Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምመቋጫ ያጣው የሶሪያ ፍልሚያ

መቋጫ ያጣው የሶሪያ ፍልሚያ

ቀን:

ሶሪያውያን ላለፉት አምስት ዓመታት ከዘለቁበት የርስ በርስ ጦርነት እንዲወጡ ያስችላል የተባለውና ከወራት በፊት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መዝለቅ አልቻለም፡፡ አሜሪካም ሆነች ሩሲያ በሶሪያ ሰላም ለማምጣትም አልተቻላቸውም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢሆን፣ የንፁኃን ሞት ቁጥር ማሻቀቡን ከመገመት ባለፈ ለሶሪያ የፈየደው ነገር የለም፡፡ በዚህም መሃል 280,000 ያህል ሶሪያውያን ሲሞቱ፣ አብዛኛው የአገሪቱ ነዋሪም ከቀየው ተፈናቅሏል፣ ተሰዷል፡፡

የረመዳን ጾም ከተጀመረ በመጀመሪያው ሳምንት ብቻ ደግሞ ከ224 ዜጐች በላይ የርስ በርሱ ጦርነት ሰለባ መሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የጾሙ ወር በተጀመረበት ሳምንት ከሞቱት ውስጥም 50 ሕፃናትና 15 ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ 12 ደግሞ በአይኤስ የተገደሉ ናቸው፡፡

በሶሪያ የረመዳን ጾም ከመጀመሩ በሞት ለተነጠቁት ሰዎች ምክንያቱም፣ የሶሪያና ሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች በፈፀሙት የአየር ድብደባ መሆኑን፣ መቀመጫውን በብሪታንያ ያደረገው ‹‹ሶሪያን ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ›› አሳውቋል፡፡

‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶሪያ ጉዳይ ላይ የመረጠውን ዝምታ ደግመን እናወግዛለን፡፡ በሶሪያ ንፁኃን ዜጐች ላይ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል ቸል ተብሏል፤›› ሲልም ቡድኑ ቅሬታውን ገልጿል፡፡

በኢድሊብ በገበያ ስፍራ በደረሰ የአየር ድብደባ ንፁኃን ዜጐች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ቡድኑ ሲያሳውቅ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የቱርክ መንግሥት በኢድሊብ ለተፈጸመው የአየር ድብደባና የንፁኃን ሞት፣ የሩሲያን መንግሥት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ሩሲያ በበኩሏ ውንጀላውን አጣጥላለች፡፡

የሩሲያው መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው በኢድሊብ ምንም ዓይነት የአየር ድብደባ እንዳላደረገች አስታውቀዋል፡፡ ቱርክ ግን ሩሲያ በኢድሊብ ባደረገችው የአየር ድብደባ ሰዎች መሞታቸውን ገልጻለች፡፡

የሰብአዊ መብት ኦብዘርቫቶሪ ቡድኑም፣ በአንድ ምሽት 10 የአውሮፕላን ድብደባዎች በኢድሊብ በሚገኘው ሆስፒታል አካባቢና በሌሎች የከተማዋ ስፍራዎች መፈፀማቸውን አመልክቷል፡፡

አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በአማፅያንና በሩሲያ በሚደገፈው የሶሪያ መንግሥት መካከል ተኩስ ለማቆም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ፣ በኢድሊብ የተፈጸመው የአሁኑ የአየር ድብደባ ከባዱ ነው፡፡ የኢድሊብ ከተማ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ቀጣና ባትካተትም፣ ስምምነቱ ከተደረሰ ወዲህ ተነፃፃሪ ሰላም አግኝታ ነበር፡፡ መጣ ሄደት ከሚሉ ግጭቶች ባለፈም፣ ጐልቶ የወጣ እልቂት አልተሰማም፡፡ በረመዳን ጾም መጀመሪያ ሳምንት ግን ከ220 የሚበልጡ ሰዎች በአየር ድብደባው ተገድለዋል፡፡

ኢድሊብ የበሽር አል አሳድ ዋና ተቃዋሚዎች መናኸሪያ ናት፡፡ ከአልአሳድ የከዱ የጦር አባላትና የአህራር አል ሻም ፓርቲ ጥምረት የሚገኙትም እዚሁ ነው፡፡ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው አል ኑስራ ግንባርም በከተማዋ ይገኛል፡፡

የአማፅያን ከተማ እንደሆነች በሚነገረው ኢድሊብ የሚገኙ ተቃዋሚዎች፣ ከጥር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሲነገርለት በነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት፣ ሩሲያ ፍላጐቷን እያሳካች እንደሆነ፣ በተለይ ዋና የአል አሳድ ተቃዋሚዎች በሚገኙበት ከተማ የተቃዋሚዎችን መስመር እያለፈች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሩሲያ የአል አሳድን መንግሥት ስትደግፍ፣ አይኤስን ለመዋጋት በሚል ምክንያት ቢሆንም፣ የአል አሳድ መንግሥት መውረድ አለበት የሚሉትን ተቃዋሚዎችም በጐን ትወጋለች ሲሉ ይኮንኗታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው የሶሪያ አብዮት፣ አቅጣጫውን ስቶ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከተቀየረ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሜሪካና ሩሲያ ጀርባ ለጀርባ የሆኑበት የሶሪያ ጉዳይ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ መፍትሔ አላገኘም፡፡

በሶሪያ የሚገኘው ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድንም በሶሪያ ሰላማዊ ሰዎች ሲያልቁ፣ ዓለም ዓይኑን ጨፍኗል ብሏል፡፡

በሶሪያ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን መሪ ሙሳኪልዳ ዛንካዳ፣ ከአሊፖ በሰሜን አቅጣጫ በሚገኙ ስፍራዎች በጦርነቱ ሳቢያ የሟቾች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡

በአሊፖ የሚገኙ ዶክተሮችም ባለፈው ሳምንት ብቻ ሆስፒታሎች፣ መኖሪያ አካባቢዎችና የገበያ ስፍራዎች የአየር ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

ከወር በፊትም አሊፖ ላይ ለ10 ቀናት በተፈጸመ የአየር ድብደባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጐች ተገድለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተኩስ አቁም ስምምነቱ አሊፖ እንድትካተት አሜሪካና ሩሲያ ከስምምነት መድረሳቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቆ ነበር፡፡

ስምምነቱ ከተደረሰ ወዲህ ላለፈው አንድ ወር አሊፖም ተነጻጻሪ ሰላም አግኝታለች፡፡ ይህም ቢሆን ግን በሶሪያ ሰላም አልነገሠም፡፡ ፖለቲካዊውም ሆነ ወታደራዊው መፍትሔ ለሶሪያ ሰላም አላመጣም፡፡ አገሪቷም የሞትና የጥፋት መናኸሪያ ሆናለች፡፡ በዚህ መሃል ግን ሶሪያ ወደነበራት ሰላም ተመልሳና መሠረተ ልማቷ ዳግም ተገንብቶ ለማየት የሚፈልጉ የአገሪቱ ባለሀብቶች፣ የሶሪያን ሰላም እየናፈቁ መሆኑን ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡

ባለሀብቱ ዋልዲ ዛቢ፣ ሶሪያን መልሶ ለመገንባት ከሚመኙ ሚሊየነሮች አንዱ ናቸው፡፡ 60 ቢልዮን ዶላር የሚገመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ2014 የወደመባትን ሶሪያ፣ ሰላሟን ለመመለስና መልሶ ለመገንባት ብሩህ ተስፋ አላቸው፡፡

በሶሪያ ያለውን ግጭት ለማስቆም በጄኔቭ በሚካሄዱ ድርድሮች ላይም ተካፋይ ናቸው፡፡ ‹‹የሰላም ድርድር መጀመሩ በራሱ አንድ ዕርምጃ ነው›› የሚሉት ዛቢ፣ ‹‹ሰላም ተፈጥሮ መሥራት ከጀመርን ወደ ቀደመው መስመራችን እንገባለን›› ሲሉ ከዱባይ ሆነው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...