Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የሙዚቃ ማንነቴን የማግኘት ጉዞ አሁንም አላለቀም›› መክሊት ሐደሮ

‹‹የሙዚቃ ማንነቴን የማግኘት ጉዞ አሁንም አላለቀም›› መክሊት ሐደሮ

ቀን:

መክሊት ሐደሮ ነዋሪነቷን በሳንፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ ያደረገች ግጥም ጸሐፊና ዘፋኝ ነች፡፡ በመረዋ ድምጿና ገዥ በሆነው የመድረክ አያያዟ፤ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻለችው መክሊት የጃዝ፣ የሀገረሰብና የምሥራቅ አፍሪካ ሙዚቃዎችን በማጣመር የተለየ ሙዚቃ ዘዬ ማምጣት ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ የተወለደችው መክሊት ያደገችው በአሜሪካ ነው፡፡ በየል ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ የተመረቀች ሲሆን፣ የሙዚቃ ጉዞዋ የጀመረውም ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት የቴድ ግሎባል ፊሎውን ስም ማግኘት የቻለችው መክሊት ከሙዚቀኝነት በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማት እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጀርባ የጀርባ አጥንት የሆነችው መክሊት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አርቲስቶች ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክሩበት ‹‹አርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ›› ፕሮጀክት የጀመረችውም እሷ ነች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የናይል ተፋሰስ አገሮችን በሙዚቃ ሊያገናኝ የሚችል ‹‹ናይል ፕሮጀክትን›› ከጀመሩት መካከል አንዷ ነች፡፡ በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ አፍሪካን ጃዝ ቪሌጅ የሙዚቃ ዝግጅቷን አቅርባለች፡፡ በአጋጣሚውም የሙዚቃ ጉዞዋንና የምትሠራውንም ፕሮጀክቶቿን በተመለከተ ከጥበበሥላሴ ጥጋቡ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአፍሪካን ጃዝ ክለብ ውስጥ ከተካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት በተለይም ‹‹ከመከምና›› ‹‹ዓባይ ማዶ›› የሚሉት ዘፈኖችሽን ግጥም በሚረዱ አድማጮች መካከል መዝፈን ምን ዓይነት ስሜት ነበረው?

መክሊት፡- በጣም አስደሳች ነበር፡፡ ‹‹ከመከም›› ምን ያህል በአዲስ አበባ አድማጮች ጆሮ ውስጥ እንደገባ አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ‹‹ከመከም›› እንደሚሰማ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን በዚህ ያህል ደረጃ መሆኑን አላወቅኩም፡፡ በቦታው የነበረው አድማጭ ሳቀነቅን ይቀበለኝ ነበር፡፡ ከአድማጩ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት መፍጠር ችያለሁ፡፡ ለነበረው ስሜት በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የበለጠ እንድሠራ የሚያነቃቃ ነው፡፡ ከመከምን ሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን ቪዲዮውን ስንሠራ ብዙ ለፍተንበታል፡፡ ለኢትዮጵያ ተመልካቾች እንዲሆን ለማድረግ ከዳንሰኞች፣ ከዳይሬክተሩም ጋር በመሆን ብዙ ውሳኔዎችን ወስነናል፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ስለ ከመከም (ዘ ላቭ ፎር አፍሮ) ንገሪን፡፡ በተለይም በተፈጥሮ ፀጉር (ተፈጥሯዊ ፀጉር ምርጫ እንዲሆን) እንቅስቃሴዎች ባሉበት ሰዓት፣ ይኼ ዘፈን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዴት ነው የሚታየው? በሌሎች ጥቁር ሕዝቦችስ?

መክሊት፡- ከእኔ ልምድ ተነስቼ ልናገር፡፡ ከኢትዮጵያ ከሕፃንነቴ ከወጣሁ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የረገጥኩት ከአሥር ዓመት በፊት ነበር፡፡ በአጋጣሚም ከእናቴ ጋር አብረን ነበር የመጣነው፡፡ በጊዜውም የተተኮሰውን  ፀጉሬን ቆርጬ አፍሮ ፀጉር አድርጌው ለአፍሮዬ አዲስ ነበርኩ፡፡ የነበረውም ሁኔታ አስገራሚ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ፀጉሬን በመደነቅና በማፍጠጥ ነበር የሚያዩት፡፡ አሁን ከብዙ ዓመት በኋላ ተመልሸ ስመጣ ሁኔታው ተቀይሯል፡፡ የማፍጠጡ ሁኔታ የለም፡፡ ይህም በተፈጥሯዊ ፀጉር ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያሳይ ነው፡፡ ይኼንን ዘፈን የምወድበት ዋነኛው ምክንያት በአፍሮ ፀጉር ምክንያት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር እንዲሁም ከተለያዩ አፍሪካውያን ጋር የሚያገናኘን ዘፈን በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይኼንን ዘፈን ስለተቀበሉት ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ከብራዚል፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጋና በአጠቃላይ አፍሪካዊ ማንነት ካላቸው ጥቁር ሕዝቦች ‹‹ከመከም›› ለአፍሮ ያለውን ፍቅር በማሳየቱ በደስታ ስሜት መልዕክት ይልኩልኛል፡፡ በሳንፍራንሲስኮ ቤይ ካሉት የብላክ ላይቭ ማተር ሙቭመንት (በአሜሪካ ያሉ ጥቁር ሕዝቦች ተጨቁነዋል፣ ነፃ መውጣት አለባቸው የሚል እንቅስቃሴ ነው፡፡) አንቀሳቃሾች ጋር በምንወያይበትም ጊዜ ‹‹ከመከምን›› እንደ አንድ ብሔራዊ ዘፈን እንደሚያዩና በቢሯቸው ውስጥ ሁልጊዜም እንደሚያጫውቱት ነግረውኛል፡፡ ለዚህ መወደድም ዋነኛው ምክንያትም ዘፈኑ ለሕዝባችን (ለጥቁር) ሕዝብ፣ ያላቸውን ማንነት እንዲያፈቅሩና እንዲያከብሩ የሚያሳይ በመሆኑም ነው፡፡ በዚህ ዘፈንም  በዋነኛ ማስተላለፍ የፈለኩት ይኼን ነው፡፡ ማለትም በዘፈኑ ኢትዮጵያውያንን፣ አፍሪካውያንን አጠቃላይ ጥቁር ሕዝቦችን ማገናኘት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ፀጉር›› ከፀጉር በላይ ነው የሚለውን ፖለቲካዊ መልዕክት ያስተላልፋል ብለሽ ታስቢያለሽ?

መክሊት፡- ዘፈኑ ፀጉር ከፀጉር በላይ ነው የሚለውን መልዕክት በእርግጥ ያስተላልፋል፡፡ ፀጉር በዋነኝነት ማንነትን ይገልጻል፡፡ ዘፈኑም ፈጣሪ በሰጠን ፀጉርና በማንነታችን ከመኩራት ጋር ይያያዛል፡፡ ፀጉሬን በእሳት ላለመተኮስ ምርጫ ያደረግኩትም ከማንነቴ ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን በባህላችን ኩሩና በማንነታችንም ኩሩ ነን፡፡ ነገር ግን በሌላው ዓለም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ በተለይም አሜሪካ ውስጥ ባለው ሚዲያ ከጥቁር ማንነት ጋር ተያይዞ አሉታዊ የሆኑ መልዕክቶች አሉ፡፡ ከ‹‹ከመከም›› ጀርባም ያለው መልዕክት ማንነትን ከፍ የማድረጊያ ዘዴ እንዲሁም ለጥቁር ሕዝቦች መገናኛ ነጥብ መሆንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዓባይ ማዶ ቆየት ያለ ዘፈን ነው፡፡ ይኼን ዘፈን ለመዝፈን ምን አነሳሳሽ?

መክሊት፡- እንደ ዓባይ ማዶ ስላሉ ሕዝባዊ ዘፈኖች የራሴ የሆነ ፅንሰ ሐሳብ አለኝ፡፡ ይኼውም እነዚህን ሕዝባዊ ዘፈኖች አንድ ሰው ቢዘፍነው ይኼ ሰው ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የቀደሙትም ትውልዶች በዘፈኑ ውስጥ አሉ፡፡ ለማንኛውም ዓባይ ማዶን ለመዝፈን የወሰንኩበት ምክንያት ዘፈኑን ከዓመት በላይ ‹‹ዓባይ ማዶ›› እያልኩ አንጎራጉር ነበር፡፡ ተጠናውቶኝም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከአዕምሮዬ ሳላወጣውም ስቀር  ዘፈኑ መርጦኛል አልኩ፡፡ አንድ ዘፈን፣ ሲመርጥሽ፣ ደግሞ ማንገራገርና መጠየቅ አያስፈልግም፡፡ ‹‹ዓባይ ማዶ››ንም መጀመርያ በወጣው አልበሜ ‹‹ኦን ኤ ደይ ላይክ ዚስ››ም ላይ አካተትኩት፡፡ በዚህም አልበም የኢትዮጵያ ዘፈን፣ ጃዝና የራሴ የጻፍኳቸው ዘፈኖች የተካተቱ ሲሆን፣ የሚቀጥሉትም አልበሞች የዚህን አልበም ይዘት ተከትለው ነው የሄዱት፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ በምትዘፍኚበት ወቅት አድማጮችሽን በጥልቅ ስሜት የመውሰድ ባህርይ ሲኖርሽ፣ በዚሁ ጥልቀትና ተመስጦ ውስጥም የደስታና የመዝናናት የመሳቅ ስሜት ማምጣት ችለሻል፡፡ ይኼንን በምን መንገድ ነው የምታደርጊው?

መክሊት፡- አንድ የሙዚቃና የአዕምሮን ግንኙነት የሚያጠና ኒዮሮሳይንቲስሲት ጓደኛዬ የነገረኝን ልናገር፡፡ እሱም ምን ይላል ደስታና ሐዘን ብቸኛው የሚገናኙበት የአዕምሮ አካል በሙዚቃ ነው፡፡ ይኼም ምን ማለት ነው? ማንኛውም ስሜት በሙዚቃ ሲገለጽ የደስታ ስሜት አለው፡፡ እንደ ትዝታ ያሉ ዘፈኖችን ጨምሮ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌላው ከመድረክ እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ አካላዊ ግንኙነትን ከአድማጩ ጋር ለመፍጠር መሞከር፣ የተለየ ነበልባላዊ ስሜትን ማጥጣት በተለይም ውስጥ ከተደበቀው ከልጅነታችን ጋር ለመገናኘት መሞከር ከአድማጩ ጋር የምንገናኝበት መንገድ ነው፡፡ የመድረክ እንቅስቃሴ መረማመድን ለመልመድ በደስታ ስሜት እንደሚሞላ ሕፃን ልጅ መሆን አለበት፡፡ ለእኔ መድረክ ላይ ስሆን እንደዚህ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡ ቀላል የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ እግሬን ማንቀሳቀሴ የተለየ ስሜት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ በምትሆኚበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሙዚቃው ትመሰጪያለሽ ማለት ነው?

መክሊት፡- አዎ  ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ የራስሽን እንቅስቃሴ የምትታዘቢበት ጊዜ ቢኖርም፤ ወዲያው መታዘብ ሲኖር ያንን ስሜት ተወት በማድረግ ከሙዚቃው ጋር ለመገናኘት ትንሽ ፀሎት አደርጋለሁ፡፡ ከዚያም ሙዚቃውን ብቻ ይሆናል የምሰማው፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኒቨርሲቲ ቆይታሽ ፖለቲካል ሳይንስ አጥንተሻል፡፡ ወደ ሙዚቃው እንዴት ገባሽ?

መክሊት፡- ከሕፃንነቴ ጀመሮ ሙዚቀኛ መሆን ነበር የምፈልገው፡፡ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቼ አልደገፉትም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ቤት፣ ትምህርት ቤትና በበጎ ፈቃደኝነት በምዘፍንበት ወቅት ምንም ባይመስላቸውም፣ ከዚህም በተጨማሪ ሙዚቃዬን እኔ መሥራት በምፈልግበት መልኩ ሊያሳየኝ የሚችል ተምሳሌት አልነበረኝም፡፡ ብዙዎች ሙዚቃን ከትምህርትና በአካዳሚክ መንገድ በተያያዘ ሁኔታ ሲያጠኑ ማየት ደግሞ ያለውን የሙዚቃ ደስታ መነጠል መስሎ ተሰማኝ፡፡ በአሁን ወቅት ያንን ጥናትና ልምምድ በሌላ መንገድ ነው የምመለከተው፡፡ ሌላው አማራጭ የሙዚቃ መንገድ  ታዋቂ የመሆን አምልኮ ነበር፡፡ ይኼም ሆነ ያ ሁለቱም መንገዶች ለእኔ ምቹ አልነበሩም፡፡ በዚህም ምክንያት ሙዚቃን የጀመርኩት ዘግየት ብዬ በ24 ዓመቴ ነው፡፡ በብዙ ዘርፎች ዘግየት ብለው ለሚጀምሩ ሰዎች ድጋፍ ያለኝ እኔ ሙዚቃን ዘግየት ብዬ ከመቀላቀሌ ጋር ስለማያይዘው ይሆናል፡፡ ሙዚቃዬን በምን መንገድ መሥራት እንዳለብኝ የተረዳሁት ሳንፍራንሲስኮ በሄድኩበት ወቅት ነው፡፡ ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ ያገኘኋቸው አርቲስቶች በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች የተሰባሰቡ ሙዚቀኞችና አርቲስቶች ማኅበረሰቡን በተለያዩ የጥበብ ዝግጅቶችና ፌስቲቫሎች ያሳትፉ ነበር፡፡ ከእነሱ ጋር አብሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በመቀጠልም በሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው የጥበብ ማዕከል የሬድ ፖፒ አርት ሐውስ አንደኛዋ ዳይሬክተር ሆንኩኝ፡፡ በጣም ጠባብ ቦታ ብትሆንም ብዙ ሥራዎችን እሠራ ነበር፡፡ ከድምፅ ማስተካከል ጀምሮ ላቤ ጠፍ እስኪል ትልልቅ የሙዚቃ ስፒከሮችን ማንሳት እንዲሁም ሌሎች ዕቃዎችንም እሸከም ነበር፡፡ እንደዛም ሆኖ በጣም አስደሳችና   በሕይወቴ ልዩ ቦታ የምሰጠው ጊዜ ነው፡፡ ለየት ያለ ሙዚቃ የሚሠሩና ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ሙዚቀኞችን ተዋውቄያለሁ፡፡ ጃዝን ከራሳቸው አገር ሙዚቃ ጋር በማጣመርም ይሠሩ ነበር፡፡ የመጣንበትን ባህል ሳንለቅ አሁን ላለው ጊዜ መሰማት የሚችል ሙዚቃ እንዴት መሥራት እንችላለን የሚሉትን ጥያቄ መመለስም ችለናል፡፡ አንድ አገር ላይ ስር መሠረታችንና ማንነታችን አለ፡፡ ግን የምንኖረው ሌላ አገር ነው፡፡ ይኼንን ሊያሳይ የሚችል ሙዚቃም ብዙዎቹ ይሠሩ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ሙዚቃ በጀመርሽበት ወቅት ምን ዓይነት ሙዚቃ ነበር የምትጫወችው? ያሁኑን የሙዚቃ ማንነትሽን የማግኘት ጉዞ ምን ይመስላል?

መክሊት፡- እንደ ሙዚቀኛ በአድማጮች ፊት ከማደግ ውጭ ምንም ምርጫ የለም፡፡ ሙዚቀኛ ከሆንሽ መደበቅ አይቻልም፡፡ በዓመታት ውስጥ የተረዳሁት የሰዎችን ማንነትን ለመግለጽ (ለማሳየት) ብርታት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ የሙዚቃ ማንነቴን የማግኘት ጉዞ አሁንም አላለቀም፡፡ እየቀጠለ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት የነበረኝ የሙዚቃ ስብጥር ጃዝ የኢትዮጵያና የራሴን ሥራዎች የያዘ ነበር፡፡ አሁን ሐምሌ ላይ ልንቀርፀው ባሰብነው ሥራ ላይ ግን ሦስቱም የሙዚቃ ዓይነቶች በአንድ ሥራ ላይ ተጣምረው ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ሦስቱን የሙዚቃ ዓይነቶችን የማጣመር ሥራ እስካሁን ድረስ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል አላውቅም ነበር፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ባለው የሙዚቃ ሥራዬም የበለጠ የሙዚቃ ማንነቴን እያገኘሁ ይመስለኛል፡፡ እኔ አሁንም ለሙዚቃው አዲስ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ገና 11 ዓመቴ ነው ከጀመርኩ፡፡ ሙዚቃ የሕይወት ጊዜ ሥራ  ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሙዚቃ ዕድገቴ አዳዲስ ነገሮችንም ከመሞከር ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ አስተያየቶች ይኼንን መንገድ እንድከተል አነሳስተውኛል፡፡ ጃዝን እኛ እንደተጫወትነው አትጫወቺ ይለኛል፡፡ የእኔ አስተዋጽኦ የት ላይ እንዳለ እንዲሁም ይኼንን ሙዚቃ የት እንደምወስደው በተደጋጋሚ ይጠይቀኛል፡፡  የሦስቱን ሙዚቃ ጥምረት በአንድ ላይም መሥራቴ ዶክተር ሙላቱ ለሚያነሳልኝ ጥያቄዎች መልስ ነው፡፡ በዓመታት ውስጥም ከሙዚቃ ጉዞዬ ጋር ተያይዞ ሙያዊ ሥነ ምግባር አዳብሬያለሁ፡፡ በየቀኑ ስቱዲዮ እሄዳለሁ፣ ጊታር እለማመዳለሁ እንዲሁም ሙዚቃዎችን እፅፋለሁ፡፡ ይህ ሙያዊ ሥነ ምግባር ለወደፊቱም ዋጋ ያስገኝልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃሽ ለየት የለ ከመሆኑ አንፃር አድማጮችሽ እነማን ናቸው?

መክሊት፡- ብዙ ዓይነት የሙዚቃ አድማጭና አድናቂ ነው ያለኝ፡፡  በምጫወትባቸው አጋጣሚዎች ኢትዮጵያውያን አይጠፉም፡፡ ለዚህ ድጋፋቸውን ከማመስገንም በተጨማሪ መድረክ ላይ አብረውኝ እንዲዘፍኑና እንዲደንሱ ይዤያቸው እወጣለሁ፡፡ ይኼ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ውጭ ላለው ሌላው ማኅበረሰብ ኢትዮጵያውያን እዚህ አሉ የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ብዙ አሜሪካውያን አድናቂዎችም አሉኝ፣ እንግሊዝ የነበረኝም የሙዚቃ ዝግጅት ጥሩ ነበር የናይሮቢ የሙዚቃ ዝግጅቼም በሙዚቃ ወዳጆች ጥቅጥቅ ያለና ደስ የሚሉ ነበሩ፡፡ በየትኛውም የሙዚቃ ጉዞዬ ሰዎች እየሰሙኝ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ ብዙ ሰዎች ከግሪክ ይጽፉልኛል፡፡ ግሪክ የሙዚቃ ዝግጅት ኖሮኝ ባያውቅም የተለያዩ የግሪክ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሙዚቃዬን ያጫውታሉ፡፡ በፌስቡክም ስሜን ሲያነሱ አያለሁ፡፡ ይኼ የሚያሳየው ሙዚቃ ምንም እንኳን አንድ ቦታ ላይ መሠረት ቢኖረውም ሁልጊዜም ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ላገኘሁት የሙዚቃ መድረክ እንዲሁም የአድማጮቼን እንክብካቤ አመሰግናለሁ፡፡ ምክንያቱም በሙዚቃ ቢዝነስ ውስጥ ምንም ዓይነት ዘለቄታዊ ዋስትና የለም፡፡ አሁን ሙዚቃ እየተሰማ ከሆነ የሚቀጥለው ዓመት ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአራት ዓመት በፊት ‹‹ኧርዝባውንድ የሚል›› ኢትዮጵያዊ ሳይንሳዊ ልብወለድ፣ (ሳይንስ ፊክሽን) ሒፕሆፕ ኦፔራ አልበም አውጥተሻል፡፡ ይኼ ፕሮጀክት እንዴት እንደመጣ እስቲ ንገሪን?

መክሊት፡- ይኼ አልበም ለእኔ ለየት ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሳይንሳዊ ልብወለድ ሂፕ ሆፕ ኦፔራ ከዚህ በፊት መኖሩን አላውቅም፡፡ ሳይንሳዊ ልብወለድ (ሳይንስ ፊክሽን) የወደፊቱን ከማሰብ፣ የወደፊት አማራጮችን ከመፍጠር፣ ጋር በተያያዘ ተጠቅመንበታል፡፡ ይኼንን አልበም የመሥራት ፍላጎት የተፈጠረው በአጋጣሚ ነው፡፡ የቅርብ ዘመዴ ገብርኤል ቴዎድሮስ እንዲሁም ጓደኛዬ ኤልያስ ፉል ሞር ወይም በቅፅል ስሙ የሚታወቀው በርንት ፌስ (የተቃጠለ ፊት) ቤት ውስጥ ተቀምጠን እያወራን ዘፈኖቹን የመሥራት ሐሳብ በአጋጣሚ ተፀነሰ፡፡ በዚያው ምሽት ዘፈኑን ጻፍነው፡፡ የየራሳችንን የዘፈን መስመሮችና ገፀ ባህርያት ፈጠርን፡፡ የገብርኤል ቴዎድሮስ ገፀ ባህርይ ግማሽ ሰው ግማሽ ኤሊየን (ከሌላ ዓለም የመጣ ፍጡር) ሲሆን የኤልያስ ገፀ ባህሪይ ፕሮፌሰር አስካለ ቢላቅ የሚባል ኢትዮጵያዊ በሌላ ፕላኔት ሊኖረው የሚችለውን ልምድ እንዲሁም የእኔ ገጸ ባህሪይ ኮ-አይ ጊዜ የማይገድባትና በሁለንታ (በዩኒቨርሲቲ) ውስጥ መጓዝ የምትችል ነች፡፡ ናሳ ውስጥ ከሚሠራ የአስትሮ ፊዚክስ ምሁርም ጋር በመቀናጀት የከዋክብትን ድምፅም ማግኘት ችለናል፡፡ እነዚህ የከዋክብት ድምፆችም በሙዚቃችን ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ናይጄሪያዊ አሜሪካዊት የሳይንሳዊ ልብወለድ (ሳይንስ ፊክሽን) ጸሐፊ ከሆነችው ኔዲ ኦክራፎር ጋር በመጣመርም ሠርተናል፡፡ ይህቺ ጸሐፊ  በአፍሪካ የሳይንስ ልብወለድ (ሳይንስ ፊክሽን) ጽሑፍ ከፍተኛ ቦታ ያላት ናት፡፡ ሳይንስ ፊክሽን ማሰብ እንዲሁም ማለም የማንችላቸውን ሐሳቦች እንደሚቻሉ ማሳየት የሚችል ነው፡፡ ከሳይንስ ልብወለድ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ ያለው የአፍሮ ፊውቸሪዝም እንቅስቃሴም በዓለም ላይ እያደገ ነው፡፡ ለእኔ አፍሮ ፊውቸሪዝም ሰዎች ነገሮችን የሚያዩበት ሁኔታ ነው፡፡ ይኼ እንቅስቃሴ እንደነ ሰንራ፣ ጆርጅ፣ ክሊንተን፣ ፓርላሜንት ፈንካዴሊክ ባሉ አርቲስቶች ነው የተጀመረው፡፡ ይኼም እንቅስቃሴ የአፍሪካውያን የወደፊት ሁኔታን በጽሑፎቻቸው በጥበብ ሥራቸው እንዲፈጥሩ ወይም እንዲያዩ የሚያስችል ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ይኼ የሳይንስ ፊክሽን ሂፕ ሆፕ አልበም ተቀባይነቱ እንዴት ነው?

መክሊት፡- በሂፕ ሆፕ ማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነቱ በጣም ደስ ይላል በሙዚቃ ጉዟችንም ወቅት ከብዙ ሰዎች ጋር ሐሳብ የመለዋወጥና የመገናኘት ሁኔታ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሙዚቃዬ ግራ የተጋቡም አልታጡም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ የሚያውቁኝ ለስለስ ባለ ሙዚቃዬ ስለሆነ ይሆናል፡፡ የብዙዎችም አስተያየት ከአሁን በኋላ ሂፕ ሆፕ ብቻ ነው እንጂ ሌላ ሙዚቃ አትሠራም የሚል ነበር፡፡ ይሄ የሚያሳየው ሙዚቀኞች በሕይወታቸው ዘመን ብዙ ዓይነት ሙዚቃ ሊሠሩ እንደሚችሉ ብዙዎች መረዳት እንደሚከብዳቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የራስሽን ግጥም ከመጻፍሽ አንፃር በሙዚቃሽ ውስጥ ጠቃሚ የምትያቸው መልዕክቶች ምንድናቸው?

መክሊት፡- ስለማንኛውም ጉዳይ መዝፈን እንደምችል የተረዳሁበትን ጊዜ የተረዳሁት አንድ ዘፈን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ ይኼም አጋጣሚ የተፈጠረው ካይትኖ ቬሎሶ የሚባል ብራዚላዊ ዘፋኝ ‹‹ኦ ሊያዚንሆ›› (ትንሹ አንበሳ) የሚል በብራዚል ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ዘፈን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ ስለ ብርቱካን፣ ልብ መሰበር፣ ስለሕዝቦችሽ ተስፋ የምታደርጊው ጥሩ ነገር፣ ስለ ሕይወት ውጣ ውረድ ስለ ሌላ ዓለማት መዝፈን ይቻላል፡፡ ሙዚቀኞችም ይኼንን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃ የሕይወት መስታወት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ስለወጣው ‹‹ዊ አር አላይቭ›› ስለሚለው አልበምሽ እናውራ በዚህ ዘፈን ‹‹ምንም እንኳን ቢከብድም ወይም ሕይወት ጣፋጭ ቢሆንም በሕይወት አለን (ዊ አር አላይቭ) ይላል፡፡ ይኼ ዘፈን ላንቺ ምን ማለት ነው?

መክሊት፡- ‹‹በሕይወት አለን›› (ዊ አር አላይቭ) ማለት ሕይወታችን ጨለማ በተሞላበትም ጊዜ በሕይወት አለን፡፡ በሕይወት መኖራችንን የምናስታውሰው በደስታ ጊዜ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ከባድና ፈታኝ ብትሆንም በእግራችን ቆመን ስለሄድን፣ ስለተነፈስን በሕይወት መኖራችንን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለእኔ ይኼ ዘፈን ስንገዳገድና  ልሰምጥ ስል እንደ ከለላ ሆኖ የሚያድነኝ ዘፈኔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ሙዚቃ የሱዳን ፔንታቶኒክ ስኬል ተፅዕኖ አለው? እንዴት ሙዚቃው እንደተሠራ ንገሪን?

መክሊት፡- ይኼ ሙዚቃ ናይል ፕሮጀክት ሥንሠራ የተጠነሰሰ ነው ናይል ፕሮጀክት  በናይል አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችን በሙዚቃ ማስተማር፣ ማስተሳሰር እንዲሁም የአካባቢው ሁኔታ የማይነካበትን ዘላቂ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ በመጀመርያ ለእኔ ናይል ፕሮጀክት መሄድ ከምችልባቸው የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች በላይ የሙዚቃ ትምህርት ቤቴ ነው፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያዊ የባህል ሙዚቀኞች እንዲሁም ከናይል አካባቢ አገሮች ሙዚቀኞች ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ አህመድ ሰይድ የሚባል ሱዳናዊ አርቲስት ነው፡፡ ይሄ ሙዚቀኛ ከፔንታቶኒክ ስኬል በተጨማሪ ፋይፍ ካውንት (አምስት ድምፆችን በመቁጠር) ምት እየጫወተ ነበር፡፡ ይኼ ምት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአሜሪካም አዲስ በመሆኑ በጣም ነው ያስገረመኝ ያስደሰተኝም በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የእንግሊዙ ባንድ ሬዲዮ ሄድ ‹‹ፊፍቲን ስቴፕስ›› የሚል ሙዚቃ ስሰማ ሁለቱን ሥራዎች የማጣመር ሐሳብ መጣልኝ የሁለቱ ጥምረት ምርጥ የሆነ ዘፈን ወጣው፡፡

ሪፖርተር፡- የናይል ወንዝ በጣም ሰፊና ትልቅ ነው፡፡ እነዚህን የናይል ተፋሰስ አገሮችን በሙዚቃ ጉዞ መሸፈን አይከብድም? ልምዱን እንዴት ታይዋለሽ?

መክሊት፡- ሙሉ ናይልን የሙዚቃ ጉዞዬ አላጠቃለለም ናይል በጣም ሰፊና ወንዙን ተከትለሽ ስትሄጂ የተለያየ ሕዝብ ነው፡፡ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ናይልን በጣም መውደዳቸውና የሕይወታቸው መሠረት መሆኑ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ናይል ሲታሰብ ግብፅ ብቻ ነች የምትታወቀው፡፡ ናይል ግን ከግብፅ በላይ ነው፡፡ በዚህም ፕሮጀክት ይሄንን አስተሳሰብ በመጋፋት የላይና የታች ናይል ተፋሰስ አገሮችን በሙዚቃ አንድ ላይ አምጥተናቸዋል፡፡ የፕሮጀክቱም ሐሳብ የመነጨው ፈንዲቃና ደቦባንድ ተጣምረው ኦክላንድ የሙዚቃ ዝግጅት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡ እኔና ግብፃዊው ኤትኖሚዩዚኮሎጂስት (የሙዚቃን ባህላዊ አንድምታ የሚያጠና) ጓደኛዬ ሚና ጊርጊስ በሙዚቃው በጣም ተደመምን ከዚያም የተነሳው ጥያቄ እንዴት የኢትዮጵያ ሙዚቃን ለመስማት ኦክላንድ እንመጣለን? የሚል ነበር፡፡ እኛ አፍሪካውያን በደንብ አንተዋወቅም ለዚህም ብዙ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማኅበረሰብ ባህል የተለያየ መሆን ራሱ ኢትዮጵያን የመረዳት ሥራን ያከብደዋል፡፡ ለዚያም ነው ሙዚቀኞችን ከታችና ከላይ ናይል ተፋሰስ አገሮች አምጥተን ልምድ እንዲለዋወጡ ያደረግነው፡፡

ለእኔ ብዙ የተማርኩበት ፕሮጄክት ነው፡፡ ለትልቅ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ማቀናበርን  ተምሬያለሁ፡፡  ለጊዜው ይኼንን ፕሮጀክት ተወት አድርጌ በአሁኑ ወቅት ወደ ራሴ ሙዚቃ ያተኮርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም በናይል ፕሮጀክት ከዓመት በላይ  አሳልፌያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ራሴ ሙዚቃ መመለስ ያለብኝ መስሎ ስለተሰማኝ ለጊዜው ወደ ጎን ተወት አድርጌዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምስት ዓመት በፊት የመጣሽበት ፕሮጀክት አርባ ምንጭ ኮሌክቲቭስ (የአርባ ምንጭ ስብስብ) አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?

መክሊት፡- የአርባ ምንጭ ኮሌክቲቭ (የአርባ ምንጭ ስብስብ) ዋና ዓላማ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ አርቲስቲቶችን በአንድ ላይ ማምጣት ነው፡፡ በሌላ ዓለም የሚኖሩ ብዙ ዳያስፖራ አርቲስቶች ተመሳሳይ ፍላጐት አላቸው፡፡ ይሄውም ከኢትዮጵያ ጋር በጥበብ ሥራቸው ግንኙነት መፍጠርንና ኢትዮጵያን በመንፈስ ማስታወስ ናቸው፡፡ ይሄንንም ሁኔታ ኢትዮጵያ ሳንሄድ ልንፈጥረው አልችልም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተቀየረች ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በቤተሰቦቻችን የተነገረን ታሪክ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አሜሪካ ውስጥ ሳድግ በደርግ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣት አንችልም ነበር፡፡ ብዙዎቻችንም ባለመምጣታችን ኢትዮጵያን የምናስብበት (የምንቀርጽበት) መንገድ የቤተሰቦቻችን ታሪክ ነው፡፡ የቤተሰቦቻችንን ታሪክ መርሣት የለብንም፡፡ ነገር ግን  የራሳችን የሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ ልንገነዘብ ልንፈጥር ይገባል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊ መሆንን እንደ አንድ የግንኙነት ማዕከል በማድረግ ሊቀጥሉ የሚችሉ ታሪኮችን ለመጋራት ሁለት ጊዜ የሙዚቃ ጉዞዎችን በ2001 ዓ.ም. እንዲሁም በ2003 ዓ.ም. አድርገናል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እነዚህን ጉዞዎች ማዘጋጀት ከባድ ሆነ፡፡ ይሄንን ሳዘጋጅ የነበርኩት እኔ ብቻ ስለሆንኩኝ ወደ ሙዚቃዬ ፊቴን ሳዞር የሚሠራው ጠፋ፡፡ በአሁኑ ወቅት አብረን ጉዞ ከማድረግም በላይ ወደ ጥምረት ሊያድግ ይገባል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ የተለያዩ አርቲስቶች የዚህ ጉዞ አካል እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ብዙ አዳዲስ ኢትዮጵያውያን የጥበቡን ዓለም እየተቀላቀሉ ስለሆነ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላኛው ፕሮጀክትሽ ‹‹ሆም አዌይ ፍሮም ሆም›› (ከቤት ርቆ ቤት) ነው፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክት ብታብራሪልን? ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደሽ አሜሪካ ከማደግሽም ጋር ‹‹ሆም›› (ቤት) የት ነው? ሆም (ቤት) የማይጨበጥ ሐሳብ አይመስልሽም?

መክሊት፡- ‹‹ሆም አዌይ ፍሮም ሆም›› ከሁለት ዓመት በፊት ኒውዮርክ ውስጥ በሚገኘው የርባ ቡየና የጥበብ ማዕከል ተነሳሽነት የተሠራ ፕሮጀክት ነው፡፡ የማኅበረሰብ ተሳትፎን አትኩሮት ሰጥቶ የሚሠራ ማዕከል ነው፡፡ ይሄ ፕሮጀክት ወደ እኔ ሲመጣ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ የተውጣጡ አርቲስቶችን ጋበዝኩ፡፡ ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው እነዚህ አርቲስቶች ከተለያዩ የባህልና የጥበብ ተቋማት ጋር ግንኙነታቸውን በማጠናከር በገንዘብ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያውን ሬዚደንሲ፣ ግራንትና ኮሚሽን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የመጀመሪያውን ሬዚደንሲ (ቦታና ብር ተሰጥቷቸው ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ)፣ ግራንት (ለጥበብ ሥራቸው የሚሰጥ ብር) እና ኮሚሽን (የጥበብ ሥራቸውን እንዲሠሩ መቅጠር) ሰጥተናቸው ጥበብ፣ ሙዚቃና ባህልን በማተኮር ሁለቱን ማኅበረሰቦች ‹‹ሆም አዌይ ፍሮም ሆም›› የሚለውን ሐሳብ እንዲሠሩበት አደረግን፡፡

ሥራቸውን የሚያሳዩበት ጋለሪ ኦክላንድ ውስጥ ሜሪት ሐይቅ አካባቢ ጎጆ ቤት ሠራን፡፡ ይሄ ዝግጅት ለሁለት ቀን የነበረ ሲሆን ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ግጥምና ምግብንም ያካተተ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አባባሎች ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሙን በሩ አካባቢ በእንሥራ አስቀመጥናቸው፡፡ ይኼንን ቦታ ብዙዎች የጎበኙት ሲሆን፣ በሩ አካባቢ የነበሩትንም አባሎች ይወስዱ ነበር፡፡ እውነት ነው ቤት የሚለው የሚቀያየርና የማይጨበጥ ነው፡፡ ለዚያም ነው ቤትን በግንኙነቶች የማየው እዚህ አዲስ አበባ ከአክስቴና ከአያቴ ጋር ስለሆንኩ ቤቴ እነሱ ናቸው፡፡ አሜሪካ ደግሞ እህቴ፣ እናቴና አባቴ ቤቴ ናቸው፡፡ ቤት ልባችንን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ እነዚህም ግንኙቶች እንደዚያው፤ አስታውሳለሁ ስናድግ እናቴ ስለኢትዮጵያ ስታወራ ሁልዜም ቤቴ እያለች ነው የምታወራው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያም መጥታ አሜሪካን አገሬ (ቤቴ) ማለት ጀመረች፡፡ ይኼ ልክ እንደ ትዝታ ዘፈን ቤት የሚለው ሐሳብም የማይሟላና ሁሌም የምናፍቃቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚያሳየው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...