Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ታሰሩ

በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ታሰሩ

ቀን:

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሦስት ወራት በፊት ባካሄደው ጉባዔ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው አግዷዋቸው የነበሩትን የክልሉን የግብርና ቢሮ  ኃላፊና የሱሉልታ ከተማ ምክትል ከንቲባ በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ታግደው የነበሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ጀማነህና የቀድሞ የሱሉልታ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዲሮ ዲሜ በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰኔ 3  ቀን 2008 ዓ.ም. መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጨፌ ኦሮሚያ (የክልሉ ምክር ቤት) ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ የሁለቱም ተጠርጣሪዎች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ካደረገ በኋላ ነው፡፡ አቶ ዘለዓለም የተጠረጠሩት የክልሉ መንግሥትና ድርጅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ አመራር አድርጎ ሾሟቸው በሠሩበት ወቅት፣ የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ ወደ ጎን በመተው ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመው የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ከፍተኛ ክትትልና በሰበሰባቸው ማስረጃዎች፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል የሚል ጥርጣሬ ላይ ሊደርስ በመቻሉ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የክልሉን መንግሥት በጠየቀው መሠረት ተቀባይነት በማግኘቱ ተግባራዊ ሊሆን መቻሉን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ከአቶ ዘለዓለም ጋር ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የሱሉልታ ከተማ የቀድሞ ምክትል ከንቲባ አቶ ዲሮ ደሜ በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ አቶ ዲሮ የተጠረጠሩት በሕግ ከተፈቀደላቸው በላይ በርካታ መሬቶች በራሳቸውና በዘመዶቻቸው ወስደዋል በሚል መሆኑንም የሪፖርተር ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ምክትል ከንቲባው የሕዝብና የመንግሥት መሬት ሕገወጥ በሆነ መንገድ የወሰዱትና ለመዘመዶቻቸውም ስም የሰጡት፣ በከተማው የመኖሪያ ቦታ ለማግኘት ደረሰኝ ከቆረጡ በኋላ ሳይሰጣቸው በቀሩ ነዋሪዎች ስም ሳይሆን እንዳልቀረ ጥርጣሬ ማደሩንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ ዲሮ በሱሉልታ ከተማ ለማልማት ሥራ ከይዞታቸው በተፈናቀሉ ነዋሪዎች ስም መሬት በመውሰድ፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ከወሰዱ በኋላ፣ ለሌሎችም በጥቅም ለሚገናኟቸው አስተላልፈዋል በሚልም መጠርጠራቸውን ምንጮቹ አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ቢታወቅም በምርመራ ሒደት የተገኙ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በሱሉልታ ከተማ የቀድሞውን ከንቲባ ጨምሮ ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. 15 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው መታሠራቸው ይታወሳል፡፡ የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው 15 ግለሰቦች በደን የተሸፈነን የመንግሥትንና የግል ይዞታ በሕገወጥ መንገድ ለግለሰቦች አከፋፍለዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑን በወቅቱ ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ኦሕዴድ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ምክንያት ለማጣራት ባደረገው ጉባዔ፣ ከአቶ ዘለዓለም በተጨማሪ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ዳባ ደበሌን ከሥልጣን ማንሳቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኩቹም ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ በአቶ ዳባ ደበሌ ቦታ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ በከር ሻሌ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡ በአቶ ሰለሞን ቦታ ደግሞ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ በዙ ዋቅቤካ የክልሉ የአስተዳዳርና የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...