የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ግብፅ ያላትን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ እስራኤል ጣልቃ በመግባት እንድትሸመግላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንደጠየቁ የግብፅ ጋዜጦች ያሰራጩት ዘገባ አመለከተ፡፡
ጋዜጦቹ የወሬ ምንጭ ያደረጓቸው የዓረብ አገሮች ዲፕሎማቶችን ሲሆን፣ ግብፅ በግድቡ የግንባታና የውኃ ማጠራቀም ሥራ ሒደት ለምታቅርብላት የትብብር ጥያቄ ኢትዮጵያ ፈቃደኛ አልሆን ብላለች ማለታቸው የተነገረው ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ለሽምግልናው ኔታንያሁ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
የጋዜጦቹ ምንጮች ብለዋል ተብሎ እንደተጠቀሰው ከሆነ አልሲሲ ወደ ኔታንያሁ ሽምግልና ለመጠየቅ የተገደዱት በዓረብ አገሮች በኩል ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ነው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋር የሆነችው እስራኤል በሁለቱ አገሮች መካከል እንድትሸመግል ጥያቄ ለማቅረባቸው መነሻ የሆነው ምክንያት ተደርጎ ቀርቧል፡፡
የግብፅ ዲፕሎማቶች ግን እስራኤል በአሸማጋይነት መሳተፏ የናይልን ውኃ ግብፅ ለእስራኤል አሳልፋ እንድትሰጥ ሊያስገድድ ይችላል በሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት እስራኤል፣ በጠቅላይ ሚኒስትሯ የተመራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ በሚጠበቅበት ወቅት እንዲህ ያሉ ዘገባዎች መደመጥ መጀመራቸው ከኔታንያሁ ጉብኝት ጋር ሊያያዝ ስለመቻሉ የታወቀ ነገር የለም፡፡