Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ወረገኑ አካባቢ ይኼ ሁሉ ቤት ሲሠራና ይኼ ሁሉ ሰው ሲሰፍር የወረዳው መዋቅር የት ነበር? የሚለውን በዝርዝር ይታያል››

  ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሰሞኑን መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ በዚህ ስብሰባ ከንቲባ ድሪባ፣ የአስተዳደሩን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ የምክር ቤት አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ 138 አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ላነሳቸው ጥያቄዎች የቢሮ ኃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ከንቲባ ድሪባም በቂ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ባሏቸው ነጥቦች ላይ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡ በወቅቱ የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል የጤና ዋስትና የተሰጣቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ አለመሆናቸው፣ የግል ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆናቸው፣ የመሬት ባለቤትነት አሠራር መዘበራረቅና የጠፉ የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ወቅታዊ ሁኔታ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከንቲባ ድሪባ ለምክር ቤቱ የሰጡትን ማብራሪያ ውድነህ ዘነበ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

   

  ጥያቄ፡- የነፃ ሕክምናና መንግሥት ከሚያቀርበው መድኃኒት የመጠቀም መብት ያላቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ አይደሉም፡፡ በዘርፉ አድሎአዊ አሠራር እየታየ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

  ከንቲባ ድሪባ፡- በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የከፋ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የለም፡፡ መድኃኒት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ነው፡፡ ችግሩ የሚቀርበው መድኃኒት በተለያየ መንገድ በተለይ በጤና ጣቢያዎች፣ በሆስፒታሎች፣ በፋርማሲዎች ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ሳይገባ ዜጎች በአግባቡ የሚጠቀሙበት የአሠራር ስልት የመዘርጋትና የመከታተል ችግር ነው፡፡ ለነገሩ ተቆጣጣሪው አካል የመድኃኒትና ምግብ አስተዳደር ባለሥልጣን አለ፡፡ ይህ ተቋም በምን ደረጃ ነው ይህንን ችግር እየፈታ ያለው? የሚለው በትኩረት መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት እነዚህን ጉዳዮች በተደጋጋሚ አንስተናል፡፡ ነገር ግን የመጣው ለውጥ አጥጋቢ አይደለም፡፡ መሻሻል ቢኖርም መሠረታዊ ለውጥ አልመጣም፡፡ የመድኃኒት አስተዳደር ላይ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣበት ደረጃ ስላልደረሰ ጉድለቱ በአመራሩ በደንብ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ መድኃኒቶች በየሆስፒታሉ ሾልከው የሚወጡበት፣ የሚሰረቁበት፣ ያለአግባብ ጥቅም በሚፈልጉ ግለሰቦች እጅ የሚገቡበት መንገድ አለ፡፡ ይህንን ጉዳይ መቆጣጠር የመድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣንም ዋና ሥራ ስለሆነ ከሕዝቡ ጋር በትብብር ሕገወጥ አሠራሩን ሊገታ ይገባል፡፡ በቅርቡ የሕግ ማዕቀፍም ስለወጣ እሱን የሚተገብር ማሻሻያ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱም ይህን መከታተል ይጠበቅበታል፡፡

  በሁለተኛ ደረጃ የጤና ኤክስቴንሽን ላይ ለውጥ ቢኖርም ለውጡ ግን ያን ያህል አጥጋቢ አይደለም፡፡ በሽታን መከላከል ወሳኙ የጤና ፖሊሲ ምሰሶ ነው፡፡ የፖሊሲው ዋና ተልዕኮ በሽታ መከላከል ነው፡፡ የበሽታ መከላከል ሥራ ከብዙ ነገር ጋር ይገናኛል፡፡ ከጽዳት፣ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ከምግብና ከውኃ ጥራት ጋር ይገናኛል፡፡ ከከተማው የፍሳሽ ማስወገድና ማኔጅመንት ጋርም ስለሚያያዝ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራችን በከተማ ደረጃ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር ዘንድሮ የተሻለ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን አጥጋቢ አይደለም፡፡ ምክር ቤቱም ያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ ኤክስቴንሽን ላይ ያለው ችግር ምንድነው? ጤና ቢሮ ይህን ለማስተካከል በተለይ አመራሩ ምን እያደረገ ነው? የሚለው በዝርዝር አይተን እናስተካክላለን፡፡

  ሦስተኛ፣ አስተዳደሩ የጤና ጣቢያዎችን በሰፊው እየገነባ ቢሆንም መብራትና ውኃ ባለመግባቱ የተወሰኑ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም መባሉ ትክክል ነው፡፡ መሠረተ ልማቱ ተገንብቶ፣ መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶችና የሰው ኃይል ተሟልቶ ወደ ሥራ ያልገቡ አምስት የሚደርሱ ጤና ጣቢያዎች አሉ፡፡ የከተማው መሠረተ ልማት ተቋማት ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው በአጭር ጊዜ ችግሩን መፍታት አለባቸው፡፡

  በአራተኛ ደረጃ፣ የሚኒሊክ ሆስፒታል የአሠራር ለውጥ አምጥቷል፡፡ ይህንን ለውጥ ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡ የአስክሬን ምርመራ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሥራ ተጀምሯል፡፡ የአስክሬን ምርመራ አገልግሎት ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ የአስክሬን ምርመራ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ብቻ ለምን ታጥሮ ይቀመጣል፡፡ ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ አገልግሎቱ ያን ያህል የተወሳሰበ አይደለም፡፡ ባለሙያዎችን በአገር ውስጥ ማሠልጠን ወይም ከውጭ አምጥቶ ማሠራት ይቻላል፡፡ የአስክሬን ምርመራ አገልግሎት ወደ ክልል ጭምር ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ያለበትና ብዙ ዜጎች እየተጉላሉ የሚገኙበትም ስለሆነ፣ ጊዜ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በቀላሉ መፈታት ይችላል፡፡ ችግሩ የገንዘብ አይደለም፡፡ ሕዝብ እስከፈለገ ድረስ ገንዘብ መመደብ ይቻላል፡፡

  ጥያቄ፡- ወቅቱ የ2009 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ የሚካሄድበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ለወላጆች አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ አስተዳደሩ ይህን ጉዳይ በቸልታ ለምን ይመለከታል?

  ከንቲባ ድሪባ፡- የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ እያደጉ ነው፡፡ ችግሩ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ የዋጋ ጭማሪው ከምን እንደሚመጣ ሁሉም የምክር ቤት አባላትና እኛም እንገነዘባለን፡፡ በተለይ የግል የትምህርት ተቋማት ላይ ችግሩ አለ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሊያደርግ የሚችለውን መለየት አለብን፡፡ መንግሥት በምንም መልኩ የራሱ ሥራ የሆነን በግዴታ መፈጸም አለበት፡፡ ኅብረተሰባዊ ትርጉም ያለው ነገር የትምህርት ጥራቱ ነው፡፡ የትምህርት ጥራቱን መንግሥት መከታተል አለበት፡፡ መንግሥት በሚያስቀምጠው አሠራርና የጥራት ደረጃ እያንዳንዱ የግል የትምህርት ቤት መተግበር ይኖርበታል፡፡ በግል ትምህርት ቤት የተማረ ተማሪም በልማቱ፣ በዴሞክራሲውና በተለያዩ የአገር ተልዕኮዎች የሚሳተፍ ነው፡፡ ስለዚህ ጥራት ላይ የሚመጣውን ችግር መንግሥት በፍጹም አይታገሰውም፡፡ መፍታት ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ማድረግ የሚችለው የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ነው፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤትን ጥራት ማሻሻል ነው፡፡ ተደራሽነቱን ማስፋት ነው፡፡ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር ካለ በፍላጎቱ እንጂ፣ ተገፍቶ በችግር ለምሳሌ በአካባቢው የመንግሥት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወይም አማራጭ ስላጣ ብቻ ተገፍቶ ልጁን ወደ ግል ትምህርት ቤት እንዲያስገባ የሚያደርጉ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ በአዲስ አበባ አብዛኛው ዜጋ ልጆቹን የሚያስተምረው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ነው፡፡ ዋጋን የመጨመር አዝማሚያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ውድድር እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች የውድድር መንፈስ እንዲጎለብት ማድረግ አለብን፡፡ ዋጋ የሚመለከተው ልጆቹን የግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምር ወላጅ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን በዚህ ዋጋ አስተምሩ በዚያ ዋጋ አታስተምሩ አይልም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው የጨመሩት ዋጋ አግባብ ነው ወይስ አግባብ አይደለም የሚለውን ጉዳይ መመርመር ነው፡፡ ወላጆች በዚህ ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉና እንዲከራከሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ በነፃ ገበያ ውስጥ የሚቀርብ አገልግሎት በነፃ ገበያ ማዕቀፍ ውስጥ መካሄድ አለበት፡፡ የግል ትምህርት ቤት ማስተማር ነፃ ገበያ ነው፡፡ የግል ትምህርት ቤት ዋጋ የሚጨምርበት የራሱ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ ወይም ከስግብግብነት የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ የትኛው ነው ሚዛን የሚደፋው? ለዋጋ ጭማሪው መንስዔ ዋነኛ ምክንያቱ ምንድነው? በሚለው ጉዳይ መንግሥት፣ ወላጅና ትምህርት ቤቶቹ፣ አንድ ላይ የሚወያዩበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡

  ጥያቄ፡- በኢንዱስትሪና በንግድ ዘርፍ ባለሀብቱን ለማስተናገድ አለመቻሉ ምክንያቱ ምንድነው? የኢንዱስትሪ ዞኖች መሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የታቀደው ዕቅድ እንዳይሳካ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ኅብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ችግር እየተዳረገ ነው፡፡ ይህን ለመፍታት አስተዳደሩ ምን እያደረገ ነው?

  ከንቲባ ድሪባ፡- ኢንዱስትሪ ቢሮ ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ወዲህ የመሠረተ ልማት ችግሮችን መፍታት ጀምሯል፡፡ ከባለሀብቱ ጋር የመወያያ መድረኮች ተፈጥረዋል፡፡ ዘንድሮ እኔም ባለሁበት ባለሀብቶችን ሰብስበን አወያይተናል፡፡ ማኑፋክቸሪንግና ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ችግሮች ምንድናቸው? በሚለው ላይ ተወያይተናል፡፡ የባለሀብቶችን ጥያቄ ተቀብሎ፣ ተቀባይነት ያለውን ችግር በመፍታት በኩል ችግር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለሀብቱ ራሱ መፍታት ያለበትን ችግር ወደ መንግሥት የመግፋት ዝንባሌ ታይቷል፡፡ ዘንድሮ አለ የሚባለው ለውጥ መድረኮች መፈጠራቸውና ከአስተዳደሩ ጋር ውይይት መጀመሩ ነው፡፡ በተለይ ማነቆ ሆነው የቆዩ የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የቴሌና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ችግር የመፍታት እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በኢንዱስትሪ ዞኖች የተናጠል ጥያቄዎችን ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ ይኼ ግን በቂ አይደለም፡፡ ሁሉም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተዋናይ የሚያነሷቸውን ችግሮች ለቅሞ አውጥቶ ችግሮቹን በፍጥነት መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በጅምር ደረጃ ጥሩ ቢሆንም፣ ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር ግን ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡ ሌላው ለአዳዲስ ባለሀብቶችና ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለተሸጋገሩት ከዚህ በኋላ መሬት በማቅረብ ብዙ ርቀት መሄድ አንችልም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የመሬት ሀብት ውስን ነው፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከት ሁሉም መሬት ግንባታ ያረፈበት ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ግንባታ የቀረው መሬት ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ሊሆን የሚችለው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ባለሀብቶች ወደ ፓርኮች ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ማለት ግን መሬት መስጠት ጭራሽ እናቆማለን ማለት አይደለም፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እስኪገነቡ ድረስ ልማቱ መቆም የለበትም፡፡ በተወሰነ ደረጃ ያለንን የመሬት ሀብት ከግምት እያስገባን እንሰጣለን፡፡ በዕቅድና በፕላን ደረጃም አስቀምጠናል፡፡ ነገር ግን ለባለሀብቱ ለምንሰጠው ድጋፍ፣ በተቻለ መጠን የተቀናጀ እንዲሆን፣ ሰብሰብ አድርጎ ለመደገፍ አመቺ ስለሚሆንም፣ መንግሥት ላይም የሚኖረውን ጫናም ስለሚቀንስ ኢንዱስትሪያሊስቶቹም እርስ በርስ እንዲማማሩና እንዲመጋገቡ ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጥር ይህን መንገድ እንከተላለን፡፡ የኢንዱስትሪ ቢሮ ከዚህ አንጻር የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያለማ ኮርፖሬሽን እንዲያቋቁም ተወስኗል፡፡ የሕግ ማዕቀፍም እየተዘጋጀ ነው፡፡

  ጥያቄ፡- በትራንስፖርት ዘርፍ ኅብረተሰቡ እየተማረረ ነው፡፡ በዘርፉ የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮችን በሚመሩ አካላት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሰፍኗል፡፡ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው?

  ከንቲባ ድሪባ– በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አጣርቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የማጥራት ሥራው እንዳለቀ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡ በኮንትራት አስተዳደር፣ በትራንስፖርት ዘርፍና በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ኮሚቴው አጣርቶ ሲያቀርብ አስተዳደሩ የማስተካከያ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ በትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ በውኃና ፍሳሽ ያለው ችግር ተጣርቶ አልቋል፡፡ እኔም ባለሁበት ሪፖርት ቀርቦ ተወያይተናል፡፡ የንግድ ዘርፉም እንደዚሁ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ማየት የሚገባው ማጥራት የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ ማጥራት ብቻ አይደለም ተቋምን የሚለውጠው፡፡ ማጥራት ብቻ ቢሆን በየተቋሙ ያለውን ሌባ ሰብስቦ አስሮ መቀመጥ ይቻል ነበር፡፡ ተቋሙ ከጠራ በኋላ የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ደረጃ ደርሷል ወይስ አልደረሰም የሚለው ነው፡፡ ሰው ስለተወለጠ አይደለም ለውጥ የሚመጣው፡፡ በአሠራር፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በአስተሳሰብ ምን ደረጃ ደርሷል የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ቁልፉ የሕዝብ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በመሬትና በደንብ ማስከበር ዘርፍ ብዙ ሰው ከጨዋታ ውጪ አድርገናል፡፡ ጥያቄው ተቋሙ ተለውጧል ወይ የሚለው ነው፡፡ 700 የመሬት ዘርፍ ኢንጂነሮች አሰናብተን፣ ሌሎች 700 አዳዲስ ተመራቂ ኢንጂነሮች ተክተናል፡፡ እነዚህ ተመራቂዎች ወደዚህ ሲመጡ ይዘው የሚመጡት ኋላቀር አስተሳሰብ እንዳይኖርና ውጤታማ ካላደረግን በስተቀር ውጤት አይመጣም፡፡

  ጥያቄ፡- የከተማው አስተዳደር የኮንዶሚኒየም ቤቶች በመገንባት ላይ ቢሆንም በማስተላለፍ በኩል ዳተኛ ነው፡፡ ግንባታው እየተጓተተ መሆኑ ይታያል፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅትም ብዙ ጉድለቶች ታይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተሠሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች መጥፋታቸው እየነገረ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ ምንድነው?

  ከንቲባ ድሪባ፡- የከተማው አስተዳደር ቤቶች እየገነባ ነው፣ 39 ሺሕ ቤቶች ግንባታ ወደ መጠናቀቁ ነው፡፡ ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ማስገባት ላይ ችግር በመኖሩ ቤቶቹን ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሪክ ማስገባቱ የተጀመረ በመሆኑ የመብራት ማስገባቱ እንደተጠናቀቀ ቤቶቹ ይተላለፋሉ፡፡ በግንባታው የፌዴራል መንግሥት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ቀንሶ ነው በዚህ ዓመት 15 ቢሊዮን ብር ብድር የፈቀደው፡፡ መንግሥት ይህን ያህል ገንዘብ ለቤቶች ግንባታ ፈቅዶ አያውቅም፡፡ ስምንት ቢሊዮንና አሥር ቢሊዮን ብር ነበር በዓመት የሚፈቅደው፡፡ ዘንድሮ 15 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ነበር፡፡ ነገር ግን የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቱ እጅግ በመግዘፉ (171 ሺሕ ቤቶች) የግንባታ መጓተት ታይቷል፡፡ የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት የፈቀደው ገንዘብ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን ገንዘብን መልቀቅ ላይ ትንሽ ወቅቱን የጠበቀ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት በበጋ ወራት ግንባታው የተጓተተ ነበር፡፡ 52 ሺሕ ቤቶች በ20/80 ፕሮግራም፣ 40 ሺሕ ቤቶች በ40/60 ፕሮግራም እየነባን በመሆኑና በክረምትና በሚቀጥለው ዓመት በዚሁ መንገድ በጀት የሚፈቀድ ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው ይገባደዳል፡፡ በቤት በኩል ቁልፍ ችግር ተብሎ ከምክር ቤት የተነሳው ዕጣ ወጥቶላቸው የባንክ ዕዳ እየከፈሉ ቤት ያልተሰጣቸው አሉ የተባለው አሳሳቢ ነው፡፡ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ሪፖርት ለአስተዳደሩ መቅረብ አለበት፡፡ ችግሩ ከየት እንደመጣም ዝርዝሩ ይታያል፡፡ ይህ ጉዳይ ተቀባይነት የለውም፡፡ በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ ዕድሜ ጊዜ ውስጥ የነበሩ ቤቶች ተደምረው 200 ሺሕ አይበልጡም ነበር፡፡ መንግሥት ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ የገነባቸውና እንዲገነቡ ያመቻቸው ሦስት መቶ ሺሕ ቤቶች ናቸው፡፡ የቀበሌ ቤቶች ላይ በ2007 ዓ.ም. ቆጠራ አካሂደናል፡፡ ከዚህ ቀደም በቀበሌ ቤቶች ምንም ቆጠራ አልተካሄደም፡፡ በቆጠራ ወቅት እጅግ በጣም ብዙ ሕገወጥነት ተገኝቷል፡፡ ይህን ለማስተካከል ሕግ ማውጣት የሚፈልጉ ጉዳዮች ጭምር አጋጥሞናል፡፡ ቀበሌ ቤት እየከፋፈሉ ማከራየት፣ የቀበሌ ቤት ግቢ ውስጥ ሌላ ቤት ገንብተው የሚያከራዩ፣ የማካካሻ ቤት የተባሉ ሁሉ አሉ፡፡ ስለዚህ የከተማው አስተዳደር ይህን ችግር ማጥናቱ መልካም ሥራ ነው፡፡ ችግሩን ማወቅ ለመፍትሔ አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፍ ተጠናቆ ወደ ተግባር ይገባል፡፡ መንግሥት በቆጠራው የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ከሕግ ውጭ እንዳደረጉ ተገንዝቧል፡፡ ሕጋዊ አሠራር የማይፈቅደውን ምናልባት ከታችኛው የአስተዳደር ክፍል አመራሮች ጋር በመመሳጠር ሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ አሠራሩ በየትኛውም ሕግ አይፈቀድም፡፡ የቀበሌ ቤትንና የቀበሌ ግቢን ከፋፍሎ ብዙ ዓይነት ቤት አድርጎ በማይገባ መልኩ ለግል ጥቅም ማዋል አግባብ አይደለም፡፡ አሁን ችግሩን አውቀናል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ምን ዓይነት የቤት አስተዳደር ሥርዓት እንከታተላለን የሚለው ወደ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ይወስደናል፡፡ ሁለተኛው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ አካሂደናል፡፡ ይህንን ቆጠራ ያካሄድነው ከቀበሌ ቤቶች ባገኘነው ልምድ ነው፡፡ ከዚህ ቆጠራም የተጠቀሱትን ችግሮች አውጥተናል፡፡ ችግሩ ሳይባባስ በፍጥነት ደርሰንበታል፡፡ አሁንም ያልደረስንባቸው ችግሮች ይኖራሉ፡፡ የቆጠራውን ግኝት ኦዲት እናደርጋለን፡፡ ይኼ ነው ዘላቂ መፍትሔ ያለው ሥርዓት እንድንዘረጋ የሚያስችለን፡፡ ኮንዶሚኒየም ላይ የታዩ የአስተዳደር ችግሮች ለመፍታት አንድ ሶፍትዌር እየተገነባ ነው፡፡ ከሌሎችም አገሮች ሁሉ ልምድ ተወስዶ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በኋላ በዘመቻ የሚሠራ ሥራ የለም፡፡ በአሠራር ሥርዓት ነው ሁሉም የሚሠራው፡፡

  የጠፉ የኮንዶሚኒየም ብሎኮች የተባሉትን አንድ ደረጃ ለማጥራት ሞክረናል፡፡ ከከተማ ልማት ሚኒስቴርና ከከተማ አስተዳደሩ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ለማጥራት ሞክሯል፡፡ የመጀመርያ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከዚህ በኋላም ሪፖርቱ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል፡፡ ይህን ካደረግን በኋላ ተጨማሪ ኦዲት እንደሚያስፈልግ እየተገለጸ በመሆኑ ሥራው በቀጣይ ይሠራል፡፡ እነዚህ ቤቶች በ1990ዎቹ፣ በ2002 እና በ2003 የተገነቡ ናቸው፡፡ አሁንም ባሉት ላይ ጭምር ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር ካለ ኦዲት እናደርጋለን፡፡ ዋና ኦዲተር ይህን ሥራ በባለቤትነት እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ የፌዴራል ኦዲትም ጨምሮ ይህን ጉዳይ በዝርዝር አጥንተው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ችግር ለመፈለግ ሳይሆን ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር እናከናውናለን፡፡ እየሠራን ያለነው ግዙፍ ሥራ ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮችን ስጎበኝ በዚህ ደረጃ በመንግሥት የሚገነባ ቤት የለም፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ይህን ያህል ሀብት እየፈጠረ፣ ለሕዝቡ ያለውን ውግንና በተግባር ያረጋገጠበት ሥራ ነው፡፡ በዚህ ትልቅ ግንባታ ውስጥ የሚፈጠር ስህተት ካለ ስህተቱ እንዴት እንደተፈጠረ አይቶ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እየገነባን ያለነው ከተማ ነው፡፡ ሆን ብለው ችግር የፈጠሩ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ በኮንዶሚኒየም የጋራ መጠቀሚያ በኩል የማኅበራት ኮሚቴዎች ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ አብዛኛዎቹን ኮሚዩናሎች በማኅበራት ኮሚቴዎች ተከራይተዋል፡፡ ሊያከራዩ ግን አይገባም፡፡ ማከራየት ካስፈለገ መንግሥት ራሱ ገዝቶ ማከራየት ይችል ነበር፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በኮሚይናሎች ሥራ እየሠሩ ራሳቸውን ሊደጉሙ ይገባል፡፡ የእኛ መዋቅርም በዚህ ችግር እጁ አለበት፡፡ በፍጥነት ወደ ማስተካከል እንገባለን፡፡

  ጥያቄ፡- በአዲስ አበባ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ተንሰራፍቷል፡፡ የከተማው አስተዳደር ከፊሉን ሕጋዊ ያደርጋል፡፡ ከፊሉን ደግሞ በዘመቻ ያፈርሳል፡፡ ይህ አድሎአዊ አሠራር አይደለም? በማፍረስ ሒደቱ የሰው ሕይወት ጠፋ እየተባለም ነው፡፡

  ከንቲባ ድሪባ፡- በቅርቡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑ አካባቢ ዕርምጃ መውሰድ ተጀምሯል፡፡ የመሬት ወረራውን ለመግታት በተካሄደው የቤቶቹን የማፍረስ ሒደት የሰው ሕይወት አልጠፋል፡፡ በእርግጥ ይህ ዘመቻ ሲካሄድ ከበድ ያለ ግፊት ነበር፡፡ ከፖሊስ ጋር ግጭትም ነበር፡፡ የሰው ሕይወት ግን አልጠፋም፡፡ በአብዛኛው ከሦስት ዓመት ወዲህ የተገነቡ ቤቶች ናቸው፡፡ ወረገኑ አካባቢ ይኼ ሁሉ ቤት ሲሠራና ይኼ ሁሉ ሰው ሲሰፍር የወረዳው መወቅር የት ነበር? የሚለው በዝርዝር ይታያል፡፡ ቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር፡፡ ሁለትና ሦስት ቤቶች ሲሠሩ ማስቆም ይቻል ነበር፡፡ ይህ የመሬት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ችግር የሚያሳየው ነው፡፡ በየአካባቢው ፖሊስ አለ፣ ደንብ ማስከበር አለ፡፡ ሰፋ ያለ ቁጥር ያለው የእኛ መዋቅር አለ፡፡ በፍጹም በዚህ ደረጃ ሕገወጥነት ሊስፋፋ አይገባም ነበር፡፡ ውስጥ ገብተን ስናይ ከፀጥታ መዋቅራችንም በሕገወጥ ተግባሩ ላይ ተከፋይ የሆኑ አሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ከኋላ ሆኖ እያስገነባ ነበር፡፡ መሬት በመዝረፍ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልግ ኃይል ነበር፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰብ እርግጠኛ ነኝ 90 በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ መሬት እንዲወረር አይፈልግም፡፡ ሕገወጥነትን ይታገላል፡፡ የተወሰኑ ደላሎችና መሬት ማግኘት እንችላለን በማለት ከክልል የሚመጡም አሉ፡፡ የየራሳቸውን ሰፈር ገንብተው መኖር የጀመሩም አሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በተቻለው መጠን የመሬት ወረራን ማስቆም ይኖርበታል፡፡ ወረራውን ለማስቆም ከየክልሉ ፈልሰው የሚመጡ ሰዎችን ባሉበት አካባቢ መኖሪያ እንዲያገኙ፣ የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ ያሻል፡፡ እዚህ [አዲስ አበባ] ትርፍ መኖሪያ ቤት የለም፡፡ አዲስ አበባ ይህን ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡ እዚህ ያለውም ነዋሪ በመኖሪያ ቤት እየተቸገረ ነው፡፡ ሥራ አዲስ አበባ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ክልሎችም ሥራ እየፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህ ክልሎች ላይ በሚሠራ ሥራ የሕዝቡን ሕይወት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ከመጣም መሬት እንዳይወረር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ መሬት የሚወር ግለሰብ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ ወረገኑ ላይ ያለው ሰው አብዛኛው መሬቱን የገዛው ከአርሶ አደር ነው፡፡ ከ300 እስከ 500 ብር በካሬ እየከፈለ 300 ካሬ መሬትና ከዚያ በላይ መሬት ይዟል፡፡ መሬት በሕገ መንግሥቱ አይሸጥም፣ አይለወጥም፡፡ የሊዝ አዋጅም እንደዚያው ነው የሚለው፡፡ አብዛኛው ሰው ግን ገዝቶ ነው የሰፈረው፡፡ ይህን ሁሉ ብር አውጥቶ የገዛ ሰው ብር ያለው ሰው ነው፡፡ ድሃ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የመኖሪያ ችግር ያለባቸው በተጀመሩ የቤት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ካገኘሁት ገቢ ላይ ግብር መክፈል አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ብዙ ይቀረዋል›› አቶ ሙሉጌታ አያሌው፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት

  የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለና በመንግሥትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ከታክስ ጋር በተያያዙ የሚነሱ አመግባባቶችን የሚመለከት ተቋም ነው፡፡ ግለሰቦችና ነጋዴዎች...

  ‹‹የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው›› አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር

  ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም ከኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ በሄልዝ ኦፊሰርነት ተመርቀዋል፡፡ ገና ባህር ዳር...

  ‹‹የሰላም ስምምነት ተደረገ ማለት በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይታለፋሉ ማለት አይደለም›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

  ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በአዳማ ዳኞች መታሰራቸው ከሰሞኑ ትልቅ መነጋገሪያ የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡ በሐዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ ጭምር ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑና በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ...