Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለቀጣዩ በጀት ዓመት 3.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለማስገባት ታቅዷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የነዳጅ ፍላጎት በአሥር በመቶ አድጓል

የ2009 በጀት ዓመት የአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ በአሥር በመቶ እንደሚጨምር ታሳቢ በማድረግ የ3.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ በግዥ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መታቀዱ ተገለጸ፡፡

ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለበጀት ዓመቱ ከሚያስፈልገው ነዳጅ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ናፍጣ ነው፡፡ ለ2009 በጀት ዓመት ፍጆታ ይውላል ተብሎ ለመግዛት ከታቀደው 3.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ውስጥ የተወሰነውን ነዳጅ ለመግዛት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ጨረታም በመጪው መስከረም 2009 ዓ.ም. እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የተወሰነው የግዥ ጨረታ የሚወጣውም እስከ ታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የነዳጅ ፍላጎት የሚያሟላ ግዢ ኮንትራት ከሱዳንና ከኩዌት ኩባንያዎች ጋር በመፈራረሙ ነው፡፡ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በኋላ ያለውን የነዳጅ ፍላጎት ግን በጨረታ አሸናፊ የሆነው ኩባንያ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከ ታኅሳስ 2009 ዓ.ም. ድረስ ያለው አብዛኛውን ነዳጅ ለማቅረብ ወጥቶ የነበረውን ጨረታ አሸናፊ ሆኖ የነበረው የኩዌቱ ቪቶል የተባለው ኩባንያ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቪቶል እስከ 950 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቤንዚንና 850 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ናፍጣ ለማቅረብ ተስማምቶበት የነበረው ዋጋ 644 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

የአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን የሚያመለክተው መረጃ በተለይ የናፍጣ ፍጆታ ከሌሎች ምርቶች በተለየ ፍጆታው እየጨመረ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በ2009 በጀት ዓመትም 1.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን ናፍጣ ግዢ ይፈጸማል፡፡ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከነበረው ከ1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጋር ሲነጻጸር የፍላጎቱን ጭማሪ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ፣ የናፍጣ ፍላጎት ለመጨመሩ ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ያለው ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታ ማደጉና የተሽከርካሪዎችና የማሽነሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣት ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት በቀን ከስድስት እስከ አምስት ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ ይገባ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ታደሰ፣ በቀጣዩ ዓመት ፍጆታው ግን በቀን በአማካይ ከሰባት ሚሊዮን ሊትር በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ አገሪቱ ውስጥ እየገባ ካለው ነዳጅ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነውን ቤንዚን ከሱዳን የሚገባ ነው፡፡ ለአውሮፕላን የሚሆነውን ነዳጅ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የምታቀርበው ኩዌት ነች፡፡ ከዚህም ሌላ 60 በመቶ የሚሆነው ናፍጣም ከኩዌት የሚገባ መሆኑን አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ከጠቅላላው የቤንዚን ፍላጎት 25 በመቶውን እንዲሁም 40 በመቶ የሚሆነውን ናፍጣ ደግሞ በጨረታ የሚገዛ ነው ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ የሚፈጸመው የነዳጅ ግዢ የሚወጣው ወጪ ግን ከቀደመው ዓመት ብልጫ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ይህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች