ጨለማዋ አኅጉር፣ ታዳጊዋ፣ ጥቁሯ ወዘተ. እየተባለች ስትጠራ የኖረችው አፍሪካ ወደ አንድ ቢሊዮን ሕዝብ የሚደርስ ነዋሪ ያሏትና በ53 ባንዲራዎች የሚታወቁ አገሮችን ያቀፈች ናት፡፡ የአፍሪካ የረጅም ዘመን መገለጫዎች በቀኝ ግዛት መያዝ፣ ባርነትና ግዞት፣ የእርስ በርስ ጦርነት ድኅነትና ረሃብ እንደነበሩም በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
ከቅርብ አሠርት ዓመታት ወዲህ ግን አኅጉሪቷ በተለይ የልማት ተስፋ እየታየባት እንደመጣች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት መጽሔት የሆነው ‹‹African Review›› ሚያዝያ 2016 ዕትም እንደሚያስረዳው አማካኝ የአኅጉሪቱ ዓመታዊ ዕድገት ከአራት እስከ አምስት በመቶ እያስቆጠረ ለስምንት ዓመታት መሄድ ችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያን የመሰሉ ከ12 የማያንሱ አገሮች ከስምንት እስከ አሥራ አንድ በመቶ ዓመታዊ ዕድገትን ለተከታታይ ጊዜ እያመጡ ነው፡፡
አፍሪካዊያን በጋራ ያቋቋሙት ኅብረታቸው 2060 መርኃ ግብሩም በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚ ተመጋጋቢነት፣ በሰላምና መረጋጋት የትብብር ምዕራፍ መግለጣቸው፤ ቀጠናዊ ድርጅቶችም በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት ላይ አተኩረው ወደ ተሻለ ሥራ መግባታቸው የአፍሪካ የተስፋ ብርሃንን ሊያጎሉ ችለዋል፡፡
ይሁንና አሁንም አገራችንን ጨምሮ ብዙዎቹን የአፍሪካ አገሮች የሚያሳስቡ አስጨናቂ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ አንደኛው ሙስና ነው፡፡ ሌላው የመልካም አስተዳደር እጦትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የብዙዎቹ የጨለማዋ አኅጉር ሕዝቦች ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ነው፡፡ እንደ ሦስተኛ ፈተና የሚወስደው የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን በማምጣት ረገድ በሕዝቦች ላይ የወደቀው ጫና ነው፡፡ በተለይ ግብርና መሩ ኢኮኖሚ ከኋላቀርነት ጋር ተጠብቆ አፍሪካን የበይ ተመልካች አድርጎት መቅረቱ ዛሬም ድረስ የዝናብ ጥገኛና በድርቅ ተመች አኅጉር ሆኖ እንዲቀር ነው፡፡ ኢንዱስትራላይዜሽኑም ከዕውቀት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ እጥረት ጋር በተያያዘ የፈጠረው ጫና እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡
እንደ አኅጉር ይህን በጥቅል ካነሳን በተጨባጭ የችግሮቹን አገራዊ አንድምታ በመፈተሽ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማነፃፀርን የዛሬው የትኩረታችን ማጠንጠኛ ለማድረግ ሽተናል፡፡
አኅጉር ቆርጣሚው ሙስናና ሀብት ማሸሽ
ሰሞኑን የአፍሪካ፣ ካሪቢያን፣ የፓስፊክና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች የፓርላማ አባላት የጋራ ስብሰባ በዊንድሆክ ውስጥ ሲጀመር የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦም ምቤኪ ባቀረቡት ጥናት፣ ከአፍሪካ በየዓመቱ 90 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ይወጣል ብለዋል፡፡
‹‹ይህ ገንዘብም የአፍሪካ አገሮች የሚያገኙትን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት 150 በመቶ ያህል ይሆናል፤›› ያሉት ምቤኪ፣ ይህንን ገንዘብ የሚወጣው በአብዛኛው ከወንጀል ድርጊት፣ ከግብር መደበቅና ከሙስና ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች የሚገኝ እንደሆነም አውስተዋል፡፡ ከአዳጊ አገሮች ጋር (እንደነቻይና) በሚካሄድ የንግድ ልውውጥ የሚገኘውን ገቢ መዛባትም ለዚህ ሕገወጥነት አስተዋጽኦ አለው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ‹‹የአፍሪካ ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ጉዳይ ከፍተኛ ቡድን (High-level Panel on Illicit Financial Flows from Africa›› ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው ምቤኪ፣ ራሳቸውም ይህንኑ አደጋ ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ በሐሰት ኩባንያዎች ስም የሕዝብ ገንዘብ ከየአገሮቻቸው ያወጡ ሰዎችን ዝርዝር የያዙ 11.5 ሚሊዮን ሰነዶች ‹‹የፓናማ ሰነዶች›› በሚል ይፋ ከወጡ በኋላ፣ በእነዚህ አካላት ላይ ምርመራና የአገር ሀብት የማደን ሥራ እንዲጀመር እየወተወቱ ይገኛሉ፡፡
ስለ አኅጉሪቷ ይህን ያህል ካልን በአገራችን እውነታዎች ላይ ሐሳብ መሰንዘርም ተገቢ ነው፡፡ ‹‹የፓናማ ሰነዶች›› በተባለው መረጃ ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ከሚወጣባቸው 18 የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ 16ኛ ደረጃ ላይ ተጠቅሳለች፡፡ ከዚህ ቀደምም ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለ የፀረ ሙስና ተቆርቋሪ ተቋም በአሥር ዓመታት ውስጥ ከአገሪቷ እስከ 11.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሀብት በሕገወጥ መንገድ ወጥቷል በማለት መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ አኃዝ ከወጣ በኋላ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የመጣ ለውጥ ወይም የተባባሰ ሁኔታ ስለመኖሩ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ነገር ግን በገሃድ የሚታዩ የአንዳንድ ሰዎች የውንብድና ምልክቶች የአገር ሀብት በውጭ ስለመቅረቱ ማሳያ ናቸው፡፡ ተሽከርካሪዎችን እናስመጣላችሁ፣ አክሲዮን መሥርተናል ተመዝገቡ፣ በሚሉ አጭበርባሪዎች ብዙዎች እየተዘረፉ ነው፡፡ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት የግብርና ታክስ ዕዳ እየነበረባቸው ከአገር የኮበለሉና ያለበቂ ማስያዣ የልማት ባንክ የኢንቨስትመንት ብድርን ውጠው ከአገር የተሰወሩ (ብዙዎቹ እነደ አበባ እርሻ ባለ መስክ የተሰማሩ የውጭ ዜጎች) ሰዎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡
ግዙፍ የሚባሉ የስኳር ከርፖሬሽን ዓይነት ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ሥራውን በታሰበው ጊዜና በጀት ከማጠናቀቅ ይልቅ እያድፋፉና እያረዘሙ ያሉ የውጭ ኩባንያዎችም ከዚህ ኃጢአት ንፁህ እንዳልሆኑ ይገመታል፡፡ ከሁሉ በላይ በከፍተኛ የዘረፋ ወንጀልና ሙስና እየተጠረጠሩ ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ተባባሪዎቻቸው ጠዋትና ማታ በሚመላለሱባቸው የውጭ አገሮች የተከማቸ ገንዘብ እንደሚኖራቸው መጠርጠሩም ሌላ አብነት ነው፡፡
ምንም እንኳን በሕግ የተያዘንና የፍርድ ውሳኔ ያላገኘን ጉዳይ ለጋዜጣ ንባብ ማብቃት ሕጉ የማይፈቅድ ቢሆንም፣ በሺዎች በሚቆጠሩ የመሬት ሽያጮች፣ በመንግሥት ከፍተኛ ጨረታ የሚካሄድባቸው ግዥዎችና የስምምነት ክፍያዎች ላይ በውጭ ተቀማጭ የሚደረጉ የኩባንያዎች ‹‹ኮሚሽን›› (ሕጋዊ ሙስናዎችም) አሉ፡፡ እነዚህን ጨምሮ ከታክስና ቀረጥ (በተለይ የቀረጥ ነፃና ትራንዚት ጨዋታ) በአገር ውስጥ ቱባ ዘራፊዎች ከበለፀጉበት በላይ የአገር ሀብት እያሸሹ የማይኖሩበትን ነገን ለመንደላቀቅ የሚመኙን እንዳሰባሰበም መጠርጠር ተገቢ ይሆናል፡፡
አፍሪካ ከሸማችነት ያልወጣች ድሃ ናት
ወደ ኢኮኖሚያዊ የአኅጉሪቷ ተግዳሮቶች ስናማትር አፍሪካ ከኋላቀር ግብርናና እርሻ አለመላቀቋ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትራላይዜሽንም የሚፈለገውን ያህል አለመረማመዷ ዋነኛ መሰናክል ነው፡፡ የቻይና ብሔራዊ ልሳን እንደሆነ የሚነገረው ‹‹ቻይና ዴይሊ›› የተባለው ጋዜጣ በቅርቡ ባደረገው ትንተና ‹‹የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎችና የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ አለመጠናከርና ተወዳዳሪ ያለመሆን ከአቅምና ቴክኖሎጂ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ይልቁንም ደካማ ክህሎት፣ ዝቅተኛ መሠረተ ልማትና ተመጋጋቢነት እንዲሁም የሕዝቡ ኋላቀር አኗኗርና የትራንስፎርሜሽን ዘዴ አመራር እጦትም እግር ከወርች አስሯቸዋል፤›› ነበር ያለው፡፡
በግብርናው መስክ ያለው አዝማሚያም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዲሴና (Akinwumi Adesia) በቅርቡ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የዓለምን 65 በመቶ ለእርሻ አመቺ የሆነ መሬት የያዘችው አፍሪካ ራሷን በብቃት መመገብ አቅቷት በየዓመቱ 35 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቀለብ (እህል) ትሸምታለች፡፡ ይህ አኃዝ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ስለሚመጣ እ.ኤ.አ. በ2025 110 ቢሊዮን ዶላር ለመሸመቻ የሚያስወጣ እንደሆነም ተተንብዪዋል፡፡
የአገራችንም እምብዛም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ የአገሪቱ የመኸርና የበልግ ምርት ከነበረበት 90 ሚሊዮን ኩንታል (አጠቃላይ) ወደ 320 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ መቻሉ አይታበልም፡፡ ይህ ጥርጣሬ፣ የአገዳ እህል፣ ጤፍና የጓሮ አትክልትን ጨምሮ የሚሰላ ሲሆን፣ የሕዝብ ቁጥሩም ከሞላ ጎደል በእጥፍ እንደጨመረ የሚታወቅ ነው፡፡
ብዙዎቹን የዘርፍ ሙያተኞችና የምጣኔ ሀብት ሊቃውንት የሚያሳስበው እውነታ ደግሞ አገሪቱ ከዚህ በላይ ምርት የምታሳድግበት ትግበራ ያለመጀመሯ ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁን ያለውን መሬት ሁሉ ፈግፍጎ የማረስ፣ ውኃ ገብ እርሻዎች ላይ የመስኖ ሥራን በመጀማመርና የጓሮ አትክልት ልማት ብቅ ብቅ ማለት ከቴክኖሎጂና ግብዓት አንፃራዊ መሻሻል ጋር ተዳምሮ እዚህ አድርሷል፡፡
በ25 ዓመታት ውስጥ ግን የትልልቅ የመስኖ ልማትና መካናይዝድ እርሻዎች አለመጠናከር (ጅምሮች ቢኖሩም ፍሬ አላፈሩም) ግብርናው ከበሬ ጫንቃና ከሞፈር ቀንበር ያለመላቀቁ፣ የአርሶ አደሩ አኗኗርና አመጋገብ ቢሻሻልም ምርታማነትን ሊያሳድግ በሚችል ደረጃ አለመሆን፣ ሰፋፊ የበረሃ እርሻ መሬቶች በታሰበው ደረጃ የውጭ የግብርና ኢንቨስተሩን ትኩረት አለመሳባቸው ወዘተ. ውጤቱ እንዳይጠበቅ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሳለፍነው በጋ ወራት ተከስቶ እስከ ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎችን ለዕርዳታ ተጋላጭ ያደረገ ድርቅ ነበር፡፡ አሁንም ቢያንስ የጀመረው ዝናብ ተጠናክሮ እስኪቀጥልና ፍሬ እስኪታይ ድረስ ዕርዳታው ይፈለጋል፡፡ ለዚህ የዕርዳታ አቅርቦት ብቻ ታዲያ በመቶ ሺዎች ቶን የሚቆጠር ስንዴና አልሚ ምግብ መንግሥት ብቻ እስከ 15 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ገዝቷል፡፡ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ግለሰቦች ድጋፍ ሲታከልበትም ቁጥሩ እንደሚያሻቅብ ይታመናል፡፡
ድርቁ ቢኖርም ባይኖርም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናቸው ያልተረጋገጠና በሴፍቲኔት ሥር ያሉ እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች አሏት፡፡ ለእነዚህ ወገኖች ዕርዳታና በከተሞች የእህል እጥረቱን ገበያ ለማርገብም በቢሊዮን ብሮች የሚገመት እህል ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ለመግዛት የሚገደድ መንግሥት ነው ያለን፡፡
ይህ እውነታ በተፈጥሮ በታደለችና ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትና የሰው ጉልበት ባላት አገር ውስጥ ሲወሳ ያለጥርጥር አፍሪካዊቷ ምድር መሆኗን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አገራችን ለሰብል ልማት ብቻ አይደለም አመቺ ሥነ ምኅዳርና ተፈጥሮ ያላት፡፡ በእንስሳት ሀብት ረገድም ያላት አቅም ገና ያልተነካና እየመከነ ያለ ነው፡፡
በዓለም ስምንተኛ በአፍሪካ አንደኛ የዳልጋ ብዛት የሚገኝባት ኢትዮጵያ፣ መስኩ የጥራት መጓደል፣ የሕክምናና አመጋገብ አለመሻሻል፣ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የቀንድ ከብቶች፣ በግና ፍየሎች ግመሎችና ዶሮን የመሰሉ አነስተኛ የቤት እንስሳት ቁጥራቸው እንጂ ብዙው ገቢያቸው ሊበዛ አልቻለም፡፡
በዚህ ረገድ ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ መካድ ያስቸግራል፡፡ በተለየ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴርን አቋቁሞ፤ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ዘርግቶ የሚያደረጋቸው የድጋፍ ተግባራትም አሉ፡፡ እነኝህ ሥራዎች ሁሉ ግን በቂ አይደሉም፡፡ ከአፍሪካዊ ኋላቀርነት ወጥቶ ዘላቂ ትራንስፎርሜሽንን እውን ማድረግ የግድ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች በቀዳሚነትና በበጎ የምትጠቀስባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በዚያው ልክ ከብዙዎቹ ድሃ አገሮች እኩል የምትወቀስባቸው ድክመቶችም ፈተና ላይ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶችና ፈተናዎች በብቃት ለማለፍ ሕዝብን ባሳተፈ ሁኔታ መንቀሳቀስ ካልተቻለ፣ የሚጠበቀው ውጤት ሊመጣ ያዳግታል፡፡ ስለዚህ ትኩረት ከችግሮች ለመውጣት እንላለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡