የአዲስ አበባ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ተዘጋጀ
ለመጻሕፍትና ለጸሐፊዎቻቸው ዕውቅና የሚሰጥ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ማዘጋጀቱን አንጓ ቢዝነስ ሚዲያ ግሩፕ (አንጓ) አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ለሪፖርተር በላከው መግለጫው እንዳስታወቀው፣ ‹‹አዲስ አበባ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት›› የተሰኘው የሽልማት መርሐ ግብር አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችንና ጸሐፊዎች ለማበረታታትና የአገሪቱን የሥነ ጽሑፍ አስተዋጽኦ የበለጠ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ሽልማቱ በአምስት ዘርፎች ልቦለድ፣ ግጥም፣ ግለታሪክ ኢልቦለድና የሕፃናት የተመደበ መሆኑና ከአማርኛ ውጪ በተለያዩ ቋንቋዎች ለተጻፉ መጻሕፍት፣ እንዲሁም በተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች በኢትዮጵያውያን ለተደረሱ መጻሕፍት ዕውቅና ይሰጣል፡፡
እንደ አንጓ መግለጫ፣ የመጀመርያ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ታትመው ለገበያ የቀረቡ መጻሕፍት ናቸው፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ዲሲፕሊኖች በተመረጡ ዳኞች በሚገኘው ውጤት መሠረት፣ የሽልማት ሥነ ሥርዓት የሚከናወነው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚሆን ተቋሙ አስታውቋል፡፡
የመጽሐፍ ምርቃት
ዝግጅት፡- በታደለ ሲሳይ የተጻፈው ‹‹ፊልሞና›› የተሰኘ መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ ጥበባዊ መርሐ ግብሮችም ይቀርባሉ፡፡
ቀን፡- ሰኔ 12 ቀን 2008 ዓ.ም.
ሰዓት፡- 8፡00
ቦታ፡– ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ
****
የሥዕል ዐውደ ርእይ
ዝግጅት፡- ‹‹ኮንቴስትድ ደሜስቲሲቲ›› በተሰኘው ዐውደ ርእይ የማርጋሬት ፓርትና ጋብርዮል ደርማን ሥራዎች በመታየት ላይ ናቸው፡፡
ቦታ፡- አስኒ ጋለሪ
****
የዮጋ ቀን
ዝግጅት፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጁን 21 የዮጋ ቀን ብሎ የሰየመ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የዮጋ ቀን በኢትዮጵያ ይከበራል፡፡ የህንዱ አምባሳደር እንዲሁም ብዙ የዮጋ መምህራንም በዝግጅቱ እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡
ቀን፡- ሰኔ 18
ሰዓት፡– 3፡00
ቦታ፡- ሸራተን አዲስ
አዘጋጅ፡- ህንድ ኤምባሲ