የሳር ውስጥ እባብ (Grass Snake) ባብዛኛው ውኃ ገብ ወይም ረግረግና ሳር በበዛባቸው አካባቢዎች ይኖራል፡፡ ጥቁር አረንጓዴ ወይም ቡናማ ቀለም ሲኖረው ወደጭንቅላቱ አካባቢ ጣል ጣል ያለ ቢጫ ቀለም አለው፡፡
በመዋኘት ችሎታው የሚታወቀው ይህ ዝርያ እንቁራሪት፣ ወፍ፣ እጭ፣ ጉንዳንና ትላትል ይመገባል፡፡ በባህሪው ደግሞ የሞተ ነገርን አይመገብም፡፡
በኪድስ ባዮሎጂ ድረ ገጽ እንደሰፈረው፣ የሳር ውስጥ እባብ ምግቡን የሚያድነው ቀን ላይ ነው፡፡ ረዥም ጊዜውን የሚያሳልፈው ሳር ውስጥ ሲሆን፣ ጠላት በመጣበት ጊዜ የሞተ መስሎ ይተኛል፡፡ የሞተ መስሎ በሚተኛበት ጊዜ በአፍና አፍንጫው ደም ያመነጫል፡፡ የሞተ መስሎ በወደቀበት ሥፍራ የሚተናኮለው ከመጣ፣ አፉን ሳይከፍት ራሱን ይከላከላል፡፡ ራስ በመከላከል ጊዜ የሚናከሰውም ከስንት አንዴ ነው፡፡
አንዲት እባብ በአንድ ጊዜ እስከ 40 የሚደርሱ እንቁላሎች የምትጥል ሲሆን፣ ለመፈልፈልም ሁለት ወራት ይወስዳል፡፡ በሰሜን እስያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ በብዛት የሚገኘው ግራስ ስኔክ መርዛማ አይደለም፡፡