳ መቶ ሐይቆች ሳያይ የሚመለስ የለም፡፡ ሐይቁን ለመንከባከብ፣ ሥርዓት የሌለው የዓሳ ንግድንስ ሥርዓት ለማስያዝ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ሐዋሳ ከተማ አረንጓዴና ፅዱ የሚለውን ሕግ በጥብቅ የምታከብር ከተማ ነች፡፡ በተለይ ሐይቁን መጠበቅ ሐዋሳን እንደመጠበቅ ነው የምናየው፡፡ በዛ አካባቢ ተደራጅተው የሚሠሩ በርካታ ማኅበራት አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራትም ቱሪዝሙ ከሚያመጣው ኢኮኖሚ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ከፍቅር ሐይቅ ጀምሮ እስከ ዓሳ ገበያ ያሉ ማኅበራት ሐይቁን የመንከባከብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህንንም እየተገበሩት እንደሆነ እኛ እንከተላለን፡፡  በቅርቡም እንደውም ብዙ ዓመት ሠርተው ባለ ሀብት የሆኑ አሉ፡፡ እነዚህ በሌላ መተካት ስላለባቸው ቀጥለው የሚመጡት ከአረንጓዴ ልማት ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግ ከአሁኑ በተሻለ ሐይቁን የመንከባከብ ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡ ሌላው በሐይቁ አካባቢ ያለው የዓሳ መገበያያ ነው፡፡ ዓሳ ተጠምዶ በጥሬው ከመብላት ጀምሮ ትልቅ ግብይት የሚካሄድበት ነው ለቱሪስቱ አንዱ መስህብ ነው በሌላ መልኩ ደግሞ ድርጊቱ በአግባቡ ስለማይከናወን የሐይቁ አካባቢ በሽታና በከፍተኛ ቆሻሻ እየተበከለ ይገኛል፡፡ ይህንንም ለማስወገድ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ወጪ በመመደብ ዘመናዊ የዓሳ መገበያያና ማዘጋጃ ለማስገንባት ጨረታ አውጥቶ ተጫራች እየጠበቀ ይገኛል፡፡ የቱሪስት መስህቡን ሳይለቅ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ቱሪስት የመኝታ ክፍል ብቻ ከፍሎ በእግሩ ተንቀሳቅሶ ሐይቁን ጎብኝቶ ነው የሚሄደው የሚያመጣው ዶላር እዚህ እንዲቀር ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- አንድ ቱሪስት ቆይታው የሚራዘመው በሁለት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው ሐዋሳ ከተማ ያሏትን ተፈጥሯዊ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም አሁን በብዛት በከተማችን እየተለመደ ያለውን የቱሪዝም ኮንፈረንስ በመለየት እነዚህን በማልማት ሰፊ መሠረተ ልማት በመዘርጋት ከተማዋን እንደዚሁም መዳረሻዎችን በማስተሳሰር ትልቅ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ቆይታውን ደግሞ የሚያረዝመው ብዙውን ጊዜ በሆቴሎች አካባቢ ያለው ነገር ነው፡፡ ይህንንም ለማስተካከል በቅርቡ ከሆቴል ባለቤቶች ማኅበር፣ ከሆቴል ሥራ አስኪያጆች ጋር ጥምረት በመፍጠር አገልግሎት አሰጣጣቸውን ከመግቢያው ጀምሮ በሠለጠነ ሰው ኃይል በማደራጀት እንደዚሁም ባላቸው አቅም ጥሩ እንክብካቤ እንዲሰጡ ስላሉን መስህቦች እንዲያስተዋውቁ  ለማድረግ ትልቅ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሌላው የቱሪስቱን ቆይታ ለማራዘም አጎራባች ከተሞችንም እያስተዋወቅን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሲዳማ ዞን ብዙ የሚጎበኙ ሥፍራዎች አሉት፡፡ እንደዚሁም ገዳሞችን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን ጋር በመተባበር እንሠራለን፡፡ በዚህም አንዳንድ ለውጦችን እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቱሪስት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ በርካታ ሆቴሎችም ተገንብተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ የፀጥታ፣ በሆቴሎች የቆሻሻ አወጋገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የምሽት መዝናኛዎች ደረጃ አለመጠበቅ እንዲሁም የትራንስፖርት ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ለማስወገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መመልከት ጥሩ ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታት ሐዋሳ ከሌሎች ከተሞች ቀድማ ነው የተገኘችው ይህም ከፍተኛ ወጪዎችን በመመደብ የአስፓልት የኮብልስቶን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ዘርግታለች፡፡ እነዚህ ለመኪናም ለባጃጅም ለእግረኛም ለሞተረኛም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከአንዱ ከተማ ጫፍ ወደ ሌላኛው የከተማ ጫፍ ያለምንም ችግር በመረጠው መጓዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ ሌላው በከተማ ውስጥ የመንቀሳቀሻ ትራንስፖርትን በተመለከተ ወደ ሐዋሳ ለመግባት በአየር ትራንስፖርት እንዲሁም ደረጃውን በጠበቁ አውቶቡሶች ጭምር ነው ጎብኚዎች ወደ ከተማችን የሚገቡት፡፡ ይህ ለእኛ በጣም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ይህን ዕድል ይበልጥ ለመጠቀም አሁን በተበጣጠሰ መልኩ ተሳፋሪዎችን የመጫንና የማውረድ ነገር አለ፡፡ ይህ በቅርቡ የምናስተካክለው ነው፡፡ ወደ ከተማዋ የሚመጡትን ሰዎች ተቀብሎ ወደሚፈልጉት ቦታ የሚያደርሱም አሉ፡፡ እዚህም ላይ ግን ደረጃ መጠበቅ እንደለበት እናምናለን፡፡ ለነዋሪዎችም ቢሆን ይህ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ አስተዳደሩ ደግሞ ትልልቅ የከተማ አውቶቡሶችን እያቀረበ ይገኛል›› ባለሀብቶችም እዚህ ላይ የሚሰማሩበትን መንገድ እያሰብን እንገኛለን፡፡ ፀጥታ በፖሊስ ብቻ ማስከበር ስለማይቻል እኛ ያደረግነው ኅብረተሰቡን በማወያየት ችግሮቹን መለየት ነው በለየነው መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ጀመርን፡፡ ለምሳሌ ከእነዚህ ውጥስ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ባጃጆች ነበሩ፡፡ በተለይ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ እዚህ እናደርሳለን፣ በማለት ያልሆነ ቦታ በመውሰድ፣ ከእጥፍ በላይ በማስከፈል ፀጥታውን ሲያውኩ ነበር፡፡ እሁን ግን ከተወሰነ ሰዓት በኋላ እንዳይሠሩ በማድረግና ኅብረተሰቡ ደግሞ በራሱ ተነሳሽነት አንዳንድ አምፖል በሩ ላይ በመስቀል ብርሃን በማድረግ ወንጀለኞችን መደበቂያ በማሳጣት በአሁኑ ወቅት በፈለገው ሰዓት ወጥቶ በፈለገው ሰዓት መግባት ተችሏል፡፡ ዕድገት ተከትሎ የሚመጡ ብዙ ጥቅሞች አሉ፡፡ ይህንን ጥቅም በሕጋዊ መንገድ የሚጠቀሙም፣ በአቋራጭ ለመጠቀም የሚሞክሩም አሉ፡፡ በዚህ በሕገወጥ መንገድን ለመጠቀም ከሚሞክሩ አብዛኞቹ የከተማችን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ብዙ የምሽት ክለቦች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አብዛኞቹ በግሮሰሪ ፈቃድ ነው የሚሠሩት የእነሱ ጉዳይ ከጤና፣ ከግብርና፣ ከፀጥታ፣ ከሕገወጥ ንግድ፣ ከብዙ ችግሮች ጋር የተያያዘ ጭምር ስለሆነ ከሚመለከተው አካል ሁሉ ጋር በመነጋገር እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ ዕርምጃ በመውሰድ መፍትሔ የምንሰጥበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ ችግሩ እንዳለ እናምናለን፡፡ ሌላው ለሆቴሎች እንደዚሁም ለከተማችን ነዋሪ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ለመፍታት በብዛት ወጣቶችን እያደራጀን በዚህ ሥራ እንዲሰማሩ አድርገናል፡፡ በዚህ ችግሩ እየተቀረፈ ይገኛል ለምሳሌ በዚህ ከተማ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የእንቁላል እጥረት ነበር፡፡ በእነዚህ ባደራጀናቸው ማኅበራት በተሠራው ሥራ ዛሬ ያ ችግር የለም፡፡ አሁንም አቅርቦቱ በቂ ነው የሚል እምነት የለንም ከተማም ከነዋሪዎች ፍላጎት በተጨማሪ በየቀኑ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ቱሪስት እየጨመረ እየመጣ ስለሆነ ይህንን ፍላጎት ደግሞ ከግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር የከተማዋን ግብርናን ለማስፋፋት ጥረት ላይ እገኛለን፡፡ የቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ አሁንም ከተማዋ አረንጓዴ ፅዱና ውብ በማድረግ ከኅብረተሰቡ ከተማዋ ውስጥ ካሉ ሆቴሎች ምክክር በማድረግ ምንም ዓይነት ቆሻሻ ወደ ጎዳና እንዳይወጣ ሆኗል፡፡ በእርግጥ የተጠራቀሙትን በማንሳት በኩል አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፡፡ በውስጥ ለውስጥ በጋሪ ነው የሚነሳው፡፡ ይህንንም መቀየር ያስፈልጋል የከተማ አስተዳደሩም ከሐዋሳ ከተማ ወጣ ብሎ የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማከማቻ በማስገንባት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ጋር በተያያዘ በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም የከተማዋ ክልል አደጋ ቢከሰት ዘመናዊ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ቢሮ ከነ ሙሉ ትጥቁ ስላለን በዚህ በኩል ሙሉ በሙሉ ከችግሩ ነጻ ነን ማለት ይቻላል፡፡ በተረፈ ይህን ሁሉ ችግር ብቻችን ሠርተን የፈታነው አይደለም፡፡ ወደፊትም እነዚህ ችግሮች ይቀጥላሉ፡፡ ምክንያቱም እያደገች ያለች ከተማ ስለሆነች ባለሀብቶችም ከሆቴል በተጨማሪ በተለያዩ መስኮች መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በትራንስፖርቱ፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ ራሱንም ጠቅሞ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ፈጣሪ መሆን አለበት፡፡ ሌላው ይህ ሁሉ ስኬት የተገኘው በአደረጃጀቶች ነው፡፡ አሁንም አጠናክረን እንቀጥልበታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከሆቴል ባለቤቶች ወይም ከማኅበራቱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ምሕረት፡- ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ በተናጠልም ይሁን በጋራ የሚፈልጉትን ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ማንኛውም ኢንቨስት ለሚያደርግ ወይም ላደረገም ችግሩ ካለ ቢሯችን ክፍት ነው፡፡ ማኅበሩም እንዲጠናከር እንፈልጋለን፡፡ በቅርቡም ሙሉ የቢሮ ዕቃ በማሟላት ቢሯቸውን ልናስረክብ በዝግጅት ላይ ነን፡፡ ወደፊትም የሚጠይቁንን አቅም በፈቀደ መጠን እናደርጋለን፡፡ እኛም ከእነሱ የምንጠብቀውን የጥራት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲፈጽሙ እንጠብቃለን፡፡ ሌላው በቅርቡ የተደረገው የሆቴሎች የደረጃ አሰጣጥ እጅግ ደስተኞች ነን፡፡ እኛ ካሉን ሆቴሎች አሥራ አንዱ ለኮከብ ይበቃሉ ብለን ነበር የጠበቅነው፡፡ በመጀርያው የኮከብ አሰጣጥ ቅር ተሰኝተው የነበሩትና ግን ከተስተካከለላቸው ጭምር 20 ባለኮከብ ሆቴሎች ናቸው ያሉን፡፡ ስለዚህ ከጠበቅነው በላይ ስላገኘን በጣም ነው ደስ ያለን፡፡ ይህ ደግሞ ለሚመጣው የቱሪዝሙ ዕድገት ከወዲሁ መዘጋጀት ስለሚያስፈልግ ከማኅበራቶቹ ጋር ጠንክረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የተሠሩ ሥራዎች አንዳሉ ሆነው በቱሪዝሙ የኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ ምሕረት፡- እስካሁን የሠራናቸው ሥራዎች ብዙ ኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አድርገዋል ብለን እናምናለን ወደፊትም የቱሪዝም ሴክተሩን እያለማነው በሄድን ቁጥር በአካባቢው ያሉት ሰዎችን ከመጥቀም ይጀምርና ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ሴክተሩን ባዘመንን ባበለፀግነው ልክ ከቡና ማፍላት ጀምሮ እስከ ሆቴል ማናጀር ደረጃ ያለ ይጠቀማል ማለት ነው፡፡ በማኅበራት በመደራጀትም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ይኮናል ማለት ነው፡፡ ሌላው የከተማዋን ነዋሪ እንዲሁም በአጠቃላይ የክልሉን የገቢ ምንጭ ያሳድገዋል ብለን ተስፋ የጣልንበት በቅርቡ ግንባታው የሚጠናቀቀው ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ ለከተማዋ እንደ ቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ እዚህም ላይ ሥራ መሥራት ጀምረናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች