Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቀዳሚው የስቃይና የሞት ምክንያት

ቀዳሚው የስቃይና የሞት ምክንያት

ቀን:

ካንሰር ማለት ህዋሳት (ሴሎች) መሠረታዊ ከሆነው የሥነ ሕይወታዊ የህዋሳት መራባት ቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ ራሳቸውን ሲያራቡ የሚፈጠር ሕመም ነው፡፡ እነዚህ ባህሪያቸውን የቀየሩት ህዋሳት ከተፈቀደላቸው መጠን በላይ በማደግ በአቅራቢያቸው ወደ ሌሎች አካላት በመሠራጨት ሕመሙ አስከፊ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋሉ፡፡

በመሆኑም ካንሰር ማንኛውንም የሰውነት አካል ሊያጠቁ እንደሚችሉ፣ በ2004 ዓ.ም. በወንዶች ዘንድ በብዛት በሕክምና ተለይተው የታወቁት የካንሰር ዓይነቶች የሳምባ፣ የፕሮስቴት፣ የአንጀት፣ የጨጓራና የጉበት ካንሰሮች ሲሆኑ፤ በሴቶች ዘንድ ደግሞ የጡት፣ የአንጀት፣ የሳንባ፣ የማሕፀን፣ የማሕፀን ጫፍና የጨጓራ ካንሰሮች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዶ/ር ኩኑዝ አብደላ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር ቁጥጥር ቴክኒካል አማካሪ ናቸው፡፡ እንደ አማካሪው ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 100 የካንሰር ዓይነቶች መካከል መጀመርያ የጡት፣ ቀጥሎ የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር 50 ከመቶ ያህል ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ልየታ ብቁ የሚባሉ ስድስት ሚሊዮን እናቶች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጥር 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ‹‹እንችላለን፡ እችላለሁ›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የካንሰር ቀንን አስመልክቶ በዕለቱ በተከናወነው ስብሰባ ላይ አማካሪው እንዳብራሩት፣ ለቅድመ ልየታ ብቁ ከሚባሉትም መካከልም ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 49 ዓመት የሆኑ 100 ሺሕ እናቶች የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ልየታ ተደርጎላቸዋል፡፡

ልየታ ከተደረገላቸው እናቶች መካከል ሰባት ሺሕ እናቶች ፖዘቲቭ ሆነው በመገኘታቸው ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡ የቀሩት 93 ሺሕ እናቶች በየአምስት ዓመቱ የቅድመ ካንሰር ልየታ እንዲያደርጉ ተነግሮአቸዋል፡፡ የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ልየታና ሕክምና የተካሄደውም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ከ200 በላይ በሚሆኑ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ውስጥ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ከካንሰር ሕሙማን መካከል አብዛኞቹ ወይም 75 በመቶ ያህል ለምርመራና ሕክምና ወደ ጤና ተቋማት ዘግይተው እንደሚመጡ፣ ይህ የሆነበትም ምክንያት በሽታው በወቅቱ ሳይደረስበት ቀርቶ፣ ወይም ሰዎች በካንሰር ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ሆኖ በመገኘቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ መዘግየት ደግሞ በሕክምናውና ታክሞ በመዳን ላይ ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ትንበያ ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ወደ 61 ሺሕ አካባቢ የሚሆኑ አዳዲስ ካንሰሮች ይመዘገባሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በዓመት ውስጥ የሚታከሙት ግን 10 ሺሕ እንኳን አይሞላም፡፡ ከዚህ አኳያ ከስድስት የካንሰር ሕሙማን መካከል አንዱ ብቻ ሕክምናውን ቢያገኝ ነው፡፡ የሞት መጠኑ ደግሞ ሲታይ ከ61,000 ውስጥ 44,000 ወይም 75 ከመቶ የሚሆኑት ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ነው ዶ/ር ኩኑዝ የተናገሩት፡፡

በበሽታው የመያዝና የሞት መጠኑ ሲታይ ከፍተኛ እንደሆነ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ልዩ ልዩ ሥራዎች እንደተከናወኑ፣ ከተከናወኑት ሥራዎች መካከልም የብሔራዊ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መካከል መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ መቅረቡና ብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያና መከላከያ መርሐ ግብር የአምስት ዓመት ዕቅድ ፀድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይገኝበታል፡፡ የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ መመሪያ መውጣቱና ሌሎችም ሊያሠሩ የሚችሉ ሰነዶች መዘጋጀታቸው ከተከናወኑት ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን፣ ‹‹የሕዝቡ ቁጥር በየጊዝው መጨመርና ከሥልጣኔ ጋር በተያያዘ የአመጋገብ ሥርዓታችን ጤናማ ባልሆኑ ሁኔታዎች መለወጡ፣ የትምባሆ፣ የአልኮል መጠጥና የሌሎች ዕፆች አጠቃቀም መስፋፋት፣ እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በተለይም ለካንሰር ሕመም ሥርጭት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› ብለዋል፡፡

በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምም በተለይ በተከለሰው የከተሞች የጤና ፕሮግራም ላይ ካንሰር ተካትቶ እየተሠራ እንደሚገኝ፣ የካንሰር ልዩ ሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግም አንፃር አማካይ በሆኑ ቦታዎች ማለትም በጎንደር፣ መቐለ፣ ጅማ፣ ሐዋሳና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ራሳቸውን የቻሉ የካንሰር ማዕከላት በመገንባት ላይ እንደሆኑና ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች ተጠናቅቀው አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎች በመሟላት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከተሟሉትም የሕክምና መሣሪያዎች ውስጥ በድምሩ በ600 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ ስድስት የጨረራ መሣሪያዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስት የጨረራ መሣሪያዎች በሐሮማያ፣ በጅማና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ውስጥ በመገጠም ላይ ሲሆኑ በቅርቡም አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቀሩት የጨረራ መሣሪያዎች በቀጣይ በጎንደር፣ መቀለና ሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታሎች ይገጠማሉ፡፡

እንደሚኒስትሩ ገለጻ፣ የጡት ካንሰር ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በተመረጡ 20 ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰጥበት ምቹ ሁኔት በመመቻቸት ላይ ነው፡፡ ለዚህም የሚያስፈልጉ የሕክምና መሣሪያዎች በግዢ ላይ ናቸው፡፡ የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር በመጪው ትውልድ ላይ እንዳይከሰት ለማድረግ በተወሰደው ዕርምጃ መሠረት ለአቅመ ሔዋን ላልደረሱ ወጣት ሴቶች በዚህ ዓመት ክትባት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ በአገሪቱ አራት ብቻ የነበሩት የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስቶች (ኦንኮሎጂስት) በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ቁጥራቸው ወደ 50 እንዲደረሰ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ቁጥሩ በተጠቀሰው ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ግን የሙያው ባለቤት የሆኑ የውጭ አገር ዜጎችን ለመቅጠር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብሮ እየሠራ ነው፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገድቦ ያለውን የካንሰር ሕክምና አገልግሎት ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ክልሎች እንዲዳረስ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የብሔራዊ የካንሰር ኮሚቴ ሊቀመንበር ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ በሽታው ‹‹በእንጭጩ ገና ሲጀምር ለመቅጨት የሚያስችሉ ሕክምናዎች የሚከናወኑት በኦንክሎጂስቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ባለሙያዎችም ጭምር ሊከናወኑ የሚችሉበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ በአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችም ሊሳካ ይችላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ ቀዳማዊት እመቤት አገላለጽ፣ በሽታው ሥር ሳይሰድ አስቀድሞ ወደ የጤና ተቋማት ያለመሄድ ልማድ መቀየርና ባሉት የጤና ተቋማትና አገልግሎቶች በመታገዝ የጤንነት፣ የደም ግፊትና የስኳር መጠንን በቀላሉ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሕክምናና መድኃኒቶች ዋጋቸው እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነና ኅብረተሰቡም ይህንን ተገንዝቦ ወደ ጤና መድን ዋስትና እንዲገባ የተጀመረው ሥራ በስፋት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ከቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...