Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትራንስፖርትን ለማዘመን አማራጮች አይዘጉ

በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዙሪያ ያለው ችግር እጅግ በርካታ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያለው የትራንስፖርት ችግር ለወጪ ወራጁ በቅርብ የሚታይ ከመሆኑ አንፃር ብዙ ሲተችበት ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝብ በማመላለስ አገልግሎት ላይ ያለው ችግር ግን ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ በአብዛኛው እንግልትና ግድፈቶች የሚታዩበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በክልሎች ከአንድ ከተማ ወደ ሌላው ለመጓዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚታየው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ በእንከኖች የታጨቀ ነው፡፡ የትራንስፖርት እጥረቱም አማራሪ ሆኖ መታየቱ እንዲሁ ነው፡፡  

በአጠቃላይ በአገሪቱ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ችግሮች መገለጫቸው ብዙ ነው፡፡ ዋና ዋና ችግሮች ተደርገው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ከፍላጐት ጋር የተጣጣመ አገልግሎት የሚሰጡ በቂ ተሽከርካሪዎች አለመኖራቸው ነው፡፡ አገልግሎት ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎችም ቢሆኑ ዕድሜ የጠገቡ፣ ለተገልጋዩ ምቾች የማይመጡ ናቸው፡፡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች የተገነቡት መንገዶች ላይ የሚሽከረከሩ አሮጌ መኪኖች ጥንቱን የፈበረኳቸው አሁን ቢዘጉም፣ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ስምሪት ውስጥ ዛሬም ድረስ ላይ ታች እያሉ ሕዝብ አጭቀው እየተመላለሱ ነው፡፡ ብቃታቸው አጠራጣሪና ሥጋት ላይ የሚጥሉ ተሽከርካሪዎች ሕዝብ አሳፍረው የሚጋልቡት በኢትዮጵያ ነው፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም ሕዝብ እንደ ሸቀጥ ታጭቆ የሚጓጓዝባቸው አጋጣሚዎች የተለመዱ ናቸው፡፡ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል የአገሪቱ የትራንስፖርት ችግር መገለጫ ተደርጐ ሆኗል፡፡

ለሕዝብ አገልግሎት ተብለው የተገነቡ ወይም የተከለሉ መናኸሪያዎችም ቢሆኑ ምቾት የሌላቸው፤ ፅዳታቸው የማይጠበቅ ከመሆን አልፈው መፀዳጃ ቤቶች የሌላቸው ካላቸው የማያገለግሉ የበሽታ መናኸሪያ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡

በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተወጠረውን የአገልግሎት ዘርፍ ለመቀየርም ሆነ የተሻለ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ጤናማ ተሽከርካሪዎችን አቅርቦት የሚሻ ነው፡፡ በጥራትም፣ በብዛትም ወደ ስምሪት የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን የሚናፍቅ ዘርፍ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ለማዘመን መንግሥትና የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የተሰማሩ ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡

የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አንዳንድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታመናል፡፡ ግን ካለው ፍላጐት አንፃር አነስተኛ ነው፡፡ ብዙ አማራጮችን ያልተመለከተ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ይህም ሆኖ በዘርፉ አማራጭ ተደርጐ የሚወሰደው በልዩ ፈቃድ በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች እየቀረበ የሚገኘው የሕዝብ ማመላለስ ሥራ አንዱ ነው፡፡

ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ የገቡ በረዥም ርቀት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች መፈጠራቸውና ወደ ሥራ መግባታቸው መልካም ነው፡፡

በልዩ የትራንስፖርት ፈቃድ በረዥምና አገር አቋራጭ የትራንስፖርት መስክ አገልግሎት ለመስጠት የተፈቀደላቸው ድርጅቶች ከሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች የተለየ የራሳቸውን ታሪፍ አውጥተው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

መንግሥት ታሪፍ ከሚወስንላቸው በተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪዎች በተለየ የራሳቸውን ታሪፍ አውጥተው የሚሠሩት የልዩ የትራንስፖርት አውቶብሶች ባለንብረቶች በእርግጥም አገልግሎት አሰጣጣቸው የተለየ ተደርጐ ስለሚታይ የተለየ ዋጋ መጠየቃቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን አውቶብሶች ይዘው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ የገበያ ድርሻቸው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ተገልጋዩም መርጦ የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ታሪፋቸው ከሌሎች መለየቱ ላያስገርም ይችላል፡፡

ፈቃዱ ሲሰጣቸውም የሚጠቀሙበት ተሽከርካሪ ዘመናዊነቱ እንዲሁም በተሽከርካሪዎቹ የሚጠቀሙ ተጓጓዦች በጥሩ ምቾት እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ አገልግሎት መስጠት ስለሚጠበቅባቸው ዋጋቸው ይጨምራል፡፡ በምርጫ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አቅም ያገናዘበ አሠራር እንዲሰጡ የማይጠበቅባቸው መሆኑም ይታመናል፡፡ ከሰሞኑ እንደተሰማው ግን መንግሥት የእነዚህን ድርጅቶች ዋጋ እወስናለሁ እያለ ነው፡፡ ይህ ውሳኔው በተለያየ መልኩ ሲታይ፣ በድርጅቶቹም ሆነ በምርጫ ለመጠቀም ተፈጥሮ የነበረውን ዕድል ሊዘጋ የሚችል ሥጋት ግን አሳድሯል፡፡

መንግሥት የእነዚህን ድርጅቶች ታሪፍ እወስናለሁ ብሎ የተነሣው ዋጋቸው ተጋኗል በሚል መነሻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እርግጥ ነው መንግሥት ዘርፉን የሚቆጣጠርበት የራሱ አሠራር ያለው ቢሆንም፣ እንዲህ ያለውን የአገልግሎት አማራጭ እንዲያሳጣ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በልዩ ትራንስፖር ዘርፍ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች አሠራር መፍቀድ ተገቢ መሆኑን አምኖ ፈቃድ ሰጥቶ በፈለጋችሁት ዋጋ ሥሩ ብሏል፡፡ ፈቃዱንም ሲሰጥ በእነዚህ አውቶብሶች የሚጠቀሙ እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገናዝቦ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ታሪፋቸውን እየወሰኑ ቢሠሩ ለዘርፉ ይጠቅማሉ እንጂ ጉዳት ያደርሳሉ የሚል እምነት የለም፡፡ ስለዚህ ታሪፋችሁን እኔ ልወስንላችሁ ቢባል ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ባይሆን እነዚህን ማብዛት ይገባዋል እንጂ፡፡ ሥጋት ላይ ሊጥላቸው አይገባም፡፡ ለእነዚህ ድርጅቶች ታሪፍ አወጣለሁ ከማለት ይልቅ እንዲበራከቱ የሚያስችል አሠራር በመፍጠር በውድድር ዋጋ የሚቀንሱበት ሁኔታ ማመቻቸት የበለጠ ጥቅም ይሰጣል፡፡ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ድርጅቶችን ለማበራከትም ሁነኛ መፍትሔ ይኸው ነው፡፡

እንደተገልጋይ ስናስብም ተገልጋዮች በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ አቅም ላይ የሚገኙ በመሆኑ ሁሉም በአቅሙ መርጦ የሚጠቀምባቸው አውቶብሶች እንዲኖሩ የሚፈልግ መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አልጋ ያለው ተሽከርካሪ ቢኖርና በዚህ መጠቀም ከፈለገ ውድ የሚባለውን ቢከፍል ከልካይ ለምን ይመጣበታል? በአነስተኛ ሆቴል አልጋና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አልጋ መካከል ያለው ዋጋ እንደሚለያይ ሁሉ በትራንስፖርቱም እንዲህ ዓይነት አሠራር ቢለመድ አስቸጋሪነቱ አይታይም፡፡ ችግር የሚሆነው አብዛኛው ተገልጋይ የሚጠቀምበት የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ዋጋ ሲቆለል ነው፡፡ ይህንን መንግሥት ቢወስን ትክክል ነው፡፡

ነገር ግን እንደ አማራጭ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው አገልግሎቶች አስፈላጊነት በተለየ መንገድ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ነፃ ገበያ ከታየም ታሪፉ በገበያ ዋጋ መተመን አለበት፡፡

ተገልጋይ አቅም የተለያየ ነው፡፡ ትንሹም ትልቁም በአቅማቸው መስተናገድ የሚችሉበት አሠራር መፍጠር ተገቢ ስለሚሆን እስካሁን ሲሠራበት የነበረው የልዩ ትራንስፖርት ዘርፍ ፈቃድ አሠራር ሊቀጥል ይገባል፡፡

መንግሥት ለአብዛኛው ተገልገይ በማሰብ ከዘረጋው አሠራር ጐን ለጐን በራሳቸው ታሪፍና ስምሪት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ባይሆን ከእነዚህ ድርጅቶች ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓትን በአግባቡ እያሳደጉ መሆን አለመሆናቸውን መቆጣጠር የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡

እንዲህ ባለው መንገድ ማላመድ ካልተሻለ የአገልግሎት አሰጣጡን ማርዘም ከባድ ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ዘርፉን ለማዘመን ሌሎችንም በዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ ሁሉንም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ መመካከርና የተሻለው የቱ ነው ብሎ ማየትም ይጠይቃል፡፡

ይህ ማለት ግን እነዚህም ድርጅቶች ቢሆኑ የትርፍ ህዳጋቸው የተመጠነ አገልግሎታቸውን የተስተካከለ መሆን እንደሚገባው መዘንጋት የለበትም፡፡ አሁንም ይህ መታየት አለበት፡፡

  

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት