Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክንግድን ያለንግድ ፈቃድ የማከናወን ልዩ መብት

ንግድን ያለንግድ ፈቃድ የማከናወን ልዩ መብት

ቀን:

ለዚህ ሳምንት በርዕስነት የተጠቀምንበት ‹‹ንግድን ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን›› እርስ በርሱ የሚጋጭና ትርጉም የሌለው ይመስላል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን ማንኛውም ሰው በንግድ ሥራ ለመሰማራት የንግድ ምዝገባና የንግድ ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ የንግድ ፈቃድ የማግኘት ውጤትም ፈቃድ የተወሰደበትን የንግድ ሥራ ለማከናወን መቻል ነው፡፡ የንግድ ፈቃድ ሳይኖር ወይም ሳይታደስ የንግድ ሥራ ማከናወንም እስከ 15 ዓመት ድረስ በሚደርስ እስራት ያስቀጣል፡፡ ይህ በሁሉም የታወቀና በሕግ የተደነገገ ነው፡፡ ከዚህ መነሻ አንፃር ንግድን ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡ ይሁንና አከራካሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ንግድን ያለንግድ ፈቃድ የማከናወን ልዩ መብት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት በአዋጅ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በየዓመቱ በሰኔ ወር መጀመሪያ የሚከበረውን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን ምክንያት በማድረግ በዚህ ጽሑፍ ማኅበራቱ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩ መብትና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ንግድ ያለንግድ ፈቃድ ስለሚከናወንበት ሁኔታ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠውን የመብቱን ምንነትና ወሰን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ልዩ መብት

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በፌዴራል ደረጃ በአዋጅ ቁጥር 147/1991፣ እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 402/1996 እና ደንብ ቁጥር 106/1996 መሠረት የተደራጁ ሲሆን፣ ክልሎችም ከፌዴራሎቹ ሕግጋት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አዋጆች ቀርጸዋል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 147/1991 መሠረት ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበር›› ማለት ‹‹ሰዎች በፈቃደኝነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት የሚያቋቁሙትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩት ማኅበር ነው›› የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሆነ ከንግድ ማኅበራት የሚለዩበት ዐቢይ ባህርይ የሚቋቋሙበት ዓላማ ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የመቋቋማቸው ዓላማ የአባላትን ተመሳሳይ ፍላጐት በአነስተኛ ወጪ ማሟላት እንጂ ለአባላት ትርፍ ለማስገኘት አይደለም፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 4 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚቋቋሙበትን ዓላማዎች የዘረዘረ ሲሆን፣ በዝርዝሩ ውስጥ ለአባላት ትርፍ ለማስገኘት በሚያስችል ሥራ እንደሚሳተፉ አይገልጽም፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 35 አንድ ማኅበር ለአባላት ወይም በዚህ አዋጅ መሠረት ለተቋቋመ ሌላ ማኅበር ካልሆነ በቀር ብድር መስጠት እንደማይችል መደንገጉም ለዚህ ነው፡፡ በተግባር ግን አንዳንድ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአባሎቻቸው ከሚሰጡት አገልግሎት ባለፈ አባል ላልሆኑ ግለሰቦች ጋር የንግድ ልውውጥ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ የተወሰኑ ማኅበራት ደግሞ በብዙ ካፒታል የሚንቀሳቀሱ፣ ሰፊ የንግድ ሥራ የሚያከናውኑና ከአባላታቸው ውጭ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጭምር አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ ማኅበራቱ ከሌሎች የንግድ ማኅበራት ጋር ያላቸው ልዩነት የሚጠበውና የንግድ ፈቃድ አስፈላጊነት ወይም ፈቃድ ያለማውጣት ልዩ መብት የሚያከራክረው በዚህ ዐውድ ነው፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያላቸው ልዩ መብቶች በአዋጁና በማሻሻያው የተዘረዘሩ ሲሆን፣ በማሻሻያው አንቀጽ 6 ከተጨመሩ ልዩ መብቶች /Privileges/ አንዱ ማኅበራት የንግድ ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው በማንኛውም የንግድ ሥራ ላይ መሰማራት የመቻላቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የንግድ ፈቃዱ ልዩ መብት አከራካሪነቱ በሁለት መልኩ ነው፡፡ በአንድ በኩል መብቱ ንግድን ያለንግድ ፈቃድ ለማከናወን የሚፈቅድ በመሆኑና ማኅበራቱ ከሚሠሩት ሥራ ውጭ ባሉም የንግድ ሥራዎች ተፈጻሚ ስለሚሆን የንግድ ውድድርን ትርጉም ያሳጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበራቱም ከተቋቋሙበት ዓላማና ከመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መርሆች እንዲወጡ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል፡፡

የዚህ ልዩ መብት አከራካሪነት ጡዘት የደረሰው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 6(1) ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሳይመዘገብ ማናቸውም የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ ሥራ መሥራት አይችልም፡፡››፣ በአንቀጽ 31(1) ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው የጸና የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው የንግድ ሥራ መሥራት አይችልም፡፡” በአንቀጽ 42 ‹‹ተገቢው የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖረው በሌላ ዓይነት ፈቃድ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆንበትን የንግድ ሥራ ሲያካሂድ የነበረ ማንኛውም ሰው ይህንኑ ሥራ ለማካሄድ ይህ አዋጅ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በ12 ወራት ውስጥ አግባብ ያለውን ቅጽ ሞልቶ ማመልከቻ በማቅረብ ተገቢውን የንግድ ሥራ ፈቃድ ማውጣት አለበት፡፡›› በሚል ከመደንገጉ በተጨማሪ በአንቀጽ 63(2) ማንኛውም ሌላ ሕግ ከአዋጁ ጋር የሚቃረን ሆኖ ከተገኘ ተፈጻሚ እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለንግድ ፈቃድ ንግድ እንዲያከናውኑ የሚፈቅደው የአዋጅ ቁጥር 402/1996 ዕጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ በጊዜ ቅደም ተከተል በቅርብ የወጣ በመሆኑና በድንጋጌው ያለንግድ ፈቃድ ንግድ ማከናወን ስለሚከለክል የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ልዩ ጥቅም ተሽሯል ይላሉ፡፡ ሌሎች በተቃራኒ ደግሞ ይህንን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን የማይመለከት በመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 402/92 ‹‹ን›› ተፈጻሚነት አይከለክልም ይላሉ፡፡ ይህ የግራ ቀኝ ሙግት አካዳሚያዊ ቢመስልም በተግባርም የኀብረት ሥራ ማኅበራቱ የንግድ ሥራ ሲያከናውኑ የሚያጋጥማቸው ዐቢይ ተግዳሮት መሆኑን የፍርድ ቤቶቻችንን መዛግብት ስናገላብጥ እንገነዘባለን፡፡ ለዚህ ዐቢይ ማሳያ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ሰበር የደረሰና ሰበር ችሎቱ በቅጽ 18 ካካተታቸው ፍርዶች በሰበር መዝገብ ቁጥር 103717 ሐምሌ 03 ቀን 2007 ዓ.ም. የተሰጠው ገዥ የሕግ ትርጉም ይጠቀሳል፡፡ በሚከተለው የጽሑፉ ክፍል በአጭሩ ጉዳዩን ገልጸን ምልከታ እናድርግበት፡፡

የሰበር ችሎት አቋም

የወንጅ ስኳር ፋብሪካ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሕግ ሰውነት አግኝቶ አባላቱንና የአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ያገለግላል፡፡ በወንጂ አካባቢ ወፍጮ ቤትና ዳቦ ቤት ከፍቶ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የአዳማ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ይህ የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ሥራ ያለንግድ ፈቃድ መሠራቱ አልተመቸውም፡፡ እናም ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. አቶ ዘላለም ታዬ፣ ወ/ሮ በድርያ ሁሴንና አቶ ዮናስ አስፋው የተባሉ ሠራተኞቹን ልኮ የንግድ ቤቶቹ እንዲታሸጉ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ማኅበሩ በአዳማ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤትና በሠራተኞቹ ላይ ክስ ያቀርባል፡፡ ማኅበሩ በጠየቀው ዳኝነት ያለንግድ ፈቃድ የንግድ ሥራ የማከናወን መብት በአዋጅ ተሰጥቶት እያለ የወፍጮና የዳቦ ቤቴን በማሸጋቸው ሱቆቹን እንዲከፍቱ፣ ለደረሰብን ጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ የሚል ነው፡፡

 ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት በሰጠው የመከላከያ መልስ ማኅበሩ በአዋጅ ቁጥር 147/91 የተቋቋመ ቢሆንም ከዚህ አዋጅ በኋላ የወጣው አዋጅ ቁጥር 686/02 ማንኛውም የንግድ ሥራ የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገው መሆኑን በመደንገጉና ተጠሪ የማስፈጸም ግዴታ ስላለበት ያለ ንግድ ፈቃድ ማኅበሩ የሚያንቀሳቅሳቸውን የወፍጮ ቤትና የዳቦ ቤት ማሸጌ ተገቢ ነው የሚል ክርክር አቅርቧል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት በግራ ቀኙ መካከል የተደረገውን ክርክር መርምሮ ግለሰብ ተጠሪዎቹን ከክሱ እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ከሕግ አወጣጥ የጊዜ ቅደም ተከተል አንፃር በቅርብ የወጣው አዋጅ ቁጥር 686/2002 ሲሆን፣ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 31/2/ እና 42 ላይ ማንኛውም የንግድ ሥራ የሚሠራው በንግድ ፈቃድ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህ አዋጅ ከአዋጅ ቁጥር 147/91 በአዋጅ ቁጥር 402/96 እንደተሻሻለው ይልቅ አዲስ በመሆኑና የበላይ ተፈጻሚነት ያለው ስለሆነ ማኅበሩ ያለንግድ ፈቃድ ንግድ ሲያከናውን መገኘቱ ሕገወጥ ነው በማለት ማኅበሩ ላይ ፈርዷል፡፡

ይግባኝ የቀረበለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የኦሮሚያ ሰበር ችሎት የሥር ፍርድ ቤትን አቋም በመያዝ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ንግድን ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን አይችሉም ሲሉ ፍርድ ሰጥተዋል፡፡

 ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተያዘውን አቋም ሽሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅንና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅን ዓላማ ከተነተነ በኋላ ማኅበራት በመሠረታዊነት ለትርፍ ተብሎ የሚቋቋሙ ሳይሆን የአባላታቸውን ፍላጎት በአነስተኛ ወጪ ለማሟላት የሚቋቋሙ በመሆኑ ለትርፍ ሥራ የሚሠሩ የንግድ ሥራዎች የሚያስፈልጋቸውን የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ የሚገደዱበት የሕግ አግባብ የለም ሲል ፈርዷል፡፡ ሰበር ችሎቱ የአዋጅ ቁጥር 402/96 አንቀጽ 6 የኅብረት ሥራ ማኅበራት የንግድ ፈቃድ እንደማያስፈልጋቸው በግልጽ መደንገጉን አስታውሶ የአዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 31 እና 42 ድንጋጌዎች ከማኅበራቱ መሠረታዊ ዓላማና ባህርይ አዋጁ ሊያሳካው ካሰበው ግብ አንፃር ሊታይ ሲገባ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ አዋጆቹ የወጡበትን የጊዜ ቅደም ተከተል ብቻ መሠረት አድርገው ለማኅበራት የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ መጠየቃቸው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው ሲል ገልጿል፡፡

በጭብጡ ላይ  ምልከታ

በሰበር ፍርዱ የታየው ዋና ጭብጥ ቀደም ብለን ስለ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልዩ ጥቅም በተለይ ማኅበራቱ ንግድ ያለንግድ ፈቃድ መከናወን ስለመቻል አለመቻላቸው ነው፡፡ እንደ ጸሐፊው እምነት ማኀበራቱ ያለ ንግድ ፈቃድ እንዲነግዱ የሚፈቅደው አዋጅ ቁጥር 402/96 እና ማንኛውም ሰው ያለንግድ ፈቃድ ንግድ እንዳያከናውን በሚከለክለው አዋጅ ቁጥር 686/2002 መካከል ተቃርኖ አለ፡፡ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ይህ የሕግ ተቃርኖ ሕግጋቱ የወጡበትን የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት በማድረግ የሚደግፋቸውንም ድንጋጌዎች ከንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ ላይ በመጥቀስ ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ በጊዜ ቅደም ተከተል በቅርብ ጊዜ የወጣው የንግድ ምዝገባ አዋጅ ንግድን ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን በመከልከሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከአምስት ዓመት በፊት በአዋጅ ቁጥር 402/96 ያገኙትን መብት ሽሮታል የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጆቹ መካከል ተቃርኖ መኖር አለመኖሩን በውስጥ ታዋቂነት ካልሆነ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ የሰበር አቋም የንግድ ምዝገባ አዋጁ ከማኅበራት መሠረታዊ ዓላማና ባህርይ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ በማኅበራት ላይ ተፈጻሚ አይሆንም የሚል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአባሎቻቸውን መሠረታዊ ችግር በአነስተኛ ወጪ ለመቅረፍ የሚቋቋሙ በመሆኑ በንግድ ሥራ ቢሰማሩ እንኳን መሠረታዊ ዓላማቸው ትርፍ ማትረፍ ሳይሆን የአባላቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር መቅረፍ በመሆኑ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ ሊጠየቁ አይገባም ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሰበር ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቶች ከጊዜ ቅደም ተከተል አንፃር የአዋጆቹ ተቃርኖ መፍትሔ ማግኘት አለበት የሚለውን አቋም ቅቡል የሚያደርጉትን ምክንያቶች ሲጠቁም አናስተውልም፡፡ ሕግጋት በተቃረኑ ጊዜ መፍትሔ የሚገኘው ሕግጋቱን በመተርጎም በመሆኑ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ከጊዜ አንፃር ሕግጋት ሊተረጎሙ ይገባል የሚለውን አቋም የወሰዱ ሲሆን፣ የሰበር ችሎቱ ለአቋሙ መነሻ ያደረገውን መርህ በፍርዱ ላይ በግልጽ አላመለከተም፡፡ ከፍርዱ ሃተታ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ግን ሰበር ችሎቱ ከሕግጋቱ ጀርባ ያለውን የሕግ አውጭውን መንፈስ በመመርመር ሕግ አውጭው ለትርፍ ዓላማ ያልተቋቋሙትን ማኅበራት የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ የማስገደድ ዓላማ የለውም ማለት ይቻላል የሚል ነው፡፡ ለፀሐፊው ሰበር ችሎቱ የደረሰበት መደምደሚያ አሳማኝ ቢሆንም የሰጠው የሕግ ትንተናና ለፍርዱ መሠረት ያደረገው የአተረጓጎም መርህ አሳማኝ አይመስልም፡፡

የሕግጋቱ ተቃርኖ ሊፈታ የሚችልበት ሁኔታና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ንግድ ያለንግድ ፈቃድ ሊያከናውኑ ስለመቻል አለመቻላቸውን ጸሐፊው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ሁለት የሕግ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡ ሁለቱ ምሁራን የያዙት አቋም ልዩነት በጉዳዩ ላይ የሰበር ችሎቱ የያዘው አቋም ለክርክር የተጋለጠ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጴጥሮስ ከኅብረት ሥራ ማኅበራቱ አዋጅ ይልቅ ለንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ወግነው ይከራከራሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አስተሳሰብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ በጊዜ ቅደም ተከተል በቅርብ የወጣ ሲሆን፣ አገሪቱ የምትከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊስ መሠረት አድርጎ የወጣ የንግድ አሠራርን ወጥ ለማድረግና ሥርዓት ለማስያዝ ያለመ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ይላሉ አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ አዋጁ ንግድን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የቅድሚያ ተፈጻሚነት አለው፣ በይዘቱ ምንም ዓይነት ልዩ ሁኔታ ያላስቀመጠ በመሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም የንግድ ሥራ እስከ ሠሩ ድረስ ፈቃድ የማያወጡበት አሳማኝ የሕግ ምክንያት የለም ይላሉ፡፡ ‹‹የንግድ ሥራ ለማከናወን የንግድ ፈቃድ አስፈላጊ ነው አይደለም የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ›› ይላሉ አቶ ፈቃዱ ‹‹የንግድ ፈቃድ ያስፈልጋል በሚል አዋጁ ከወጣ በኋላ በሁሉም ሰው ላይ ተፈጻሚ መሆኑ አከራካሪ አይደለም›› ሕጉ ልዩ ሁኔታ ያደርጋል ከተባለም የልዩ ሁኔታው ምንጭ ካፒታልን መሠረት ያደረገ አነስተኛ ነጋዴዎችን (Petty traders) የሚጠብቅ መሆን ይገባዋል በሚል የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ንግድ ያለንግድ ፈቃድ መሥራታቸውን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ፡፡

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁር ዶ/ር ምስጋናው ክፈለው ግን የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ዓላማ፣ ባህርይና ተግባራዊ ፋይዳ በመተንተን ንግድ ያለንግድ ፈቃድ ሊሠሩ እንደሚገባቸው ይተነትናሉ፡፡ ዶ/ር ምሥጋናው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአባላቶቻቸው ፍላጎት የተቋቋሙና ምንም ዓይነት ትርፍ ለማግኘት ዓላማ የሌላቸው በመሆናቸው በመርህ ደረጃ ከንግድ ሕግ ማዕቀፍ ውጭ ናቸው ይላሉ፡፡ ሁለቱን ሕግጋት ተቃርኖ በተመለከተ ዶ/ር ምስጋናው ሲገልጹ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ለማኅበራቱ ያለንግድ ፈቃድ ንግድ እንዲያከናውኑ ልዩ መብት የሚሰጥ በመሆኑ ቅድሚያ ተፈጻሚነት ያለው ልዩ ሕግ ነው ይላሉ፡፡

ማኅበራቱ ንግድ ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን ስለመቻል አለመቻላቸው የሚነሳው ክርክር መገለጫ የሁለቱ ምሁራን አቋም ቢሆንም ጉዳዩ በሕግ አውጭው አካል ተገቢ ትኩረት እንዳልተሰጠው ግልጽ ነው፡፡ ሕግ አውጭው የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ልዩ መብት በአዲሱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ላይ በልዩ ሁኔታ ቢደነግገው ወይም እነሱንም እንደሚጨመር ቢገልጽ ኖሮ ችግሩን ከምንጩ ባደረቀው ነበር፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድ የጥሩ ሕግ አወጣጥ ባህርይ ነው፤ ሕጉ ምሉዕና ቀደም ሲል የተሰጡ መብቶችን ያገናዘበ በሆነ ነበር፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ሁለቱ አዋጆች መቃረናቸው ያልተከደነ ሐቅ ነው፡፡ ሁለቱ አዋጆች ይቃረናሉ ካልን ደግሞ ተቃርኖውን በጊዜ ሒደት ወይም በሚሸፍኑት ጉዳይ ባህርይ በመተርጎም ተቃርኖውን ልንፈታው ይገባል፡፡ በተያዘው ጉዳይ የአዋጆቹ ልዩ ይዘትን መመርመር የወጡበትን የጊዜ ቅደም ተከተል ከመተንተን ሊቀድም ይገባል፡፡ አዋጅ ቁጥር 402/96 የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኢትዮጵያ ሕግ ያላቸውን ልዩ መብቶች (Privileges) የሚዘረዝር በመሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በተመለከተ ልዩ ሕግ ነው፡፡ ከእነዚህ ልዩ መብቶች አንዱ ንግድ ያለንግድ ፈቃድ ማከናወን በመፍቀዱ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ልዩ መርህ አስቀምጧል፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ሲወጣ ከአምስት ዓመት በፊት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሰጠውን ልዩ ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ የወጣ በመሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱን የንግድ አሠራር በተመለከተ በአዋጅ ለማካተት የሕግ አውጭው አልፈለገም፡፡ ስለሆነም ከኅብረት ሥራ ማኅበራት አንፃር አዋጅ ቁጥር 402/96 ከአዋጅ ቁጥር 686/2002 ይልቅ ልዩ (Specific) ሕግ በመሆኑ የሰበር ችሎቱ ማኅበራቱ ንግድ ያለንግድ ፈቃድ እንዲያከናውኑ መፍቀዱ በውጤት ደረጃ ትክክል መሆኑን ጸሐፊው ያምናል፡፡ ልዩ ሕግ ከጠቅላላ ሕግ ተቀዳሚ ተፈጻሚነት ስለሚኖረው፡፡ ሰበር ችሎቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ለአባላቶቻቸው ጥቅም እንጂ ለትርፍ አልተቋቋሙም የሚለውን መርህ መነሻ ማድረጉ ግን በጥሞና ለመረመረው ረዥም መንገድ ላያስኬድ ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት አተረጓጎም አሁን በተግባር ከአባላታቸው ማኅበራዊ ጥቅም ባለፈ እንደማንኛውም የንግድ ተቋም ለማትረፍ ብቻ የሚያልሙ፣ ብዙ ሚሊዮን ካፒታል ያላቸውን፣ በተግባር ነጋዴዎችን የሚገዳደሩ ማኅበራትን በኅብረት ሥራ ማኅበራት ዓላማ መጠበቅ ሳያሰቸግር አይቀርም፡፡ እንደ ፀሐፊው እምነት የሕግ አውጭው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ ሲረቀቅ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ትዝ ብለውት ቢሆን ኖሮ አሁን በተግባር የተንሰራፉትን ነጋዴ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ንግድ ያለንግድ ፈቃድ እንዲያከናውኑ ባልፈቀደላቸውም ነበር፡፡         

 አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ