Tuesday, November 28, 2023

የአመራሮች ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና ለሳይበር ኢንዱስትሪ ልማት ፈተና እንደሆነ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • ፓርላማው ለሳይበር ልማት የውጭ ዕርዳታ ባለማፅደቅ እንዲተባበረው ጠይቋል

‹‹ሳይበር››ን ከሁለንተናዊ አገራዊ ጥቅሞችና ፍላጐቶች ጋር በማጣጣም አገራዊ የሳይበር ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ስትራቴጂካዊ ግብ ጥሎ በመንቀሳቀስ ላይ ቢሆንም፣ የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ስትራቴጂክ አመራሮች ስለጉዳዩ ያላቸው ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና ዓላማውን እውን ለማድረግ ዋነኛ ፈተና እንደሆነበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ለፓርላማው አሳወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተክለ ብርሃን ወልደአረጋይ የሚመሩትን ተቋም የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የጀመረችው የኢንዱስትሪ ልማት ከሳይበር ወይም ሃይቴክ ቴክኖሎጂ ውጪ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የሳይበር ኢንዱስትሪን በአገር አቀፍ ደረጃ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በዚህ ደረጃ እያሰበ አለመሆኑንና የሳይበር ኢንዱስትሪ ልማት የቅንጦት ጉዳይና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ብቻ የሚያስፈልግ አድርገው እንደሚመለከቱት ጠቁመዋል፡፡

ሳይበር በኢንዱስትሪ ደረጃ ሊታሰብ ይገባል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ምክር ቤቱ ይህንን አቋማችንን ቢጋራን በጣም ደስ ይለናል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ሻለቃ ቢንያም ተወልደ በበኩላቸው የሳይበር ቴክኖሎጂ ሦስተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየፈጠረ መሆኑን፣ በዚህ የተነሳም አዳዲስ የቢዝነስ ሞዴሎች እንዲፈጠሩ፣ ዕውቀትና መረጃ በማጋራት ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍም ግለሰቦችም ሆኑ ትናንሽ ቡድኖች የሳይበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ቀድሞ የነበረውን የተማከለ የዓለም ፖለቲካዊ ጉልበት ሚዛን በመበተን ያልተማከለ እያደረጉት ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኃያላን አገሮች የሳይበር ኢንዱስትሪ መጠንን በማፍረስ ከአገራዊ ቅርፅ እንዲወጣና ዓለም አቀፋዊ የሳይበር ግዛት እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የሳይበር ግዛት ተፈጠረ ማለት የአገሮች ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የሳይበር ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ገና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ወይም ገና በመገራት ላይ መሆኑንና በፍጥነት ከዚህ ደረጃ ለመውጣት ስለ ሳይበር ኢንዱስትሪ ማሰብ እንደሚገባ ገልጸው፣ የሥራ አስፈጻሚው ስትራቴጂክ አመራሩ ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና ወይም አስፈላጊነቱን በዚህ ደረጃ አለመረዳት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹አመራሩ የሳይበር ቴክኖሎጂን የመገንዘብ ችግር አለበት፡፡ የሳይበር የሰው ኃይል ችግር አለ፡፡ ሳይበርን በኢንዱስትሪ ደረጃ እየፈጠርን አይደለም፤›› ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ የአመራሩ የንቃተ ህሊና ችግር በዋናነት መቀረፍ አለበት ብለዋል፡፡

የአገሪቱ የመሬት አስተዳደር በቴክኖሎጂ እንዲመራ በመንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የአዲስ አበባ መሬትን በካዳስተር ለማስተዳደር ቴክኖሎጂውን ያለማ ቢሆንም፣ ትግበራው መዘግየቱንና ይህ ለምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ዋና ዳይሬክተሩ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ሜጀር ጄነራል ተክለ ብርሃን፣ የአዲስ አበባ ካዲስተር ወደ ትግበራ ለመግባት የዘገየበት ምክንያትም በተመሳሳይ በስትራቴጂክ አመራሩ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የሁለት ጐራ ጦርነትም ይኖራል፡፡ በአንድ በኩል በጥገኝነት ለመኖር የሚፈልግ አመራር አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሕና ልማት የሚፈልግ ሕዝብ አለ፤›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በእነዚህ መካከል ግልፅ የሆነ ትግል አለ ብለዋል፡፡

‹‹የካዳስተር ቴክኖሎጂ መኖር መሬትን እንደፈለጉ ለመሸንሸን፣ ለመለወጥ፣ ለማዞር አያስችልም፡፡ በመሆኑም እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ 

‹‹ስለዚህ ነው ስትራቴጂክ አመራሩ በአስተሳሰብ መለወጥ ያስፈልገዋል የምንለው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ከመንግሥት ባንኮችና ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ የተቋማቸው የስትራቴጂክና ኦፕሬሽን አመራር አካል አድርገው ስለማይወስዱት አስቸኳይ ነው ወይም ዕርዳታ/ብድር ይገኝበታል በማለት ለቁጥጥር አመች ያልሆነ ሥርዓቶችን በማበልጸግ አገራዊ ደኅንነት ላይ ተጋላጭነት እየፈጠሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹በእኛ ድምዳሜ ዕርዳታ ለዚህ ዘርፍ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የራሱ ድብቅ ዓላማ አለው፤›› ያሉት ሜጄር ጀነራል ተክለ ብርሃን፣ ‹‹ለሳይበር ልማት ተብሎ የሚመጣ ዕርዳታ ባለማፅደቅ ብታግዙን ለግብርና ወይም ለሌላ የመሠረተ ልማት ቢውል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በአጠቃላይ ሳይበርን በኢንዱስትሪ ደረጃ ለመምራት የመሪነት ሚና የሚጫወቱ ተቋማት እንዲደራጁ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም የሳይበር ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም የሚረዳ ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑንና የሳይበር ሥልጠና ተቋም መቋቋሚያ ደንብ ተዘጋጅቶ ለካቢኔ መላኩን ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -