Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፖለቲካና ሳቅ ኦፍሳይድ የለው!

ሰላም! ሰላም! አንዳንዱ ሰሞንን መጠንሰስ ሲያቅተው፣ ሰሞን በሚጠነስሰው ወሬ ውሎና አዳሩን ሲሳለቅበት ታገኙታላችሁ። እና አንድ ወዳጄን እንቅስቃሴው እንዴት ነው? ብለው፣ ፈንጂ የረገጠ ሰው ምኑን ይንቀሳቀሳል አለኝ። እኔ ደግሞ ተፍ ተፉን ብቻ እያየሁ የተናገረኝ ሊገባኝ አልቻለም። መሄዱን ይሄዳል እግሬ መች ይደክማል ሲባል እንዳልሰማ ሁሉ። ለካ ዘንድሮ በዚህ ከአፈር ተጠፍጥፎ የተሠራው ሥጋችን ወዲያ ወዲህ ሲንገላታ በማየት ብቻ፣ የመንፈስን ነገር ርስት አርገነዋል ለካ እናንተ። ታዲያ ከቁም ሞት ይሰውርህ ሲሉን አበው፣ በምኞት ደመና ሐሳብ ባክኖ ሲቀር የመንፈስ መሰበርን መናገረቸውም አይደል። እንግዲያ ይኼ ካልሆነ እንኳን ፈንጂ ዓይነ ምድር መርገጥ እኮ ዕድሜ ለልማታችን ታሪክ ሆኗል። ድንቄም ታሪክ ትሉ ይሆናል እኮ በሆዳችሁ። በበኩሌ እንኳን በሆዳችሁ በአፋችሁም አያገባኝም። አንዱ እኮ በቀደም  ለታ የእኛ ዝምታ ነው፣ እውነት የዴሞክራሲ መስፈን ነው፣ መንግሥታችንን ፀሐይ ያስባለው ብሎ ቢጠይቅ የባሻዬ ልጅ ከጎኔ ነበርና ስማ እንጂ አለው። እኛ እኮ በጽሑፍ ቢረቅም ባይረቅም ለሦስት ሺሕ ዘመን የኖርነው በዴሞክራሲ ነው። በቅኔ፣ በግጥም፣ በሽሙጥና በአግቦ ያንጀታችንን ስንናገር የኖርን ኩሩዎች ነን። ያውም እንኳን ሥጋ ለባሹን፣ እግዜሩን ሳንፈራ ‹‹ብቻውን ለመኖር እግዜር አስፈራው፣ ብቻውን ለመኖር እግዜር ቢያስፈራው ካለመኖር እንቅልፍ ይህን ዓለም ሠራው›› እስከማለት እንደ ባለቅኔው አድማሱ ጀንበሬ ነፃነት የነበረን ነበርን አለው። ኋላ ብቻችንን ስንሆን እሱ ፊት ያልነገርኩህን ልጨምርልህ አለና አንድ ንጉሥ ነበር፤ በግዛቱ ደግሞ ክፉኛ ያስቸገረው ተረበኛ አዝማሪ ነበር አሉ። እና በየግብሩ በየመኳንንቱ ስብሰባ ማሲንቆውን እየገዘገዘ በቅኔያዊ ግጥም ያሻውን እየለደፈ ሲያስቸግር ንጉሡ ምላሱን አስቆረጡት። ኋላ እንደልማዱ ንጉሡና መኳንቶቻቸው በተሰበሰቡበት ተጠራና አዝሜ፣ እንግዲህ በምንህ ትሰድበን ብሎ ቢለው አዝማሪው ያቺኑ የተቆረጠች ምላሱን አወጣበት ይባላል። ‹‹ሰፍተሽው ሞተሻል አፌን እንደኪሮሽ፣ እየጮኸ ሆዴ የማይጠግብ መስሎሽ›› አለ ያገሬ ሰው!

ስለእነ አምታታው በከተማ አጫውቻችሁ አላቅም አደል? በቃ ዛሬ ስሙኝ። እነአምታታው በከተማ ያው ከተማውን በማምታታት የዕለት ጉርሳቸውን ከእነ ጥበብ ዛፋቸው ጭምር በመሸፈን ሕይወትን በጨበጣ የሚገፉ የመንደሬ ወጣቶች ናቸው። ከዕለታት አንድ ቀን ወጣቶች ሳሉ ቆመው በመቅረታቸው  በዛው ዕድሜያቸው የቆመ መስሎን እንጂ ዛሬ አናታቸው ሽበት አዝርቷል። ሰባተኛ ክፍል ስለሪላቲቪቲ የተማርኩት ጽንሰ ሐሳብ የገባኝ በእነሱ ጊዜና ዕድሜ ነው። ማለት፣ እኔ ውር ውር በማለት ጠዋት ወጥቼ ማታ ስለምገባ እነሱን ሳይ ስልክ እንጨት እንደማየት ነው። ለእነሱ ደግሞ ሌላ ነው። አንድ ቀጠሮ ይዤ የጎረስኩት ሳልውጥ፣ ማንጠግቦሽ ከኋላ ከኋላዬ እየተከተለች፣ ይችን አፈር ስሆን ስትለኝ እነአምታታው በከተማ ጠሮባቸው ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ኖረው ካዩኝ ጉረስላት እንጂ ጋሽ አንበርብር። ደግሞ ለዚህች አፈር ዓለም ምን በወጣት እሷ አፈር የምትሆን ብለው ያቃጥራሉ። ይኼን ስትሰማ ተላላዋ ሚስቴ ቀበል አርጋ ኑ በሉ ቤት ያፈራውን ቀማምሱ ብላ ትጎትታቸዋል። መግደርደራቸው ሳይገባደድ ቤቴ ገብተው ጥላቸው ይሰውረኛል። ማምታታት አንድ በሉት። ባሻዬ በእነዚህ ወጣቶች ፈት የፈት ኑሮ በጣም ስለሚናደዱ አንዳንዴ በሚቀመጡባቸው ድንጋዮችና በእነአምታታው በከተማ መሀል ያለው ልዩነትን ሲገልጹ ድንጋዮቹ ከሥር እነሱ ከላይ መሆናቸው ብቻ ነው ይላል። ልጃቸው በዚህ አይስማማም። የእኛም እጅ አለበት ይላቸዋል። እኛ መንግሥት ነን? ይላሉ ባሻዬ ተናደው መንግሥት እኮ ሕዝብ ነው ይላል ምሁሩ ወዳጄ። ይህ ብሎ ኪሱ ገብቶ አፋቸውን እየጠራረጉ ላቤን ጠብ አርጌ የሞላሁትን ሌማት አራቁተው ሲወጡ ፍዘዙበት ብሎ መቶ ብር ያሽራቸዋል። ወዲያው የጥበብ ዛፋቸውን ሸምተው አምባቸው ላይ ጉብ ሲሉ ሠራተኛው የመንደሩ ነዋሪ ኑሮ ሲያስጨንቀው ሲያስጠብብ መዋሉን ይቀጥላል። እሾህ ላጣሪው ነዋ!

እንግዲህ ይህን ጨዋታ ያመጣሁት  በቀደም አምታታው በከተማ የለመዷትን ስልት ተጠቅመው ቤቴ በልተው ጠጥተው ወጡና መፍዘዣችን ዛሬ ቻለን በውል አፈጠጡብኝ። ዛሬ ለምን ስላቸው ዛሬ እኮ በዓል ነው። የዓመቱ ትዝታ ነው። ትዝታ ደግሞ በባዶ አይዘፈንም። የሚታወስ ያስፈልጋልና ልናስታውስህ ወደናል አሉኝ። ተስፋ የቆረጠ ሰው ነጋችሁ እንደሚያበላሸ ሰይጣንም ቢሆን ስለማያበላሸው ሠግቼ፣ ቀመራቸው የተስማማኝ መስዬ እምታታላቸዋለሁ። ስምታታላቸው ለካ አንድ አራት ፎቅ ሕንፃ የሚገዛ ደንበኛዬ መኪናውን አቁሞ ያየኝ ኑሯል። ቤቴ መጥቶ ተያይዘን ወደሚሸጠው ሕንፃ ይዤው ልጓዝ ቀጠሮ ነበረን። ሰላም ተባብለን ስናበቃ ምንድናቸው እነዚያ ልጆች? አለኝ። የነገርኳችሁን ነገርኩት። ለምን ሥራ አይፈጥሩም አለኝ። ለመፍጠር እኮ መፈጠር ይጠይቃል። ሥራ ፈጠራን በተመለከተ መንግሥት አላገናዝበው እያለ የተቸገርነው ዋነኛ ነገር እኮ ተፈጥሮን ነው። ከዚያ ነው አስተዳደግ ትምህርት ወሳኝ ድርሻ ያለው አልኩት። ተመስጦ ቆየና ለቅጠላ ቅጠላቸው የሠፈሩ ሰው በሙሉ የውዴታ ግዴታ እንዳለበት የነገርኩት ላይ አስምሮ፣ አንድ ዮሐንስ አድማሱ የተባለ የታወቀ የአገራችን ገጣሚ ለወሎዋ የጻፋትን ግጥም ሐሳብ አብራራልኝ። እሱ እንዳለኝ የተገጠመላት በአካባቢው ያደገች የኖረች እንስት ከመጋላው ውላ፣ ሐሳቧን ጭንቀቷን የሕይወትን ውጣ ውረድ በሚሉ ደንታ ሳትሰጠው፣ ገበያ ውላ እቃዋን ሸክፋ ስትመለስ ልጇን ከጀርባ እንዳዘለች፣ ሸከፏን በአናቷ እንደተሸከመች በብብቷ ሃባ ጫቷን ገዝታ ይዛ ትገባለች። የሕይወትን ገደቢስነትና ትርጉም የለሽነት በደንታ ቢስነቷና በጫቷ ኃይል ትቋቋመዋለች ይላል ሲለኝ፣ ሀቅ ለሁለት ተሰንጥቃ ሰነጠቀችኝ። የሪላቲቪቲ ትምህርቴ ከንቱ እንዳልነበረ ሲገባኝ ከስፍራና ከጊዜ አንፃር እንጂ ጭቅጭቅ ወጋችን ሁሉ ቆሎ ማይደፋ መሆኑ ታየኝ። ለካ ከተማውን እያምታታ ያስቸገረው ያለቦታው የገጠመ ብሎን ነው እናንተ! ወይ ከተማና ከተሜነት!

አሸዋ በሩቅ ሲያዩት ውኃ ይመስላል አሉኝ ባሻዬ ሰለስትና። አንድ አምስት ሺሕ ብር እንዳበድራቸው ጠይቀውኝ፣ ለቃቅሜ ከሰጠኋቸው በኋላ ቡና እያስፈላን እንጫወታለን። ያ ሕንፃ ውሎ ሳያድር ጉዳዩ ስላለቀ ዘና ብያለሁ። ምን አባቱ! የታዳጊዋ አገራችን ከዋለችን ውለታ አንዱ ጠዋት አሠርቶ ከሰዓት ማስተኛት ነው። ይኼ ዕድሌ ደግሞ እንደምታውቁት ከዚህ ወዲያ ብዙ የሚዘልቅ አይመስልም። ዕድሜ ለኢኮኖሚ ዕድገታችን ብሎም ፀንተን መዋለዳችን እንኳን ተተኝቶ ተባትሎም ኑሮ አልሰምር ብሏል። እኛ ሠፈር ግን ሰላሜ ነው። ይኼው እኔና ባሻዬ ቁጭ ብለን እንቀዳለን። ባሻዬ የአያታቸው በነበረ ርስት ወንድማቸው ይገባኛል ብሎ ከሷቸው ፍዳቸውን እያዩ ነው። ፍርድ ከሰማይ ነው ቢሉም ምድሩን አልተውትም። እና የርቀትን አደናጋሪነት በምሳሌ ሲገልጹ ምን ላይ ደረሱ ብዬ ጠየኳቸው። አታየኝም ምን ላይ እንደደረስኩ ብለው መሀል አናታቸውን ፊቴ ላይ ደቀኑት። ሳስቶ አታየውም ፀጉሬ? ፀጉር የሚጨርስ በሽታ ካንሰርን ነበር የሰማሁ። ነገር እንደሚመልጥ መች አውቄ? እያሉ ተብሰለሰሉ። ኋላ ቆይተው ቆይተው ድንገት ብድግ አሉና የኖርኩትን ያህል ላልኖር እንዳለ ሰጥቼ የማልገላገል እኔስ ምን ሆኜ ነው ሲሉ ቀልድ መስሎን ነበር። እነሆ ይኼው ቀልድ ያልኩት የምር ሆኖ ባሻዬ በውርስ ከአያታቸው ያገኙትን ርስት ሳያፍር ሳያጥር ይገባኛል ብሎ ችሎት ላቆማቸው ወንድማቸው ማስተላለፋቸውን ሰማሁ። ላያቸው ቤታቸው ብመላለስ በፍርድ መጓተትና ውኃ በማይቋጥር ሙግት እንቅልፍ ያጡባቸውን ቀናት ለማካካስ ስለተኙ ላገኛቸው አልቻልንም። በቃ በገዛ እጃችን በፎርፌ ካልተሸነፍን እንቅልፍ የለንም ማለት ነው? ነዋ እንግዲህ!

በሉ እንሰነባበት። ወደምናዘወትራት ግሮሰሪ ጎራ ብለን እኔና የባሻዬ ልጅ አንድ አንድ ይዘናል። ሰው ከፍላት ስክሪን ስልኩ፣ ወደፍላት ስክሪኑ ቴሌቪዥን ዓይኖቹን እያመላለሰ ወሬ ቀዝቅዟል። ሰው የናፈቀው አንድ ሰካራም ይኼ ኳስ አያልቅም እንዴ? ይላል። ገና መች ተጀመረ ይላል ከጎኑ የተቀመጠው። አይሰለቻችሁም? ብሎ መልሶ ይጠይቃል። የሚጫወቱልን ሳይሰለቻቸው እኛን ምን ብሎ ይሰለቸናል ይላል ፊት ለፊቱ አረንጓዴ ካፖርት በቢጫ የአንገት ልብስ አጣጥሞ የለበሰ ጎልማሳ። ይኼን አይቶ ያ፣ ሰው እያለ ሰው የራበው ሰካራም ኢትዮጵያም አለችበት እንዴ? ሲል አቦ ዝም በል ኳስ እንይበት። ብሎ አንዱ ተቆጣው። እሺ ኤርትራስ? ሲል ታዳሚው አላስችል ስላለው በሳቅ ፈረሰ። አሁን ገና ስለኳስ አወራህ ቢለው አንዱ ሞቅ ብሎት ዋዠኛው በተሳሰረ አፉ የምሬን ነው! የራሳችንን ጨዋታ ሳንጨርስ የሰው ሰው ግጥሚያ ስናይ ይገርመኛል። ብሎ መሬት ሲጠበው ሲያይ ያ ጎልማሳ ምን አባታችን እናርግ ወዳጄ። የእኛ ንትርክና ግጭት የሰዓት ገደብ የለው፤ ዕረፍት የለው ውጥረት የለው፤ ዳኛ የለው፤ ምን የለው ምን የለው። ቢያንስ እነሱ ቢጣሉም ቢራገጡም ዘመንና ጊዜ ይለያሉ ብሎ ቴሌቪዥኑን ሲጠቁመው አይዞህ፤ ያልከው ቅደም ተከተል፣ ሥርዓት አስከባሪ ባይኖረን አራጋቢ ስላለን አይዞህ ብሎ ቢል አሁንም ቤቱ ሳቅ በሳቅ ሆነ። የገባውም ያልገባውም ሳቀ። ሞኝ ሦስቴ ይስቃል ነውና እኛም ሲስቁ አይተን ሳቅን። እስኪ እናንተም ሳቁ። ፖለቲካና ሳቅኦፍ ሳይድ የለው! ግድ የለም ሳቁ። መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት