አቶ ግዛቸው አንዳርጌ፣ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ከተመሠረተ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የአካባቢውን ባህል እንዲሁም የተለያዩ ጥበብ ነክ ጉዳዮችን ማጥናት ማዕከሉ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በማዕከሉ ዓመታዊ ዐውደ ጥናትም ይካሄዳል፡፡ በቅርቡ አራተኛው ዐውደ ጥናት ‹‹ኪነ ጥበብ ለማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት›› በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በዐውደ ጥናቱ እንዲሁም በማዕከሉ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የማዕከሉን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አንዳርጌን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ምን ዓላማ አንግቦ ተቋቋመ?
አቶ ግዛቸው፡- የሐዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የተመሠረተው ታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ሦስት ተልዕኮዎች አሏቸው፡፡ መማርና ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት ናቸው፡፡ ማዕከሉ ከእነዚህ ተልዕኮዎች የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠትና ጥናትና ምርምር ማድረግን አጠናክሮ በመቀጠል በተለይ በኪነ ጥበቡና በባህሉ ዘርፍ በመመራመርና በመሰነድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው የተቋቋመው፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ ለባህል ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ማዕከሉ ሲመሠረት ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበት ጐጃም አካባቢ ያለው የኪነ ጥበብ ጅረት እንዲቀጥልም በማሰብ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን የአካባቢው የኪነ ጥበብ ምንጭ የሆኑትን አማተሮች ለመደገፍና የትውልድ ቅብብሉን ለማስጠበቅ ይሠራል፡፡ ማዕከሉ አማተሮች ነገ ለአገሪቱ ታላቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ምንጩ እንዳይነጥፍ ታስቦ ተቋቁሟል፡፡ አማተሮችን ከመደገፍና የኪነ ጥበብ ጥናቶች ከመሥራት ባሻገር ባህል እንዲጠበቅና በማኅበረሰቡ ያሉ ጐጂ ባህላዊ ድርጊቶች እንዲሻሻሉ ይሠራል፡፡ በአካባቢው ባህል ላይ ጥናትና ምርምር መሥራትም በዩኒቨርሲቲው የተሰጠው ተልዕኮ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባሮች ቢገልጹልን?
አቶ ግዛቸው፡- ተቋሙ የተሰጠውን ዋነኛ ተልዕኮ ከግምት በማስገባት አማተሮችን የማበረታታት ሥራ እንሠራለን፡፡ ጎጃም ውስጥ የጮቄ ተራራ አለ፡፡ ከተራራው 53 ወንዞች ይወጣሉ፡፡ ወደ 273 የሚደርሱ ትንንሽ ምንጮችም አሉት፡፡ ጎጃም ከዚህ ተፈጥሯዊ የውኃ ምንጭ በተጨማሪ ለአገሪቱ ኪነ ጥበብ በርካታ ነገር ሲመግብ ቆይቷል፡፡ የኪነ ጥበብ ምንጩ ይቀጥል ዘንድ አማተሮችን በማበረታታት የሠራናቸው ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የአማተሮችን የግጥም ሥራዎች በማሰባሰብ ሐዲስ ሐዲስ ቅጽ የተሰኘ የግጥም መድበል እናሳትማለን፡፡ አሁን አራተኛውን ዙር ማተሚያ ቤት ልከናል፡፡ የተቋሙ ባለሙያዎች ለግጥሞቹ አርትኦት ያደርጋሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መምህራንም ሙያዊ ግምገማ ይሰጡበታል፡፡ ሌላው የምናዘጋጀው ወርኃዊ የኪነ ጥበብ ምሽት ነው፡፡ በአንድ ዓመት ቢያንስ ስምንት ትልልቅ ወርኃዊ የኪነ ጥበብ ምሽቶች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ይካሄዳሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ተማሪዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ትንሿ ኢትዮጵያ ማለት ናቸው፡፡ በኪነ ጥበብ ምሽቶቹ ተማሪዎች ከትምህርት ጐን ለጐን ያሏቸውን ጥበባዊ ክህሎቶች እንዲያወጡና እንዲያጐለብቱ ይደረጋል፡፡ ለኪነ ጥበቡ ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም መድረክ ይፈጥራል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ወጥተን ደብረ ማርቆስ ዙሪያ ያሉ ወጣቶች በኪነ ጥበብ ምሽቱ እንዲሳተፉም እናደርጋለን፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሦስት ዙር የድምፅና ውዝዋዜ ውድድር አድርገናል፡፡ ያሸነፉትንም ሸልመናል፡፡ ከሽልማት ባሻገር ወጣቶቹን በመከታተል ዩኒቨርሲቲው ማድረግ የሚችለውን በማድረግ እየሠራን ነው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሒስ ሥራዎችንም እንሠራለን፡፡ ለአብነት ያህል፣ እብደትና ጉዱ ካሳ በሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› መጽሐፍ እንዴት ተገለጸ በሚለው ሐሳብ ከተቋሙ የፍልስፍና፣ የሥነ ልቦና፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍሎች መምህራንን በማሰባጠር ሙያዊ ትንታኔ እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ ውይይቱን ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ መምህራንም እንዲታደሙ ተደርጓል፡፡ የጌትነት እንየው ‹‹የሐበሻ ልጆች›› ግጥምና የበእውቀቱ ሥዩም የወግ መጽሐፍ ‹‹ክንፋማ ህልሞች››ን መነሻ በማድረግ በአካልና በመንፈስ መሰደድ በማንነት ላይ ያለው ተጽእኖ እንዴት ተገለጸ በሚል ከሥነ ልቦና፣ ፖለቲካል ሳይንስና ፍልስፍና አንፃር የሥነ ጽሑፍ ሒስ መድረክ አዘጋጅተናል፡፡ በማዕከሉ የሥነ ጽሑፍ፣ የባህላዊና የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል የቴአትር፣ የግዕዝ ጥናት፣ የባህል ጉዳዮች ጥናትና ምርምርና የቤተ መዛግብት ማዕከል ስላለ በየክፍላቸው የሚሠሩት ሥራዎች አሉ፡፡ መሠረታዊ የግዕዝ ትምህርት የሚል ኮርስ አዘጋጅተን ለአካባቢው ማኅበረሰብ በነፃ በሳምንት ሁለት ቀን ሐሙስና ቅዳሜ እየሰጠን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 140 የሚጠጉ ተማሪዎች አሉ፡፡ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎችም ይማራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ለዋሽንት ተጫዋቹ ዮሐንስ አፈወርቅ ያዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም የተሠራው እንዴት ነበር?
አቶ ግዛቸው፡- ዓላማ አድርገን የተነሳነው ታላቅ አገራዊ ሥራዎችን የሠሩት ዮሐንስ አፈወርቅን መዘከርን ነው፡፡ ብዙ ታላላቅ ሥራዎች ቢሠሩም በአግባቡ አልተዘከሩም፡፡ ስለዚህ ለአገር ላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ለማመስገን ነው፡፡ አሁን ጡረታ ወጥተዋል፡፡ ከጎናቸው ማንም ስለሌለ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሚኖሩት በቀበሌ የኪራይ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ የእሳቸውን ኑሮ በተወሰነ መልኩ እንዲደግፍ ለማድረግ አስበን ነው፡፡ ፊልሙ የእሳቸውን ሥራና የሕይወት ተሞክሯቸውን ለአማተር ባለሙያዎች የሚያስተላልፍም ይሆናል፡፡ እሳቸው በሕይወት እያሉ ሥራዎቻቸው ተሰንደው መቀመጥ አለባቸው፡፡ የፊልም ሥራው በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዐውደ ጥናት አለ፡፡ የዘንድሮው ጉባኤ ትኩረቱን ያደረገው በምን ዓይነት ጥናቶች ላይ ነው?
አቶ ግዛቸው፡- ዘንድሮ አራተኛ ዐውደ ጥናታችንን አካሂደናል፡፡ በየዓመቱ ባህል ተኮር የሆኑ ጥናትና ምርምሮች ይቀርባሉ፡፡ የዘንድሮው ጭብጥ ኪነ ጥበብ ለማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት የሚል ነበር፡፡ እኔ ልማትን የምስለው እንደ እንጀራ ነው፡፡ የዚህ አካባቢ ማኅበረሰብ ደግሞ ጤፍ በማምረትና እንጀራ በመጋገር ይታወቃል፡፡ እንጀራ ሲጋገር ብዙ ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እንጨቱ፣ ምጣዱ፣ ማዞሪያው፣ ጤፉና ሌሎችም ግብአቶች ተደማምረው ነው ጥሩ እንጀራ የሚያደርጉት፡፡ ለምሳሌ ማገዶው ካልተመጠነ ይጨሳል፡፡ ሲጨስ ደግሞ ጋጋሪዋ ታለቅሳለች፡፡ በተመሳሳይ ልማት ጭስ የሌለው መሆን አለበት፡፡ ስለልማት ሲነሳ የመልካም አስተዳደር እጦትን የመሰሉ ችግሮች ሰው የልማት ሥራዎችን የኔ ናቸው ብሎ እንዳይቀበል ቢያደርጉም፣ ኪነ ጥበብ ቦታ ከተሰጣት ልማትን የማሳለጥ ፋይዳ ይኖራታል፡፡
ሪፖርተር፡- የጥናት ወረቀቶችን ከማቅረብና የውይይት መነሻ ከማድረግ ጐን ለጐን በማሳተም ጥናቶችን ተደራሽና የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊ የማድረግ ነገር አለ?
አቶ፡- የሚቀርቡትን የጥናት ወረቀቶች ሰብስበን አርትኦት ይደረግላቸውና ይታተማሉ፡፡ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ዐውደ ጥናቶች የቀረቡትን ጥናቶች በሦስት ክፍል አሳትመን ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ሰጥተናል፡፡ በጥናቶች የተገኙ ውጤቶችን ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እንደ ግብአት የማቅረብ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ቅርስ ላይ የተደረጉ ጥናትና ምርምሮችን አሳትመናል፡፡ በአገራችን ደግሞ ቅርስ አመዘጋገብ ላይ ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ጥናቶቹ ችግሮቹን ስላሳዩን ባለፈው ዓመት በቅርስ አያያዝና እንክብካቤ ዙሪያ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለሚገኙ የቅርስ ባለሙያዎች፣ ለቤተ ክህነት፣ ለፍርድ ቤት ዳኞችና ለፖሊሶች ጭምር ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ምክንያቱም ቅርሶች ተሰርቀው ፖሊስ ጣቢያ ይያዛሉ፡፡ ተይዘው ግን የብዙዎቹ ባለቤት ስለማይገለጽ ከጦር መሣሪያ ጋር ይቀመጣሉ፡፡ ምስጥ ይበላቸዋል፣ ብዙ ጉዳትም ይደርስባቸዋል፡፡ ይህንን ጥናቱ ስላመላከተን ግንዛቤ መስጫ ሥልጠና ወደ መስጠት አምርተናል፡፡ የጥናት ወረቀቶችን መደርደሪያ ላይ ከማዋል በዘለለ ለሚመለከታቸው ተቋማት እንሰጣለን፡፡ ጥናቶቹ ያመለከቱንን የመፍትሔ ሐሳቦች ዩኒቨርሲቲው የሚችላቸው ከሆነም እንተገብራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በጎጃም አካባቢ ስላለው ማኅበረሰብ ባህል የተሰነዱ ጥናቶች አሉ?
አቶ ግዛቸው፡- ቀድሞ የማዕከሉ የምርምር ትኩረት አቅጣጫዎች አልተለዩም ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን ለማኅበረሰቡ ማዕከሉ ምን እንዲሠራላቸው እንደሚፈልጉ የሚገልጹበት መጠይቅ አዘጋጅተን በተንን፡፡ ማኅበረሰቡም ቢጠናለት አስፈላጊ ይሆናል ብሎ ያሰባቸውን ገልጿል፡፡ ለምሳሌ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ኪነ ጥበብ፣ ትምህርትና ልማት፣ ባህልና ሥነ ልቦና የሚሉት ጭብጦች ማኅበረሰቡ እንዲጠኑለት ይፈልጋል፡፡ በእኛ ባለሙያዎች አጥንተን ሰነድን ከምንለው አንዱ የሌፎ ሌፎ የአጨፋፈር ሥልት ነው፡፡ ጎጃም ውስጥ ካሉ የጭፈራ ሥልቶች የተለየ ነው፡፡ ስለአጨፋፈር ሥልቱ አጥንተን እየሰነድን ነው፡፡ ጎጃም የሚታወቅበት ከቅዱስ ያሬድ ዜማዎች አንዱ የሆነው የአጫብር ዜማና የገና ባህላዊ አጨዋወት ላይም ጥናት ተሠርቷል፡፡ የተቋሙ የምርምር የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምሁራን ንድፈ ሐሳብ ቀርጸው እንዲያመጡልን ከዛም በጀት መድበን እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ በየዓመቱ ለጉባኤ የሚሆን መሪ ቃል እናወጣና አገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ምሁራን በሙሉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ ከዛም የጥናትና ምርምር ዐውደ ጥናቱን እናካሂዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚገጥሙ ችግሮች አሉ?
አቶ ግዛቸው፡- ዩኒቨርሲቲው ማዕከሉን ሲያቋቁመው ባህል ልማት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ስለሆነ አስፈላጊ ግብአቶች በመስጠት እገዛ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ባህል ላይ ጥቅል የሆነ ጥናትና ምርምር በእኛ ባለሙያዎች ማሠራት የጀመርነው በዚህ ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይም ጥናቶቹን በዩኒቨርሲቲው ፈንድ እንሠራለን ብለን እናስባለን፡፡ ትልቅ ፈተና ይገጥመን የነበረው አዳራሽ ያለመኖሩ ነበር፡፡ ይህን በዚህ ዓመት ፈተናል፡፡ ግቢው ውስጥ በሐዲስ ዓለማየሁ የሚሰየም ሕንፃ (3,500 ሰው የሚይዝ አዳራሽ) ተሠርቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ረገድስ?
አቶ ግዛቸው፡- በዛ በኩል የገጠመን ችግር የለም፡፡ ምክንያቱም ለኪነ ጥበብ ዕድገትና አማተሮችን ለማበረታታት የቆመ ማዕከል ስለሆነ መድረኩ የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ዝግጅቶች ስናዘጋጅ የሚጠፋው ቦታ እንጂ ታዳሚ አይደለም፡፡ ከማኅበረሰቡ እንዲህ ብታደርጉ ወይም ይኼ ይሠራ የሚል ግፊት ይመጣል፡፡ ግፊቱ ደግሞ በርትተን እንድንሠራና የማኅበረሰቡን የኪነ ጥበብ ልማት ጥያቄን እንድንመልስለት ግብአት ይሆነናል፡፡ ቀድሞ የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሰባት አውራጃዎች ነበሩት፡፡ የሞጣ አውራጃ፣ የደብረማርቆስ አውራጃ፣ የአገው ምድር አውራጃ፣ የባህር ዳር አውራጃ፣ የመተከል አውራጃና የብቸና አውራጃ ማዕከላቸው ደብረማርቆስ ነበረች፡፡ ከ1930ዎቹ ጀምሮ የነበሩ መዛግብትን ከደብረማርቆስ አስገብተን ሰንደናል፡፡ ወደ 11,800 የሚጠጉ እነዚህ አቃፊ ፋይሎች ከ1930ዎቹ እስከ 2000 ዓ.ም. የሚደርሱ መረጃዎች አሏቸው፡፡ በውስጣቸው በርካታ ለፖለቲካ፣ ለባህልና ለኪነ ጥበብ ጥናት ጠቀሜታ ያላቸው ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ስለባሪያ ንግድ የተጻፉ ደብዳቤዎች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ የሚገኘው የብሉ ናይል ማስተር ፕላን (ማለትም ከ1958-1964 ዩናይትድ ስቴትስ ቢሮ ኦፍ ሬክላሜሽን ያጠናው የዓባይ ማስተር ፕላን) ሙሉ መረጃዎች እኛም ጋ ይገኛሉ፡፡ ጎጃም ውስጥ በየአካባቢው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ማመንጫ ወይም የመስኖ ፕሮጀክት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ጥናቶች ተካተዋል፡፡ በሕግ፣ በግብርና፣ በውትድርና፣ በፖለቲካ አስተዳደር፣ በፋይናንስና በግብርና ዘርፍ ታላቅ ጠቀሜታ ያላቸው ታሪካዊ መዛገብትን አሰባስበናል፡፡ አሁንም በማሰባሰብ ላይ ነን፡፡ አሁን ከብቸና ከተማ፣ ከሞጣ ከተማ ወደ 7,000 የሚጠጉ ከ1940ዎቹ ጀምሮ ስለበላይ ዘለቀ ታሪክ ሁሉ ለማጥራት የሚጠቅሙ ሰነዶች በዳሰሳ ጥናት አግኝተናል፡፡ ሁሉንም አስገብተን ባንጨርስም፣ በቤተ መዛግብቱ በኩል ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለተመራማሪዎች ክፍት ናቸው?
አቶ ግዛቸው፡- እኔ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የታሪክ መምህር ስለሆንኩም ይመለከተኛል፡፡ መዛግብቱ ታሪካዊ ፋይዳቸው በጣም የጎላ ነው፡፡ ለመዛግብቱ ማውጫ አዘጋጅተን ለአጥኚዎችና ተመራማሪዎች ክፍት አድርገናል፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጭም የሚመጡ ተመራማሪዎች ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመሥራት እንደ ግብአትነት እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡ እነዚህን ዲጂታላይዝ የማድረግ ፕሮጀክት በመቅረጽ ላይ ነን፡፡