Monday, June 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለውይይትና ለውሳኔ የቀረበ አጀንዳ ሳይኖር ውሳኔ አይኖርም በሌለ ውሳኔም የሚጣስ ውሳኔ የለም

በዐምደሚካኤል ተክሌ

የነገው ሰው ትምህርት አክሲዮን ማኅበር አስመልክቶ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣውን ዘገባ ተመልክተናል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በአክሲዮን ማኅበራችን ላይ የሚወጡ የተለያዩ የሚዲያ ዘገባዎችና የጥቂት አባሎች ጉሸማ የአክሲዮን ማኅበራችንን ምን ደረጃ ላይ እንደሚጥለው ዛሬም ያልተረዱ ጥቂት ባለአክሲዮኖች በሚሰጡት መረጃ መነሻ የሚወጡ ዘገባዎች ላይ ከልማዳዊና ተራ አመለካከት ለመውጣት ሲባል ጊዜን መስዋዕት በማድረግ መልስ መስጠት አስፈላጊ ሆኗል፡፡

  1. ቦርዱ የጣሰው የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ስላለመኖሩ

ቦርዱ እንደጣሰው ተደርጎ የቀረበው የኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉባዔ ምልአተ ጉባዔ ባለመሙላቱ ለሦስተኛ ጊዜ የተጠራ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ነበር፡፡ በአክሲዮን ማኅበሩ ችግሮች ዙሪያ በ2004 ዓ.ም. በጠቅላላ ጉባዔው ተሰይሞ የነበረው አምስት አባላት ያሉት አጥኚ ኮሚቴ ባቀረበውና በውስጥ ችግሮቻችን ምክንያት እየተንከባለለ ያለውሳኔ አድሯል ይባል በነበረው ሪፖርት ላይ ኮሚቴው በመጨረሻ አማራጭነት ባቀረባቸው ‹‹ኩባንያው ይከራይ ወይም ይሸጥ›› በሚሉ ሁለት የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ውሳኔ ለማሰጠት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሠረት የተጠራው ድንገተኛ ጉባዔ በእነኚህ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ የሚያሳልፈው ውሳኔ ‹‹ውሳኔ የሚሆነው›› በጉባዔው ከተገኘው ድምፅ በሁለት ሦስተኛው ከሁለት አንዱ የውሳኔ ሐሳብ ሲደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን በዕለቱ ከተገኘው ድምፅ ውሳኔ የቀረቡት ‹‹ይሸጥ ወይም ይከራይ›› የሚለው አማራጭ የውሳኔ ሐሳብ አንዳቸውም በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ባለመደገፋቸው ጉባዔው በዚህ የአጥኚ ኮሚቴ የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሰጠው ውሳኔ የለም፡፡ ከእነኚህ አጀንዳዎች ውጪ የትምህርት ሥራው መቀጠል አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጭብጥ በአጀንዳነት አልቀረበም፡፡ ውይይትም አልተደረገም፡፡ ድምፅም አልተሰጠበትም፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው በዚህ ላይም አልወሰነም፡፡

‹‹አክሲዮን ማኅበሩ ባለበት፣ በተቋቋመበትና በተሻሻለው ዓላማ መሠረት ሥራውን እንዲቀጥል ወስነናል፤›› በሚለው የቃለ ጉባዔው አገላለፅ ላይ የቦርዱ ሊቀመንበር የተወሰነ ውሳኔ አለመኖሩን ተናግሯል የተባለው፣ በአጀንዳ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ የሕጉን መስፈርት አሟልቶ የተላለፈ ውሳኔ እንደሌለ ለማመልከትና የትምህርት ሥራው እንዲቀጥል በግልጽ የተሰጠ ውሳኔ አለመኖሩን ለማመልከት እንጂ በቃለ ጉባዔው ላይ የሰፈረውን ቃል አልተጻፈም ለማለት አለመሆኑን ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለሆነም ከቃለ ጉባዔው የመጨረሻ አነጋገር መገንዘብ የሚቻለው ለጉባዔው ውሳኔ አጀንዳ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ የውሳኔ ሐሳቦች ውድቅ መሆናቸውን በጥቅሉ የሚያሳይ፣ ከፍ ሲልም አክሲዮን ማኅበሩ ሕልውናውን እንደያዘ በተቋቋመበትና በተሻሻለው ዓላማ መሠረት ሥራውን እንዲቀጥል መባሉ ቦርዱ ከደረሰበት ውሳኔ ጋር የሚቃረን አይሆንም፡፡

ኩባንያው የተቋቋመው አንድም ለአባሎቹ ትርፍ ለማስገኘት ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲሻሻል ያደረገው አንዱና ዋነኛው ተግባር ኩባንያው የማከራየት ሥራን በዓላማው ውስጥ እንዲያካትት የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ ማሻሻሉን ነው፡፡ ስለዚህ የተቋቋመበትን ትርፍ የማግኘት ዓላማ ለማሳካት አንደኛው አማራጭ ሥራ የሚሆነው ማከራየት ከሆነ ቦርዱ ከኩባንያውና ከባለአክሲዮኖቹ ጥቅም አንጻር ለአሥራ ስምንት ዓመት ከተዳከመና በጭቅጭቅ የዳከረበትን መንገድ ማጽዳት በምንም መስፈርት ከኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ጋር አይገናኝም፡፡ ይገናኛል ከተባለም የቦርዱ ውሳኔ የተሻሻለውን የአክሲዮን ማኅበሩን የማከራየት ዓላማ ወደ አትራፊነት መለወጡ መሠረታዊ ከሆነው የባለአክሲዮኖቹ ጥቅም አንጻር ጠቃሚ ሥራ መሆኑን የቦርዱ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ መሥራችና ባለአክሲዮንም የውሳኔውን ትክክለኛነት እንደቦርድና በግል ጭምር የምንደግፈው ለትክክለኛነቱ የምንቆምለት ነው፡፡

  1. በዘገባው ላይ የተነሱ አሳሳችና አደናጋሪ ግን በግልጽ መታረም ያለባቸው እውነታዎች
  1. የነገው ሰው ትምህርት አክሲዮን ማኅበር የተቋቋመው ብር 250.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ብር) ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን በመሸጥ ሆኖ በጊዜው መሥራች የተባሉት 104 ሰዎች አክሲዮን ሲገዙ የተከፈለው ገንዘብ ብር 2,709,250.00 (ሁለት ሚሊዮን ሰባት መቶ ዘጠኝ ሺሕ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር) ብቻ ነበር፡፡ ይህ የአክሲዮን የካፒታል መጠን በብዙ ጥረት፣ ልፋትና እንዲያም ሲል ማግባባት እየታከለበት መሥራቾቹም የተወሰነ አክሲዮን ሲጨምሩ፣ አዳዲስ ግለሰቦችንም ወደአክሲዮን በመጋበዝ ላለፉት 18 ዓመታት አክሲዮን ማኅበሩ እሸጠዋለሁ ካለው 200,000 (ሁለት መቶ ሺሕ) አክሲዮንና ይህንም ሸጬ አገኘዋለሁ ካለው ብር 50,000,000 (ሃምሳ ሚሊዮን ብር) ውስጥ የሸጠው አክሲዮን 33,752 (ሰላሳ ሦስት ሺሕ ሰባት መቶ ሃምሳ ሁለት) 28 በመቶ የተከፈለ ካፒታሉም ብር 8,468,000 (ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሰላሳ ስምንት ሺሕ) ብቻ ነው፡፡ ለአክሲዮን ማኅበሩ የትምህርት ሥራ ስኬት ማጣት በቂ ካፒታል አለመገኘትና ወሳኝ የሆነ ድምፅና ካፒታል ያለው ባለአክሲዮን አለመኖሩ ነው፡፡ ይህንም አጥኚ ኮሚቴው ያረጋገጠው እውነት ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ በባለአክሲዮኖች መካከል ጥርጣሬን በሚከት ሁኔታ አክሲዮን ማኅበሩ የተከፈለ ብር 34,970,500 ካፒታል እንዳለው ተደርጎ በጋዜጣው መዘገቡ ስህተት በመሆኑ የአክሲዮን ማኅበሩ የተከፈለ ካፒታል ብር 8,438,000 (ስምንት ሚሊዮን አራት መቶ ሰላሳ ስምንት ሺሕ ብር) ብቻ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
  2. አክሲዮን ማኅበሩ ለትምህርት ሥራ አገልግሎት ይጠቀምባቸው የነበሩ ክፍሎችን ያከራየው ትርፋማ ባለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በውስጥና በውጭ በተፈጠሩበትና አጥኚ ኮሚቴው ባረጋገጠው ተጨባጭና ገፊ ምክንያቶች መሠረት ‹‹ጥራት ጥልቀትና ምጥቀት ያለው›› የትምህርት ሥራ አገልግሎት የማቅረብ ተልዕኮውን ማሳካት አለመቻሉ በመሠረታዊነት ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ዛሬ ለአብነት ያህል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ቁጥር ወርዶ ወርዶ ሰባት የሶሻል ሳይንስና አሥር የተፈጥሮ ሳይንስ፣ በጠቅላላ 17 ተማሪዎችን በሁለት ክፍል ይዞ መጓዙ ብቻ ሳይሆን፣ ባለአክሲዮኖቹ ራሳቸው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ነው፡፡ ምናልባት አንዳንዶቹ አመሠራረቱን ተስፋ አድርገው በጅምሩ ጊዜ ልጆቻቸውን ለማስገባት ቢሞክሩም እያወጡ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ለመውሰድ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ አንዳንዶቹም ልጆቻቸው ከሌላ ትምህርት ቤት በሥነ ምግባር ጥሰት ሲባረሩባቸው ትምህርት ቤቱን ማገገሚያ ከሚያደርጉት በቀር በትምህርት ሥራው ላይ እምነት አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን…›› እንደሚባለው ሆነና ዛሬ ለራሳቸው ልጆች የማይመርጡትን ትምህርት ቤት ‹‹መቀጠል›› ነበረበት ሲሉ ትርፍ የሌለው ግን በሌላው የሰው ልጅ የትምህርት ሕይወት ላይ መፍረድ ምን ትርፍ ለማግኘት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
  3. ባለድርሻዎች እነማን ናቸው? በመሠረቱ ሕንጻዎቹንና ንብረቶቹ ማከራየት ወይም መሸጥ የሚል ሐሳብ ያቀረበው ጠቅላላ ጉባዔ ሳይሆን፣ የነበረው አጥኚ ኮሚቴ እንጂ ባለድርሻ የሚባል ቡድን የለም፡፡ በጋዜጣው ባለድርሻ የተባሉት ተቃውመዋል ሲባል ይህን የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት አጥኚ ኮሚቴውን ለማመልከት ከሆነ ስህተት ነው፡፡ በአጥኚ ኮሚቴው ውስጥ ከነበሩ ሁለቱ ባለአክሲዮኖች ዛሬም በቦርዱ ውስጥ የሚያገለግሉ በመሆኑ ‹‹ባለድርሻዎች›› የሚል ቅጽል የሰጣቸው ሰዎች የአጥኚ ኮሚቴውን ውሳኔ እንዳቀረቡ ተደርጎ የቀረበው ዘገባም ትክክል አይደለም፡፡
  4. ሌላው ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የአክሲዮን ማኅበራት የሚመሩበት ሥርዓት በሕግ የተበጀ ነው፡፡ በተለያዩ የንግድ ሕጉም ሆነ በመመሥረቻና መተዳደሪያ ደንቡ ላይ የአክሲዮን ማኅበራት ጉባዔ ስብሰባ የሚጠሩበት ውሳኔ የሚወስኑበት ወይም ቅሬታ የሚደመጥበት አካሄድ የድምፅ ልኬትና መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በአናሳ ድምፅ የአብዛኛው ባለአክሲዮን መብትና ጥቅም እንዳይጎዳ ለመከላከል ነው፡፡ ለምሳሌ ቦርዱ በወሰደው ዕርምጃ በጋዜጣው ባለድርሻ የተባሉትን ሰዎች ድምፅ አናውቅም እንጂ፣ ምናልባት ቢያንስ በቦርድ ውስጥ ካሉት ያነሰ ድምፅ ያላቸው ቢሆኑ እንኳ በአነስተኛ ድምፅ አብዛኛውን ድምፅ መጫን የሚቻልበት ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ጋዜጣው ዘገባውን ከማውጣቱ በፊት አክሲዮን ማኅበራችን ከ1-1088 አክሲዮን ያላቸው የ570 ሰዎች ስብስብ በመሆኑ ባለድርሻ ተብዬዎቹ በሕግ ዘንድ የሚኖራቸው ድምፅ የአብዛኛውን ወገን መብትና ጥቅም የማይጻረር መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደነበረበት እናምናለን፡፡
  5. ከዚህ ውጪ የኪራይ ሒደቱ በጨረታ ለምን አልተደረገም የተባለው ቢያንስ የተወሰኑ ባለአክሲዮኖችን ጠርተን ባወያየንበት ወቅት በቅንነት ለማስረዳት ተሞክሯል፡፡ በመሠረቱ የጨረታ ሥርዓት በግዴታነት የተቀመጠበት አሠራር በአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሥርዓት ውስጥ የለም፣ ጨረታ ግልፅነት ይኖረዋል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ ለአብዛኛው የአሠራር ጥፋትና ጉድለት ጨረታ ሽፋን ነው፡፡ በሌላ በኩል ምናልባትም ያሉትን አነስተኛ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ባሉበት ወቅት ጨረታ ወጥቶ ባይሳካ በጊዜው ሊፈጠር የሚችለውን የሥነ ልቦና ጫናና በቦርዱም ላይ ሊወርድ የነበረው ውግዘት ሲታሰብ የጨረታ ጥያቄ በነበረው ሁኔታ የማያስኬድና ተጨባጩን ውጤት መምረጥ የቦርዱ እምነትና ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ስለዚህ ጨረታ መከላከያ የማይሆንበት አጋጣሚን ማወቅ ቀላል ነው፡፡ በዚህ ሒደት ቦርዱ የተከተለው ግልጽ የሆነ ድርድርን ነው፡፡ ድብቅ ሳይሆን ለቦርዱ ግልጽ በሆነ አካሄድና አሠራር የአካባቢውን ዋጋ ግምት በመውሰድ በአጠቃላይ በሁለት ደረጃ በመደራደር ከተጨማሪ እሴት ታክስ በፊትና በኋላ በድምሩ በአጠቃላይ የብር 45,000,000 (ብር አርባ አምስት ሚሊዮን) ገቢን ግብ አድርጎ በመደራደር ተዋውሏል፡፡

ይህም ለባለአክሲዮኖች የተወሰነ ትርፍ ለመንግሥት ደግሞ በታክስ መልክ የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ፕሮጀክት እንጂ፣ በወር ብር 300,000.00 (ሦስት መቶ ሺሕ ብር) እንደተባለው ተቃሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህ የኪራይ ፕሮጀክት ደግሞ የአክሲዮን ማኅበሩን መርከብ ከወጀብ የሚታደግ፣ ቦርዱም ሆነ ባለአክሲዮን ስለቀጣዩ የቢዝነስ ዓላማና ስለካፒታል ዕድገት ረጋ ብሎ የሚያስብበትና ወደተሻለ ደረጃና ተግባር የሚሸጋገርበት የተሻለ ወቅትንና መንገድ እንደፈጠረ ቦርዱ ያምናል፡፡ ከዚህ ውጭ ‹‹የሕዝብን ንብረት የሚያባክን›› የሚለው ሥጋት ውኃ የማይቋጥር ምንም ዓይነት ተጨባጭ መሠረት የሌለው ነው፡፡ ሥጋት ያለባቸው ወገኖች ቢኖሩና ማንኛውም በቦርዱና በማኔጅመንቱ በሚወሰደው ዕርምጃ ሥጋታቸውን ለማስወገድ በቅንነት ለሚተባበሩና ለአክሲዮን ማኅበሩ ዕድገት ለሚተጉ በጎ አባሎቻችን የአክሲዮን ማኅበሩ ጽሕፈት ቤት በማንኛውም ጊዜ ተባብሮ ለመሥራት በሩ ክፍት መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles