Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዶ/ር ነጋሶን የሕክምና ወጪ ለመሸፈን ወሰነ

የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዶ/ር ነጋሶን የሕክምና ወጪ ለመሸፈን ወሰነ

ቀን:

የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የነበሩት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሕክምና ወጪያቸውን ሲሸፍንላቸውና መኪና ሊገዛላቸው እንደሆነ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

‹‹የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ድጋፍ እንዲሆነኝ የተወሰነ ገንዘብ ሰጥቶኛል፡፡ በተረፈ መኪና ይገዛልሀል ተብዬ እርሱን እየጠበቅኩ ሲሆን፣ የሕክምና ወጪዬን በተመለከተ ደግሞ በምፈልግበት ጊዜ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወጪው እንደሚሽፈን ተገልጾልኛል፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ገንዘብ እንደተሰጣቸው የገለጹ ቢሆንም፣ የተሰጣቸው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ሕክምናውን መቼ ለመጀመር እንዳሰቡ በተመለከተ የአውሮፓና የአሜሪካ ክረምት ካለፈ በኋላ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹አሁን ለሕክምና የትም አልሄድም፡፡ እዚሁ ሆኜ በሽታውን በመድኃኒት እቆጣጠረዋለሁ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ከሆነ ደግሞ እዚህ ያሉ የልብ ሐኪሞች ዘንድ በየጊዜው በመሄድ እየተመረመርኩ መድኃኒት የሚጨመር ከሆነ እጨምራለሁ እንጂ፣ ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ የምሄደው የእነሱ የክረምት ወቅት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ድርጀቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ባለፉት 13 ዓመታት የገጠማቸውን ችግር ለድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማስረዳታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ተመካክረን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤቱን እንነግርሃለን ባሉት መሠረት›› በአካል ተገኝተው ውሳኔውን እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ያለሁበትን ሁኔታ በመረዳት ከጎኔ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ ሆኖም በየወሩ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፣ ቤትም ይገዛላቸዋል የሚባለው ትክክል አይደለም፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ኦሕዴድ የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈንና መኪና ለመግዛት ቢወስንም፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የተሰናባች ባለሥልጣን ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ ያለው ውዝግብ መፍትሔ አለማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡

ይኼንን ጉዳይ በተመለከተም አዲሱ አዋጅ ከወጣ በኋላ ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከቱ ለሁለቱ አፈ ጉባዔዎች በግልባጭ፣ ለፕሬዚዳንቱና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ሁለት ጊዜ ደብዳቤ እንደጻፉ ገልጸው ደብዳቤያቸው ግን ምላሽ አለማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከሁለት ዓመታት በፊት በድጋሚ ለፕሬዚዳንቱ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሁለቱ አፈ ጉባዔዎች ጉዳዩን እንዲያዩት ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር አስታውሰው፣ ሆኖም ደብዳቤው ምላሽ አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህም ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲመለከተው ዘጠኝ ገጽ ደብዳቤ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርቡልኝ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳን በመጋቢት 2009 ዓ.ም. ጥያቄ አቅርቤ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ አላገኘሁም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

‹‹ይኼን ውሳኔ ላስተላለፈው የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ፣ በአጠቃላይ ለኦሮሚያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ፤›› ብለው፣ ‹‹ባለፉት 13 ዓመታት የሕክምና ወጪዬን ስትሸፍን የነበረችው ባለቤቴ ነበረች፡፡ አሁን በተወሰነው ውሳኔ እርሷም ምሥጋና አቅርባለች፤›› በማለት ስለተደረገላቸው ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ ክፍፍል ከተፈጠረ በኋላ በያዙት አቋም ምክንያት ከኢሕአዴግ አመራርነትና አባልነት የተሰናበቱት ዶ/ር ነጋሶ፣ ፕሬዚዳንትነታቸውን ግን ያስረከቡት የአምስት ዓመት ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ መስከረም 1994 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት በሽግግሩ መንግሥት ወቅት በማስታወቂያ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡ በፈቃዳቸው እስከለቀቁ ድረስም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲን በመቀላቀል የፕሬዚዳንት ሥልጣን ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚያ ቀደም ሲል በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ የፓርላማ አባል ሆነው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...