ከዓመታት በፊት ባሌስትራን ወርቅ በማስመሰል ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተፈጸመው ወንጀል ሁላችንንም ጉድ ያሰኘን አፋችንን ያስያዘ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ድፍረት የታከለበት ይህ ድርጊት ከባድ ወንጀል መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአገርንም ክብር የነካ ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡ እንዲህ ያሉ ለማሰብ የከበዱ ስልቶችን በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሕጋዊነት ስም የሚፈጸሙ ስለመሆናቸው በተከታታይ ከሰማናቸው ድርጊቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
በግብይት ውስጥ የምንሰማቸው የአንዳንድ ድርጊቶች አደገኛነት ማቆሚያ ካልተበጀላቸው ደግሞ የግብይት ሥርዓቱን ጤና ከማናጋት በላይ የሚደርሰው ጉዳትም የሰፋና የከፋ መሆኑ አይቀርም፡፡ የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ኩባንያ መሥርተው ወደ ሥራ በገቡ ኩባንያዎች ይፈጸማሉ የሚባሉት ድርጊቶች አገልግሎት ተቀባዮችን ወይም ሸማቾችን ሥጋት ላይ እየጣሉ መጥተዋል፡፡
በቅርቡ ተሽከርካሪዎችን እናስመጣለን ብለው ከደንበኞቻቸው ወስደዋል ከተባለው ገንዘብ ጋር በተገናኘ እየተሰማ ያለው ሮሮ አንድ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ መጠለያ ጐጆ እናገኛለን ያሉ ዜጐች በሕግ ወደ ተመዘገቡ ‹‹የሪል ስቴት አልሚዎች›› ሄደው ቤት እንዲገነባላቸው የከፈሉት ገንዘብ ‹‹ውኃ በላው›› በማለት ሐዘን የተቀመጡ ዜጐች ጉዳይም ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንደሰማነው ተሽከርካሪ በማስመጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች ከደንበኞቻቸው ጋር የገቡትን ውል አለማክበር ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ኪሳቸው አስገብተዋል ተብሏል፡፡ እንደሰማነው መኪና አስመጪዎቹ ደንበኞቻቸው የሚረከቡበትን ቀን ቆርጠውላቸው፣ ገንዘብ ተረክበዋል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ ሰነድ ተፈራርመው ነበር፡፡ ነገር ግን መኪናውም ገንዘቡም የሉም መባሉ የችግሩ መነሻ ሆኗል፡፡
ዜጐች አገልግሎት አገኛለሁ፣ ንብረት አፈራለሁ ብለው በእምነት የከፈሉት ገንዘብ ውኃ በላው የሚለው ዜና ሲሰማ ሕመሙ የገንዘቡን ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ወገን መነካካቱ አይጠረጠርም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕግ ባለበት አገር ዜጐች እንዲህ ዓይነት በደል እንዴት ሊፈጸምባቸው ይችላል የሚለውን ቁጭትም ያሳድራል፡፡ ከቁጭትም በላይ ግን ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል፡፡
ሰሞኑን የሰማናቸው ዜናዎች ከብደው ታዩ እንጂ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ድርጊት ደንበኞች ያለቀሱባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ አስተማሪ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት የወንጀል ድርጊቱ ቀጥሏል፡፡ ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ችግር ሊያጋጥም ይችል ይሆናል፡፡ መፍትሔ የሚሆን አንድ ወጥ አሠራር ባለመዘርጋቱ ይመስላል ድርጊቱ ብሶበት እየመጣ መሆኑን ግን ሊያስገነዝበን ይችላል፡፡ የያኔው ድርጊት በእንጭጩ ቢቀጭ ኑሮ ዛሬ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የዜጐች ገንዘብ በጮሌዎች እየቀለጠ መቀጠሉን ባልሰማን ነበር፡፡
እንደ ተሽከርካሪዎች ግዥ ሁሉ ዜጐች በእምነት የሰጡት ገንዘብ እንደጠበቁት ንብረት አላስገኝ እያለ የሚገኘው ዘርፍ ሪል ስቴት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚታየው ግድፈት በአንድ ኩባንያ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በርከት ባሉት ኩባንያዎች ዘንድ የሚታይ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ለከፈሉት ገንዘብ ቤት ያለማግኘት ብቻ ሳይሆን ቤቱን ታገኛላችሁ ከተባለበት ጊዜ በላይ የተራዘመ ጊዜ በመውሰድ ደንበኞች በመጠበቅ እንዲንገላቱ ሲዳርጋቸው ይታያል፡፡ በታሰበው ዲዛይን ያለመሥራት ችግርም የዚህ ዘርፍ መገለጫ ነው፡፡ ነገሩን በደንብ ካየነው ቤት ፈላጊዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘባቸውን በእምነት የሰጡት መንግሥት ያወቃቸው፤ ፈቃድ ያላቸው ኩባንያዎች ናቸው በማለት ነው፡፡
እርግጥ ነው መንግሥት እያንዳንዱ ኩባንያ ደጃፍ ላይ ዘበኛ ቀጥሮ ሊቆጣጠር አይችልም፡፡ ፈቃድ ሲሰጣቸውም ኅብረተሰቡን በታማኝነትና በገቡት ቃል መሠረት ያገለግላሉ የሚል እምነት ጥሎባቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከአገልግሎታቸው ከሚያገኙት ትርፍም ሕጋዊ ግብር ከፍለው ራሳቸውንም ሌላውን ይጠቅማሉ ብሎ በማመኑ ነው ፈቃድም ዕውቅናም የሚሰጣቸው፡፡
ነገር ግን ባገኙት ፈቃድ ከለላ አማካይነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየተበራከቱ መምጣታቸው የግብይት ሥርዓቱን እየረበሸ በአገልግሎት ተቀባይና ሰጪ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን እያደበዘዘ መምጣቱ ያሳስባል፡፡ ደፋሮች ሕጋዊ ኩባንያዎች ስለመሆናቸው ገልጸው የሚፈጽሙትን ያልተገባ ተግባር ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ በሕጋዊ ፈቃድ አማካይነት የሚፈጸም ወንጀል ከተበራከተ፣ የመንግሥት ኃላፊነት እስካሁን በነበረው የመንግሥት አሠራር እንደማይቻል ብቻ መዝለቅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የዜጐችን መብት ለማስከበር አሠራሩን መለወጥ ግድ ይላል፡፡ እስካሁንም መዘግየት አልነበረበትም፡፡
ለምሳሌ በአክሲዮን የተመሠረቱ ኩባንያዎች ችግሮች እየተበራከቱ ሲመጡ ንግድ ሚኒስቴር ይህንን የሚከታተል አንድ ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ተነስቶ ነበር፡፡ ሐሳቡ መልካም ቢሆንም ምን ያህል ተግባራዊ ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡ በአክሲዮን ኩባንያዎች አካባቢ ያለውን ችግር ለመፍታት ተቋቋመ እንደተባለው ዳይሬክቶሬት ሁሉ መኪና እናስመጣለን ወይም እንዲህ ያለ ምርት እናቀርባለን ብለው በተለያየ መንገድ ገንዘብ በመሰብሰብ ችግር የመፍጠሩ አባዜ ከዚህ በኋላም ይገታል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ስለዚህ እንዲህ ያሉ ስምምነቶች በትክክል ስለመፈጸማቸው ለማረጋገጥ ወይም ደንበኞች እንዳይጭበረበሩ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ግድ ነው ማለት ነው፡፡
ለዚህ ኃላፊነቱን እንዲወስድ የሚጠበቀው መንግሥት ነው፡፡ የኃላፊነት ድንበራቸው የት ድረስ እንደሆነ መረዳት ቢያቅትም የሸማቾችን መብት ለመጠበቅ በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ ከሰሞኑ እንደሰማነው ደንበኞች የግዥ ውለታ ሲፈጽሙ እንደ ንግድ ሚኒስቴር ላሉ መንግሥታዊ ተቋማት ቢያሳውቁ ነገሩን ከሥሩ መከታተል ይችላል ተብሏል፡፡ ሆኖም ይህንን ለመተግበር ደንበኞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሊገለጽላቸው ይገባል፡፡
ከደንበኞች ገንዘብ ሰብስበው ከአገር ጠፉ የተባሉ ግለሰቦችን ሁሉ እያፈላለጉ ለሕግ ማቅረብ ተጨማሪ ሥራ የሆነበት ፖሊስ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቢወሰንባቸው እንኳ ገንዘባቸውን ያጡት ዜጐች መልሰው እንዴት ሊያገኙት ይችላሉ የሚለው ብዙ ሲታሰብበት አይታይም፡፡
ስለዚህ እንዲህ ያሉ ውሎች በሌላ ሕጋዊ አካል እንዲረጋገጡ የማድረጉ ልምድ እንዲዳብር ማድረግ አንድ ነገር ሆኖ፣ አገልግሎቱን እሰጣለሁ የሚለውም ኩባንያ ቢሆን የተፈለገውን ለማድረጉ ማረጋገጫ የሚሰጥበት አሠራር ሊፈጠር ይገባል፡፡ መንግሥት እነዚህን ተጠርጣሪዎች ካሉበት ቦታ አፈላልጐ ማምጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ገንዘባቸው የተወሰደባቸው ሰዎች ገንዘባቸውን መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ሊመቻች ይገባል፡፡