Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየመድብለ ፓርቲና የአውራ ፓርቲነት በምርጫ ፖለቲካ

የመድብለ ፓርቲና የአውራ ፓርቲነት በምርጫ ፖለቲካ

ቀን:

በሒሩት ዲባባ

ዛሬ ስለምርጫ፤ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና አውራ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ልንነጋገር ወደድን፡፡ እርግጥ ይህን ጉዳይ በዚህ ወቅት ማንሳታችን ተጋግሎ ስለሰነበተው የአሜሪካው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማውራት አይደለም፡፡ ይልቁንም በእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፉን ተሞክሮ በመዳሰስ የአገራችንን ሁኔታ ለማየት ነው፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ሕዝብ እንደመሆኑ የመንግሥትነት ኃላፊነት የሚረከበው አካልም በሕዝብ የተመረጠ መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም በየአምስት ዓመቱ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ይሁንና በምርጫው ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ፍትኃዊና ዴሞክራሲያዊነት ላይ የሚነሡ የተለያዩ እንከኖች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ በአሳታፊነት መሥፈርት ሲመዘን ግን አመርቂ ገጽታ ያለው ነው፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ በመራጭነት የሚመዘገቡ ዜጎች ብዛትና ስብጥር ብቻ ሳይሆን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዛትም (ምንም እንኳን ተዋህደው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ባለመቻላቸው ቢተቹም) የበዛ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አሠርት በተካሄዱ ምርጫዎች የሚጠቀሰው እንከን ግን ገዥው ፓርቲ የመንግሥትን መዋቅር፣ መገናኛ ብዙኃንና የፀጥታ ኃይል ተጠቅሞ የፖለቲካ ምኅዳሩን ሲያጠብ ተቃዋሚዎች በነፃ የመደራጀት፣ የመቀስቀስና የመንቀሳቀስ መብታቸው ይገደባል መባሉ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለውን ሁኔታ መዳሰስ ተገቢ ይሆናል፡፡

መድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለን?

በኢትዮጵያ ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በቀዳሚነት ሕገ መንግሥቱ የመደራጀት፣ የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የተቃውሞና ድጋፍ ሠልፍ ማድረግን ፈቅዷል፡፡ ምንም እንኳን አፈጻጸም ላይ ያሉት እንቅፋቶች ቀላል ባይሆኑም፡፡

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ማለት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በአገራዊ ምርጫ ለሥልጣን የሚወዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡ በተናጠል ወይም በጥምር ደረጃ የሕዝብ ሥልጣን ፓርቲዎች የሚረከቡበት ሒደትም ነው፡፡ ለአብነት ያህል በጀርመን ከ2013 ምርጫ በኋላ በክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን እና በሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተፈጠረው ጥምረት ዓይነት ነው፡፡

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የእነአሜሪካን ከመሰለው ፕሬዚዳንታዊ ይልቅ በፓርላሜንታዊ ሥርዓቶች የተሻለ ዕድል እንዳለው ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ በሕግ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ሳይሸራርፉ በኃላፊነት ስሜት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከተቻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በታይዋን፣ በፊሊፒንስ፣ በስፔን፣ በብራዚል፣ በጀርመን፣ በአየርላንድ፣ በህንድ፣ በእስራኤል፣ በጣሊያን፣ በሜክሲኮ፣ በኖርዌይ፣ በፓኪስታንና በዴንማርክ ባሉት አገሮች ያለው ተሞክሮ ይኼውና ይኼው ብቻ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ፓርላሜንታዊ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አራማጅ አገሮች ያለው የምርጫ ፉክክር ግን ከአምስት በአነሱ የፖለቲካ ማኅበራት የሚፈፀም ነው፡፡ በፓርቲዎቹ መካከል ያለው የፖለቲካ ፍልስፍና ልዩነትም ግልጽና የማያሻማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ገጽታንም የተላበሰ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ወደርና አቻ ያለው አይደለም፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የተባሉ የፍልስፍና ምሁር በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ ‹‹በምርጫ ወቅት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ገቢ መሰብሰበያ ፓርቲ ከሚመሠረቱ ተለጣፊ ድርጅቶች እስከ ግልጽ ፖሊሲና የፖለቲካ ልዩነት ማሳያ አልባ የብሔር ፓርቲዎች ድረስ እንደ አሸን የፈሉባት አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡››

ይህ አባባል እውነት አይደለም ብሎ መከራከር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በየአምስት ዓመቱ ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ድርጅቶች ‹‹ፓርቲ›› ተብለው አባላትና ደጋፊዎቻቸው ሳይታወቁ፣ ግልጽ ስያሜያቸውና የፖሊሲ አማራጮቻቸው እንኳን ሳይታወቁ በምርጫው ይወዳደራሉ፡፡ ይኼ ደግሞ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካን ከማሳደግ ይልቅ የገዥውን ፓርቲ አውራነት የሚያጠናክርና ዴሞክራሲ ባህሉን የማይገነባ ነው፡፡

ሌላው የአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንቅፋት የሐሳብና የአመለካከት ነፃነትን ለማጎልበት የሚያስችል የመገናኛ ብዙኃን አሠራር አለመጠናከሩ ነው፡፡ በሐሳብ ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ተፎካካሪነትን የሚያበረታታ ዝንባሌ ተቀዛቅዟል፡፡ ጫፍና ጫፍ ላይ በቆሙ ፅንፈኛ አካሄድ ሊመጣ የሚችል ሥር ነቀል ለውጥ አይኖርም፡፡

ከሁሉ በላይ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቴ›› እያለ ሳያፈገፍግና ሲሸሽ በኖረ ማኅበረሰብ ውስጥ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት መታማት የሚያስፈራ መሆኑ አይቀርም፡፡ በእርግጥም ያስፈራል፡፡ ዛሬ ዛሬ እንኳንስ የፖለቲካ ተወዳዳሪነት ካባ ለብሶ ይቅርና ገዥው ፓርቲ ላይ ከረር ያለ ትችት መሰንዘር የሚያስነጥል ሆኗል፡፡ አንድ ጊዜ የተቃውሞውን ጎራ የተቀላቀለው ኃይልም ቢሆን በመስዋዕትነት እየተሽሎከለከ መንቀሳቀሱ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ውስጥ ትልቅ ጋሬጣ መደቀኑን ያመላክታል፡፡

አውራ ፓርቲነት ብቻ ነውን?

ኢሕአዴግ ባለፉት አምስት ብሔራዊ ምርጫ በተከታታይ እያሸነፈ ሥልጣን በመያዙም ሆነ ሲያሸንፍም እስከ 100 በመቶ ወንበር ጠቅሎ (ከነአጋር ፓርቲዎቹ) በመያዙ ‹‹አውራ ፓርቲ ነኝ›› እንዲል አድርጎታል፡፡ እርግጥ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በሌሎች አገሮችም ያጋጥማል፡፡

የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ከ1994 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተደጋጋሚ እየተመረጠ አገሪቱን የሚያስተዳድር አውራ ፓርቲ ነው፡፡ ሰሜናዊ አየርላንድ ከ1921 እስከ 1972 ድረስ (ለ51 ዓመታት) የተሠራችው በኦል ስታር ዩኒየኒስቲ ፓርቲ አውራነት ነበር፡፡ በጃፓን፣ በጀርመን፣ በታይዋንና በሌሎችም አገሮች እንዲህ ዓይነት ልማዶች አሉ፡፡

በእነዚህ ሁሉም አገሮች ያሉ ‹‹አውራ›› የሚባሉ ፓርቲዎች ግን ከኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ የሚለዩበት አንዳንድ መገለጫዎች አሉ፡፡ አንደኛው በምንም መንገድ ከሞላ ጎደል ‹‹በሙሉ›› ሊባል በሚችል ደረጃ የፓርላማ ወንበሮችንና የክልል ምክር ቤቶችን ጠቅለው ሊይዙ አይችሉም፡፡ ይህ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊና ፍላጎታዊ ልዩነት በሞላበት ዓለም ፍፁም ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡

ለአብነት ያህል በደቡብ አፍሪካ ገዥው ፓርቲ ለተከታታይ ዓመታት ሥልጣን ላይ ቢቆይም፣ በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ ጥያቄ እያነሱ በፓርላማ የሚገዳደሩት አዳዲስ ፓርቲዎች ሳይቀር አሉ፡፡ ኤኤንሲ ከነፕሬዚዳንቱ ጀምሮ እየደረሰበት ያለው የሙስና ወንጀልና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊት ወደ ሽማግሌ ፓርቲነት እያወረደው የመጣው የተገዳዳሪው ኃይል ድምፅ ተደማጭ እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡

ሌላው የአውራ ፓርቲ ባለባቸው አገር ያለው መልካም ተሞክሮ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ አመቺ የሆነው የምህዳር ጉዳይ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ እንቅስቃሴ እንደማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሁሉ ገደብ የተጣለበት ነው፡፡ (ለምሳሌ ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ፣ መከላከያና ፖሊስ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍላጎትም ውጭ በሆነ መንገድ 1ለ5 የሚባል ‹‹ጥርነፋ›› አይኖርም) በሌላ በኩል ሌሎቹ የፖለቲካ ኃይሎችም የመደራጀት፣ የመቀስቀስና የመንቀሳቀስ መብት ጥበቃና ዋስትና ያገኘ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች እየተቃኑ፤ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትም በገለልተኝነትና በእኩልነት ማስተናገድ ከቻሉ ግን አውራ ፓርቲ መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትንም ሊያውክ አይችልም፡፡ በመሠረቱ አውራ ፓርቲ ማለት የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ማለት አይደለም፡፡ እነ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ሰሜን ኮርያ ያሉበት የአንድ ፓርቲ አልፋና ኦሜጋነት ነው የአንድ ፓርቲ ሥርዓት የሚባለው፡፡ ስለዚህ በአውራ ፓርቲ ስም ወደ እነዚህ ወደለየላቸው አገሮች የዴሞክራሲ ጨለማ እንውረድ ካልተባለ በስተቀር በአውራ ፓርቲ ስም መድብለ ፓርቲን ለመደፍጠጥ አይቻልም፤ አይገባም፡፡

የምርጫ ፖለቲካ ፋይዳ ምንድነው?

የሰው ልጅ ፍላጎት አማራጭን ግድ ማለቱ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለው ተለዋዋጭ ዓለም ደግሞ ካለምርጫ ሊቆም አይችልም፡፡ በፖለቲካው ዓለም ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው ውድድርም ሆነ ሕዝቡ የፈቀደውን የመምረጥ መብት የሚታየው ከዚሁ አንፃር ነው፡፡

በመሠረቱ የዴሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ መኖር ፋይዳው ድርብርብ ነው፡፡ በአንድ በኩል ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሰዎች በሕዝብ ለመመረጥ ሲሉ በሀቀኝነት፣ ፍትኃዊነትና ከሙስና በፀዳ መንገድ ሕዝብ ለማገልገል ይዘጋጃሉ፡፡ ተጠያቂነትም ስላለባቸው ሕዝብ ፈርቷቸው ሳይሆን ሕዝብን እንደፈሩ ይኖራሉ፤ ያስተዳድራሉ፡፡

በሌላ መልኩ ሕዝቡ በነፃነትና በአብላጫ ድምፅ የመረጠው አካል ወደ ሥልጣን ሲመጣ በከፍተኛ ደረጃ የእኔነት ስሜት ይፈጠራል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነትም ይበልጡኑ ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ የአብላጫው ብቻ ሳይሆን የንዑሳን (አነሳው) ድምፅ የሚደመጥበት ሥርዓት ከመጎልበቱ ባሻገርም ኢ ዴሞክራሲያዊና ፀረ ሰላማዊ መንገድን ለመከተል ለሚሹ ኃይሎች ሁሉ በሩ ይዘጋባቸዋል፡፡

በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥልጣንና ፖለቲካ የሚራመድ ማኅበረሰብ ከማንኛውም በጭቆናና ከፊል አፈና ውስጥ ካለ ማኅበረሰብ በተሻለ ነፃ፣ አምራችና ውጤታማ ነው፡፡ በብዙዎቹ የዓለም አገሮች እንደሚታየው የዜጎች በነፃ የማሰብ፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብት ከምርጫ ፖለቲካ ውጭ ሊታይ አይችልም፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የትውልድ ቅብብሎሽን ያስቀጠሉ አገሮችም የመፍረስና የመንሸራተት አደጋ ሊያጋጥማቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም አንዱ በሌላው ላይ እየደመረ፤ ተጨማሪ ውጤትን ነው እያስቀጠሉ ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዕድልን ማስፈን ከዴሞክራሲ ባህል ግንባታው ተነጥሎ አይታይም፡፡ የተጀመረውን የአገሪቱ የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ እንደማስቀጠልም ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ስለሆነም ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ዘውጎችን የማጠናከርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያብቡ የማድረግ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ያሻል፡፡ የማኅበራትና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት፣ የፍርድ ቤቶች፣ ምርጫ ቦርድ፣ እንባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ተቋማት ገለልተኝነትና ነፃነት እንዲሁም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ በማያሻማ መንገድ ሊጠናከር ግድ ይላል፡፡

እዚህ ላይ ወደ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብቻ የማይወረወሩ ተግባራትም አሉ፡፡ አንደኛው የአገሪቱ ምሁራን የፖለቲካ ኃይሎችና ካፒታሊስቶች በዚች አገር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል እንዲጠናከር ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ላብ አደሮች፣ አርሶ አደሮችና ልዩ ልዩ ማኅበራትም እንዲሁ ይህ ማለት ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ እየመሠረተ ይወዳደራል ማለት አይደለም፡፡

ይልቁንም የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ፣ ምርጫን የመሰሉ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች በተቀመጠው ዓለም አቀፍ መለኪያ መሠረት እንዲፈጸሙ የወጡ ዓለም አቀፍና የአገሪቱ ሕጎች እንዲከበሩ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ አሸን እየፈሉ የመጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የአካዳሚክ ነፃነታቸውን ጠብቀው የዴሞክራሲ ‹‹ዲስኮርስ›› ሊጀምሩ ግድ ነው፡፡ ለመሆኑ ከአሁኑ ውይይት፣ ምክክርና ክርክር ካልተጀመረ የትኛውን አገር ተረካቢ ለመፍጠር ይቻላልና ነው ‹‹አውቆ›› የተተኛው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ንቃት ያዳብሩ ሲባል እንደ ቀደመው ትውልድ ነውጥና ሁከትን ይፍጠሩ ማለት አይደለም፡፡ ወይም ሕንፃ ማቃጠልና ማፍረስን ይፈጽሙ ማለት አይደለም፡፡

ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች መሠረት ሐሳብን የመግለጽ፣ ዓለም አቀፍ ልምዶችን የማዳበር፣ የእኛን አገር የታሪክ ድክመት ጥንካሬዎችን መፈተሽ፣ የዛሬውን ብርቱና ደካማ ሁኔታዎችን መበርበር አለባቸው፡፡ ብሎም ለብሔራዊ መግባባት የግድ አስፈላጊ በሚባሉ ጉዳዮች እየተቀራረቡ መሥራት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ማጠናከር ይጠበቃል፡፡ ይህን ማመቻቸት ደግሞ በዋናነት የየተቋማቱና የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡

ሲጠቃለል የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚያቆጠቁጥበትም፤ የሚጨነግፍበትም ዕድል ከፊታችን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ሁሉም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ማጠናከር ከቻለ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወዳለቀ ደረጃ ያድጋል፡፡ በአውራ ፓርቲ ስም ፈላጭ ቆራጭ የሆነ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት አየሩን እንዲሞላው ከለቀቅነው ግን ቀስ በቀስ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ መጨንገፉ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...