Wednesday, October 4, 2023

የተመጣጣኝ ዕርምጃ ፖሊሲና የኢትዮጵያ ኤርትራ ፍጥጫ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በያዙባቸው ሳምንታት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በኤርትራ ላይ ያራምዱት ከነበረው ምንም የፖሊሲ ለውጥ እንደማያደርጉ ገልጸው ነበር፡፡ የኤርትራ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ አሸባሪዎች በማስረግ ትርምስ ከመፍጠርም በተጨማሪ፣ በተደጋጋሚ ድንበር ውስጥ በመዝለቅ በርካታ ዜጎች አፍኖ ይወስዳል፡፡

በዚህ ዓመት ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩት ኢትዮጵያውያንን መውሰድን ጨምሮ በአገር ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው ሕገወጥ ድርጊት እንደሚፈጽም ይነገራል፡፡

የኤርትራ ወጣቶች በአስመራ መንግሥት ከሚያደርስባቸው አፈና፣ ወታደራዊ ግዳጅ፣ ስቃይና ሞት ለማምለጥ በሕዝቡ እንደ ዋነኛ ጠላት እንድትቆጠር የተደረገችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደተለያዩ አገሮች እየሸሹ ይገኛሉ፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የአገሪቱ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠየቁ ሪፖርት ካወጣ ሳምንት አልሆነውም፡፡

በየመን እየተሰባሰበ ያለው የዓረብ አገሮች ኅብረት አባል በመሆን ከፍ ያለ ድጋፍ ማግኘቱ የተነገረለት የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የማተራመስ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተሰግቶ የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዶች ምልክቶችም ታይተው ነበር፡፡ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አባል የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአልሸባብ ጉዳት ሲፈጸምባቸው በርከት ያሉ የኤርትራ ዜግነት ያላቸው መማረካቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ በቅርቡ በአርባ ምንጭ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የግንቦት ሰባት አባሎችም፣ በኤርትራ መንግሥት ሙሉ ሥልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተመድ ጠንካራ ሪፖርት የወጣበት የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢትዮጵያ መንግሥት ይገልጻል፡፡

ባለፉት 16 ዓመታት የነበረው ሰላምም ጦርነትም የተለየው አካባቢ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ጥቃት እንደተፈጸመበት ቀድሞ ባወጣው መግለጫ ሁኔታዎቹ የተለወጡ መስለው ነበር፡፡ ጦርነት ማን እንደጀመረው እስካሁን በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፣ ከኤርትራ መከላከያ ኃይል ኮብልለው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ላይ በነበሩ ወጣቶች ላይ በኤርትራ ወታደሮች የተተኮሰ ጥይት እንደተጀመረ ገደብ ኒውስ የተባለው የኤርትራውያን ሚዲያ ዘግቧል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ቀድሞ የተናፈሰው ይኼው ጦርነት፣ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን የመጨረሻ ይሆናል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር፡፡ ይሁንና ሰኔ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጦርነቱ መቋረጡን መንግሥት አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰዱን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጦርነቱ ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ ‹‹በኤርትራ መንግሥት ባህሪ ይወስናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ጦርነት ሊቀጥልም ላይቀጥልም ይችላል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ጦርነት ባህሪ ይቀየራል የሚል እምነት ባይኖረንም፣ እንደየሁኔታው ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ተመጣጣኝ›› የሚለው የመንግሥት አገላለጽ ለብዙ ሰዎች ግልጽ አይመስልም፡፡

ብዙ ሰዎች ጦርነቱን አስመራ ድረስ በመሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲጠናቀቅ የሚጠይቁ ሲሆን፣ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ይኼው መፍትሔ እንደማይሆን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

ወጣት አብርሃም ተወልደ የግጥምና ዜማ ደራሲ አርቲስት ሲሆን፣ ከኤርትራ ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት መካከል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓመት ሞልቶታል፡፡ በተፈጠረው ነገር እጅግ ማዘኑን ይናገራል፡፡ ‹‹በዚህ ጦርነት ወንድማማቾችን ሲገዳደሉ ከማየት በላይ ምን ያሳዝናል?›› ሲል ይጠይቃል፡፡

ኤርትራ ውስጥ ያለው ሥርዓት አንድ ትውልድ ሙሉ እያጠፋ እንደሆነ ገልጾ፣ ‹‹ለኤርትራ ሕዝብ ያልሆነ ለጎረቤት ጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ ለሁላችን ሞትና ለስቃይ የዳረገ ሥርዓት ነው፤›› ብሏል፡፡

ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ግን ያነሳል፡፡ ‹‹ጦርነት ውስጥ የተማገደው ማን ነው?›› በማለት አጥፊዎቹ የችግሩ ቀማሽ እንዳልሆኑ ይናገራል፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ለኤርትራ ሕዝብም ለአካባቢም አደጋ መሆኑ አያጠራጥርም፤›› የሚለው አብርሃም፣ ይኸው ሥርዓት በሚፈጥረው ትንኮሳ እየተጠቃ ያለው ግን መውጫ ያጣ፣ ወገን የሌለውና በኃይል የተያዘ ኤርትራዊ ወጣት መሆኑና ከጦርነት ውጪ ሌላ አማራጭ መፍትሔ እንዲፈለግ ይጠይቃል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ጀነራል አበበ ተክለ ሃይማኖት በበኩላቸው፣ በዚሁ ሰላም አልባ ጦርነትና ሁኔታ እየባከነ ያለው የሰው ሕይወትና የኢኮኖሚ ኪሳራ መታደግ ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ እንደ ጀነራሉ እምነት፣ የኤርትራ መንግሥት ባህሪ እንደማይቀየር እየታወቀ የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲውን መቀየር አለመቻሉን ይተቻሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥትን ከሥልጣን ማውረድ የኤርትራ ሕዝብ ጉዳይ ቢሆንም ‹‹ኢትዮጵያን በግልጽ አፈራርሳታለሁ›› ለሚል ኃይል ሁሌም ተመጣጣኝ የሚባል ዕርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ ጀነራል አበበ ሁኔታውን በአጠቃላይ በቀጣናው እየሆነ ካለው ሁኔታ የሚመለከቱት ሲሆን፣ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ያላቸው አገሮች በየመን ተሰባስበው የኤርትራን መንግሥት የእነሱ መሣሪያ እያደረጉት በመሆኑ ለየት ያለ ፖሊሲ መውጣት እንዳለበት ይጠይቃሉ፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት ግንቦት ሰባትን ጨምሮ በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጁት ኃይሎች የሚያስታጥቅ ከሆነ መከላከል ብቻውን በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ መከላከል ላይ የሚያተኩረው ፖሊሲ ጠላትን ወደ መመከት መሸጋገር እንዳለበት የሚጠይቁት ጀነራል አበበ፣ የኢትዮጵያ ፖሊሲ በቀጥታ ውጊያ ከመክፈት ይልቅ በኢትዮጵያና በተለያዩ ዓለማት ላሉ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች አስፈላጊው የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲና የወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ሥርዓቱ እንዲወገድ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹አገርን በግልጽ አተራምሳለሁ የሚል ጎረቤት ተቀምጦ ዝም ብሎ ማየት አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አርቲስት አብርሃም ተወልደ ሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ሕዝብ ነፃነት የማይወላውል መሆኑ ያምናል፡፡ ሆኖም ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ አገር እንደ አገር እየፈረሰ አያገባኝም ብሎ መቀመጥ እንደሌለበት ይናገራል፡፡ በተመጣጣኝ ዕርምጃ፣ ጥቃት እየተፈጸመበት ያለው በተጨቆነው የኤርትራ ወጣት ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹እኔ እንደ መንግሥት አልቆጥረውም፡፡ የሽፍታ ሥርዓት ነው፡፡ መደበቂያው ደግሞ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ሲደረግበት የሥልጣን ዕድሜውን አራዘመ ማለት ነው፤›› ብሏል፡፡ ይኼ መንግሥት የሚወድቅበት መንገድ ከዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር አዲስ ስትራቴጂ እንዲቀይስም ይመክራል፡፡

የኢዴፓ የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው የኤርትራን መንግሥት በጦርነት ኃይል ማስወገድ የሚቻል ቢሆንም፣ ከብክነትም ከመርህም አንፃር ትክክል አይደለም ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስደውን የአፀፋ ምላሽ ቢደግፉም በዚህ ሁኔታ መቀጠል ትክክል እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹የአስመራ መንግሥት በጦርነትም በድርድርም የሚወገድ አይሆንም፤›› በማለት የኤርትራን ሕዝብ በማይጎዳ መልኩ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በማስተባበር ሥርዓቱን በመነጠል የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በዘላቂነት በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ተጨማሪ ጠባሳ የሚፈጥር ነገር ከማድረግ መንግሥት እንዲቆጠብም ይመክራሉ፡፡

ሙሉ ጦርነት አድርጎ የኤርትራ መንግሥትን ማስወገድ መፍትሔ እንደማይሆንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሌላ ሶማሊያ ከመፍጠር ውጪ ቦታው ላይ ማን ይተካል?›› ተብሎ መጠየቅ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ችግሩ የሌሎች ኤርትራውያንም ችግር ነውና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጣልቃ እንዲገቡበት ማድረግ ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች በራሳቸው ፍላጎትና መስመር አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ የመጨረሻ ዕልባት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንዲነጠል ማድረግም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይጠይቃሉ፡፡

ሰላምም ጦርነትም አልባ

የኢትዮጵያና የኤርትራን መለያየት ተከትሎ ለጥቂት ዓመታት የነበረው መልካም ግንኙነት በብዙዎች ‹‹ኮንፌዴሬሽን›› ዓይነት ቅርፅ እንደነበረው ይገለጻል፡፡ ሆኖም የኤርትራ መንግሥት አገሪቷን ከኢትዮጵያ ከገነጠለ ጊዜ ጀምሮ ከጎረቤት አገሮች በሙሉ ጦርነት ያደረገ ሲሆን፣ ከሰባት ዓመት በኋላ ሰኔ 1990 ዓ.ም. በድንበር ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብቷል፡፡ እጅግ ደም አፋሳሽ በተባለው ጦርነት፣ ከሁለቱም ወገን እስከ 70 ሺሕ የሰው ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ሁለቱም አገሮች በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሎባቸዋል፡፡

ይኼው ለሁለት ዓመት የቆየው ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ወታደራዊ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የኤርትራ መንግሥት ወደ ድርድር ተገዶ የገባ ሲሆን፣ ይግባኝ የሌለው የዘሄግ ፍርድ ቤት ኮሚሽን ጉዳዩን ይዞታል፡፡ የግልግል ኮሚሽኑ የጦርነቱ ዋና መናኸሪያ የሆነችውን ባድመን ለኤርትራ የሰጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የተቀበለችው ሰፊ የኤርትራ መሬትም ለኢትዮጵያ በማስረከብ ዕልባት ሳያስገኝለት ነበር የተበተነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በመርህ ደረጃ ውሳኔውን በመቀበል ‹‹ባለ አምስት ነጥብ›› የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትም አግኝቷል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የመፍትሔ ሐሳቡን ያልተቀበለ ሲሆን፣ እስከዛሬ የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚንቀሳቀሱ የትጥቅ ኃይሎችን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥትም እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ ባያደርግላቸው፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ያስተናግዳል፡፡ ላለፉት 16 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ፣ ለተቃጣ ማናቸውም ጥቃት ተመጣጣኝ የአፀፋ ምላሽ መስጠት ሲሆን፣ አሁን አሁን ይኼው ፖሊሲ ብዙዎቹ ጥያቄ ውስጥ እየከተቱት ይገኛሉ፡፡

ኤርትራ ጣሊያኖች ለግማሽ ክፍለ ዘመን፣ እንግሊዝ ለአሥር ዓመት ተፈራርቀው በቅኝ ግዛት የገዟት ሲሆን፣ በቅኝ ገዢዎቹ አዲስ ማንነት እንደተቀረጸለት ይነገራል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ በንጉሡ ዲፕሎማቲክ ጥረት ወደ አገሯ ተመልሳ ነበር፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ1952 የሁለቱም አገሮች ፌዴሬሽን ቅርፅ ከፈረሰ በኋላ የተጀመረው ‹‹የነፃነት›› ትግል ሰላሳ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

ደርግን በጋራ የተዋጉ የኤርትራ ሕዝባዊ ግንባርና የኢሕአዴግ መሥራች ከድል በኋላ የተለያዩ አቅጣጫዎችን ተከትለዋል፡፡ የኤርትራ አዲስ አመራሮች በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሒደት ላይ ለማሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ ሲሆን፣ ኤርትራ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ በ1987 ዓ.ም. በተመድ ነፃ አገር ሆና ተመዝግባለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -