Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ በባለሙያዎች ዕይታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተሻሻለውና በቅርቡ እንደሚፀድቅ የሚጠበቀው ረቂቅ የገቢ ግብር በርካታ ማሻሻያዎችን ይዞ እንደመጣ  እየተነገረ ነው፡፡ ረቂቅ የገቢ ግብር ማሻሻያው አካቷቸዋል ከተባሉት ለውጦች መካከል ብዙ ሲያነታርክ የቆየውና ለይግባኝ ማስያዝን ይጠይቅ የነበረው የ50 ከመቶ ቅድሚያ ክፍያ አንዱ ነው፡፡

የተጠየቁት ግብር አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩ ግብር ከፋዮች፣ ለግብር ቅሬታ ሰሚ ጉባዔ ጉዳያቸው እንዲታይ ለማቅረብ ቅድመ ሁኔታ ሆኖ የተቀመጠው የተጠየቁትን ግብር 50 ከመቶ፣ ወለድና መቀጫውን አካተው በቅድሚያ እንዲያሲይዙ ይደረግበት የነበረው አሠራር ወደ 25 ከመቶ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ ከዚህ ቀደም ይጠየቅ የነበረው የወለድና የቅጣት መጠንም እንዲነሳ አለያም እንዲቀንስ በአዲሱ ማሻሻያ መታሰቡ ከለውጦቹ መካከል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ምሁራን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ወለላ አባሆዴ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት ማሻሻያው በብዙ ጎኑ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ እንደ ዶ/ር ወለላ ማብራሪያ፣ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ያህል ማሻሻያ ሳይደረግበት መቆየቱ በራሱ አሁን ካለው ፈጣንና ተለዋዋጭ ለውጥ አኳያ ተመጣጣኝና ምላሽ የሚሰጥ የገቢ ግብር ሕግ ይዞ መገኘት ጊዜው የሚጠይቀው በመሆኑ መሻሻሉ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ለ15 ዓመታት ተመልካች እንዳላገኘ የሚነገርለት የገቢ ግብር ሕግ፣ ተሻሽሎ በቅርቡ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ሕጉ እንዲሻሻል ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ልዩ ልዩ ጥናቶችን ሲያጠኑና ድጋፍ ሲጠይቁ ከርመዋል፡፡

ብዙ ተለፍቶበት፣ በርካታ ምክክሮችና ስብሰባዎች ተደርገውበት፣ አያሌ ጥናቶች ታክለውበት በመጨረሻም ረቂቅ ሕጉ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ተችተውበታል የተባለው አዲሱ ማሻሻያ በባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁንና የአብዛኛውን ቀልብ ሊስብ መቻሉ ግን አጠራጥሯል፡፡ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተስነጋባውም ይህንኑ የሚጠቁም ነው፡፡

መንግሥት ይፋ ያደረገው ረቂቅ ማሻሻያ ይጠበቅ ከነበረው አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ሳይሆን ከተገኘበት ነጥብ አንዱ ለደመወዝ ግብር በሚከፈለው ላይ የተደረገው ማስተካከያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ከቆዩት አኳያ የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተደረገው ማሻሻያ ከደመወዝ ለሚገኝ ገቢ የተሰጠው ቅናሽና ሲጠበቅ የነበረው ለውጥ አልተጣጣሙም፡፡ ይሁንና መንግሥትም ሆነ የታክስ ባለሙያዎች ግን የአገሪቱን የታክስ ሥርዓት በጥልቀት የሚለውጥ፣ ከዓለም አቀፍ አሠራሮች ጋር የተቀራረበ በርካታ ማሻሻያዎችን ያስተዋወቀ እንደሆነ በመግለጽ እያወደሱት ይገኛሉ፡፡

የቀረበው አዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ ፕሮጀክት ላይ በዓለም ባንክ የፋይናንስ ዋና ክፍል የሆነው የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ለመንግሥት በዚህ ረገድ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በኮርፖሬሽኑ በኩል ሲካሄድ የቆየውን የ‹‹ታክስ ሲምፕሊፊኬሽን ፕሮጀክት›› ሲያስተባብሩ የቆዩት ዶ/ር ወለላ አባሆዴ ናቸው፡፡

ዶ/ር ወለላ በዚሁ በገቢ ግብር ማሻሻያ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ እንደ ዶ/ር ወለላ ከሆነ የገቢ ግብር ማሻሻያው ከወትሮው ይልቅ በርካታ ያልተለመዱ ለውጦችን ይዞ መጥቷል፡፡ 

ምንም እንኳ አዲሱ ሕግ ያመጣቸውን ያህል ማሻሻዎች ሳያካትታቸው የቀሩ፣ አሻሚ ትርጓሜ የያዙና የንግድ ተቋማትን የሚመለከቱ ችግሮችን አሁንም እንዲሁ በዝምታ ማለፉን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ለዚህ አባባል ዋቢ ከሚደረጉት አንዱ በትርፍ ድርሻ ወይም በዴቪንድ ታክስ ላይ የሚታየው ነው፡፡ ዶ/ር ወለላ እንደሚያብራሩት፣ አዲሱ ሕግ እስካሁን ለነበረው አተረጓጎምና አተገባበር ምላሽ መስጠት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ባለድርሻዎች ባለድርሻ ከሆኑበት ኩባንያ የትርፍ ድርሻቸውን በብድር መልክ፣ በቅድመ ክፍያ ወይም በሌላ ምክንያት ወጪ ቢያደርጉ፣ ይህ የትርፍ ድርሻ እንደተወሰደ ተቆጥሮ ታክስ ይከፈልበታል ይላል፡፡

ምንም እንኳ ይህ መሆኑ ቅሬታ ባያሳድርም፣ የተሻሻለው ሕግ ያልተከፋፈለ የትርፍ ድርሻን ከተከፋፈለው የትርፍ ድርሻ መለየት አለመቻሉ ግን አስተችቶታል፡፡ ዶ/ር ወለላ እንደሚያምኑትና በሌሎች አገሮች ሲደረግ እንደሚያውቁት የዴቪደንድ ታክስ የሚጣለው በተከፋፈለ ዴቪደንድ ላይ ነው፡፡ ሆኖም አዲሱ ሕግ በተከፋፈለና ባልተከፋፈለ ዴቪደንድ ላይ ልዩነት ሳያደርግ ሁለቱም ላይ ታክስ እንዲከፈል ለማድረግ መነሳቱን አልተቀበሉትም፡፡

ኩባንያዎች ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻን ሳያከፋፍሉ በራሳቸው ለሚያቆዩት ገንዘብ (ሪቴይንድ ኧርኒንግ) የትርፍ ድርሻ ነውና ታክስ ትከፍሉበት ዘንድ ትገደዳላችሁ መባሉ ሊታረም ይገባው እንደነበር የሚያብራሩት ዶ/ር ወለላ፣ መንግሥት በርካታ ገንዘብ አከማችተው ይዘው ለማቆየት ሲሉ የትርፍ ድርሻ ከማከፋፈል ተቆጥበዋል ያላቸውን ኩባንያዎችን ለመቅጣት በማሰብ ታክስ እንዲከፍሉ ለማድረግ ከሆነም፣ የሚከፍሉት ታክስ ትርፍ ድርሻ ወይም ዴቪደንድ ሳይሆን ሪቴይንድ ኧርኒንግ ታክስ መባል እንደሚገባለው ይከራከራሉ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ታክሱ መጣል ያለበት ኩባንያዎች ላይ እንጂ ባለአክሲዮኖች ላይ መሆን እንደሌለበትም ይሞግታሉ፡፡

      ባለሙያዋ የአሜሪካ ተሞክሮን በአስረጂነት አቅርበዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ሪቴይንድ ኧርኒንግ ላይ የሚጣለው ታክስ ከቅጣት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይኸውም በርካታ ኩባንያዎች በትርፍ ድርሻ ክፍፍል ወቅት የሚከፍሉት ታክስ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት ይህንን ለመሸሽ በማሰብ የትርፍ ድርሻ ሳያከፋፍሉ ገንዘብ አከማችተው በሚያቆዩት ላይ የሚጣል የታክስ ዓይነት ሲሆን፣ ስያሜውም ከትርፍ ድርሻ ታክስ ጋር ተለያይቶ የሚቀርብ ነው፡፡

      ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያዎች የትርፍ ድርሻን ሳያከፋፍሉ አከማችተው በማቆየት ታክስ ላለመክፈል ይጣጣራሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ስንቶቹ ኩባንዎች ናቸው እንደልብ የሚያወላዳ የፋይናንስ አቅም ያላቸው? ስንቶቹስ ናቸው እንደ ብድር ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት በቀላሉ የሚያገኙት? እንዲህ ባለው ሒደት ውስጥ መንግሥት በተከፋፈለ የትርፍ ድርሻና ባልተከፋፈለው ላይ ልዩነት ሳያደርግ ሁለቱንም በትርፍ ድርሻነት በመመልከት ታክስ ማስከፈሉ ሊታይ ይገባው ነበር፤››

      ከዚህ ባሻገር መንግሥት በአዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ ሕግ ውስጥ ማካተት ይገባው ነበር በማለት በዶ/ር ወለላ የተጠቀሰው የኪሳራ ዘመን ማሸጋገሪያ ጊዜ ገደብ ነው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር መሠረት መንግሥት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ኪሳራ ያጋጠመው ኩባንያ ለሁለት ጊዜ ያህል ብቻ የኪሳራ ማራዘሚያ ይፈቀድለታል፡፡ 

ሆኖም እንደ ዶ/ር ወለላ ሦስት ዓመት በጣም አጭር በመሆኑ ቢያንስ ወደ አምስት ዓመት እንዲያድግ ሊደረግ ይገባው ነበር፡፡ ሌሎች አገሮችም ኪሳራ ላጋጠማቸው ኩባንያዎች ይህንን ያህል ጊዜ ይፈቅዳሉና፡፡ ኪሳራው ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያጋጥም አለመፈቀዱም ሌላው የአዲሱ ማሻሻያ አሉታዊ ጎን ሆኗል፡፡

በአብዛኛው በሌሎች አገሮች ኩባንያዎች የሚያጋጥማቸው ኪሳራ ሁለት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ተብሎ ገደብ አይጣልበትም፡፡ ከሁለት ጊዜ በላይ የከሰረ ኩባንያ ምንም ቢከስር ታክስ የመክፈል ግዴታ ይጣልበታል ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ኩባንያዎች በሕይወት ዘመናቸው ኪሳራ እንዲያስተናግዱ የሚፈቀድላቸው ለሁለት ጊዜ ብቻ በመሆኑ እየተለወጠ በመጣው የቢዝነስ ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ገደብ የማይስኬድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እንዲህ ያሉ አንኳር ጉዳዮችን ወደ ጎን ብሏል የተባለው አዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ ሕግ ግን፣ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ 

       

     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች