Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣው የመንገድ ግንባታ ተጀመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚሠራው መንገድ 93 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ ይፈልጋል

ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወደብ አገልግሎት ታገኝበታለች ተብሎ ወደሚታመነው ታጁራ ወደብ የሚወስደው የዲቺቶ – ጋላይ መገንጠያ – አሊደርቦለሆ 81 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ተጀመረ፡፡

ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀውን ይህን መንገድ በሦስት ዓመት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ውል የተገባ ሲሆን፣ ግንባታውን እንዲያከናውን በጨረታ አሸናፊ ሆኖ የተረከበው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንደገለጸው፣ ጂቡቲ እያስገነባች ወዳለችው ታጁራ ወደብ ድረስ የሚዘልቀው ይህ መንገድ ኢትዮጵያን በታጁራ ወደብ ለመጠቀም የሚያስችላት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ መንገዱ በአፋር ክልል ያለው ፖታሽ ተቀነባብሮ ወደ ውጭ ገበያ መቅረብ ሲጀመር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ የተፈለገበት አንዱ ምክንያት ይኼው ተስፋ የተጣለበትን የፖታሽ ምርት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲያግዝ ታስቦ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ወደ ወደቡ ከሚዘልቀው መንገድ ኢትዮጵያ የምትገነባው የሁለቱ አገር ድንበሮች ድረስ ሲሆን፣ ጂቡቲም ከታጁራ ወደብ ድንበር ድረስ እየገነባች ነው፡፡

በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የሚገነባው ይህ መንገድ፣ ከሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለየ በሲሚንቶ ኮንክሪት የሚገነባ ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባ ረዥሙ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ በመሆን ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንደገለጸው፣ በሲሚንቶ ኮንክሪት የተሠራው መንገድ ከአሥር ኪሎ ሜትር የበለጠ አይደለም፡፡

የታጁራ መንገድ ግንባታ በሲሚንቶ ኮንክሪት መገንባቱ ሌሎች መንገዶችንም በተመሳሳይ መንገድ ለመገንባት የሚያስችል እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድም ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ፣ ለዚህ መንገድ ግንባታ ከ93 ሺሕ ቶን በላይ ሲሚንቶ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የአገሪቱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ግንባታው ለአስፓልት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረትም አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች