Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው የተንሰራፋውን የቤቶች አስተዳደር ችግር ለመፍታት አዲስ ዕቅድ እያዘጋጀሁ ነው አለ፡፡

በዚህ ዕቅድ የቀበሌ ቤቶችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች በዘመናዊ መንገድ የሚተዳደሩበት ዘመናዊ አሠራር ተቀይሷል ተብሏል፡፡

የቀበሌ ቤቶችንና የኮንዶሚኒየም ቤቶችን የማስተዳደር ሥልጣን ያለው የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ አዲስ አሠራር እንደሚዘረጋላትም ታውቋል፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት እጥረት ብቻ ሳይሆን ቤቶቹን የማስተዳደር ችግርም እየተስተዋለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው በከተማው በአጠቃላይ 328 ሺሕ ቤቶች ይገኙ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 200 ሺሕ የሚሆኑት የቀበሌ ቤት ሲሆኑ፣ እነዚህ ቤቶች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት የዋሉ ናቸው፡፡ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ 150 ሺሕ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህ መኖሪያ ቤቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ በተለይ የቀበሌ ቤቶችን በ2007 ዓ.ም. ቆጠራ በማድረግ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ጥናት አካሂዷል፡፡

በዚህ ዓመት ደግሞ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ቆጠራ ያካሄደ ሲሆን፣ በቤቶች ቆጠራ ወቅትም ቀላቅሎ መያዝ፣ በሕገወጥ መንገድ ሰብሮ መግባትና ማከራየት፣ የባንክ ዕዳ ሳይከፍሉ ይዞ መገኘትና የመሳሰሉት ችግሮችን አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም የጋራ መጠቀሚያ (ኮሚዩናሎችን) ማከራየት ተጠቃሽ ችግር መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹በቀበሌ ቤቶች የታየው ሕገወጥ ድርጊት የከፋ ነው፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ችግር ቢኖርም ቀደም ብለን ደርሰንበታል፤›› በማለት የተናገሩት ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹በቀበሌ ቤቶች ቆጠራ ወቅት ከገጠሙ ችግሮች መካከል ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የቤቶች ቆጠራ ባለመካሄዱ የመረጃ ችግር ነበር፤›› በማለት የችግሩን ስፋት አስረድተዋል፡፡

ይህ ችግር በአሁኑ ወቅት እየተገነቡና በቀጣይነት በሚተላለፉት 171 ሺሕ ቤቶች፣ ብሎም ወደፊት በሚገነቡ ቤቶች እንዳያጋጥም፣ የከተማው አስተዳደር መላ መዘየዱን ከንቲባው አብራርተዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ይህንን ችግር ለመፍታት ተጨማሪ ሕግ ማውጣት ማስፈለጉን እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ልምድ በመውሰድ ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል ራሱን የቻለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ዘመናዊ የቤቶች አስተዳደር አሠራር እየተቀየሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ይህ አሠራር ቀደም ብሎ መምጣት የነበረበት ቢሆንም፣ ዘግይቶም ቢሆን መተግበር የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች በመልካም ጎኑ  አንስተውታል፡፡

ባለሙያዎቹ የከተማው አስተዳደር ከዚሁ ጎን ለጎን ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ያሉትንም ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

በወታደራዊው መንግሥት (ደርግ) የሥልጣን ዘመን ከግለሰብ የተወረሱ ቤቶች በቀበሌ ስም ተመዝግበው በግለሰቦች ጊቢ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙ አንድ ባለሙያ፣ እነዚህን የግል ባለይዞታዎች የሚሰጣቸው የይዞታ ካርታ ‹‹ፕሮፖርሽናል›› እንደሚያስገኝ አስገንዝበዋል፡፡ ግለሰቦቹ የግል ይዞታቸውን ለመሸጥ፣ ለመለወጥ እንዲሁም የአካባቢ ልማት ጥናት (LDP) በሚያዘው መሠረት ለማልማት መቸገራቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ይህ ሁኔታ ዜጎች የራሳቸውን ሀብት ለሚፈልጉት ዓላማ ለማዋል ያስቸገረ በመሆኑ፣ አስተዳደሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ይህ ችግር ባለይዞታዎቹን መግቢያ መውጫ ብቻም ሳይሆን፣ ከተማውን ቅርፅ አልባ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል በመሆኑ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ሌላ ባለሙያ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የግል አልሚዎች የከተማውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ ግንባታዎችን እያካሄዱ ቢሆንም፣ ግንባታው ዘገምተኛ በመሆኑ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከዚሁ የመኖሪያ ቤት ችግር ሳይወጣ፣ የተገነቡ ቤቶች ላይ ሕገወጥነት መንሰራፋቱ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አቅመ ደካማዎች መገልገል እንዳይችሉ ሆኖ ለኪራይ ዓላማ መዋሉ አሳሳቢ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

ከንቲባ ድሪባም ሆነ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ይህ ድርጊት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአደባባይ ቢናገሩም፣ አስቸኳይ ዕርምጃ በመውሰድ በኩል ብዙም ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየታየ አይደለም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...