Saturday, April 1, 2023

የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር እንደ ቁርጠኝነት ማሳያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እጅግ እዚህ ግባ ለማይባል ጉዳይ አንድ የፖሊስ መኮንን የኢትዮጵያ ዜጋን ሲመታው ወይም ሲያሰቃየው ማየት ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ፍርድ ቤቶች በጠበቃ አለመጎብኘትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል በማለት የሚያቀርቡትን ቅሬታ መስማት የዕለት ተዕለት ሥራቸው እየሆነ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጠሩ የፀጥታ መጓደሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሁሌም ያልተመጣጠነ ኃይል ይጠቀማሉ ተብለው መወቀስ እንዲሁ የተለመደ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ለሆነና ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ ለሚሰጥ አገር እነዚህ የመብት ጥሰቶች ምላሽ ሊያገኙ የሚገባው ከረጅም ጊዜ በፊት መሆን ነበረበት፡፡ ይሁንና ከዚህ በተቃራኒ የተለያዩ አካላት የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ እነዚህ ጥሰቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰባቸው መጥቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መንግሥት እያወጣቸው ባሉ ፖሊሲዎች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ ተቋማዊ አደረጃጀቶችና ተግባራዊ ዕርምጃዎች እየታገዘ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ ላይ በየጊዜው እየተሻሻሉ የሄዱ ግን ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ማምጣቱን ይከራከራል፡፡ ለመንግሥት እነዚህ ጥሰቶች እንዳለመታደል ኃላፊነት በማይሰማቸውና ሥነ ምግባር በጎደላቸው አካላት የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንጂ የሥርዓቱ መለያዎች አይደሉም፡፡

መንግሥት በተጨማሪም ለሰብዓዊ መብቶች አፈጻጸም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳየቱንም ይሞግታል፡፡ የዚህ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የቅርብ ጊዜ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀሰው ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም. ሥራ ላይ የነበረው የመጀመሪያው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ነው፡፡ የመርሐ ግብሩ ዋና ዓላማ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቀናጀና ከሌሎች ዕቅዶች ጋር በተጣመረ አኳኋን በሕገ መንግሥቱ ለተረጋገጡት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የበለጠ ጥበቃ የሚያበጁ ስልቶችንና አቅጣጫዎችን መቀየስ ነው፡፡

የድርጊት መርሐ ግብሩ በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ በበርካታ መሥፈርቶች ኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባታል በሚል በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ግለሰቦችና አካላት ቅሬታ ያቀርቡባታል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ተቃውሞዎች፣ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች በኦሮሚያ፣ በአማራና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልሎች መከሰታቸው ሁኔታዎችን ይበልጥ አወሳስቧል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጣርቶ ባለፈው ሳምንት ሪፖርቱን ለፓርላማው አቅርቧል፡፡ ፓርላማውም ሪፖርቱ ላይ ተመሥርቶ የውሳኔ ዕርምጃ አሳልፏል፡፡ እርግጥ ነው ሪፖርቱ የሁሉንም ወገኖች ይሁንታ አላገኘም፡፡

በእነዚህ ውዝግቦች መሐል መንግሥት የሁለተኛውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ረቂቅ ሰነድ በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ውይይት ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲካሄድበት ቆይቷል፡፡ በቅርቡ (ምናልባትም በመጪው ሳምንት) የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁንታ ካገኘ ፓርላማው ለዕረፍት ከመዘጋቱ በፊት ሕግ ሆኖ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና ይህ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን በተለያየ ምክንያት የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የድርጊት መርሐ ግብር እንደ የመንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳያ

የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር የማዘጋጀት ጉዳይ እ.ኤ.አ. በ1993 በተካሄደው በሁለተኛው የቪየና የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮንፈረንስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በአገሮች መካከል መግባባት የተደረሰበት አጀንዳ ነው፡፡ የዚሁ ኮንፈረንስ ውጤት በሆነው የቪየና ዴክላሬሽንና የትግበራ ፕሮግራም ክፍል ሁለት አንቀጽ 71 አገሮች የሰብዓዊ መብቶችን በማስፋፋት፣ በማስጠበቅና በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን አፈጻጸም ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊወስዱት የሚገባውን ዕርምጃ በግልጽ የሚያመለክት አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር የማዘጋጀትን አስፈላጊነት በአፅንኦት እንዲቃኙት አሳስቧል፡፡

የመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው የድርጊት መርሐ ግብር በዚሁ መንፈስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር እየተናበበ የሚፈጸም ነው፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ አካላት በተናጠል ይፈጽሙት የነበረውን ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር እንቅስቃሴ በተጠናከረ፣ በተዋሃደና በተቀናጀ አኳኋን ለመፈጸም ያለመ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ከሚመለከታቸው የልማት አጋሮች፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚፈጽሙትም ይጠበቃል፡፡

የድርጊት መርሐ ግብሩ በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ይዞታ በመገምገምና ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ ሐሳቦችን ያስቀምጣል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ 23 መብቶችን በመለየትም ተለይተው የታወቁ ወደ አንድ ተጨባጭ ግብ የሚያደርሱ ዕርምጃዎችን አካቷል፡፡ በዚህም የተጠቀሱትን መብቶች ለማስከበር፣ ለማስጠበቅና ለማሟላት በመንግሥት የተወሰዱ ዋና ዋና አስተዳደራዊና ተቋማዊ ዕርምጃዎች የተመለከቱ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ ሰብዓዊ መብቶችን በማስጠበቅ ረገድ መንግሥት የወሰዳቸውን ዕርምጃዎች በመግለጽና አመላካች የሚሆኑ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን በማስቀመጥ ነው የተዘጋጀው፡፡ በዕቅዱ ዘመን ውስጥ መብቶቹን የበለጠ ለማክበር፣ ለማስጠበቅና ለማሟላት መከናወን የሚገባቸውን ዋና ዋና ተግባራት፣ የሚፈጸሙበትን ጊዜና የውጤት አመላካቾቻቸው ተለይተው በዕቅድ መልክ ተዘርዝረዋል፡፡ በመጨረሻም የእነዚህን ተግባራት አፈጻጸም ለመከታተልና ለመገምገም የሚያስችል የክትትልና ግምገማ ሥርዓት ተቀምጧል፡፡

ሁለተኛው የድርጊት መርሐ ግብር የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን፣ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ባህላዊ መብቶችን እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶችን (የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋዊያን፣ የኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች መብቶች) በዝርዝር በመዳሰስ ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰነዱ የልማትና የአካባቢ ደኅንነት መብቶችንም ይሸፍናል፡፡

የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው፣ ‹‹በዓለም ላይ ካሉ ሰፊ የድርጊት መርሐ ግብሮች አንዱ ነው፡፡ 23 ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አካተናል፡፡ በጣም በዝርዝር ነው የቀረቡት፡፡ ሰፊ የሆነ የመንግሥት ቁርጠኝነት የታየበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበራት፣ በምሁራን፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለያዩ በሕይወት መስኮች ከተሰማሩ ሰዎች መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተገናኘ ክስና ትችት የሚቀርብበት መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳየት የጀመረው ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ እንደሆነና ይህም በየጊዜው እየጨመረ እንደመጣ በመከራከር ተቺዎቹን ይቃወማል፡፡

ሁለተኛው የድርጊት መርሐ ግብር ረቂቅ ሰነድ ላይ ሕዝባዊ ውይይት በተጀመረበት ወቅት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ መንግሥት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማረጋገጥ፣ ማክበርና ማሟላትን እንደ ቁልፍ የህልውና አጀንዳ እንደሚወስደው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መልኩ የተረጋገጠበት አገር ለመገንባት ያደረግነው የሁለት አሠርት ጉዞ መሠረታዊ የሽግግር ጉዞና ውጤታማ ሒደት መሆኑ በወል እየታወቀ ይህንኑ በመካድ፣ እስካሁን በዘርፉ ያስመዘገብናቸውን ድሎች በማንኛውም ዓለም አቀፋዊ መለኪያ የሚያበረታታ መሆኑን እያወቁም ጭምር ላለመቀበል የወሰኑ የተወሰኑ አካላት የሰብዓዊ መብት ጠበቃና ተሟጋቾች ነን ባዮች የአገሪቷን ገጽታና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪከርዷ ላይ ጥላሸት ለመቀባት መፈንቀል የሚችሉትን ድንጋይ ሲፈነቅሉ ከርመዋል፡፡ ዕውነታው ግን ያላቸውን ርዕዮተ ዓለማዊ የሆነ ልዩ ፍላጎትና ዓላማ እጅ በመጠምዘዝ ለማሳካት ያለመ እንጂ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አያያዝ ሥርዓታችን እነሱ በሚሉት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን ሕዝባችን ጠንቅቆ የሚረዳው ሃቅ ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ለበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ኢሕአዴግና ባለሥልጣናቱ ሰብዓዊ መብትን ማክበር የህልውና ጉዳይ ነው በሚል የሚሰጡት ገለጻ አይዋጥላቸውም፡፡ ይሁንና ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ጨምሮ አንኳር የመንግሥት የፖሊሲ ሰነዶች ‹‹ሰብዓዊ መብትን ሳይከበር ዘላቂ ብሔራዊ ልማትን ማሳካት›› እንደማይታሰብ ያትታሉ፡፡

አቶ ይበቃል የማንኛውም አካል ነፃና ገለልተኛ ግምገማ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ስኬት መመዝገቡን እንደሚያረጋግጥ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹እነዚህን መሠረታዊ ለውጦችና ስኬቶች የሚጠራጠሩና የሚክዱ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ አካላትን መነሻ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ አካላት የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን የሚገመግሙበት አግባብ ከመንግሥት ይለያል፡፡ የእነሱ ፍላጎት የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠር ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ግን የድርጊት መርሐ ግብሩ ስለተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ እንደ ሥርዓት ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መስፈን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአቶ ይበቃል ግምገማ በመንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚቀርበው ትችት የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ ለዚህ እንደ አብነት የጠቀሱት የግንዛቤ እጥረትን ነው፡፡ የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር ትልቅ ስኬት አድርገው የጠቀሱትም በዚህ ረገድ ያመጣውን ለውጥ ነው፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት ባህል እየገነባን ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ባህል ሲሆን፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትልቅ ዋስትና ነው፡፡ ይህን ባህል የመፍጠር ጉዳይ ግን በአንድ ምሽት ተከናውኖ የሚጠናቀቅ ተግባር አይደለም፡፡ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምና ዝግጅቱ

የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ መሠረታዊ መርሆዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ፣ ተቋማትን መፍጠር፣ የተቋማትን አቅም መገንባት መንግሥት በሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ላይ ክፍተቶች ለምን ተፈጠሩ በሚል ለሚቀርብለት ጥያቄ ከሚሰጣቸው ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች እስካልተቀረፉ ድረስ በአፈጻጸም ላይ ክፍተቶች መኖራቸው እንደማይቀር የመንግሥት እምነት ነው፡፡ ብዙዎች ግን እነዚህ ጉዳዮች እንደ ሰበብ የማይጠቀሱበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ አቶ ጌታሁን ካሳ፣ የሰብዓዊ መብት ይዞታን ለመገምገም የሕግ ማዕቀፍ፣ የተቋማት ግንባታና አፈጻጸም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያስገነዝባሉ፡፡ መንግሥት ባለፉት 25 ዓመታት የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋትና ተቋማትን በመገንባት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ የሚቀበሉት አቶ ጌታሁን፣ አፈጻጸም ላይ ግን በጣም የሚያሳስቡ ጉዳዮች እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል፡፡

‹‹መብት አስከባሪ ተቋማት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ወይ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መብት የመንግሥት ስጦታ አይደለም፡፡ መብቶችን ማክበር እንደውም የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት መብት ሲጣስ ኃላፊነትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ የሆነ የመፍትሔ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባዋል፡፡ ሕግን የጣሱ ሰዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ክፍተቶች ይስተዋላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ላይ ስላለው ችግር ሲነሳ በመንግሥት የሚሰጠው የተለመደ ምላሽ ‹‹ትክክለኛና ተገቢ የሆኑ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና ተቋማት አሉ፡፡ የአፈጻጸም ብቃታችንን ማሻሻል ብቻ ነው የሚጠበቅብን፤›› የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አቶ ጌታሁን ሲናገሩ፣ ‹‹የአፈጻጸም ችግር ብቻ ነው በማለት ሁሌም ምክንያት እያቀረብክ ልትቀጥል አትችልም፡፡ ፖሊሲ የማይፈጸም ከሆነ ካለመኖር ምንም አይለይም፡፡ ፖሊሲና ሕግ የሚወጣው እንዲፈጸም ነው፡፡ የአፈጻጸም አቅም እንደ ምክንያት ለመቅረብ ጊዜው አልፎበታል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት በነበረበት፣ ተቋማዊ የአቅም ውስንነት በነበረበት ጊዜ ምላሽ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ለአቶ ይበቃል የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር ለተሻለ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መሠረት የጣለና ለሁለተኛው ጥሩ መሸጋገሪያ ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡ ‹‹መንግሥት ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ሰፊ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ ሠርቷል፡፡ በዚህም ሰፊ ለውጦች መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ፍጹማዊ የሆነ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማረጋገጥ ጉዳይ በባህርይው በየትኛውም የዓለም አገር ተከናውኖ የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁልጊዜ በሒደት እየተጠናከረ የሚሄድ ነው፡፡ የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር ተጨማሪ ርቀት ወስደናል፡፡ በተመሳሳይ ቀጣዩም የራሱን እሴት ይጨምራል፤›› ብለዋል፡፡

ካለፉት ሥርዓቶች ሲነጻጸር በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕግ ማዕቀፍ ዝርጋታና በተቋማት ግንባታ የተሻለ ስለመሆኑ ማንም ይመሰክርለታል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዋነኛው የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚደረጉት የሐሳብ ልውውጦች በአብዛኛው ሕገ መንግሥቱን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንድ ሦስተኛ ስለሰብዓዊ መብት የሚደነግግ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ጉልህ ሚና የተጫወተው መንግሥት ለሰብዓዊ መብት መፈጸም ያለኝ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲልም ያቀርበዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱን ይበልጥ የሚዘረዝሩ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፎች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶችም ወጥተዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህን ድንጋጌዎች የሚያስፈጽሙ ተቋማት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች የተዋረድ ሕጎች ተቋቁመዋል፡፡

ሰብዓዊ መብት የተሻለ ይዞታ እንዲኖረው ማድረግ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትም ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ዋነኛው የዚህ ኃላፊነት ተሸካሚ መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት በተለይ የሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚያደርገው ገደብ በልዩ ሁኔታ ሊፈጸም ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ላይ መንግሥት ገደብ የሚያደርገው በሕግ የተቀመጡትን መሥፈርቶች በሞላ መልኩ አይደለም በሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡ ይህ የመንግሥት ድርጊት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ አለመሥራታቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ‹‹የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቋማት አቋቁመን ውስጣዊ አቅማቸውን በማጠናከር በሰብዓዊ መብት አጠባበቅና አተገባበር ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የጀመሩ ተቋማት መሆን ጀምረዋል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና የተለያዩ ጥናቶች የሚያሳዩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ነፃና ገለልተኛ እንዳልሆኑ ያሳያሉ፡፡ አቶ ጌታሁን በሁለቱ ተቋማት ላይ ጥናት ካደረጉ ተመራማሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ከቆዩበት ጊዜና ከሚጠበቅባቸው አንፃር ያከናወኑት ሥራ በቂ አይደለም፡፡ በርካታ ሰዎች ገለልተኝነታቸውንና ነፃነታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ተቋሞቹ ዋናውን ሥራ ሳይሆን ጥቃቅኑን ነገር ነው የሚሠሩት ተብለው ይተቻሉ፡፡ አስፈላጊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሳያነሱ ያልፋሉ በሚልም ይወቀሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ የተጠያቂነት ሚዛንን የማስጠበቅ ሥራ በበቂ ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ረቂቁ ድርጊት መርሐ ግብር ገለጻ ከሆነ፣ ላለፉት 12 ዓመታት በተከታታይ የተመዘገበው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት የሰብዓዊ መብት ይዞታን እያሻሻለው ነው፡፡ ‹‹ይህ መሠረተ ሰፊና ድሃ ተኮር የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያስቻለ በመሆኑ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች አፈጻጸም በእጅጉ ለማጎልበት አቅም ፈጥሮልናል፤›› ሲል ያትታል፡፡

በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ሲነሳ አብሮ የሚጠየቀው ጥያቄ መንግሥት ለሁሉም መብቶች እኩል ትኩረት ይሰጣል ወይ? የሚለው ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ‹‹በተለይም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ከማረጋገጥ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ረጅም ርቀት ተጉዘናል፤›› ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው መብት እንደሌለ ተከላክለዋል፡፡ ‹‹ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ከማረጋገጥ አኳያ የመብቶች ፍረጃና ቅደም ተከተል ሳናስቀምጥ የጋራና የግል መብቶች፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መብቶች ሳይነጣጠሉ ተደጋግፈውና ተቻችለው የሚተገበሩበትና የሚረጋገጡበት ሥርዓት በመዘርጋታቸው በመስኩ ለሰላማችን፣ ለልማታችን፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓታችን ጠንቅ የነበሩ ምክንያቶችን ማስወገድ ችለናል፤›› በማለትም አብራርተዋል፡፡

ምናልባትም በዚህ ምክንያት ይመስላል አቶ ይበቃል የኢኮኖሚ ዕድገቱን በየጊዜው እየተሻሻለ ነው ካሉት የሰብዓዊ መብት ይዞታው ጋር አመሳስለውታል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት ይዞታው እያደገ ይሄዳል፡፡ ልክ እንደ ኢኮኖሚያችን ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን ስንመለከት የዛሬ አሥር ዓመት ከነበርንበት ይልቅ የተሻለ አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ሀብታም አገር አይደለችም፡፡ ሰብዓዊ መብቱም ልክ እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉ በጊዜ ሒደትና በተከታታይ ጥረት የሚሻሻል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ተቺዎች ከአወዛጋቢው ምርጫ 97 በኋላ ሲቪልና ፖለቲካ መብቶች መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ይበልጥ እየታፈኑ እንደሄዱ ይከራከራሉ፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበራት ሕጎች ላይ ያለውን ክፍተትም ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ሕጎች ከወጡ በኋላ የመብቶቹ አፈጻጸም ላይ የሚታይ ውስንነትና አፈና መስተዋሉንም ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ እርግጥ ነው ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ እጅግ ተመናምኖ አሁን ዜሮ ላይ ይገኛል፡፡ የሕትመት ሚዲያ ውጤቶች ቁጥር ወርዷል፡፡ የፖለቲካ አድቮኬሲ (ውትወታ) የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት ቁጥር እዚህ ግባ አይባልም፡፡ በተቃራኒው የታሳሪና ተሳዳጅ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፖለቲከኞች ቁጥር ግን አሻቅቧል፡፡

በየትኛውም መሥፈርት የኢሕአዴግ የሰብዓዊ መብት ይዘት ካለፉት ሥርዓቶች የማይነፃፀርና እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ስላሉበት የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ክፍተቶች ሲጠየቅ ዘሎ ወደ ቀደሙት ሥርዓቶች መሮጡ ብዙዎችን ያሰለቸ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሰብዓዊ መብትን የሚለካበት የራሱ መሥፈርት የዘረጋ በመሆኑ በእነዚሁ መሥፈርቶች ስኬቶቹን እንዲለካም ብዙዎች ይመክራሉ፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዘብ ሊቆም የሚገባው መንግሥት ራሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል የዜናዎች ርዕስ መሆኑ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በእነዚህ ሥጋቶች ምክንያት መንግሥት በተደጋጋሚ በስሜት የሚያወጋውን ተጨባጭ ለውጥ ለማስረዳት አዳጋች ሆኗል፡፡ የድርጊት መርሐ ግብሩ ለተለዩት 23 መብቶች የሚከናወኑ ተግባራት፣ ፈጻሚ አካላት፣ የሚከናወን ጊዜና የውጤት አመላካች አስቀምጦ መዘጋጀቱ በእርግጥም የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን በመርሐ ግብሩ የሚወጡ በርካታ አዳዲስ ሕጎች እንዳሉ የተገለጸ ቢሆንም፣ መንግሥት ለውጥ ለማምጣት በዋነኛነት አሁንም የተማመነው በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ነው፡፡ ይኼው የግንዛቤ እጥረት የሚለካው በስብሰባና በሥልጠና ተሳታፊዎች ብዛት ይመስላል፡፡ እነዚህ ሠልጣኞችና ተሳታፊዎች ግንዛቤውን ስለመያዛቸው ማረጋገጫው ምን እንደሆነ ግን ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -