Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴት አስጎብኚዎች ጉዞ

የሴት አስጎብኚዎች ጉዞ

ቀን:

በአብዛኛው ስልኳ ሲያቃጭል የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ አልያም ሰው ሠራሽ ሀብቶች ለመጎብኘት የፈለጉ ቱሪስቶች ስለሚሆኑ ጊዜ ሳታጠፋ ትመልሳለች፡፡ ለቱሪስቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱሪስት መዳረጃ ቦታዎችን ታሳውቃለች፡፡ የበለጠ ትኩረታቸውን የሳቡት ስለመሰሏት አካባቢዎች ይበልጥ ትገልጽና ምርጫቸውን ይወስዳሉ፡፡ በሚጎበኙት አካባቢ የሚቆዩበትን ጊዜና የሚከፍሏትን ገንዘብ ከተሰማሙ በኋላ ደግሞ የጉዞ ቀን ይቆረጣል፡፡

ፍሬ ሰናይ በዚህ ሁኔታ ላለፉት አምስት ዓመታት በአስጎብኚነት ሠርታለች፡፡ ወደ ሙያው የገባቸው የቱር ኦፕሬተርነት ትምህርት እንዳጠናቀቀች ነበር፡፡ የአስጎብኚነት ሥራውን የምትሠራው በግሏ ስለሆነ፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አስጎብኚ የሚፈልጉ ቱሪስቶች ሲኖሩ፣ የተለያዩ ተቋሞች ወይም ግለሰቦች ወደ እሷ ይመሯቸዋል፡፡ ፈረንሣይኛ፣ እንግሊዝኛ ዓረብኛ መናገር እንደምትችል ትናገራለች፡፡

በአንድ ወቅት እንደወትሮው ይደወልላትና ከዓረብ አገር የመጡ ቱሪስቶች አስጎብኚ ስለሚፈልጉ በአካል አግኝታቸው እንዲነጋገሩ ትጠየቃለች፡፡ ብዙ ጊዜ ጎብኚዎችና አስጎብኚዎች ወደሚገናኙበት ጣይቱ ሆቴል ታመራለች፡፡ አንዲት ኢትዮጵያዊት ከዓረቦቹ ጎብኚዎች ጋር ነበረች፡፡ ዓረብኛ ለጎብኚዎቹ ዓረቦች የቱሪስት መዳረሻዎችን ትዘረዝርላቸው ጀመር፡፡

ኢትዮጵያዊቷ ድንገት ታቋርጣትና ዓረቦቹን ከማስጎብኘት በተጨማሪ ‹‹ሌላ አገልግሎት›› ትሰጥ እንደሆነ ትጠይቃለች፡፡ ፍሬ ጥያቄው እንግዳ ነገር ስለሆነባት ግራ በመጋባት ስትመለከታት፣ ኢትዮጵያዊቷ ‹‹እነሱ ፈታ ማለት ነው የሚፈልጉት፡፡ ምሽት ላይ አብረሻቸው መዝናናት ትችያለሽ?›› ትላታለች፡፡ ባልጠበቀችው ጥያቄ የተበሳጨችው ፍሬ፣ ሥራዋ አስጎብኚነት እንደሆነና ጥያቄያቸው የሙያውን ስም የሚያጎድፍ መሆኑን ትናገራለች፡፡

ኢትዮጵያዊቷ ፍሬን ተሰምቶ የማያውቅ አዲስ ነገር እንዳልጠየቋትና ነገሩን አክብዳ ማየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ለማስረዳት የሞከረችው በንዴት ተሞልታ ነበር፡፡ ዓረቦቹ ሌሎች አስጎብኚዎች እንድትጠቁማቸው እስከመጠየቅ ሁሉ ደፈሩ፡፡ ፍሬ ግን እነሱ የሚፈልጉትን የሚሠራ ሰው እንደማታውቅ ገልጻ ተለየቻቸው፡፡ ይኼ የአንድ ጊዜ አጋጣሚዋ ቢሆንም፣ ብዙ ሴት አስጎብኚዎች የዚህ ዓይነቱ ነገር ብዙ እንደሚያጋጥማቸው ታስረዳለች፡፡ ሥራ ለማግኘት ከሚገጥማቸው ውጣ ውረድ ጀምሮ፣ በሥራ ወቅት የሚደርሱባቸው ወሲባዊ ትንኰሳዎችና ስለ ሴት አስጎብኚዎች ያለው የተዛባ አመለካከት ይፈታተኗቸዋል፡፡

እሷ እንደምትለው፣ የሴት አስጎብኚዎች ፈተና የሚጀመረው በአስጎብኚ ድርጅቶች ለመቀጠር ከሚሞክሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ብዙ ጎብኚዎች ሴት አስጎብኚ ቢመርጡም ሴቶችን ለመቀጠር ፍቃደኛ የሆኑ አስጎብኚ ድርጅቶች  ጥቂት ናቸው፡፡ ሴት አስጎብኚዎች በሚያስጎበኙበት ወቅት በቱሪስቶች እንዲሁም በሥራቸው  በሚገጥሟቸው ሰዎች ወሲባዊ ትንኮሳ ሲደርስባቸው ይታያል፡፡

‹‹በእርግጥ ሴቶች በማንኛውም ሥራ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ፈተናዎቹን መወጣት አልችልም ብሎ ሥራውን ከመሥራት ወደኋላ ማለት ግን ችግሩን አይፈታም፤›› ትላለች፡፡

ሴት አስጎብኚዎች ከሙያው መውጣት እንዳይገደዱ ጥቃትና ትንኮሳዎች  እንዲቀሩ መሥራት ይገባል ትላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የሴት አስጎብኚዎች ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ትናገራለች፡፡ ሴት አስጎብኚዎች በመተባበር ችግሮቻቸው የሚፈቱበትን መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው ትገልጻለች፡፡

ሦስት ቋንቋዎች ስለምትችል ቱሪስቶችን ለማግኘት እንደማትቸገር ትናገራለች፡፡ ሌሎች ሴቶች አስጎብኚዎችም በቀላሉ ከሰው ጋር በማግባባትና ብዙ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ በመናገር ብቃቸው ብዙ ጎብኚዎች እንደሚመርጧቸው ትጠቁማለች፡፡ የጠቀሰቻቸው ችግሮች ቢቀረፉ በርካታ የሙያው ፍቅር ያላቸው ሴቶች ዘርፉን እንደሚቀላቀሉም ታምናለች፡፡

ሐሳቡን የምትጋራው አስጎብኚ ቤዛዊት ደነቀው እንደምትለው፣ የሴት አስጎብኚዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ማኅበረሰቡም ለሴት አስጎብኚዎች የተሳሳተ አመለካከት አለው፡፡ የቱር ኦፕሬሽን ሱፐርቪዥን ትምህርት ካጠናቀቀችበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ዓመት ገደማ በአስጎብኚነት እየሠራች ሲሆን፣ ችግሩ ማስጎብኘት ለሴት የሚሆን ሥራ አይደለም ከሚለው የተዛባ አመለካከት ይጀምራል ትላለች፡፡ በእርግጥ እንደ ኤርታሌ ያሉ አካባቢዎች ፈታኝ ሊሆኑ ቢችሉም፣ ሙያው ለሴትም ለወንድም እንደሚሆን መታወቅ አለበት ስትል ታስረዳለች፡፡

እሷ እንደምትለው ሴቶች ቱር ኦፕሬተር (አስተባባሪ) እንጂ አስጎብኚ ሆነው እንዳይሠሩ ጫና ሲደረግባቸው ይስተዋላል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ያለው አገልግሎት አሰጣጥና አቀባበል ሴት አስጎብኚዎችን ያማከለ መሆን አለበት፡፡ ‹‹አገሬን እወዳታለሁ፣ ስለአገሬ ብዙ ነገር ማወቅም እፈልጋለሁ፤ ሙያውን ስማረው ጀምሮ ፈተናዎች እንደሚገጥሙኝ ግን አውቅ ነበር፤›› ትላለች፡፡

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ቤቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች የሚሠሩ ባለሙያዎች ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና የመቅረፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው ታስረዳለች፡፡ ሁለቱ አስጎብኚዎች በአገሪቱ ካሉ ጥቂት ሴት አስጎብኚዎች መካከል ሲሆኑ፣ በሙያቸው የሚገጥሟቸው ውስብስብ ችግሮች ተፈተው ማየት ይሻሉ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬትም በችግሩ ዙሪያ ጥናት አሠርቶ፣ በዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተዘራ ማሞ ቀርቧል፡፡ ‹‹የሴት አስጎብኚዎች መልካም አጋጣሚና ተግዳሮቶች›› በሚል የተዘጋጀው ጥናት ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በራስ አምባ ሆቴል ቀርቦ ነበር፡፡ ሴት አስጎበኚዎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና የአስጎብኚዎች ማኅበራት በችግሮቹና የመፍትሄ ሐሳቦች ላይ ተወያይተዋል፡፡

እንደ አጥኚው ገለጻ፣ ሴት አስጎብኚዎች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል በአስጎብኚ ድርጅቶች መቀጠር መቻል ከባድ መሆን ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ አጥኚው ያነጋገራቸው አስጎብኚ ድርጅቶች ሴቶችን የመቅጠር ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ገበያው ላይ ሴት አስጎብኚዎች በብዛት እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡ የሴት አስጎብኚዎች አስተያየት ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በሙያው ሠልጥነው የወጡና የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ሴት አስጎብኚዎች  ቢኖሩም ሴት በመሆናቸው ብቻ ሥራ ለማግኘት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ አካላዊ ብቃት ማነስና ከቤተሰብ ወይም ከሌሎች አካሎች የሚደርስባቸው ጫና በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ነገር ግን በአስጎብኚ ድርጅት ተቀጥረው ወይም በግላቸው ለዓመታት ያስጎበኙ ሴቶች መኖራቸውም ሊታወስ ይገባል፡፡

ሌላው ጉዳይ ሴቶች በአስጎብኚነት እንዲሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች አለማበረታታቸው ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች አስጎብኚ በመሆን ያሉ ጥሩ የሥራ አማራጮችን በማስተዋወቅና ሴቶች በአስጎብኚነት እንዲሰማሩ ጥሪ በማድረግ ቢያነሳሷቸው መልካም ይሆናል፡፡ በአስጎብኚነት ከሚመረቁ ሴቶች መካከል በሙያው የሚዘልቁት ጥቂት የሆኑት ሙያው ፈታኝ በመሆኑ እንደሆነ ጥናቱ ያመለክታል፡፡ በዘርፉ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ያህል ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑንም እጥኚው ተናግሯል፡፡

የተለያዩ አገሮች ቱሪስቶች በሰጡት አስተያየት መሠረት፣ ሴት አስጎብኚዎች ተመራጭ ናቸው፡፡ ከቱሪስቶች ጋር በቀላሉ መግባባት እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ በቱሪዝሙ ዘርፍ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ስለሚያስፈልግ፣ በሚያስደስቷቸው አስጎብኚዎች ቢታገዙ የተሻለ እንደሚሆን በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

አጥኚው አቶ ተዘራ እንደሚናገረው፣ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ባሉ ሠራተኞችና በቱሪስቶችም ሴት አስጎብኚዎች ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ትንኰሳዎች ሥራውን ፈታኝ አድርገውታል፡፡ በማኅበረሰቡም ዘንድ ሴት አስጎብኚዎችን እንደ ባለሙያ ከማየት ይልቅ ሙያውን ያላግባብ ገንዘብ ለማግኘት እንደሚጠቀሙ ሰዎች የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ባለሙያዎች በእነዚህና ተያያዥ ችግሮች ተገፍተው ዘርፉን ትተው ሲወጡ የሙያውን መርህ የማይከተሉ ሰዎች የሚቀላቀሉት ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ አጥኚው፣ መንግሥት በአስጎብኚዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግና ለሴት አስጎብኚዎች ከለላ በመስጠት ረገድ ብዙ እንደሚጠበቅበት ይገልጻል፡፡

ለሴት አስጎብኚዎች የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖሩ በሙያው ያሉት እንዳይቆዩ ፍላጎቱ ያላቸውም እንዳይገቡ ማድረጉ፣ ከባለሙያዎቹ በተጨማሪ የአገሪቱን ቱሪዝም እንደሚጎዳ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ በዘርፉ ያሉ መንግሥታዊም ይሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች አስጎብኚነት ጾታን መሠረት ካደረገ መድልዎ የፀዳ ሥራ እንዲሆን ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ ሴት አስጎብኚዎች መካከል፣ ሴት አስጎብኚዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ማኅበር ቢመሠረት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለዋል፡፡ የሕግ ከለላ የሚያገኙችባቸው መንገዶች እንዲኖሩም ያግዛል ብለዋል፡፡ በዘርፉ ያሉ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ከመቅረፍ ጎን ለጎን የማኅበረሰቡ ግንዛቤ መለወጥ እንዳለበትም የገለጹ ሴት አስጎብኚዎች አሉ፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ቤቶች ሴት አስጎብኚዎችን ብቁ አድርገው ቢያሠለጥኑና ለሚገጥሟቸው ችግሮች ዝግጁ ቢያደርጓቸው፣ ችግሩ በመጠኑም ይቀንሳል የሚል ዕምነት ያላቸው አስጎብኚዎችም አሉ፡፡

በውይይቱ ላይ የአስጎብኚዎች የብቃትና የሥነ ምግባር ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በአስጎብኚዎችና ጎብኚዎች መካከል ያለው ግንኙት ያላግባብ ገንዘብ ማግኛ ሲሆን እየታየ፤ በሌላ በኩል ከጊዜ ወደጊዜ የወሲብ ቱሪዝም እየተስፋፋ እንደመጣ የተናገሩ አስጎብኚዎች ጉዳዩ ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳውቀዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገረው የአዲስ አበባ የግል አስጎብኚዎች ማኅበር ጸሐፊ አቶ በየነ አርዓያ፣ ሴት አስጎብኚዎች የሚላኩባቸው ቦታዎች የተመቻቹ መሆን እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ሙያው ለሴቶችም ለወንዶችም ፈታኝ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ገልጾ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ሥልጠና በመስጠት ለችግሮቹ ሊያዘጋጁዋቸው ይገባል ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...