Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለተኛው ዙር የባቡር ፕሮጀክቶች በግል አልሚዎች እንዲከናወን መንግሥት አቅጣጫ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • እየተገነቡ ላሉት የባቡር ፕሮጀክቶች መንግሥት ሰባት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለበት

የአዲስ አበባም ሆነ የአገር አቀፍ የባቡር ፕሮጀክቶች የግል ባለሀብቶች ራሳቸው ፋይናንስ በማቅረብ እንዲዘረጉ እንዲደረግ መንግሥት አቅጣጫ መስጠቱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶ/ር ጌታቸው በትሩ እንደገለጹት፣ ከመንገደኞችና የጭነት ክፍያ ብቻ የባቡር መስመርን መዘርጋት በረጅም ጊዜ ካልሆነ በስተቀር አዋጭ አይደለም፡፡ በመንግሥት ላይም ትልቅ የዕዳ ጫና ያመጣል የሚለው ሐሳብ በሥራ አስፈጻሚው ዘንድ እየጐላ በመምጣቱ አማራጭ ጥናት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ጥናቱን ለመንግሥት እናቀርባለን፡፡ ከዚያ በኋላ በሚሰጠን አቅጣጫ መሠረት መሥራት እንጀምራለን፤›› ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እያጠና ያለው በሁለተኛው ዙር ውስጥ የተካተቱት የባቡር ፕሮጀክቶች እንዴት የግል ባለሀብቱን ሊስቡ ይችላሉ በሚለው ላይ ሲሆን፣ ከኮሪደር ልማት ጋር ማያያዝ በዋናነት የተያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ማስፋፊያ ብቻ በመንግሥት ሊከናወን እንደሚችል የተቀረው ግን ከሪል ስቴት ልማት ጋር ተያይዞ በግል ባለሀብት እንዲለማ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ማስፋፊያ ውስጥ የሚካተቱት ከጊዮርጊስ አደባባይ ወደ ሽሮሜዳ፣ ከጦር ኃይሎች ለቡ አገር አቀፍ ባቡር ጣቢያ፣ ከአያት ወደ ለገጣፎና ከአቃቂ ወደ ቃሊቲ የሚስፋፉት መስመሮች ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የባቡር ዘርፍ ዋና ዋና ግቦች በአምስት ኮሪደሮችና ስድስት መስመሮች በጠቅላላው 2,782 ኪሎ ሜትር አገራዊ የባቡር ኔትወርክ ግንባታ ማጠናቀቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ መቀሌ ሃራ ገበያ (268 ኪሎ ሜትር)፣ ሃራ ገበያ አሳይታ (229 ኪሎ ሜትር)፣ አሳይታ ታጁራህ ወደብ (210 ኪሎ ሜትር)፣ አዋሽ ሃራ ገበያ (309 ኪሎ ሜትር)፣ አዲስ አበባ/ሰበታ ኢጃጂ-ጂማ-በደሌ-ቴፒ-ዲማ (740 ኪሎ ሜትር)፣ ሞጆ-ሐዋሳ-ወይጦ-ሞያሌ (905 ኪሎ ሜትር) ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ውስጥ የመቀሌ ሃራ ገበያና የሃራ ገበያ አዋሽ መስመሮች በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎቹ ፋይናንስ የሚፈልጉ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ አቅጣጫ የተላለፈባቸው ናቸው፡፡

የውጭ የግል ባለሀብቶች በባቡር ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ የኮሪደር ልማትን አብሮ ማስተሳሰር በመፍትሔነት የተቀመጠ በመሆኑ ፕሮጀክቶቹ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ጋር፣ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ጋር፣ ከትልልቅ መጋዘኖች፣ ከቱሪዝምና ከመሳሰሉት ጋር በድጋሚ ዲዛይን ይደረጋሉ ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሥራ የጀመረውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለመገንባት መንግሥት 475 ሚሊዮን ዶላር የተበደረ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ወደብ ያለውን ለመገንባት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከቻይና ያገኘ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ ተጠናቋል፡፡

ከመቀሌ ሃራ ገበያ/ወልዲያ ያለውን መስመር ለመገንባት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከቻይና የተገኘ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡ ከሃራ ገበያ እስከ አዋሽ ያለውን መስመር ለመገንባት 1.7 ቢሊዮን ዶላር ከቱርክና ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች መበደሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በመሆኑም ሥራ ለጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መንግሥት የተበደረውን ጨምሮ መንግሥት ሰባት ቢሊዮን ዶላር ብድር ዕዳ ለባቡር ፕሮጀክቶች እንደገባ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የተገኘው ብድር ከሦስት ዓመት የችሮታ ጊዜ በኋላ መከፈል መጀመር ያለበት በመሆኑ፣ መንግሥት በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ክፍያውን መጀመር ይጠበቅበታል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች