በአማራ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችንና ተሿሚዎችን ሀብት ዳግም በመመዝገብና የምስክር ወረቀት በመስጠት ረገድ ዝቅተኛ ውጤት መመዝገቡ ታወቀ፡፡
የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በግማሽ ዓመቱ የ4,575 ተሿሚዎችንና የመንግሥት ሠራተኞችን ሀብት ዳግም በመመዝገብ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለ918 ብቻ ዳግም ምዝገባ ተከናውኖ የምስክር ወረቀት መስጠት እንደተቻለ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም 19.29 በመቶ ብቻ እንደሆነ የኮሚሽኑ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞችም ሆኑ ተሿሚዎች ሕዝብ የሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው አላስፈላጊ ጥቅም እንዳይሰበስቡ ለመከታተል፣ ሀብታቸውን እንዲያሳውቁና እንዲያስመዝግቡ የፀረ ሙስና አዋጁ ቢደነግግም፣ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የዳግመኛ ሀብት ማስመዝገብ ክንውኑ አነስተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለሁለት ተመራጮች፣ ለ171 ተሿሚዎችና ለ745 የመንግሥት ሠራተኞች የዳግም ሀብት ምዝገባ መካሄዱ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የመጀመርያው ሀብት ማስመዝገብ አፈጻጸሙ ጥሩ እንደነበር በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ወንድ 2,247 እና ሴት 840 በድምሩ ለ3,082 ተሿሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች የመጀመርያ ሀብት ምዝገባ ተካሂዶ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ አጠቃላይ አፈጻጸሙም 123 በመቶ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ በዝርዝር ሲታይም ለ23 ተመራጮች፣ ለ365 ተሿሚዎችና ለ2,694 የመንግሥት ሠራተኞች የሀብት ምዝገባ ተከናውኖ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በክልሉ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችና ተሿሚዎች ሀብትን በማስመዝገብ ረገድ ከ55.41 በመቶ ከፍ ማለት እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 44 በመቶ የሚሆኑት የክልሉ ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞች እስካሁን ድረስ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና የተመዘበረን ገንዘብ ለመንግሥት ማስመለስ እንደተቻለ፣ የክልሉ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ሪፖርት ጠቁሟል፡፡