- የፓርላማው አባላት ቅጣቱ ከፍ እንዲል ጠይቀዋል
በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተሹመው ወይም ተመድበው ተቋሙን የሚመሩ ኃላፊዎች በውስጥ ኦዲት ወይም በውጭ ኦዲት ግኝት መሠረት ተገቢውን ዕርምጃ ያልወሰዱ እንደሆነ ከብር 5,000 እስከ ብር 10,000 እንዲቀጡ የሚደነግግ ረቂቅ የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ረቂቁ በ2001 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለውን አዋጅ ቁጥር 648/2001 የሚሻሻል ሲሆን፣ የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ያለውን ችግር የሚቀርፍ ሆኖ የተቀረፀ በመሆኑ፣ በዚሁ የበጀት ዓመት ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብርሃም አማኑኤል ምክር ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
በመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ረገድ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት ዕቅድና የሒሳብ ሪፖርት በሕግ በተደነገገው ጊዜ ውስጥ ያለማቅረብ፣ በውስጥ ኦዲትና በውጭ ኦዲት ግኝት መሠረት ተገቢውን ዕርምጃ ያለመውሰድ ለረዥም ጊዜ የቆዩና መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች መሆናቸውን የማሻሻያው ማብራሪያ ይገልጻል፡፡
በመሆኑም የማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሹመኛ ወይም የተመደበ ሰው በሕጉ መሠረት የሒሳብ ሪፖርት ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ያላቀረበ ወይም በውጭ ኦዲት ወይም በውስጥ ኦዲት ሪፖርት በተመለከተው መሠረት አስፈላጊውን ዕርምጃ ያልወሰደ ወይም ዕርምጃ መውሰዱን ያላረጋገጠ እንደሆነ፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ከ5,000 እስከ 10,000 ብር አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልበት በረቂቁ ተካቷል፡፡
ከሦስት ጊዜ በላይ አስተዳደራዊ ቅጣት የተጣለበት የሥራ ኃላፊ ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ሚኒስትሩ እንደ አግባብነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወይም ለፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር ጥያቄ እንደሚያቀርብ በረቂቁ ተካቷል፡፡
ከላይ የተቀመጠው ድንጋጌ በተለይ በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ የሚቀርቡ የኦዲት ግኝቶችን የሥራ ኃላፊዎች በአግባቡ እንዲያርሙ ሊያግዝ የሚችል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ዋና ኦዲተሩ ለአብነት ያህል ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የኦዲት ግኝት ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የኦዲት ችግር ያለባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሒሳቦችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም የተቀመጠው አስተዳደራዊ ቅጣት ከሚባክነው የመንግሥት ሀብት ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑን በመጠቆም አንዳንድ የፓርላማው አባላት ቅጣቱ ከፍ እንዲል አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡
ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አንዱ ናቸው፡፡
‹‹አስተዳደራዊ ቅጣቱ በመንግሥትና ሕዝብ ሀብት ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተመጣጠነ ሊሆን ይገባል፡፡ አዋጁ ያስፈለገበት ምክንያትም ይህ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ በማዘጋጀት የብድር ጫና ሁኔታንና የመክፈል አቅምን መሠረት ባደረገ አኳኋን እንዲመራ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አካቷል፡፡ ረቂቁ ለተጨማሪ ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡